ከአሉባልታ ፖለቲካ ወደ በጎ ፈቃድ አገልግሎት
ስሜነህ
የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ሰዎች በራሳቸው መልካም ፍቃድና ተነሳሽነት የልፋታቸውን ዋጋ ሳይጠይቁ ወይም ከድርጊታቸው በስተጀርባ ሌላ አጀንዳ ሳይጠነስሱ በአብዛኛው ጊዜ በማህበራዊ ጉዳዮች ላይ የሚሳተፉበት ሰብአዊ ተግባር ነው፡፡ በአለማችን በተለያዩ አገራት የበጎ ፍቃድ ተግባር የሚያከናውኑ ግለሰቦች፣ ቡድኖችና ድርጅቶች በርካታ ናቸው። በኢትዮጵያም ዜጎች በመልካም ተግባር በመሳተፍ ማሕበራዊ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ መወጣት የሚያስችላቸው አሳታፊ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት እውን ከሆነ ወዲህ ዜጎች በበርካታ ዘርፎች ላይ የተለያዩ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከዚህ ቀደም ከነበረው በላቀ ደረጃ በተለይ ወጣቶች መስጠት የሚገባቸው እንደሆነ ሃገሪቱ ያለችበት ተጨባጭ ሁኔታ ይጠይቃል።
የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ለአገር እና ለወገን ያለው ፋይዳ የጎላ ከመሆኑ አንፃር አሁንም ትኩረት ተሰጥቶት በስፋት ሊሰራበት የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር በየክልሉ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን ለማካሄድ ሲባል በእቅድ ደረጃ ተይዞ የነበረው ስራ እዚህ ግባ ባይባልም በደን ልማት እና በአካባቢ ጥበቃ፣ በአረንጓዴ ልማት እና በጽዳት ወዘተ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ሰጪዎች እንቅስቃሴም ይህን ያህል አመርቂ እንዳልሆነም እየተነገረ ነው። ወጣቱ ከተሰጠው የቤት ስራ ይልቅ በማህበራዊ ሚዲያ ፖለቲካ መጠመዱ ያሳስባል። መጠመዱ ይሁን ፤የሚያሳስበው በአሉባልታ ፖለቲካ ተጠምዶ ሃገርን ወደ አዘቅት እያነቃነቀ መሆኑ ነው።
በአሁኑ ጊዜ ያለው የመኸር ስራ በጥሩ ሁኔታ ላይ ቢሆንም፤ በአንዳንድ አካባቢዎች በረዶ እና አሜሪካ መጣሽ ተምችን የመሳሰሉ ችግሮች አፍጠው እያየንም እንዳላየ በአሉባልታ ፖለቲካ ተጠምደናል። ፖለቲካውን ለፖለቲከኞች ትተን ህብረተሰቡ አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርግ፣ ዜጎች በበጎ ፈቃድ ላይ የተመሰረተ አገልግሎት በመስጠት ምርትን ከውድመት ለመታደግ እንዲረባረቡ ማድረግ የዚህ ክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ዘመቻችን ሊሆን ይገባል።
በግልና በቡድን የተደራጁ ወጣቶች አሁን የሚጠበቅባቸው በጎሳ ፖለቲካ መጠመድ ሳይሆን አረጋውያንን፣ በህመም የሚሰቃዩ ወገኖችን፣ ልዩ ከለላ የሚያስፈልጋቸው የተጎዱ ሴቶችንና ህፃናትን ያለምንም የልፋት ዋጋ (በገንዘብ የሚተመን ክፍያ ሳይደረግላቸው እና እነሱም ይከፈለን ብለው ሳይጠይቁ) ሙሉ አልያም ትርፍ ጊዜያቸውን በመጠቀም ማገዝ ነው ። መደመር ይሏችኋል ደግሞ ይህ ነው። የበጎ ፍቃድ አገልግሎት መገለጫው ብዙ ቢሆንም እንደወቅቱ የክረምት በጎ ፈቃድ
አገልግሎትን በተመለከተ መረጃ መለዋወጥ በራሱ መደመር ነው፡፡
የክረምት ወቅት ለአብዛኛው የአገራችን ተማሪዎች የእረፍት ጊዜ ነው፡፡ ገሚሱ ዘመድ በመጠየቅ፣ ገሚሱ ደግሞ በትምህርት ተጨናንቆ የነበረው አዕምሮውን ዘና ለማድረግ በጉጉት የሚጠብቀው ወቅት ነው፡፡ ለአንዳንዶቹ የአገራችን ወጣቶች ደግሞ የክረምት ወቅት ለማህበረሰቡ ከፍተኛ ዋጋ ያለው ተግባር ለመፈፀም በበጎ ስራ ላይ በመሰማራት ሲታትሩ የሚስተዋልበት ነው፡፡ የዘንድሮውን ጨምሮ ያለፉት ሁለት አመታትን ብናስታውስ ከስረናል። በአሉባልታ ፖለቲካ ከመጠመዳችን አስቀድሞ በነበሩት አመታት ድንቅ ልምድ የነበረን መሆኑን ስናስታውስ ይብሱን ይቆጫል።
ከተሞች አካባቢ የነበረውን የክረምት ጊዜ መለስ ብለን ብናስታውስ፤ ወጣቶች የትራፊክ ሥነ-ስርዓት በማስከበር በክረምት በጐ ፈቃድ አገልግሎት ተሳትፈዋል።
በደም እጦት ሳቢያ አደጋ ላይ ለወደቁ ዜጎች ደም በመስጠትና ሌሎችም እንዲለግሱ በማስተባበር ህይወትን ታድገዋል። በአረንጓዴ ልማትም ችግኞችን በመትከልና ደኖችን በመንከባከብ ለተፈጥሮ ሚዛን መጠበቅ የድርሻቸውን ተወጥተዋል። ኤች አይ ቪ/ ኤድስን በመከላከል፣ ችግረኛ ተማሪዎችን በማስተማርና የትምህርት መርጃ መሳሪያዎችን በማበርከትም ላቅ ያለ አስተዋፅኦ አበርክተዋል። ረዳትና ጧሪ ለሌላቸውና ለጎዳና ተዳዳሪዎች የአልባሳትና የቁሳቁስ ድጋፍ በማሰባሰብም ወገናዊ ሀላፊነታቸውን ሲወጡ ቆይተዋል። ወጣቶች በክረምት ወራት በጤና፣ በአካባቢ ልማት፣ በመንገድና ትራፊክ ደህንነት፣ በስፖርትና መዝናኛ ዘርፎች በርካታ ተግባራትን አከናውነዋል።
በርካታ ወጣቶች የክረምት ጊዜያቸውን የበጎ ፍቃድ አገልገሎት በሚሰጡ ተቋማትና አደረጃጀቶች አማካኝነት ጊዜያቸውን ለሌሎች ሲሰጡና ወገኖቻቸውን በሚጠቅም ተግባር ላይ ሲያውሉ በዚያው ልክ ደግሞ በሀገራቸው ዕድገት ላይ ገንቢ አስተዋፅኦ የሚያደርጉ መሆኑን በአሉባልታ ፖለቲካ የተጠመዱ ሃይሎች ሊገነዘቡ ይገባል፡፡
ሁሉም ባይሆኑም በዘንድሮ የክረምት ጊዜያት በተለያዩ የአገራችን ክልሎች የሚገኙ አንዳንድ ወጣቶች በበጎ ስራ ላይ ተጠምደው ይገኛሉ፡፡የነዚህን ልምድ በአሉባልታ ወደተጠመዱት ማስፋት የመንግስት ወቅታዊ ተግባር ነው። የችግኝ ተከላ በማካሄድ፣ የደም ልገሳ ንቅናቄ በማዘጋጀትና ራሳቸውም ደም በመለገስና ሌሎችም ደም በመለገስ የወገናቸውን ህይወት ማትረፍ እንዳለባቸው በመቀስቀስ አኩሪ ተግባር በመፈፀም ላይ የሚገኙ ወጣቶች ልምድ ያያተርፈናል፡፡
መዲናችን አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ የክልል ከተሞች በትራፊክ ደንብ ማስከበር አገልግሎት፣ በችግኝ ተከላና፣ በማጠናከሪያ ትምህርት በመስጠት እንዲሁም ህሙማንን በመንከባከብ በበጎ ተግባር ላይ የተሰማሩ ወጣቶች በርካታ ናቸው፡፡ አሁን አሁን ደግሞ ሀገራችን የቀየሰችውን የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂ ተከትሎ ክረምት ሲመጣ አብዛኛው ወጣትና በርካታ የህብረተሰባችን ክፍል ተረባርቦ የሚፈፅመው የችግኝ ተከላ ተግባር የማይረሳ ባህል በአሉባልታው የተረታ ይመስላል፡፡
ስለሆነም ሁሉም ወጣት አቅራቢያው ከሚገኝና በመንግስት ከተከለሉ ቦታዎች ላይ በንቅናቄ መልኩ ችግኝ በመትከል የኢትዮጵያን ብሩህ ተስፋ ሊያለመልም ይገባል፡፡ የአየር ንብረት ለውጥ ጉዳይ ዛሬም መነጋገሪያ ሆኖ እንደቀጠለ ነው፡፡ ያደጉ ሀገራት አሁን ለደረሱበት ብልፅግና ያበቃቸው የእድገት ሂደት በከባቢ አየር ላይ ያደረሰው ጥፋት ያመጣው ጣጣ በርካቶቻችንን በተለይ ደግሞ በዕድገት ወደኋላ የቀረንውን ሀገራት ሰለባ አድርጎናል።
ይህን በሰው ልጆች ላይ የተደቀነ አስከፊ አደጋ ለመታገል የተለያዩ ሀገራትና ህዝቦች
ይበጀናል ያሉትን የመፍትሔ እርምጃ ለመውሰድ ደፋ ቀና በማለት ላይ ናቸው። ሀገራችንም የማይበገር የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂ በመቀየስ ለአፍሪካና ለመላው ዓለም በአርአያነት የሚጠቀስ ጥሩ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ ነች። በቀደሙት አመታት ክረምት በገባ ቁጥር ሁሉም የሀገራችን ህዝቦች ያለ የሌለ አቅሞቻቸውን በማስተባበር በችግኝ ተከላ ላይ እየተረባረቡ ያሉትም ይህንን ሀገራዊ ግብ ለማሳካት ነው። ስለሆነም ይህን ማስቀጠሉ ከዚህ ክረምት ሊጀመር ይገባል።
ሀገራችን እ.አ.አ በ2011 የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል የሚያስችላት ስትራቴጂ ቀይሳ ለተግባራዊነቱ በንቃት መረባረብ ከጀመረች ጊዜ አንስቶ ተጨባጭ ለውጦችን ማስመዝገብ ተችሏል። በአገራችንም የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ስትራቴጂን በመተግበር
የራሳችንን የቤት ስራ መስራት ይገባናል በሚል በተደረገው እንቅስቃሴ ባለፉት ዓመታት ከጫፍ እስከ ጫፍ ህዝባችንን በማነቃነቅ ተጨባጭ ስኬቶች ማስመዝገብ ተችሏል፡፡
የተመናመኑ ደኖች ወደቦታቸው ተመልሰዋል፡፡ የደን ሽፋናችንም እየተሻሻለ መምጣት ችሏል፡፡ የሃይል አማራጮቻችን ከብክለት ነፃ ከሆኑ እንደ ውሃ፣ ንፋስ፣ የፀሃይ ብርሃንና እንፋሎት ከመሳሰሉት ምንጮች መሆኑ ሲታይ ደግሞ ሀገራችን
በአጀንዳው ላይ ያላት ቁርጠኝነት የሰው ልጆችን በመታደግ በኩል ምን ያህል ግንባር ቀደም ሚናዋን እየተወጣች እንዳለች ለመረዳት አያዳግትም።ስለሆነም በአሉባልታ ተጠምደን ይህን ወደኋላ መመለስ ከክስረትም በላይ ክስረት ነው። ስለሆነም የዚህ ክረምት ዘመቻችን የአሉባልታ ፖለቲካ ሳይሆን የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሊሆን ይገባል።
ኢትዮጵያ በአለም ላይ በፍጥነት እያደጉ ካሉ አገራት መካከል አንዷ መሆኗ ይታወቃል፡፡ ይህንን ቀጣይነት ባለው መንገድ ለማስቀጠል ደግሞ ተግዳሮቶቿን ከስር ከስር መፍታት ግድ ይላል፡፡ በአሁኑ ወቅቱ የሀገራችን ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት
ግብርና ነውና ይህም እስከ ተወሰነ ጊዜ ድረስም ይህ እውነታ እንዳለ መቀጠሉ ስለማይቀር የአየር ንብረት ለውጥና መዘዙ ደግሞ አንዱና ዋነኛው የእድገታችን ማነቆና ስጋት ነው፡፡ የግብርና ልማት ስራችን ባሰብነው ልክ የእድገታችን ምንጭ
ሆኖ እንዲቀጥል ካስፈለገ የመሬት መሸርሸርን በመከላከልና የደን ልማታችንን በማፋጠን የአየር ንብረት ለውጡ ግንባር ተጠቂ እንዳንሆን በየክረምቱ በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሊደገፍ ይገባል፡፡ ለዚህም ነው የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ልማት ከእድገታችን ጋር በቀጥታ ስለሚያያዝ በቁርጠኝነት መረባረብ አለብን የሚባለው፡፡
የክረምት ወቅት የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂያችንን በተሟላ መልኩ ለማስቀጠል አይነተኛ ሚና አለው፡፡ በአገራችን የተለያዩ አካባቢዎች በጎ ፍቃደኛ ወጣቶች ለአረንጓዴ ልማት የማይበገር ኢኮኖሚ የመገንባት ግብ ለማሳካት ሊታትሩ ይገባል፡፡
የበጎ ፍቃድ አገልግሎት መስጠት በሀገራዊ የፀረ ድህነት ትግሉ ላይ የማይፋቅ የራስን አሻራ ማኖር ነውና በዋጋ የማይተመን የመንፈስ እርካታንም ያጎናፅፋል። የበጎ ፍቃድ
አገልግሎት ከዚህ በተሻለ መልኩ መጎልበትና ባህል ሊሆን የሚገባ መልካም ተግባር ለማድረግ ደግሞ ወጣቱ አሁን የተጀማመሩ መልካም ተግባራትን ይዞ ለበለጠ ውጤትና ተጠቃሚነት መስራት ይኖርበታል። በክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት የሚሰማሩ ወጣቶች ትርፋቸው ከላይ የተመለከተው ሃገራዊ ፋይዳ ብቻ አይደለም። በተሳትፏቸው ማኅበረሰቡን ከማገልገል ባለፈ ሙያቸውን በማበልጸግ ረገድ ጠቀሜታ ያስገኝላቸዋል። የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሌላውን ኅብረተሰብ እየጠቀሙ ራስን መጥቀም ነው። ስለሆነም ወጣት ወገኖቼ ዘመቻውን ከአሉባልታ ፖለቲካ ነቅለን ወደበጎ ፈቃድ ልንመልስ ይገባል።