የተጀመረው የፖለቲካ ሪፎርም/ሽግግር ዋስትናው ምንድን ነው?
ክፍል አንድ
እንደ መግቢያ
ሃንቲነግተን የተባለው የፖለቲካ ሳይንስ ምሁር “The Third wave of Democracy” በሚባለው መጽሃፉ የፖለቲካ ሽግግር በማንኛውም ሀገረ – መንግስት ወይም ሀገር ውስጥ ከኢ – ዴሞክራሲዊነት ወደ ዴሞክራሲያዊነት የሚደረግ የለውጥ ሂደት ነው ይላል፡፡
ዞሮ ዞሮ የፖለቲካ ሽግግር ወይም ሪፎርም ከእርስ በርስ ጦርነት ወይም ከማህበራዊ ቅራኔዎች በኋላ የሚከሰት እንደሆነ የተለያዩ ምሁራን ይገልጻሉ፡፡ ለምሳሌ Nifosi(2003) ማህበራዊ ቅራኔ የስልጣን ክፍፍልን በተለይ ማን ምን አገኘ፣ በምን ደረጃ እና ለምን ያህል ጊዜ በሚሉት ጥያቄዎች ዙርያ ከሚሰጡ ምላሾች ወይም አረዳዶች የሚመነጭ ነው ይላል፡፡
ቅራኔው የሚፈጠረው ሥልጣንን ፍትሃዊ ባልሆነ መንገድ ተቆጣጥረዋል በሚባሉት እና ከስልጣን ተገለናል በሚሉት ቡድኖች እና ግለሰቦች መካከል ነው፡፡ በመሆኑም የፖለቲካ ሽግግር ሂደት የዜጎችን ፖለቲካዊ ተሳትፎ የሚያጎለብት፤ የፖለቲካ ፉክክር ህግጋቶች፣ዘዴዎች እና የመንግስት ስልጣን ለመያዝ የምንጠቀምባቸው አካሄዶች የሚቀየሩበት፤ እንዲሁም በፖለቲካ ውስጥ በርካታ ተዋንያን ወደ ሚሳተፉበት ስርዓት እና የመንግስትን ስልጣንና ሀብት የተቆጣጠሩት ተዋንያን ማንነት መለወጥን ሊያስከትል የሚችል መሆን አለበት፡፡ ይህ ደግሞ የእሴቶች፣ ልማዶች፣ ህጎች፣ እና የተቋማት መሻሻልን ወይም እንደ አዲስ መተካትን የግድ ይላል፡፡
አስቻይ ሁኔታዎች
በአንድ የፖለቲካ ሪፎርም ሂደት ውስጥ በርካታ ተዋናዮች አሉ፡፡ የእነዚህ ተዋንያን ጥንካሬ፣ ሚና እና አሰላለፍ በሚደረገው የፖለቲካ ሪፎርም/ሽግግር ላይ በአወንታዊም ይሁን በአሉታዊ መንገድ ተጽዕኖ ማሳደሩ አይቀርም፡፡
ስለዚህ አሁን በሀገራችን ከተጀመረው ለውጥ አንጻር የእነዚህን ተዋንያን አሰላለፍ እና ሚና መረዳት የለውጡን ሁኔታ ለመረዳት ወሳኝ በመሆኑ የዚህም ጽሁፍ ትኩረት በእዚሁ ጉዳይ ላይ ይሆናል፡፡
- የለውጡ ባለቤት መላው ህዝብ መሆኑ
ባለፉት ሀምሳ አመታት ብቻ በዓለማችን 90 ሀገሮች የፖለቲካ ሽግግር ለማድረግ ሞክረዋል፡፡ ከነዚህ መካከል 46 በመቶ የሚሆኑት በተሳካ ሁኔታ ወደ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ተሸጋግረዋል፤ 39 በመቶ አልተሳካላቸውም፤ 15 በመቶ ቀስ በቀስ ወደ ዴሞክራሲ ተቀይረዋል፡፡ ያልተሳካላቸው አብዛኛዎቹ ለውጡን በእርስ በርስ ጦርነት እና በመፈንቅለ መንግስት ለማምጣት የሞከሩ ናቸው፡፡ በአንጻሩ ከተሳካላቸው መካከል አብዛኛዎቹ በሰላማዊ የህዝብ እምቢተኝነት እና በዚህም ግፊት በውስጠ – ፓርቲ ትግል ለውጡን የጀመሩ እና የመሩ ናቸው፡፡
የእኛም የፖለቲካ ሽግግር በህዝብ ግፊት በገዢው ፓርቲ ውስጠ – ትግል እየተመራ ያለ ነው፡፡ የሀገራችን ህዝብ ምንግዜም ለዴሞክራሲ፣ ለእኩልነት እና ለሰላም የሚያደርገው ትግል እንደየጊዜው ተጨባጭ ሁኔታ ጠንከር – ደከም እያለ ቢቆይም ሁሌም ግን ይህን ፍላጎቱን ያልገለጸበት እና ያልታገለበት ጊዜ የለም፡፡ አሁን እየታየ ያለው ለውጥም ሕዝብ በተለያየ መንገድ ታግሎ ያመጣው እንጂ የአንድ ወይም የሌላ ፓርቲ ችሮታ አይደለም፡፡ ስለዚህ የለውጡ ባለቤት መላው ህዝብ ነው፡፡ ለውጡን የሚጠብቀውና የሚያስቀጥለውም ያው ህዝብ ነው፡፡ በመሆኑም ለውጡን ለመቀልበስ መሞከር የኢትዮጵያን ህዝብ ፍላጎት ለመደፍጠጥ መሞከር ነው፡፡ ከዚህም በላይ ታግለው ከማያሸንፉት ህዝብ ጋር ጦርነት መግጠም ነው፡፡ ህዝብን ደግሞ ከቶ ማሸነፍ አይቻልም፡፡ ከዚህ በመነሳት ለውጡ ይቀለበሳል ብሎ ማሰብ የህዝብን ሃይል ማሳነስ እና ነባራዊ ሁኔታውን አለመረዳት ይሆናል፡፡
ከላይ እንዳየነው የለውጡ ባለቤት ህዝቡ ነው ካልን የተለያዩ ህዝባዊ እና ሲቪል ማህበራት የተሻለ ሚና እንዲጫወቱ እድል ይፈጥርላቸዋል፡፡ ብዙ ጊዜ የለውጥ እንቅስቃሴው ከላይ ሲጀመር ሲቪል ማህበረሰቡ በመረጠው እና በፈለገው መንገድ ፍላጎቶቹን ለማንጸባረቅ እና ለመሳተፍ ሊከብደው ይችላል፡፡ ይሁንና አሁን በኢትዮጲያ እየተስተዋለ ያለው ለውጥ ከታች የመጣ (From below) ስለሆነ ህዝባዊ ማህበራት ለሲቪል ማህበረሰቡ አመቺ ሁኔታን የፈጠረ ነው፡፡
ይህም ማለት ዜጎች በየአደረጃጀታቸው ለውጡን ለመደገፍ እና ለማሳለጥ ምቹ ምህዳር ስለሚያገኙ ፍላጎታቸውን በነጻነት በማራመድ በተቋሞቻቸው በኩል ሕዝባዊ ግንኙነቶች እንዲጎለብቱ እና የጋራ መግባባት እንዲፈተር ሚናቸው የጎላ ይሆናል፡፡
- ተቃዋሚው (ተፎካካሪው)
ለውጡ ከታች ሲሆን ልክ እንደ ህዝባዊ እና ሲቪል ተቋማቱ ሁሉ ተቃዋሚዎችም በሚገባ ለመሳተፍ እድል ያገኛሉ፡፡ በዚህም ለውጡ ውስጥ ድምጻቸው እና ፍላጎታቸው እንዲካተት በማድረግ እንዲሁም ከለውጡ ጋር ራሳቸውን በማስማማት የለውጥ ሃይል እንዲሆኑ ያስችላል፡፡
እዚህ ላይ ልብ ሊባል የሚገባው ጉዳይ የተፎካከሪ ፓርቲዎችን ሚና የሚውስኑ ጉዳዮች የሚደረገው ድርድር ባህሪ፣ የፖለቲካ አመራሩ ጥራት እና ክህሎት፣ እና የተቃዋሚው እንቅስቃሴዎች ናቸው፡፡ ከዚህ በመነሳት የሚከተሉት ሶስት ቢሆኖች ሊከሰቱ ይችላሉ፡፡
- ደካማ ተፎካካሪ/ተቃዋሚ ፓርቲዎች ባሉበት ሁኔታ ገዢው ፓርቲ ሪፎርሙን ሰፋ ባለ ነጻነት እንዲመራ እድል ሊያገኝ ይችላል፡፡ በእንዲህ ያለ ሁኔታ ውስጥ ሪፎርም የሚያካሂዱ ሀገሮች ከሪፎርም አልፈው ዴሞክራሲያዊ ስርዓት እስከ መመስረት ሊደርሱ ይችላሉ፡፡ በዚህም ምክንያት ሪፎርሙን ያካሄደው ፓርቲ በስልጣን ላይ የመቆየት እና የሚገነባውን ስርዓት የመወሰን አድል ያገኛል፡፡
- ገዢውና ተቃዋሚዎች በመተባበር የሚመሩት ሪፎርም የሚያሳትፍ ሽግግር ሲሆን በፓርቲዎች መካከል ድርድር ይኖራል፡፡ ይሁን እና በዚህኛውም ሁኔታ ቢሆን ገዠው ፓርቲ ላቅ ያለ ሚና መጫወቱ አይቀርም፡፡
- ሶስተኛው ገዢው ፓርቲ ፍጹም አምባገነናዊ የሆነ እና ሪፎርሙን የሚቃወምበት ሁኔታ ነው፡፡ ይህ ሁኔታ ተቃዋሚዎቹን ይበልጥ በመግፋት እንዲጠናከሩ እና አዲስ መንግስት አቋቁመው ሪፎርም የሚያካሂዱበት ይሆናለ፤ ማለት ነው፡፡ በዚህ ጊዜ ገዢ የነበረው ፓርቲ በሪፎርሙ ላይ የሚኖረው ሚና አነሰ ያለ ይሆናል፡፡
ከመጀመርያውና ከሁለተኛው ቢሆኖች አንዱ የሚከሰት ከሆነ ወደ ዴሞክራሲ የሚደረገው ሽግግር የተሳካ የመሆን እድሉ ከፍተኛ ነው፡፡ ነገር ግን ሶስተኛው ቢሆን ከተከሰተ ሽግግሩን አጠያያቂ ሊደርገው ይችላል፡፡
በተጀመረው ለውጥ ነባራዊ ሁኔታ ሊከሰት የሚችለው ወይም እየተከሰተ ያለው የትኛው ቢሆን ነው የሚለውን ለመወሰን በለውጥ አራማጁ አካል እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎችን መመለከቱ ጠቃሚ ነው፡፡
- ገዢው ፓርቲ ውስጥ ለውጡን በፊትአውራሪነት መምራት የጀመሩት ጠቂቶች ቢሆኑም አሁን ላይ አብዛኛው የፓርቲ አባላት የለወጡ ጠበቃ ወደ መሆን እየተሸጋገሩ መሆኑ እየታየ ነው፡፡
- ሁሉም የተቃዋሚ/ተፎካከሪ ሀይሎች ለሀገራቸው ቅን የሚያስቡ እና ሀገር ወዳድ ስለሆኑ በሰላማዊ መንገድ በሚደረገው ክርክር፣ ድርድር እና ውይይት በመሳተፍ የለውጡ አካል እንዲሆኑ ጥሪ ቀርቧል፡፡ ምላሹም እጅግ በጣም አርኪ ነው፡፡ ሁሉም በሚባል ደረጃ ወደ ሰላማዊው ፖለቲካ በመቀላቀል የለውጡ አካል ለመሆን ጥረት እያደረጉ ነውና፡፡
- በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል ድረድሮች በስፋት እተካሄዱ ነው፡፡ የድርድሮቹ መንፈስ ደግሞ ለውጡን በመደፍ የተቃኘ ነው፡፡ ይህ እንዳለ ሆኖ ግን አሁንም በተሻለ የመፎካከር ብቃት ላይ ናቸው ለማለት ባያስደፍርም ወደዛው የሚወስዳቸውን የመዋሃድ፣ መጣመር ወዘተ ድርድሮች በማከሄድ ላይ ያሉ በርካቶች ናቸው፡፡
ከእነዚህ ሁኔታዎች በመነሳት በተግባር እየሆነ ያለውን ሁኔታ ስንገመግም የመጀመርያው እና ሁለተኛው ቢሆኖች እየተከሰቱ አንደሆነ የሚያመላክት ሆኖ እናገኘዋለን፡፡
- የፀጥታ እና ደህንነት ኃይሉ
በዴሞክራሲዊ ሽግግር የታጣቂ ሀይሉ ሚናው በሁለት መልኩ ነው፡ አንድም ለውጡን በማደናቀፍ አለያም ለውጡን በመደገፍ የለውጡ አጋዥ ይሆናል፡፡ አሁን በተጨባጭ እየሆነ ያለው የትኛው ነው?
የጸጥታ መዋቅሩ እንደ አካል ከፍተኛ ሀገራዊ እና ህዝባዊ ተልዕኮዎችን ሲወጣ የቆየ እና አሁንም እየተወጣ ያለ ነው፡፡ ይሁንና የተወሰኑ በአመራር አካባቢ ተቋማቱን የፖለቲካ ማስፈጸሚያ እና በፓርቲ ውስጥ ለሚከሰቱ ፖለቲካዊ ልዩነቶች ለአንዱ አካል ወገንተኛ የመሆን አዝማሚያ ይስተዋል ነበር፡፡ ይህ ደግሞ የጸጥታ አካላቱ ሚና ወደ አደናቃፊነት እንደያዘነብል በር ከፋች ነው፡፡
ይህን የተረዳው የለውጡ አመራር የጸጥታና የመከላከያ ተቋማትን ፖለቲካዊ ወገንተኝነት ለማስቀረት/ለመቀነስ የሚያስችሉ እቅዶችን አውጥቶ ቁልፍ ለውጦችን ለማስተዋወቅ ሥራ ጀምሯል፡፡ በዚህም አፈናን የሚያቋቁሙ አሠራሮችን፣ ሕጎችንና የፍትሕ ተቋማትን ለመለወጥ የሚያስችል በከፍተኛ ፍጥነት እየተሰራ በመሆኑ አመርቂ ውጤቶች ማየት ተጀምሯል፡፡ ለምሳሌ በቅርቡ በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ተከስቶ የነበረው ችግር የተፈታበት እና እየተፈታ ያለበት መንገድ ይህንኑ የሚያመላክት ነው፡፡
ከዚህ በመነሳት ይህ ሀይል አደናቃፊ ሳይሆን የለውጡ አጋር ሆኖ እንደሚቀጥል በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል፡፡
- ዓለምአቀፋዊ ሁኔታ
ምንም እንኳን በኢትዮጵያ የሚካሄደው የዴሞክራሲ ግንባታ ሂደትና ሽግግር የኢትዮጵያውያን ውሳኔ ብቻ መሆኑ የሚታወቅ ቢሆንም ውጫዊ ሁኔታው ለውጡን ማደናቀፍ ባይችል እንኳን በማዘግየት ወይም በመደገፍና በማፍጠን በኩል የራሱን ሚና ሊጫወት ይችላል፡፡ ከዚህ አንጻር የለውጡ መሪዎች ከተለያዩ ሀገራት እና ተቋማት ጋር ያደረጓቸው ግንኙነቶች እና በዚህም የተገኘው ምላሽ አለምአቀፋዊ ሁኔታው ከአደናቃፊነት ይልቅ ደጋፊነቱ እንዲጎላ አድርጓል፡፡
ማጠቃለያ
በሂደታዊ ለውጥ የሚያመጣ ዴሞክራሲያዊ ሽግግር ለውጡን ሊቀለብሱ የሚችሉ ሃይሎችን አቅም እየቀነሰ ስለሚሄድ ግጭትና አላስፈላጊ አሉታዊተጽኖዎችን የመቀነስ አቅም አለው። ስለዚህ በድርድር፣ በመግባባት፣ ሰጥቶበመቀበልና በይቅርባይነት ላይ የሚመሰረት ፖለቲካዊ ሽግግር የአብዛኛውን ወገን ይሁንታ የሚያገኝ በመሆኑ የሚገነባው ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ዘላቂና አስተማማኝ የመሆን እድሉ ከፍተኛ ነው። በመሆኑም ተቃዋሚ ሃይሎች እርስ በርስ ከመሻኮት ወጥተው በጋራ አቋሞቻቸው ላይ በማተኮር ሃይል የማሰባሰብ፣ የማደራጀት፣ የጠራ መስመር ለሚያዝ የሚያስችል እድልና ምቹጊዜ ይፈጥርላቸዋል።
እንዲህ አይነት አካታች የለውጥ ጉዞ ደግሞ መሰረቱ የጸና ማንም የማይደፍረው በመሆኑ ለውጣችን በአስተማማኝ ደረጃ ይሰካል ማለት ነው፡፡ እናም ለውጡ አይቀሬ መሆኑን አውቀን በሰከነና በጠራ መንገድ ይራመድ ዘንድ ሁላችንም የለውጡን አመራር በትዕግስት እና በቁርጠኝነት ልንደግፈው ይገባል፡፡
ይህን የትግል ምዕራፍ በስኬት የማጠናቀቁ ሥራ ከመቸውም በላይ በአብሮነት፣ በፅኑቁርጠኝነትና አስፈላጊውን መስዋትነትም ለመክፈል ዝግጁ ሆኖ በመገኘት ላይ የሚወሰን መሆኑን ከልብ አመኖና ተቀብሎ መራመድ የግድ ይላል።
እንደሚታወቀው በአገራችን የፖለቲካ ልሂቃን መካከል ከፍተኛ አለመግባባትና ክፍፍል የፈጠሩ አጀንዳዎች አሉ፡፡ የታሪክ ባለሙያዎች እንደሚነግሩን፣ ከቀደመው የኢትዮጵያ ምስጢራዊ ባህል ላይ ከ1960ዎቹ ወዲህ በአገራችን ነግሶ የቆየው ሌኒኒስትና ስታሊኒስታዊ አስተምህሮ የፖለቲካ ጥያቄዎችን በሰለጠነ መልኩ ተወያይቶና ተከራክሮ ከመፍታት ይልቅ፣ የተለየ ሐሳብ የሚያራምደውን ወገን በኀይል ጸጥ የማሰኘት፣ ጥላሸት የመቀባትና አላስፈላጊ ስም የመስጠት አካሄድን የተከተለነው፡፡ ይህኢዴሞክራሲያዊ ባህል ከአርባ ዓመታት በላይ የአገራችንን ፖለቲካ ተቆጣጥሮት ቆይቷል፤ በዚህም ምክንያት የውይይትና የክርክር ባህላችን ሳይዘምን እዚህ ደርሰናል፡፡ አንዱ፣ ምናልባትም ዋነኛው የአገራችን የዴሞክራሲ ሽግግር ደንቀራ ይህ የፖለቲካ ልሂቃኑ ኢዴሞክራሲያዊ ባህልነው፡፡ የዴሞክራሲ ሽግግሩ የሰመረ እንዲሆን ካስፈለገ የፖለቲካ ልሂቃኑ ቆሞ-ቀርነት መሠረታዊ ሊባል በሚችል መልኩ መስተካከል አለበት፡፡