Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የመደመር ጉዞው ለጎረቤት ሃገራትም ተርፏል

0 391

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የመደመር ጉዞው ለጎረቤት ሃገራትም ተርፏል

 

ዮናስ

 

የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አሕመድ የመደመር ጽንሰ ኃሳብ ሰፊና ጥልቅ ነው። ከመበታተን ከመከፋፈል ወደ ትናንሽነት ከመለወጥ ተደምረን እንደኖርን ሁሉ አሁንም ያለን ብቸኛው አማራጭ እንደ ሀገር ሁላችንም መደመር ነው። የመደመር ጉዞ ሀገራችንን ወደፊት ያራምዳል።

 

ከመደመር ውጭ ሀገራችንን በአብሮነት በአንድነት በሕብረት ከመታደግ ሌላ አማራጭ የለንም፤ሊኖረንም አይችልም። ያለችን ብዝሀነትን ያቀፈች የብዙ ብሔር ብሔረሰቦች ባሕሎች ኃይማኖቶች ቋንቋዎች ለሁላችንም የጋራ የሆነች ሀገር ናት። ያለን አንድና አንድ እድል በጋራ ሁነን ሀገራችንን ማልማት ማሳደግና መጠበቅ ነው።  

 

የሁሉም ዜጋ ዴሞክራሲያዊና ሰብአዊ መብቶች በእኩልነት የተከበሩባት በነጻነት ያለምንም ተጽእኖ የሚኖሩባት የጋራ ሀገርን በመደመር መንፈስ ማጎልበት ነው የሚገባን። ዘመኑ የመደመር፣ የፍቅር፣ የይቅርታ፣ የምሕረት፣ የመቻቻልና የአብሮነት ነው ሲባል ትርጉሙ ሰፊ ነው። ዛሬም የመደመር መንፈስ የመደመር አላማና ምንነት ያልገባቸው፤ በስም ብቻ ተደምሬአለሁ፤ ተደምራለች፤ ተደምረዋል፤ እያሉ የሚያላግጡ ወገኖችን መስማት የተለመደ ሆኗል።

 

የመደመር ጥልቅ ሀሳብ ከቂም በቀልና ከጥላቻ፣ ለዘመናት ሲያባላን ከነበረው፣ ሲከፋፍልን ከኖረው ክፋት፣ ተንኮልና ምቀኝነት መላቀቅም ነው። መደመር ትናንት በታሪካችን ውስጥ በተደጋጋሚ ሲከሰቱ ከኖሩት ኋላቀር አስተሳሰቦች መናቆሮች ድምርና የተናጠል ጥላቻዎች መውጣት ማለት ነው። መደመር ማለት ዘረኝነትንና ጎጠኝነትን ማውገዝ ብቻ ሳይሆን በማስወገድ ለሰው ልጅ ሰው በመሆኑ ብቻ ለክብሩና ለነጻነቱ ለመብቱ መከበር ዘብ መቆም ነው።

 

መደመር የዜጎች የትም ተንቀሳቅሶ የመኖርና የመስራት ሀብት የማፍራት፤ የመረጡትን የፖለቲካ እምነት በነጻነት የማመን፣ የመከተል መብታቸው በሕገመንግስቱ የተከበረና የተረጋገጠ በመሆኑ በአንድነትና በአብሮነት በመቀጠል ባለን ላይ በመጨመር ወደከፍታው መዝለቅ ማለት ነው። መደመር ማለት ትናንት ከኖርንበትና ዘመናት ከገፋንበት የእርስ በእርስ ሽኩቻ፣ ጥላቻ፣ ትንቅንቅ፣ መጠፋፋት፣ መወነጃጀል፣ የቂም በቀል ኋላቀር ፖለቲካ ሙሉ በሙሉ መውጣት ነው፡፡ ሁሉንም የትናንትን መጥፎ ቅሪቶች በማራገፍና በመርሳት በአዲስ መንፈስ፣ ለአዲስ ሀገራዊ ግንባታ በሰላም፣ በፍቅር፣ በወንድማማችነት እጅ ለእጅ ተያይዘን መነሳት ማለት ነው። ከዚህም በላይ ለጎረቤት መትረፍ ነው።

 

የዶክተር አብይ የመደመር መንግድ ኤርትራ ደርሷል። በበዓል ሲመታቸው ላይ ከኤርትራ ጋር ሰላም እናወርዳል ያሉት ዶክተር አብይ ጉዳዩ በብዙዎች ዘንድ የማይመስል ነው ተብሎ ነበር። ምክንያቱም አገራቱ በሃይማኖት፣ በባህል፣ በቋንቋና በሌሎች በርካታ ነገሮች ቢተሳሰሩም በተፈጠረ የድንበር ግጭት ለድፍን 18 ዓመታት ተራርቀው ነበርና። በተፈጠረው ጦርነት በሁለቱም ወገን ከ70ሺ በላይ ዜጎቻቸውን ተሰውተዋል። የዶክተር አብይ በይቅርታ የመደመር ሀሳብ “ከሰላም እናወርዳለን”ቃል ወደ ተግባር ተሻግሮ ለጎረቤት ሃገራትም ተርፏል።

 

ዶክተር አብይ፤ በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ብዙ ጉጉትና ረሃብ አለ። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በኤርትራ ካሉ ወንድሞች ጋር ማምለክ፣ የኢትዮጵያ ሙስሊሞች በዚያ ካሉ ወንድሞቻቸው ጅምዓ መስገድ በተለይም በኤርትራ ሰፋ ያሉ የካቶሊክ የእምነት ተከታዮች ስላሉ የኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እዚያ ካሉ ወንድሞቻችን ጋር ማምለክ ይፈለጋሉ።የኢትዮጵያ አትሌቶች ምጽዋና አስመራ ለመሮጥ በጣም ተርበዋል። አሁን ግን በሩ ተከፈቷል ማለት ነው።

 

ከኤርትራውያን ወንድሞቻችን ጋር በኢኮኖሚ የሚያስተሳስሩን በጣም በርካታ ነገሮች አሉ። በባህልና በእምነት የሚያስተሳስሩን ነገሮች በርካታ ናቸው። “ከሁሉም በላይ ኢትዮጵያዊያን ፍቅር ተርበናል” ያሉት ዶክተር አብይ ከኤርትራውያን በፍቅር ለመቆራኘት ያለንን ፍላጎት እውን ለማድረግ የሰላሙን ጥያቄ ተቀብለው እነዚህ ታላላቅ ሰዎች በመካከላችን እንዲገኙ ስለፈቀዱ እድሜያቸው እንዲበዛ፤ ፕሬዚዳነት ኢሳይያስ አፈወርቂም ዕድሜያቸው እንዲረዝምና ጤናቸው እንዲበዛ መመኘታቸውን እናስታውሳለን። ማሰሪያው በአዲስ መንፈስና አስተሰሰብ ጠብቋል፡፡ የሁለቱም አገራት መሪዎች ‹‹ከአሁን በኋላ በእነዚህ ህዝቦች መካከል የሚገባ ማንም የለም፡፡ ያንን የሚያስብ ካለም ራሱን ቢሰበስብ ይሻላል›› ሲሉ በመደመረቸው፤ በአንድታቸው የማይደራደሩ መሆናቸውን በህዝቦቻቸው ፊት ቃል ገብተዋል፡፡ የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በሁለቱ አገራት መካከል ያለው ግንኙነት ሰላማዊ ወደሆነ ምዕራፍ መሸጋገር እንዳለበት ያስተላለፈውን ውሳኔ ተከትሎ ከኢትዮጵያ የተዘረጉ የሰላም እጆች የዘንባባ ዝንጣፊ በያዙ እጆች ከአስመራ መንግስት የአጸፋ ምላሽ ማግኘቱን ተከትሎ ከሁለቱ አገራት አልፎ ለቀጠናው ከጥላቻ እና መለያየት ይልቅ አብሮነት፤ አንድነትና ሰላም የገዘፈ ዋጋ እንዳለው በማሳየት አዲስ ምዕራፍ ተከፍቷል፡፡

 

ኢትዮጵያ እና ኤርትራ በጋራ ያጣነውን፤ በጋራ ለማግኘት፤ ስለባለፈውም በጋራ ለፍተን ህዝባችንን ልንክስ ዳግም ወደ ትስስራችን ቃልኪዳን ለመመለስ መንገዱን ጀምረናል ብለዋል፡፡ ትስስሩን ለማደስ ከባለስልጣነት እና የልዑካን ቡድን ጉዞ በዘለለ በአጭር ጊዜ ውስጥ የህብረተሰብ ክፍሎችን ወደ አካተት እንቅስቃሴ ተገብቷል፡፡

ግዙፉ አየር መንገዳችንም እናትና ልጅ፤ ልጅና አባትን ባልና ሚስትን ከሃያ ዓመታት በኋላ ዳግም በማገናኘት ደስታዋ እጥፍ ድርብ ሆኖ ሰንብቷል፡፡ከህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱ በዘለለ በቀጣይ ቀሪዎቹ በአየር ክልሉ የበራራ መስመሮች ስራ ሲጀምሩ የሁለቱ ሀገራት አየር መንገዶች ከሚያደርጉት በረራ በተጨማሪ የሌሎች ሀገራት አየር መንገዶች በመስመሮቹ ስለሚጠቀሙ ለኢትዮጵያም ሆነ ለኤርትራ ኢኮኖሚያቸውን የሚደጉም በረከት ይዞ እንደሚመጣ አያጠራጥርም፡፡

 

በሁለቱም አገራት የሚገኘው ህዝብ የናፈቀውን ቤተሰብ ለመቀበል ቤቱን እንደሚያሰናዳ ሁሉ በመኪና ከሌላኛው ቤታችን አድርሶ ሊያመላልሱን አሊያም በኢኮኖሚ ሊያስተሳስሩን አራት መስመሮች እድፋቸውን አራግፈው፤ ከተጫጫናቸው ድብርት ለመላቀቅ ዳግም በመታደስ ላይ ናቸው፡፡ ከአዲስ አበባ- አስመራ የሚወስዱ በአድግራት-ዘላምበሳ፤ በመቀሌ-አድዋ-ራማ፤ በጎንደር- ሁመራ እንዲሁም በአዋሽ አርባ-ቡሬ-አሰብ የሚወስዱ መንገዶች ተለይተዋል፡፡ የህዝብን እንቅስቃሴ እና የኢኮኖሚ ልውውጦችን ለማሳለጥ በቀጣይ የአዳዲስ አማራጭ መንገዶች ግንባታ ሊካሄድ እንደሚችል የፌዴራል ትራንስፖርት ባለስልጣን ጠቅሷል፡፡ በሁለቱ አገራት መካከል የሰላም አየር መስፈኑን ተከትሎ የተራራቀ ቤተሰብ፤ የተነፋፈቀ ዘመድ-አዝማድ፤ አብሮ አደግ እና ጎረቤት የትዝታ ማቁን ጥሎ ለመገናኘት ቀጠሮ መያዝ ጀምሯል፡፡ ከዚህም በዘለለ አብሮ ስለማደግ እና ስለመበልጸግ አሻግሮ መመልከት ተጀምሯል፡፡

 

አሁን በምስራቅ አፍሪካ የተነሳው የሰላም ማዕበል የአካባቢውን እምቅ የሰው እና የተፈጥሮ ሀብት ወደ ብልጽግና ሊመነዝር፤ ጥላቻን አርቆ ሰብዓዊነትን ሊያነግስ በወንድማማች ህዝብ ይሁንታ አግኝቷል፡፡ ዓለምም ህልም የሚመስለውንና ዳግም እየታደሰ ያለውን ግንኙነታችንን በአገራሞት ዓይኑ ሊመለከት በጆሮው ሊሰማ ተገድዷል፡፡

 

የጥላቻ ግንብን አፍርሶ በሳምንታት እድሜ የትስስር ድልድልይ ለመገንባት የበቃው የሰላም ርምጃ የቁርኝታችንን ኃያልነትና የቁርጠኝነታችንን ጥግ የሚያመላክት ነው፡፡ የነበረው እና ወደፊትም ከወትሮ በተለየ ጠብቆ የሚኖረው ፈርጀ ብዙ ትስስራችን ዛሬን ተሻግሮ ለነገ ስንቅ እንደሚሆን አያጠርጥርም፡፡

 

ወዲህ ስንመለስ ደግሞ መደመር ማለት ኢትዮጵያ ለሁሉም ዜጎችዋ የምትበቃ ሀገር ናትና ያለምንም ልዩነት አንዱም ሳይቀርና ሳይነጠል በጋራ ጸንተን እንቁም፤መለያየቱ፣ መከፋፈሉና መበታተኑ አይበጀንም፤ ይህ ኋላ ቀር አስተሳሰብ ይብቃን ማለት ነው። አንድ ስንሆን አቅም፣ ጉልበትና ብርታት ይኖረናል። እንደ ሀገር እንደ ሕዝብም እንከበራለን። ደካሞች ሆነን ከተከፋፈልንና በሕብረት መቆም ካልቻልን ትርፉ ስደትና ተዋራጅነት ብቻ ነው የሚሆነው። ለሀገራችን እድገትና ብልጽግና ለሕዝባችን ከድህነት መላቀቅና መውጣት የተሻለ ሕይወት መኖር ሁላችንም ተደምረን በአንድነት መቆም ይኖርብናል።

የመደመር ፖለቲካ ከቀደመው ትውልድን ከበላውና ከገደለው ኋላቀር ፖለቲካ ተላቀን የትኛውም አይነት ሀሳቦች በልዩነት እንዲንጸባረቁ እንዲንሸራሸሩ፤ መጠፋፋት መወነጃጀል እንዲቀር፤በውይይትና በምክንያት በመነጋገር ማመን፤ልዩነትን በልዩነት ይዘን ግን ደግሞ ለጋራ ሀገራችን ሁላችንም በሕብረት ተጋግዘን ቆመን መስራትን ይፈልጋል። የአንድ ሀገር ልጆች በፖለቲካ አመለካከት በመለያየታቸው ብቻ እንደጠላት የሚተያዩበት ለመጠፋፋት የሚፈላለጉበት አሳዳጅና ተሳዳጅ፤ ገዳይና ሟች ሁነው ያሳለፉትና የኖሩበት የታሪክ ምዕራፍ መዘጋት አለበት፡፡ በፍቅር በይቅርታ በምሕረት ያለፈውን ሁሉ ትተን ይቅር ብለን በአዲስ መንፈስ ለሀገራችንና ለሕዝባችን ለመስራት በአንድ ላይ መደመር ይኖርብናል፡፡

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy