Artcles

ውሎቹ እንዲተገበሩ

By Admin

August 07, 2018

ውሎቹ እንዲተገበሩ

                                                       ሶሪ ገመዳ

የሁለተኛው እድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ የእስካሁኑ አፈፃፀም ተገምግሟል። በተለይ በኢኮኖሚው ውስጥ ቁልፍ ሚና ያላቸው እንደ ግብርና፣ ንግድ፣ ኢንዱስትሪ፣ መልካም አስተዳደርና አገልግሎት አሰጣጥ በመሳሰሉት ዘርፎች ቀደም ባሉት ዓመታት ያጋጠሙትን ችግሮች ለመፍታት አቅጣጫዎች ተቀምጠዋል።

የእቅዱን አፈፃፀም ውጤታማ ለማድረግ በፓርላማው ቋሚ ኮሚቴዎች እና በአስፈፃሚ አካላት መካከል የተደረጉት ውሎች እውን እንዲሆኑ እየተካሄዱ ያሉ ዝግጅቶች ወሳኝ ናቸው። ስለሆነም የእቅዱ ዋነኛ ተዋናይ የሆነው የአገራችን ህዝብ እንቅስቃሴዎቹን በመደገፍ የተለመደ ድርሻውን ማበርከት ይኖርበታል።

ምንም እንኳን የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ለውጥ ማረጋገጥ ለዕድገቱ ዘላቂነት ወሳኝ መሆኑ ቢታወቅም፣ በታቀደውና በሚጠበቀው እንዲሁም በኢኮኖሚው ልክ እየተፈጸመ አለመሆኑን ሰነዶች ያስረዳሉ። የወጪ ንግድ አፈጻጸም ባለፉት ሁለት ዓመታት ከገቢ ንግድ አፈጻጸም በእጅጉ ያነሰ መሆኑ፣ የአገሪቱ የውጭ ምንዛሪ የማፍራት አቅም ላይ ውስንነት ፈጥሯል።

በሌላ በኩል ደግሞ የአገሪቱ የውጭ ዕዳ ጫና ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣት፣ እንዲሁም የታክስ ገቢ የመሰብሰብ አቅም ከታቀደው ግብ አኳያ ከፍተኛ ጉድለት ያለበት መሆኑ የኢኮኖሚው ፈተና ሆኗል።

ሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ትግበራ የተጀመረው በ2008 ዓ.ም ነው። መገባደጃውም በ2012 ዓ.ም እንደሆነ ይታወቃል። ከሁለት ዓመት በኋላ ማለት ነው። የዚህ በ2008 ዓ.ም እና በ2009 ዓ.ም በአማካይ የ11 ነጥብ ሁለት እና 11 ነጥብ አንድ በመቶ የኢኮኖሚ ዕድገት ለማስመዝገብ የታቀደ ቢሆንም፣ የተፈጸመው ግን በቅደም ተከተል ስምንት በመቶና 10 ነጥብ 9 በመቶ ነው። አፈጻጸሙ ከዕቅድ በታች ቢሆንም፣ የዘላቂ ልማት ግቦችን ለማሳካት ታዳጊ አገሮች እንዲያስመዘግቡ ከሚጠበቅባቸው የሰባት በመቶ አማካይ ዕድገት አንፃር ሲታይ ከፍ ያለ መሆኑ ግልፅ ነው።

በ2008 ዓ.ም እና በ2009 ዓ.ም የተገኘው የውጭ ብድር እንደ ቅደም ተከተላቸው 3.4 ቢሊዮን ዶላር እና ሁለት ነጥብ ስምንት ቢሊዮን ዶላር ሲሆን፣ በ2007 ዓ.ም ብቻ ተገኝቶ ከነበረው ስድስት ነጥብ አራት ቢሊዮን ዶላር ጋር ሲነፃፀር በ53 በመቶና በ56 በመቶ ዝቅተኛ መሆኑ ተመልክቷል። ይህም በሀገሪቱ ተፈጥሮ ከነበረው የሰላም እጦት ጋር የተያያዘ ነው።

በ2010 ዓ.ም በመጀመሪያዎቹ ስድስት ወራት ብቻ የተገኘው አጠቃላይ የውጭ ብድር አንድ ነጥብ ሶስት ቢሊዮን ዶላር ነው። አጠቃላይ የአገሪቱ የውጭ ብድር ክምችት 24 ነጥብ 7 ቢሊዮን ዶላር ደርሷል።

ታዲያ ይህ የውጭ ብድር ክምችቱ ከፍተኛ መሆን፣ እንዲሁም የውጭ ምንዛሪ እጥረትና የውጭ ብድር የመክፈል ግዴታ ከፍ እያለ መምጣት ለኢኮኖሚ ዕድገቱ ቀጣይነት ፈተና እንዳይሆን መንግስት የተለየ አቅጣጫን በመከተል ችግሩን ለመፍታት እየሰራ ነው።

ከአቅጣጫዎቹ ውስጥ በመንግስት እጅ ያሉትን የልማት ድርጅቶች በከፊልና ሙሉ ለሙሉ መሸጥ ነው። ለዚህም ዝግጅቶች እየተደረጉ ይገኛሉ። የእነዚህ ድርጅቶች ወደ ግል ይዞታ መዞር የመንግስትን አቅም በማጣናከር የተጀመሩ ፕሮጀክቶችን ለመጨረስና አገሪቱ ያለባትን ዕዳ በመክፈል አመኔታን ለማግኘት የሚያስችሉ ናቸው።

ያም ሆኖ መንግስት የወጪ ንግዱን ለማጠናከር የሚያከናውናቸው ተግባራት እንደተጠበቁ ሆነው፣ የግብርናውን ዘርፍ በማዘመን ኢኮኖሚውን ለመደገፍ ጥረትም እየተደረገ ነው። ግበርናው ኢንዱስትሪውን የሚደግፍበትን ሁኔታም መንግስት እያመቻቸ ነው። ለማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪው ልዩ ትኩረት ተሰጥቶም እየተሰራ ነው።

የአገራችን ኢንዱስትሪ በተለይም የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪው ዘርፍ ለህዳሴ ጉዟችን ወሳኝ ትርጉም አለው። በመፈጠር ላይ ያለው ቀጣይና ተከታታይ ዕድገት ዘላቂ እንዲሆንና የህዳሴ ጉዟችንን መደላድል ለማስፋት በዕቅዱ ዓመታት የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ዕድገት እንዲያስመዘግብ እየተሰራ ነው። ይህም ለኢኮኖሚው መዋቅራዊ ለውጥ ጉልህ ሚና ይኖረዋል።

የአገር ውስጥና የውጭ ቀጥተኛ በአዳዲስ ኢንቨስትመንቶችም ሆነ በነባር ኢንዱስትሪዎች ውስጥ የምርታማነት የጥራትና የተወዳዳሪነት ደረጃ እመርታና መዋቅራዊ ለውጥ እንዲያመጣ በከፍተኛ ደረጃ ለመስራት ታስቧል። ይህም የወጭ ንግዳችንን ተወዳዳሪ የሚያደርገው ይመስለኛል።

ይህ ለውጥም የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪው ድርሻ በአሁኑ ወቅት ከሚገኝበት በአራት እጥፍ እንዲያድግ በማድረግ ወደ መጀመሪያው የመካከለኛ ጉዞ መንገድ ለመድረስ ለታለመው ዕቅድ ግብ ጉልህ ሚና ይኖረዋል። ዕድገታችንን ለማሳለጥ ለሚደረገው ትግል ቁልፍ ሚናም የሚኖረው ነው።

የኢኮኖሚ ለውጡን ለማምጣት በተለይም ወጣቶችንና ሴቶችን በዚህ ማዕቀፍ ውስጥ በማሳተፍና በላቀ ደረጃ ተጠቃሚ እንዲሆኑ በማድረግ የዕቅዱን ገቢራዊነት ለማረጋገጥ እየተሰራ ነው። እርግጥ መንግስት የወጣቶችንና የሴቶችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በቂት ወራቶች ውስጥ እያከናወና ያለውና በዕቅድ ደረጃ የያዛቸው የተለያያዩ የተጠቃሚነት ማዕቀፎች ተገቢ ናቸው።

ማዕቀፎቹ በጥቃቅንና አነስተኛና መካከለኛ እንዲሁም ለከፍተኛ ኢንዱስትሪዎች ትኩረት የሚሰጡ ናቸው። ይህ ሁኔታም በሁለቱም ዘርፎች ውስጥ ኤክስፖርት መር የኢንዱስትሪ አቅጣጫን ለመከተልና ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ ምርቶችን ለመቀነስ በሚደረገው ሽግግር ውሰጥ የራሱን ሚና መጫወቱ አይቀርም።

ያም ሆኖ ቀሪው የዕቅዱ አፈጻጸም ስኬታማ እንዲሆን አስፈጻሚ መስሪያ ቤቶች ከህዝብ ተወካዩች ምክር ቤት ጋር የስምምነት ውል ተፈራርመዋል። እነዚህ ተቋማት በየመስካቸው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱን የሚያስፈጽሙ በመሆናቸው ህብረተሰቡ ተገቢውን ክትትልና ቁጥጥር በማድረግ አብሯቸው መስራት ይኖርበታል።