Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የለውጥ ኃይሉ

0 636

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የለውጥ ኃይሉ

                                                        ሶሪ ገመዳ

የትኛውም አገር ያለ ህግና ያለ ስርዓት አይኖርም። ያለ ህግና ስርዓት መኖር ውጤቱ ስርዓት አልበኝነት ነው። ስለሆነም ወጣቱ የህግ የበላይነትን ምንነትና ፋይዳውን መገንዘብ አለበት። እንዲሁም ወጣቱ በለውጡ ሂደት ውስጥ ድርሻዬ ምንድነው? ብሎ ራሱን መጠየቅ ይኖርበታ።

እርግጥ የህግ የበላይነት መከበር ጠቀሜታው ለሁሉም የህብረተሰብ ክፍል በተለይም ለወጣቱ መሆኑ ግልጽ ነው። ስለሆነም የአገራችን ወጣት ወንጀለኞችን ከማጋለጥና ለህግ ከማቅረብ ውጪ ራሱ ከሳሽ፣ ራሱ ፈራጅ መሆን የለበትም። የለውጥ ኃይል የሆነው ይህ ወጣት ያመጣው ለውጥ ወደ ኋላ እንዳይቀለበስ የራሱን ሰላም ራሱ መጠበቅ ይኖርበታል። ለዚህም በተመቻቸለት ሁኔታ ከሁሉም በላይ ህግና ስርዓትን አክብሮ እና አስከብሮ ተግባሩን በኃላፊነት ስሜት መወጣት ይገባዋል።

ትናንት የህግ የበላይነት በጥቂቶች ተጣሰ፣ የዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ተገፈፉ…ወዘተ. በማለት ለመብታችን ተመሟግተን ለውጡን ያመጣነው ወጣቶች (ቄሮዎች) ዛሬ ህግና ስርዓትን ተላልፈን የታለልንበትን ጉዳይ መልሰን ልንቃረን አይገባም። በአዲሷ ኢትዮጵያ ውስጥ ህግና የበላይነቱ ጥያቄ ውስጥ የሚገቡ ጉዳዩች አይደሉምና።

ማንኛውም ግለሰብ ወንጀል ሰርቷል ቢባል እንኳን መጠየቅ ያለበት ህግና ስርዓትን በተከተለ አግባብ እንጂ፣ የህግ የበላይነትን በሚጥስና ስርዓት አልበኝነትን በሚያሰፍን መልኩ መሆን የለበትም። ህግና ስርዓት ባለበት ሀገር ውስጥ የህግ በላይነት ሊከበር እንጂ ሊጣስ አይገባም። ስለሆነም ወጣቶች ለህግ የበላይነት ልዕልና በመቆም በአርአያነት ህገ ወጥነትን መታገል ቀዳሚ ተግባራቸው ሊሆን ይገባል።

ወጣቶች የለውጡ ተደማሪዎች ናቸው። የለውጡ ሃይል እነርሱ ስለሆኑ የመደመራቸው ፋይዳ የሚገለፀው የአገራቸውን ህግና ስርዓት በመፈፀምና በማሰፈፀም ነው። የአገርን ህግና ስርዓት በራስ መንገድ በመጻረር ለውጥም ማስኬድ አይቻልም።

በአሁኑ ሰዓት ኢትዮጵያ ውስጥ በህግ ካለተደነገገ በስተቀር፣ የህግ የበላይነትን በመፃረር ለራስ ፍላጎት ማዋል ፈፅሞ አይቻልም። ሃሳቡ በራሱ ነውር ነው። በዶክተር አብይ የሚመራው አዲሱ አመራር ይህን እውን ለማድረግ እየሰራ ነው።

የደቦ ፍረጃና ፍርድ እንዲሁም ያለ ህግ በራስ ፍለጎት ቅጣት ሰጪ መሆን አገራችን ውስጥ ተግራዊ እንዳይሆምን መንግስት ይሰራል። ይህን ስራ የሚያከናውነው ወጣቱ እንዳይጎዳ ከማሰብ በመሆኑ ድጋፍ ሊቸረው ይገባል።

አገራችን ውስጥ ማንኛውም ዜጋ እንቅስቃሴዎች የሚመሩት በህግና በስርዓት ብቻ መሆኑን ግንዛቤ መያዝ ይገባል። ይህ ካልሆነ፤ ማንኛውም ዜጋ የመንቀሳቀሰና የመኖር ዋስትና ሊኖረው አይችልም። ዜጎች የመኖር ዋስትናቸውን ባላረጋገጡባት ሀገር ውስጥ ደግሞ ሰላምና መረጋጋት አይኖርም።

ህግና ስርዓትን ባለመከተል የሚፈጠሩ የህግ የበላይነትን የመጣስ ተግባሮች ሁከትን በማንገስ ዜጎች በንትርክ ተሞልተው ፊታቸውን ወደ ልማትና ዕድገት እንዳያዞሩ ያደርጋሉ።

እርግጥ ወጣቶች ይህ እንዲሆን የሚፈልጉ አይመስለኝም። ፈጽሞ። ስለሆነም የህግ የበላይነትን አለማክበር መዘዝ መልሶ ቀስቱ የሚቀለበሰው በዜጎች ላይ መሆኑን መረዳት ይኖርባቸዋል።

አገራችን ውስጥ ህግና ስርዓት እስካለ ድረስ ወንጀል ፈፅሟል የሚባል ግለሰብ ካለ የሚዳኘው በህግ አግባብ ነው። በደቦ ፖለቲካዊ ፍርድ እየተሰጠ አይደለም። ራስ ወንጃይ ራስ ፍርድ ሰጪ መሆንም አይቻልም። በዚህ መንገድ የሚመራም ሆነ የተመራ ህጋዊ አገር የለም።

እንደዚህ ዓይነት ውጥንቅጡ በወጣበት አገር ውስጥ የኢኮኖሚው ሞተር የሆኑት የግል ባለሃብቶች መዋዕለ ነዋያቸውን በመተማመን ሊያፈሱ አይችሉም። እንዲያውም ዝር አይሉም። ይህም ለወጣቶች ሊፈጠር የሚችል የስራ ዕድል የሚዘጋ ነው።

ስለሆነም በከተሞች፣ በዞኖች፣ በክልሎችና በሀገር ውስጥ ግጭቶችንና ሁከቶች ማራቅ እንዲሁም የህግ የበላይነትን አክብሮና አስከብሮ አካባቢን ለኢንቨስትመንት ምቹ ማድረግ ይገባል።

ይህን በመከወን ረገድ የለውጡ ግንባር ቀደም ተደማሪ የሆኑት ወጣቶች ህግን በማክበርና በማስከበር ቀዳሚ መሆን ይኖርባቸዋል። የህግ የበላይነትን ተጻርሮ መቆም ወጣቶች መስዋዕት ሆነው ላመጡት ለውጥ ፋይዳ ቢስ ነው። በአሁኑ ወቅት እየተፈጸመ ያለውን የፍቅርና የይቅርታ ዘመን አስተሳሰብን የሚወክል አይደለም።

እርግጥ ኢትዮጵያ ውስጥ እየተካሄደ ያለው ለውጥ ማንኛውንም ለመደመር ፍላጎት ያለውን ዜጋ የሚያካትት እንጂ፤ ግለሰቦችንና ቡድኖችን የሚያገል አይደለም። ስለሆነም ወጣቶች ማንኛውም ዜጋ ይሁን ቡድን የመደመሩ አካል እንዲሆን መገፋፋት እንጂ በደቦ ተሳስረው የህግን ልዕልና መጋፋት አይኖርባቸውም።    

በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የሚመራው የለውጥ ሃይል ችግሮችን ለመቅረፍ ከህዝቡ ጋር በመሆን እየሰራ ባለበት በአሁኑ ወቅት የደቦ ፍርድ መኖር የለበትም።

አገራችን በለውጥ አመራሩ አማካኝነት እውነተኛን ዴሞክራሲ ለማስፈን እየጣረች ነው። በዚህም ሳቢያ ስለ ዴሞክራሲ ፅንሰ ሃሳቦች የሚነሱ ጉዳዩች በሁሉም ወኖች በኩል ህፀፆችን መፍጠራቸው አይቀርም።

በዚህም ግልፅነትና ተጠያቂነት ብሎም መቻቻልን የመሳሰሉ የዴሞክራሲ እሴቶችን በተገቢውና በፈጠነ ሁኔታ ገቢራዊ ማድረግ ያስቸግራል። የደቦ ፍርድ እየታየ ያለውም ይህ ሁኔታ በሚገባ ባለመስረፁ ይመስለኛል። ታዲያ ችግሩን ለመከላከል የህግ የበላይነትን ማስፈን ያስፈልጋል። ወጣቶች ደግሞ የዚህ ተግባር ፈጻሚና አስፈጻሚ መሆን አለባቸው።

ምናልባት ከላይ የጠቀስኳቸው ፅንሰ ሃሳቦች አዲስ በመሆናቸውም በአስተማማኝ ሁኔታ ይተገበሩ ዘንድ ጊዜን ምርኩዝ ሊያደርጉ ይችላሉ። ብዥታንም መፍጠራቸው አይቀርም። ለተግባራዊነታቸው ከሂደት መማር የሚቻል ቢሆንም በሂደቱ ውስጥ ግን የህግ የበላይነትን ማረጋገጥ ወሳኝ ጉዳይ ይሆናል። መንግስት የሚያደርገውም ይህንኑ ይመስለኛል።

ወጣቶች በተሳሳተ መረጃም መመራት የለባቸውም። ራሳቸውን ለግጭት ከሚገፋፉ አካላት በማራቅ በለውጡ ስር ሆኖ ልማትንና ዕድገትን ማፋጠን አለባቸው። የትም ቦታ ቢሆን ግጭትንና ሁከትን ለመፍጠር መሞከር እየተከናወነ ያለውን የለውጥ ሂደት ከማሰተጓጎል ውጭ ምንም ትርጉም የለውም።

የህግ የበላይነትን አለማክበርና ከለውጡ ፍላጎት ውጭ አንድን ተግባር ማከናወን ችግሩ መልሶ የሚጎዳው ወጣቶችን ነው። ስለሆነም ወጣቶች ከስሜታዊነት በተቻለ መጠን መራቅና የመረጃዎችን ትክከለኛነት በመፈተሽ የሚፈጠሩ ችግሮች ቢኖሩም እንኳን ህግንና ስርዓትን በተከተለ መንገድ በመፍታት የለውጥ ኃይልነታቸውን ማረጋገጥ ይኖርባቸዋል።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy