Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የቦምብ ፍንዳታውን ያስተባበሩት የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት ባልደረቦች መሆናቸውን ፖሊስ ለፍርድ ቤት ተናገረ

0 1,387

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

 

የቦምብ ፍንዳታውን ያስተባበሩት የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት ባልደረቦች መሆናቸውን ፖሊስ ለፍርድ ቤት ተናገረ

ለሁለት ሰዎች ሕልፈትና ከ100 በላይ ለሆኑ ሰዎች ከባድና ቀላል የአካል ጉዳት ምክንያት የሆነውን የቦምብ ፍንዳታ ጥቃት ያስተባበሩት፣ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት ተቋም የፀረ ሽብር ግብረ ኃይል ማስተባበሪያ መምርያ ኃላፊ አቶ ተስፋዬ ኡርጌና የተቋሙ ግብረ አበሮቻቸው እንደሆኑ መርማሪ ፖሊስ ለፍርድ ቤት አስረዳ፡፡

ለጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ድጋፍና ምሥጋና ለማቅረብ፣ ሰኔ 16 ቀን 2010 ዓ.ም. በመስቀል አደባባይ ለድጋፍ ወጥተው በነበሩ ሰዎች ላይ የቦምብ ጥቃት መሰንዘሩ ይታወሳል፡፡

በቦምብ ጥቃቱ እጃቸው አሉበት ተብለው ከተጠረጠሩት ውስጥ፣ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት የፀረ ሽብር ግብረ ኃይል ማስተባበሪያ መምርያ ኃላፊ አቶ ተስፋዬ አንዱ ናቸው፡፡ ተጠርጣሪው በቁጥጥር ሥር ውለው ምርመራ ከተጀመረባቸው 43 ቀናት (እስከ ነሐሴ 17 ቀን 2010 ዓ.ም. ድረስ) ተቆጥረዋል፡፡ በቁጥጥር ሥር አውሎ ምርመራ እያደረገባቸው የሚገኘው የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ፣ ከአንድ ሳምንት በፊት ፍርድ ቤት አቅርቧቸው ምርመራውን እንዳልጨረሰ አስረድቶ ተጨማሪ 14 ቀናት እንዲፈቀድለት ጠይቆ ነበር፡፡ ፍርድ ቤቱ ግን ሰባት ቀናት እንደሚበቃው በማስታወቅ ፈቅዶለት ነበር፡፡

መርማሪ ቡድኑ ሐሙስ ነሐሴ 17 ቀን 2010 ዓ.ም. ቀርቦም በተፈቀደለት ሰባት ቀናት ውስጥ የሠራውን ካስረዳ በኋላ፣ ለተጨማሪ ምርመራ 14 ቀናት ጠይቋል፡፡  በምክንያትነት ደግሞ አቶ ተስፋዬ የሰኔ 16 ቀን የቦምብ ፍንዳታ ከእሳቸው በታችና ከበላያቸው ካሉ የተቋሙ ባልደረቦች ጋር በግብረ አበርነት ማስተባበራቸውን ገልጿል፡፡ በመሆኑም በማስተባበር የተሳተፉት ግብረ አበሮች ስላልተያዙ ተጨማሪ ጊዜ እንደሚያስፈልገውም አክሏል፡፡

ተጠርጣሪው አቶ ተስፋዬ ሌላም የሚጠረጠሩባቸው የወንጀል ድርጊቶች እንዳሉ የጠቆመው መርማሪ ቡድን፣ በአሁኑ ጊዜ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች በተቀሰቀሱ ግጭቶች መጠርጠራቸውን አስታውቋል፡፡ ከዚህ ጥርጣሬ ጋር በተገናኘም ቤታቸው ሲፈተሽ ቦምብና የጦር መሣሪያዎች መገኘታቸውንም አክሏል፡፡ ሌላም የጦር መሣሪያ እንዳለ ጥቆማ እንደደረሰው በመግለጽ፣ የጠየቀው 14 ቀናት እንዲፈቀድለት በድጋሚ ጠይቋል፡፡

የተጠርጣሪው ጠበቃ እንደገለጹት፣ ፖሊስ በተደጋጋሚ እያቀረበው ያለው ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ መጠየቂያ ሐሳቡ ተመሳሳይ ነው፡፡ ደንበኛቸው ከተያዙ 43 ቀናት ስለሆናቸው፣ በዚህ ጊዜ ውስጥ ምርመራውን አጠናቆ መቅረብ እንደነበረበት በመግለጽ፣ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ መጠየቁ አግባብ እንዳልሆነ አስረድተዋል፡፡ ደንበኛቸው ተጠርጥረው የተያዙት ከሰኔ 16 ቀን የቦምብ ፍንዳታ ጋር በተያያዘ ቢሆንም፣ መርማሪ ቡድኑ ግን ለፍርድ ቤቱ እያስረዳ ያለው በሌላ ወንጀል መጠርጠራቸውን መሆኑንም ጠበቃው አክለዋል፡፡ ይህም ትክክል እንዳልሆነና መርማሪ ፖሊስን ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባው መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

ፍርድ ቤቱ በመሀል ገብቶ መርማሪ ቡድኑ አቶ ተስፋዬ የተጠረጠሩበትን ወንጀል ‹‹ግድያ ነው? ወይስ ተሳትፎ?›› ብሎ በመጠየቅ እንዲያብራራ ዕድል ሰጥቷል፡፡ መርማሪ ቡድኑ በሰጠው ምላሽ አቶ ተስፋዬ የተጠረጠሩት በሰኔ 16 ቀን የቦምብ ፍንዳታና በአሁኑ ጊዜ በአገሪቱ የተለያዩ ቦታዎች እየተከሰቱ ባሉ ግጭቶች መሆኑንም አስረድቷል፡፡

የተጠርጣሪው ጠበቃ በድጋሚ ሲያስረዱ፣ በሰኔ 16 ቀን የቦምብ ፍንዳታ የተጠረጠሩ ሰዎች ምርመራቸው ተጠናቆ ክስ ተመሥርቶባቸዋል ብለዋል፡፡ ደንበኛቸውም የተጠረጠሩት በተመሳሳይ ድርጊት በመሆኑ ሊከሰሱ ወይም በነፃ ሊሰናበቱ ሲገባ፣ ሌላ ወንጀል እየተፈለገባቸው ሊታሰሩ አይገባም ብለዋል፡፡ የዋስትና መብታቸው ሊጠበቅላቸው እንደሚገባም አክለዋል፡፡

መርማሪ ቡድኑ የዋስትና ጥያቄውን እንደሚቃወም አስረድቶ፣ ጠበቃው በሌሎች ላይ ክስ ተመሥርቷል ያሉት ከእውነት የራቀ መሆኑን፣ በማንም ላይ ክስ እንዳልተመሠረተ በማስረዳት የጠየቀው ተጨማሪ የምርመራ ቀናት እንዲፈቀድለት ጠይቋል፡፡

የግራ ቀኙን ክርክር የሰማው የፌዴራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አንደኛ ተረኛ ወንጀል ችሎት በሰጠው ትዕዛዝ፣ የፖሊስ የምርመራ መዝገብ እንደሚያስረዳውና መርማሪ ፖሊስ ያስረዳው የወንጀል ድርጊት ነገሩን ወደ ሽብር ተግባር ሊወስድ የሚችል ከባድ ድርጊት እንደሆነ መረዳቱን በመግለጽ፣ የተጠየቀውን ዋስትና ውድቅ አድርጎ መርማሪ ፖሊስ የጠየቀውን 14 ቀናት በመፍቀድ ለጳጉሜን 1 ቀን 2010 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy