CURRENT

የቁርጥ ቀን ጀግና – ኢንጂነር ስመኘው

By Admin

August 01, 2018

የቁርጥ ቀን ጀግና – ኢንጂነር ስመኘው

ይቤ ከደጃች ውቤ

ነፍስ ሔር፣ ኢንጂነር ስመኘው በቀለ ሥራቸው የላቀ ስማቸው የደመቀ በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዘርፍ ውስጥ አሻራቸውን አሳርፈው ያለፋ የሀገርና የሕዝብ ኩሩ ሀብት የነበሩ ኢትዮጵያዊ የታታሪነትና አይበገርነት  ተምሳሌት ለመሆናቸው እርሳቸው ቢያርፉም ሕያው ተግባራቸው የሚመሰክረው እውነታ ነው፡፡

በግልገል ጊቤ ቁጥር አንድና ሁለት በዘርፉ በሰሩት ሥራ እና ባሳረፋት አሻራ ምክንያት በታላቁ የሕዳሴ ግድብ ግንባታ በዋና ሥራ አስኪያጅነት ተመርጠው በጉባ በረሃ እየነደዱ ሃገሬን ብለው ከቤተሰቦቻቸውና ልጆቻቸው ርቀው ኢትዮጵያ በድህነት ላይ እያደረገች ላለችው ዘመቻ በመፋለም  የሀገሪቱ የልማት አርበኛ እና የቁርጥ ቀን ጀግና መሆን የቻሉ ፋና ወጊ ሰው ነበሩ፡፡

የረጅም ዓመታት የነጻነት ታሪክ ያላት ኢትዮጵያን እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በጀግንነት ስማቸው ሲጠቀሱ የቆዩት ቅኝ ገዥዎችን በመፋለም ዳር ድንበርን በማስከበር በጦር ሜዳ የተፋለሙ ዜጎቻችን ብቻ ነበሩ፡፡ በስፖርት ሜዳም በተለይ በኦሎምፒክ አደባባዮች ከሻምበል አበበ ቢቂላ ጀምሮ በተለያዩ ሀገሮች በተካሄዱ የኦሎምፒክ የሩጫ ውድድሮች የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ከፍ ብሎ እንዲውለበለብ በማድረግ በወርቃማ ቀለም ለሀገር ምሳሌ ሆነው ስማቸውን ያጻፉ ጀግኖቻችን ይገኙበታል፡፡

ነፍስ ሔር ኢንጂነር ስመኘው በቀለ ግን በጉባ መስክ የቀን ሐሩር የሌሊት ቁር ሳይበግራቸው ድህነትን ለመዋጋት ላለፉት ሰባት ዓመታት ሲሰሩ ቆይተዋል፡፡ ምንም እንኳን የታላቁን የሕዳሴ ግድብ ለመገንባት በሚደረገው ትግል  ሲጥሩ ቆይተው ፍጻሜውን ሳያዩ በድንገት ሐምሌ 19 ቀን 2010 ዓ.ም በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ ማለዳ ላይ ድንገት አርፈው ቢገኙም ስማቸውና ታሪካቸው ግን የማያልፍና ሕያው ነው፡፡

ለዚህ ደግሞ በመስቀል አደባባይ ብቻ የነበረው ለሀዘን የወጣ ህዝብ ብዛት የሥራቸውን ተደናቂነትና ዘላቂነት የሚመሰክርበት ሃቅ ነው፡፡ በኢንጂነሩ ሕልፈተ ሕይወት የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ይስተጓጎላል ይቋረጣል ብለው የሚያስቡ ካሉ ጅሎችና ተላሎች ብቻ ናቸው፡፡

ሚስማር እንጨት ላይ ተደርጎ አናፂ ሚስማሩን በመዶሻ ሲመታው እየጠለቀ ጥብቅ እንደሚለው ሁሉ የህዳሴው ግንባታ ግድብም የበለጠ እየሞቀና እየደመቀ በእልኸኝነት መንፈስ ግንባታው ተጋግሎ ይቀጥላል፡፡ ለግድቡም አስተዋፅዖ የሚያደርጉ ሰዎች ቁጥርም የበለጠ እየጨመረ ይሄዳል፡፡ በሀገራችን ያሉ ዜጎችም ሆነ በውጪ ያሉ ኢትዮጵያውንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ይበልጥና አስተዋፅዖ ለማድረግ መጣር ይገባቸዋል፡፡ ስለዚህ የህዳሴው ግድብ ግንባታ ግለቱ የበለጠ ይጨምራል፡፡

የአሟሟታቻው ሁኔታ ሲታወቅ በፖሊስ ስለሚገለፅ ዜጎች ከስሜታዊነት ተቆጥበው ከረብሻና ሁከት ታቅበው መኖር አለባቸው፡፡ የፍትሕ አካላት ጉዳዩን አጣርተው ተጠርጣሪዎችን ለፍርድ ስለሚያቀርቡ ግለሰቦችና ቡድኖች በስሜታዊነት አደጋ ከማድረስ መታቀብ ያስፈልጋል፡፡ ተጠርጣሪዎችም ካሉ ለፖሊስ መረጃ መስጠት ከዜጎች ይጠበቃል፡፡

እነ እንቶኔ በግድያው እጃቸው ቢኖርበት፣ እነ እከሌ የእነ እንቶኔ አባሪና ተባባሪ ናቸው ተብሎ በሚናፈስ ወሬና አሉባልታ “ዐይንህን ላፈር” መባል የለባቸውም፡፡ የስም ማጥፋት ዘመቻም ሆነ የአካል ጥቃትና የንብረት ውድመት ሊደርስባቸው አይገባም፡፡ ስለዚህ ዜጎች ከስሜታዊነት መታቀብና መቆጠብ ይገባቸዋል፡፡ ንብረት ማውደምም ተገቢ አይደለም፡፡

የታላቁ ሕዳሴ ግድብ መሀንዲስ ነፍስ ሔር ኢንጂነር ስመኘው በቀለ ቢያልፉም እንኳ ግንባታው ይቀጥላል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በሰሜን አሜሪካ በዋሽንግተን ዲሲ ለሚገኙ ኢትዮጵያውያን  እንደተናገሩት “ኢንጂነር ስመኘውን መግደል እንጂ ግንባታውን ማቆም አይቻልም፡፡” ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለው እንደገለፁት መግደል መሸነፍ ነው፡፡ ማህፀነ ለምለም የሆነችው ኢትዮጵያ ባሏት ዩኒቨርሲቲዎች ብዙ ኢንጂነሮችን እያፈራች ስለሆነ መካን አትሆንም፡፡

ኢንጂነር ስመኘው እንደ አክሱም ሐውልት፣ እንደ ፋሲል አብያተ መንግሥት፣ እንደ ጀጎል ግንብ ዘመን ተሻጋሪ የሆነ የምህንድስና ሙያቸውን ተክተውና ተክለው አልፈዋል፡፡ እሳቸው ቢያልፋም የሕዳሴው ግድብ አሁን ለደረሰበት ደረጃ ሙያዊ ሚናቸው የጎላ ነው፡፡ በኤሌክትሪክ ኃይል ዘርፍ ትተው የሄዱትን ሥራ እኛም ተረክበን በማስቀጠል ፍቅራችንን፣ ኅብረታችንን፣ አንድነታችንንና መደመራችንን በተግባር ማሳየት አለብን፡፡ የሕዳሴው ግድብ ግንባታ በተጋጋለ መንፈስ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት፡፡ እናት ሀገሬን ቤቴን የሚሉ ዜጎች ሁሉ ለግድቡ ከባንኮች ቦንድ በመግዛት ሆነ የገንዘብ አስተዋፅዖ በማበርከት የዜግነት ግዴታችንን መወጣት አለብን፡፡

ነፍስ ሔር፣ አንጂነር ስመኘው በቀለ ግድቡን ለመጎብኘት ወደ ጉባ ለሚሄዱ ዜጎች ሁሉ ባለስልጣናት፣ ዲፕሎማቶችም ሆነ ለመንግሥት ሠራተኞች ታከተኝ፣ ደከመኝ፣ ሳይሉ በቅን ልቦና በትሁት ሰብዕና በማስረዳት አመርቂ የተግባቦት ሥራ ከውነው አልፈዋል፡፡ የቀብራቸውም ሥነ ሥርዓት ለአንድ ብሔራዊ ጀግና በሚደረግ መልኩ የተካሄደ ነበር፡፡

ታታሪው ኢንጂነር ስመኘው በቀለ ግድቡን ለመጎብኘት ለሚሄዱ ዜጎች “ከፍትፍቱ ፊቱ” እንደሚባለው ብሩህ ተስፋ በሚነበብበት እንደ ስልሳ ሻማ በሚያበራውና ፈገግታ በሚታይበት ፊታቸው መረጃ ለመስጠት ሲጥሩ ነበር፡፡ ኢንጂነሩ የግድቡን ሥራ እየመሩና ለመገናኛ ብዙሃንና ለጎብኝዎች መረጃ እየሰጡ በመሥራታቸው “በአንድ ወንጭፍ ሁለት ወፍ” እንደሚባለው ድርብ ጀግና እና የልማት አርበኛ መሆን የቻሉ የኢትዮጵያ ኩሩ የቁርጥ ቀን  ልጅ ነበሩ፡፡

ዜጎቻችን የንግዱ ማኅበረሰብ፣ የመንግሥትና የግል ድርጅቶች ተቀጣሪዎች፣ በውጪ ሃገር ያሉ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ግንባታውን በግለት ለማስቀጠል የበኩላቸውን አስተዋፅኦ ማበርከት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ድህነትን መዋጋትና ማስወገድ የምንችለው “ድር ቢያብር አንበሣ ያስር” እንደሚባለው ስንተባበር ነው፡፡ ኢትዮጵያ የጥቁር ህዝቦች የነጻነት ተምሳሌት የአፍሪካ ህብረትና በተመድ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ጽህፈት መሆን የቻለችው ልዩነታችንን ወደ ጎን ጥለን ሀገራችንን ብለን የውጪ ወራሪዎች ማስወገድ በመቻላችን ነው፡፡ አሁንም በመደመር መንፈስ የህዳሴውን ግድብ እናፋጥን፡፡ ባለፈው እሁድ መጋቢት 22 ቀን 2010 ሥርዓተ ቀብራቸው በመንበረ ፀባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል በተከናወነበት ወቅት  ፓትርያርኩ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ እንደተናገሩት “ጉሬዛን መግደል የግፍ ግፍ፤ ምግቡ ቅጠል ነው ኑሮው በዛፍ፤ እርግጥ ነው፤ ጉሬዛ ኑሮው ዛፍ ላይ ነው፡፡ የዛፍ ቅጠል ይበላል እንጂ እንደ ዝንጀሮ የሰው ሰብል አያወድምም፡፡ ሰላማዊ እንስሳ በመሆኑ ይህንን እንስሳ መግደል ከግፍ በላይ ግፍ ነው፡፡ ባለችኝ እውቀት እንደምረዳው አንጂነር ስመኘው ሰላማዊና ሰውን የሚጋፉ ሰው አልነበሩም፡፡ ከምንም በላይ ደግሞ ህዳሴ ግድብን የሚያህል ግዙፍ ፕሮጀክት እየመራ ፍፁም ትዕቢትና ጉራ የማይታይበት ሙያተኛ እንጂ ፖለቲከኛ አልነበረም፡፡ እናም እንዲህ ዓይነት ሰው መግደል የግፍ ግፍ ነው፡፡” ብለው ነበር፡፡