Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የተጀመረው የፖለቲካ ሪፎርም/ሽግግር ዋስትናው ምንድን ነው?

የተጀመረው የፖለቲካ ሪፎርም/ሽግግር ዋስትናው ምንድን ነው? የተጀመረው የፖለቲካ ሪፎርም/ሽግግር ዋስትናው ምንድን ነው?

0 1,079

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የተጀመረው የፖለቲካ ሪፎርም/ሽግግር ዋስትናው ምንድን ነው?

 

ክፍል ሁለት

መግቢያ

ኢህአዴግ በ27 ዓመታት የመንበረ ሥልጣን ዘመኑ የሰራቸው የልማት ሥራዎች ስለመኖራቸውና የሀገራችንም ምጣኔ ሀብት ዕድገት ስለማሳየቱ የሚጠራጠር አካል ባይኖርም በአንጻሩ ደግሞ የተሰጣቸውን ሀገራዊ ሃላፊነት ተጠቅመው የግል ጥቅማቸውን ሲያጋብሱ የነበሩ መንግሥት አካላት በመኖራቸው በአገሪቱ  ሌብነት ፣ግለኝነት፣ ቡድነኝነትና ዘረኝነት እንደተንሰራፋ መንግስት እራሱ አምኖ ንሰሀ ገብቷል፡፡ እነዚህ ከቀበሌ እስከ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት በመንግስት ጉያ ውስጥ የተሸጎጡት አካላት በፈጠሩት ችግር ምክንያት ከቅርብ አመታት ወዲህ የህዝቦች ቅሬታና ተቃውሞ ተቀስቅሶ እንደነበር የሚታወቅ ነው ፡፡ ኢህአዴግ የህዝቡን ጥያቄ ለመመለስ ለ17 ቀናት ቁጭ ብሎ ከመከረ በኋላ የነበሩበትን ችግሮች ነቅሶ በማውጣትና ህዝቡንም ይቅርታ በመጠየቅ ሥርነቀል ለውጥ ለማምጣትና ሕገ-መንግሥቱን በአግባቡ ለመተርጎም ቃል መግባቱ ይታወሳል፡፡ በዚህም ዶክተር አብይ አህመድን የድርጅቱ ሊቀመንበር አድርጎ በመምረጥ መልካም የሚባሉ የለውጥ ጅምሮችን በማሳየት ላይ ይገኛል፡፡  

በእርግጥ የልውጥ ሂደት አልጋ በአልጋ አይሆንም ፤ አባጣ ጎርባጣ ይበዛበታል፡፡ ለውጡ ለሀገሩ እድገት ቅን የሚያስበውን ብዙሃኑን የኢትዮዮጵያ ህዝብ ያስደሰተ መሆኑ ባያጠራጥርም  ጥቅማቸው የተነካባቸው ጥቂት ግለኞችንና ቡድነኞችን ግን ሳያስከፋቸው ይቀራል ብለን አናስብም ፡፡ ሁሉም ዜጋ ለውጡን ደጋፊ ነው ካልንማ የተሰጣቸውን ሀገራዊ ሃላፊነትና አደራ ተጠቅመው ሲበዘብዙ የነበሩ አካላት የሉም ማለታችን ነው፡፡ ስለዚህ እነዚህ ጥቅማቸው የተነካባቸው የአሮጌው አስተሳሰብ አራማጆች ለውጡን ለማደናቀፍ ስውር ደባዎችን ለመፈጸም ስለሚያሴሩ ተኝተው አያድሩም፡፡ እነዚህ አካላት የመንግሥትን ጭንብል በመልበስ ሕዝብን ሲያማርሩና የራሳቸውን ንብረት ሲያከማቹ የነበሩ ናቸው፡፡

ዛሬ ኢህአዴግ በገባው ቃል መሰረት ከዚህ ቀደም የነበረውን ብልሹ አሰራር ለመቀየር ጅምሮችን እያሳየ የሚገኝበት ወቅት ነው፡፡ አብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብም አዲሱን የኢህአዴግ አስተሳሰብ በመደገፍ የመንግሥት አጋር መሆኑን አሳይቷል፡፡  በአንጻሩ ደግሞ ይህን እየታየ ያለውን የብርሐን ጭላንጭል ለማጥፋትና ወደ ለመዱትና ጥቅማቸውን ወደ ሚያስከብርላቸው አሰራር ለመመለስ የሚጥሩ አካላት በየክልሉና በየፌደራል ተቋማቱ አድፍጠው እንደተቀመጡ ልብ ይሏል፡፡ አድፍጦ መቀመጥ ብቻ ሳይሆን በሕቡዕ እያሴሩ እዛና እዚህ ከሚፈጠሩት ግጭቶች ጀርባ በመሆን ለውጡን ለመቀልበስ ሲሞክሩ ይታያሉ፡፡  ለውጡ በተፈለገው ፍጥነት እንዳይሄድ የሚያደርጉትም እነዚሁ ቀደምሲል ህገ-መንግስቱን እንደጥቅም ማስከበሪያቸው ሲገለገሉበት የነበሩት ሀይሎች ናቸው፤ አሁን አዲሱን የለውጥ አመራር ቡድን እየተፈታተኑት ያሉትም የሩቅ ሰዎች ሳይሆኑ እነዚያው ለአመታት በመንግሥት የተለያዩ መዋቅሮች ውስጥ ሆነው በመጥፎ ምግባር ውስጥ ሲዋኙ የነበሩት አካላት ናቸው፡፡

ለውጡ ውጥረት የሚታይበትም በዚህ ምክንያት ነው ፡፡ ለውጥ ፈላጊው የለውጡን ገመድ ወደራሱ ሲጎትተው ለውጡን ለመቀልበስ የሚያስበውም አካል ወደራሱ ይጎትታል ፡፡ የሆነው ሆኖ ግን የሀይል ሚዛኑን ሳያጤኑ የገመድ ጉተታ ጨወታውን ለመጫወት መሞከር እንደሚሸነፉ እያወቁ አላስፈላጊ ጥረት ማድረግ ጅልነት ነው፤ ለምን ቢባል አብዛኛውን የኢትዮጵያ ህዝብ ለውጥ ለውጥ ፈላጊ መሆኑን ከተደረጉት የድጋፍ ሰልፎች መረዳት ይቻላል፡፡     

 

በ60ዎቹ፣ በ70ዎቹ እና በ80ዎቹ በሰሜን አውሮፓ፣ በላቲን አሜሪካ እና በምስራቅ አውሮፓ የተካሄዱት የፖለቲካ ሽግግሮች ፖለቲካ ሳይንስ ምሁራንን ቀልብ በመሳባቸው የፖለቲካ ሽግግር (political transition) እንደ ዋና የጥናት መስክ ሊወሰድ በቅቷል፡፡

 

በዴሞክራሲ መሸጋገርያው ድልድይ ላይ ሥልጣንን በማሳደድ ላይ ባሉት ግለሰቦችና ቡድኖች መካከልና ጭቆናና ግፍ በሰለቻቸው የሕብረተሰብ አባላትና በስልጣን አንለቅም ባዮች ፈላጭቆራጭ ገዢዎች መካከል የግጭት መፈጠር ይከሰታል። በዚህ ከፈላጭ ቆራጭ አገዛዝ ወደ ዴሞክራሲ በሚወስደው የሽግግር ድልድይ ላይ የፖለቲካ ስልጣንን ለመጥለፍ አመቺው ሁኔታ ይፈጠርና፤ በዴሞክራሲ ስም የፈላጭ ቆራጭነትን ሥላጣን መልሶ ለመገንባት አጋጣሚውን ይጠቀሙበታል። ይህን በሚገባ የሚገልጽ አባባል በኢትዮጵያችን አለ ‹‹ግርግር ለሌባ ይመቻል›› ሁሉም አይነት የሂደቱ ተካፋዮች ከያሉበት ወደ ዴሞክራሲው መሸጋገርያ ድልድይ ይሰባሰባሉ። ሁሉም አይነት ተንኮል፤ የሥልጣን ሽሚያ፤ ችግሮች ሁሉ ይመጣሉ። በኢትዮጵያ እንደታየው የታሪክ እውነታ የሚከተለውን ያስገነዝበናል። ሊሆን የሚችለውም ይህን የመሸጋገርያ ድልድዩን ዋነኛ የተባሉት የውጭ ሃይሎች የሽግግሩን ወቅትና ሽግግሩን ራሱን ሊቆጣጠሩትና ሊመሩት ፈቃደኛነታቸውን በማሳየት ራሳቸውን እንደሸምጋይ ያቀርባሉ። በዚህም ራሳቸው ያስቀመጧቸውን ምልምሎችቸውን ቦታለማስያዝ የሽግግር ድራማቸውን በማቅረብ ሕዝቡም የፈላጭ ቆራጮች አገዛዝ ሰልችቶት አዲስ ዴሞክራሲያዊ ስርአት ና ፍቋልና እነዚህ ሽማገሌ ሆነው የቀረቡት አሸማጋዮች በሽግግሩ አውቶቡስ መሪው መቀመጫ ላይ ይቀመጣሉ። ተሳፋሪዎቹንም ወደ ፈለጉት አቅጣጫ ያጓጉዟቸዋል።

 

ዋስትናችን ዴሞክራሲ ነው፡፡ ወደ ዴሞክራሲ ልንደርስ የምንችለው ደግሞ ረዥሙንና አባጣ-ጎርባጣውን የዴሞክራሲ ሽግግር ዘመን ጨርሰን ነው፡፡ ሆኖም ሽግግሩ በርካታ እንቅፋቶች የተጋረጡበትነው፡፡

 

አደጋ አንድ፡ ከነባሩ ሥርዓት የሚገጥመ ውፈተና፡-ጠቅላይ ሜኒስቴር ዶ/ር አብይ የጀመሩት የለውጥ ጉዞ ከፍተኛ ተቃውሞና ተግዳሮት የሚገጥመው የሚደረገው ለውጥ ጥቅማችንን ያሳጣናል ከሚሉ የስርዓቱ ጋሻጃግሬ ከሆኑት ወታደራዊና ሲቪል ባለስልጣናት ነው። እነዚህ ሃይሎች የህልውና ስጋት ካሸተቱ የመንግስትን ስልጣን መልሰው ለመቆጣጠር የሚያስችላቸውን መፈንቅለ  መንግስት ከማድረግ ጀምሮ ልዩ ልዩ ፖለቲካዊ ሴራዎችን እና አሻጥሮችን በመጠቀም ለውጡን እየመሩ ያሉ ግለሰቦችን እና ቡድኖችን ከማጥፋት አይመለሱም። የእነ ዶ/ር አብይ እያንዳንዱ እንቅስቃሴ የሚሊተሪውና የደህንነቱ ጥላ እንዳጠላበት መሆኑን በፅኑ ማመን የተገባ ይሆናል። በሌላ አባባል የለውጡ አራማጅ የሆኑት ቡድኖች የሃገሪቱን የስልጣን ዋንኛ መሳርያ “Deep State” የሚባለውን ወታደራዊና ፀጥታ ክንፉን ሙሉበሙሉ ባልተቆጣጠሩበት ሁኔታ፣ ዛሬም ባስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ስም የፀጥታ ሃይሉ እውነተኛውን ስልጣን በያዘበት አጋጣሚ፣ ለውጥ አራማጆቹ ከአደጋ የራቁ አይደለም።

በየቦታው የሚነሱ ግጭቶችን እና ተቃውሞዎችን እንቆጣጠራለን፣ ህግናሥርዓትን መልሰን እናሰፍናለን (to restor order) በሚል ሰበብ ነባሩ አመራር በወታደሩ እየታገዘ ስልጣን ለመቀማት አይሞክርም ማለት ዋጋ የሚያስከፍል የዋህነት ይሆናል። ለዚህም ሲባል ወታደሩን እና ጥቅም አስጠባቂውን ነባር ሃይል እያባበሉ በዘዴ መያዝ፣ ዋስትና መስጠት፣ ከተቻለም የለውጡ አካል እንዲሆኑ ማበረታታት ያስፈልጋል። ለውጥን በሚያራምደው እና የለም ጥቅሜን አላስነካም በሚለው ሃይል መካከል የተፈጠረው ፍጥጫ እና የጠላትነት መንፈስ እስኪረግብ ጊዜ ይወስዳል። ግብተኛ እና ችኩል እርምጃ መውሰድ ለውጡን ከማደናቀፍ አልፎ ሀገርን ውድ ዋጋ ያስከፍላል።

አደጋ ሁለት ፡የለውጥፈላጊ ውሃይል ግፊት፡-ህዝቡ እጅግ መራር በሆነ የጭቆና ቀንበር ተቀይዶ እንደመቆየቱ፣ ብሎም ለውጡ እንዲመጣ ከባድ ትግል እንደማድረጉ መጠን፣ ፈጣን እና አስተማማኝ ለውጥ መጥቶ ከመከራው ለመገላገል መቋመጡ የሚጠበቅነው። ከመሰንበቻው የተፈጠረው አንፃራዊ ሰላምና መረጋጋት የመጣው ህዝቡም ሆነ ሌሎች የለውጥ ጠያቂ ቡድኖች በከፊልም ቢሆን እነ ዶ/ር አብይ የምንፈልገውን ለውጥና የምንሻውን ዴሞክራሲያዊ ሽግግር እውን ያደርጉልናል የሚል መተማመን መፍጠር በመቻሉነው። የህዝቡ ጥያቄ፣ የወጣቱ ፍላጎት፣ የፖለቲካ ሀይሎቹ ምኞት፣ የመብት ተሟጋቾቹ ፍላጎት እጅግ ውስብስብና መጠነ ሰፊ ነው። እነዚህ ወገኖች የጠየቁት ሁሉ ቢቻል በአንድ ጀንበር ተሳክቶ ቢመለከቱ ደስታቸው ነው። በሌላ አነጋገር ሃገሪቱ ላይ ያለው ኑሮ ውድነት፣ ስራአጥነት፣ ፍትህ፣ ዴሞክራሲ፣ ነፃነት እና ሌሎችም ዕልቆ መሳፍርት የሌላቸው ሃገራዊ ችግሮች በፍጥነት መፈታት ሲችሉነውና ለውጥ መጣ ለማለት የሚቻለው፣ ህዝብ ለጥያቄዎቹ አፋጣኝ መልስ ካላገኘ ፊቱን ማዞሩን ብሎም ወደ ተቃዋሞች ተመልሶ መግባቱ አይቀሬ ነው። በመሆኑም ለውጡን እየመሩ ያሉት አካላት በተቻለ ፍጥነት ለቀረበው ጥያቄ ምላሽ መስጠት ሊኖርባቸው ነው። ከህዝቡና ከፖለቲካ ሃይሎቹ ለሚነሱ ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት የእነዶ/ር አብይ ቡድን የቱንም ያህል ቀና ይቢሆን የአቅም ውስንነት እንዳለባቸው ሊዘነጋ አይገባውም።

ከላይ ከተጠቀሱት ሁለት ወሳኝ ሁነቶች በመነሳት የተጀመረው የለውጥ መስመር ከስጋት የራቀ አይደለም። ስጋቱ ውስጣዊና ውጫዊነው ብለን ብናስቀምጠው፣ ከውስጥ አሮጌውን መስመር“Status Quo”አስጠባቂ የሆኑት ቡድኖች ያሰመሩትን ቀይ መስመር ላለማስደፈር ወደ ኋላ ባገኙት ሃይል ተጠቅመው ሲስቡ፣ ለውጥ ፈላጊው ህብረተሰብ ደግሞ በተቻለ መጠን ገዢው ሃይል ተገርስሶ በምትኩ አዲስ ሥርዓት እንዲተከል  ወደ ፊት ይጎትታል። እነዶ/ር አብይ የሚመሩት የለውጥ ቡድን በነዚህ ሁለት ሃይሎች በሚጎትቱት ገመድ ላይ በጥንቃቄ ለመጓዝ ይገደዳሉ። የተፈለገው ዴሞክራሲያዊ ሽግግር እንዳይደናቀፍ፣ በሌላ በኩል የስልጣን ክፍተት ተፈጥሮ ዳግም ሃገሪቱ  ከነበረችበት ትርምስ የበለጠ ቀውስ ውስጥ እንዳትገባ የማድረግ፣  ሀገርን ከውድቀት፣ ህዝብን ከእልቂት የማዳን ከባድ ሃላፊነት ታሪክና አጋጣሚ ጫንቃቸው ላይ ጭኖባቸዋል። የለውጡ መሪ ሃይሎች ሚዛናቸውን ጠበቀው በዚህ ገመድ ላይ በጥበብ ወደ ፊት የመጓዝ፣ በትግስት የሁሉንም ፍላጎት ማስተናገድ ይኖርባቸዋል። ነገር ግን ይህን ፈተና ማለፍ ከሚታሰበው በላይ ከባድ ይሆንባቸዋል።

ፈተናውን የበለጠ የሚያከብደው የለውጥ ሃይል ሆነው የወጡት ሰዎች ያለመታመን እዳ ስላለባቸው ምጭምር ነው። የአሮጌው ቡድን ክብር አስጠባቂዎች  “ከእጃችን በልተው፣ በኛ ጀርባ ታዘለው ወደ ላይ ከመጡ በኋላ ከዱን፣ አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ መስመራችንን ቀውሊብራሊስት ሆኑ” በማለት ከመንጫጫት አልፈው ክፉኛ መርዘዋቸዋል። በሌላኛው ወገን ያለው ጎትጓች በተለይም “አክቲቪስቶች” እና የተቃዋሚ ፖለቲካ ቡድኖች፣ ዛሬ ለውጡን እየመሩት ባሉት ሰዎች ላይ ከባድ የሚባል ጥርጣሬ አላቸው። ሰዎቹ ከአሮጌው ሥርዓት ብብት ውስጥ የወጡ በመሆናቸው፣ የጨቋኙ አገዛዝ አፍድፋጅ ናቸው በማለት፣ አንዳንድ ተቃዋሚዎች ገዢው ግንባር በ27  ዓመታት ጉዞው ለሚጠየቅበት ጥፋትም ሆነ ውድቀት እኩል ሃላፊነት መውሰድ ያለባቸው እንጂ የምንፈልገውን ለውጥ አያመጡልንም ብለው ያምናሉ። በመሆኑም እነዶ/ር አብይ ይህንን ሁሉ ፈተና በትጋት ማለፍ ከቻሉ ብቻነው ሀገራችን ከገጠማት ከባድ አደጋ ተሻግራ የምንመኘው ዴሞክራሲ በሀገራችን እውን ሆኖ የምናየው።

 

ምን ይደረግ

  • የህግና የተቋማት ማሻሻያዎችን ማድረግ

ኢትዮጵያ ውስጥ ህገ-መንግስቱን ጨምሮ ብዙ የማያግባቡ ህግጋቶች በስራላይ ውለዋል። ሲጀምር ህገ-መንግስቱ በርካቶች ቅቡልነትን ያጣበት ዋንኛው ምክንያት የአንድን የፖለቲካ ድርጅት አመለካከት የሚያንፀባርቅና የጠባብ ቡድኖችን ፍላጎት የሚያስጠብቅ በመሆኑነው። ህገ-መንግስቱ የግለሰብ መብቶችን በቁንፅልነት የሚያይ ከመሆን አልፎ ሃገራዊ አንድነትን አደጋ ላይ ሊጥል የሚችል አንቀፅ የተካተቱበት ነው። ከሁሉም በላይ ህገ-መንግስቱ የፀደቀበት መንገድ ብዙዎችን አያስማም። ያልተወከለ የህብረተሰብ አካል እንዳለ በስፋት ሲነገር የኖረ ጉዳይነው ።ይሁንና አንዳንድ ህገ-መንግስቱን እንደሚቃወሙ ወገኖች  እንደሚሉት ተቀዶ  ይጣል ለማለት የሚከብድ ቢሆንም እንኳን መሰረታዊ የሚባሉ ማሻሻያዎች ሊደረግበት ይገባል። የማሻሻያ ሂደቱ ግልፅና አሳታፊ መሆን ይኖርበታል። ከፌዴራሉ ህገ-መንግስት ባልተናነሰ የክልል ህገ-መንግስቶችም አንዱን የክልል ባለቤት፣ ሌላኛውን መጤየሚሉበት፣ ጠባብነትን እና አግላይነትን በከፍተኛ ደረጃ የሚያራምዱ በመሆናቸው ማሻሻያው ሊጎበኛቸው ይገባል። ለሚደረገው ዴሞክራሲያዊ የሥርዓት ሽግግር ደጋፊ የሆኑ፣ ፖለቲካዊ ታህድሶን የሚያበረታቱ ተጨማሪ እርምጃዎች መወሰድ ይኖርባቸዋል። በተለይ ከ1997  ወዲህ የወጡ አፋኝ የተባሉ ህግጋት ሊሰረዙ አልያም ማሻሻያ ሊደረግባቸው የሚገባ ነው።

ሀገራችን በተለየ መልኩ ወደ ኋላ ከቀረችባቸው በርካታ ጉዳዮች አንዱ የተቋማት አደረጃጀቶች ጉዳይ ነው። ሁሉም ሊባል በሚችል መልኩ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉት መንግስታዊ ተቋማት ከገዢው ፓርቲ ጠለል ያራቁ ብቻ ሳይሆን ብርቱ ጫና ያረፈባቸው ናቸው። ወታደራዊና ሲቪል የሚባሉት የተቋማት አደረጃጀቶች የሚመሩበት መርህና የሚመሯቸው ግለሰቦች የአንድ ፖለቲካ ፓርቲ ርዮት አራማጆች ከመሆን አልፈው፣ የገዢው ፓርቲ ፖለቲካ ግብ ማስፈፀሚያ ሁነኛ ግዞቶች ሆነው ቆይተዋል። ለዚህም ነው በመንግስትና በተቋማት መካከል ያለው መስመር ነጭና ጥቁር መሆን ያልቻለው። ይህ አይነት አደረጃጀት ለገዢዎች አመቺ ቢሆንም ዴሞክራሲን ከማኰስመን አልፎ ለሀገር ህልውና ከፍተኛ ስጋት ሆኗል። ከእንግዲህ  ወዲያ ሊኖሩን የሚገቡ ሃገራዊ ተቋማት ከፖለቲካ ወገንተኝነት የጸዱ ሆነው በራሳቸው ለሚቆሙ የሚያስችል ብቃትና አቅም ሊፈጠርላቸው የተገባ ነው። የዚህ አይነት አደረጃጀትን የሚፈቅዱ ፖሊሲዎችና ደንቦች በተገቢው ተቀርጸው ስራ ላይ መዋል ሲጀምሩ ተቋማቱ እራሳቸውን ከፓርቲ ሞግዚታዊ አገዛዝ ዐርነት እያወጡ ነፃና ገለልተኛ መሆን ይጀምራሉ። ያኔ የትኛውም ፓርቲ ወደ ስልጣን መጣ ሄደ እነኝህ ተቋማት ሃገራዊ ሆነው ይቀጥላሉ፡፡ ከዚያም አልፎ መንግስት በማይኖርበት አጋጣሚ ቢፈጠር እንኳን፣ ተቋማቱ ስራቸውን ከማከናወን የሚያግዳቸው ስለማይኖር የሀገርን ህልውና ጠብቀው ያቆያሉ። ከሁሉ በላይ ሚሊተሪውን፣ ደህንነትን፣ምርጫቦርዱን፣ የሰባዊ መብቶች ኮሚሽንን የመሳሰሉት ወሳኝ ተቋማትን በተቻለ ፍጥነት አደረጃጀቶቻቸውን በማስተካከል ከፖለቲካ ውክልና ጸድተው የሁሉም ኢትዮጵያዊ ተቋም እንዲሆኑ በስፋት ሊሰራበት ይገባል።

ከላይ የተዘረዘሩትን ህጋዊና ተቋምዊ ማሻሻያዎችን ማድረግ በአጭር ጊዜ ውስጥ የሚሞከር አይደለም። ጊዜ፣ ትግስት፣ መግባባት፣ ማመቻመችና ተባባሪ መሆንን ይጠይቃል። እነኚህን ስራዎች ለመከወን በትንሹ ከአንድ እስከ ሁለት አመት ጊዜ ሊፈጅ ይችላል። አፍርሶ መስራት አዲስ እንደመገንባት ቀላል እንደማይሆን መቼም ከማንም የተሰወረ አይደለም። ከባድ ነው። ቀላል ያማይባል ተከላካይ ሃይል መነሳቱ አልቀርም። ሆኖም በመስጠትና በመቀበል መርህ ሁሉንም ማግባባት ባይቻል እንኳን ቅሬታን በተቻለ መጠን በመቀነስ ተግባራዊ ማድረግን ይጠይቃል። ዛሬ ላይ ከለውጡ መሪዎች የሚጠበቀ ውፍኖተ-ካርታቸውን ማሳወቅና አስፈፃሚ አካላትን ማስተዋወቅ ሲሆን፣ ሂደቱ እንዲቀላጠፍ የሁሉንም ባለድርሻ አካላት ቀና ተሳትፎ ማስተባበር ነው።

 አካታች ፖለቲካን ማራመድ 

የሀገራችን ፖለቲካ አግላይ ነው። አንዱን የበኹር ልጅ ሌላውን የእንጀራ ልጅ የሚያደርግ። የፖለቲካ አደረጃጀቱ አንዱን አሳዳጅ ሌላውን ተሳዳጅ ያደረገ፣ በጠላትነት፣ በመጠፋፋትና በአውጋዥነት የተቃኘ የግራ ዘመሞች የኖረ የፖለቲካ ባህል ነው ሃገሪቱን የተጫናት። በተለይ ዘውግ ተኮር አደረጃጀት የትኛውም አይነት መስመራዊ ቅራኔ በማንነት መገለጫዎች ላይ እንዲመረኮዝ ስለሚጋብዝ እኛ እና እነሱ የሚል ክፍፍል ላይ ተንጠላጥሎ ልዩነት እንዲሰፋ ይጋብዛል። ህብረቤሄራዊ ወይም የዜግነት ፓለቲካን የሚያራምዱ የፖለቲካ ቡድኖች ከጊዜ ወደ ጊዜ ከፖለቲካው መድረክ ተገፍትረዋል። ከሁሉም በላይ የአሸባሪነት ሰሌዳ ተለጥፎባቸው ከህጋዊዉ የፖለቲካ መድረክ የተገለሉ ሃይሎች እንዳሉም የሚታወቅ ነው። እነኚህን ሃይሎች ወደ መድረኩ ለማቅረብ የሚያስችል የህግ ማሻሻያ በማድረግና በመጋበዝ የለውጥ ሂደቱ አካል እንዲሁኑ ማድረግ ሽግግሩን የሚያግዙ ለማድረግ ይቻላል። የሀገራችን ፖለቲካ ካግላይነት ወደ አካታችነት ማሸጋገር የሚኖረው ፋይዳ ያኮረፉ ሃይሎችን ከማሰባሰብ አልፎ የፖለቲካ በሃላችንን በተገቢ መልኩ የሚለውጥ በመሆኑ የጠላትነት ስሜትን በተፎካካሪነት በመለወጥ የተሻለ ነገን ለማለም ያስችላል። ለዚህ ስኬት የለውጥ አራማጆቹ ከአፋዊ ጥሪ ባለፈ አስተማማኝ እርምጃዎችን ባፋጣኝ መውሰድ ሲኖርባቸው፣ እስካዛሬ ሲንገዋለሉና ሲገፉ የኖሩት የፖለቲካ ቡድኖች ቁሮሻቸውን ወደ ጎን በመተው በቶሎ ለውጡን መቀላቀል ይኖርባቸዋል።

  • ድርድር

እነ ዶ/ር አብይ የጀመሩት የለውጥ ጎዳና የሰመረ እንዲሆን፣ ከአንባገነናዊ ሥርዓት ወደ ዴሞክራሲያዊ አስተዳደር የሚደረገው ሽግግር በስኬት እንዲጠናቀቅ በተደራጁ የፖለቲካ ሃይሎችና በስልጣን ላይ ባለው ፓርቲ መካከል እውነተኛ ድርድር ሊደረግ ይገባዋል። ድርድሩ በህግ ማሻሻያዎች፣ በፖሊሲ ጉዳዮች፣ በተቋማት አደረጃጀትና አመራር ላይ አተኩሮ ለመጪው ዘመን ምቹ መደላደልን በመፍጠር ላይ ማድላት ይኖርበታል። ድርድር መደረግ ያለበት የትላንት ሂሳብን ለማወራረድ ሳይሆን ለነገ ምን የተሻለ እንስራ በሚለው ጉዳይ ላይ እንዲሆን በጽኑ ይመከራል። ድርድሮች በቅድመ ሁኔታ ሳይታጠሩ በጋራ መግባባት (concession) ላይ አተኩረው፣ ለዩነቶችን በማመቻመች (compromising) የለውጥ ሃይሉ ጠንክሮ የተጀመረውን ሽግግር እውን ለማድረግ የሚያስችል አቅም በመፍጠር ግብ ላይ ማተኮር አለበት። ተደራዳሪዎቹ ከራሳቸው ጥቅምና ፍላጎት አሻግረው የህዝብን ደህንነት እና ሃገራዊ ህልውና ታሳቢ እንዲያደርጉ ግድ ይላቸዋል። ለዚህም ሲባል ድርድሮቹ በመርህ መገዛትና መመራት ይኖርባቸዋል።

በድርድር ሂደቱ መግባባት የሚፈጠረው በተቃዋሚዎችና በገዢው ፓርቲ መካከል ብቻ ሳይሆን በተቀዋሚ ጎራ ተሰልፈው ላይተያዩ በተማማሉት መካከልም ጭምር ይሆናል። በድርድር ሂደት ውስጥ የሚፈጠረው መቀራረብ የበለጠ እርስ በርስ ለመናበብ እድል ስለሚፈጥር በድርጅቶች መካከል ያለው ልዩነት ከጠላትነት ይልቅ የሃሳብና የርዕዮት አለም ልዩነት ብቻ እንዲሆን እድል ይፈጥራል። ሂደቱ አካታች፣ ተስፋ አስቆራጭ ሊሆን የሚችልበት ምዕራፍ ሊኖረው እንደሚችል ይጠበቃል። በመጨረሻ ውጤቱ ለዴሞክራሲ እንደሚሆን ታውቆ በእርቅና በመተማመን መንፈስ ወደ ፊት ሊገፋ ይገባዋል እንጂ ተደነቃቅፎ ወደ ኋላ መቅረት ሀገርን የሚጎዳ ይሆናል። ይሄም ሂደት ጊዜ ሳይሰጠው በፍጥነት መጀመር ይኖርበታል።

 

  • ሂደታዊለውጥ (transplacement)

ሀገራችን ላይ እንዲመጣ የምንሻው የብዝሃነት ዴሞክራሲ፣ ዝመናና ልማት፣ ልንገነባቸው የገቡን ፓለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ተቋማት፣ እንዲኖረን የምንፈልገው የፖለቲካ ባህል፣ ህግ ላይ ተመስርቶ አካታችና አሳታፊ እንዲሆን የምንሻ ፖለቲካ፣ ፖለቲከኞቻችን እንዲኖራቸው የምንፈልገው ፖለቲካዊ ተክለ-ስብዕና ከስሜት፣ ከጎጠኝነት፣ ከቡድነኝነት የፀዳ ሆኖ ምክንያታዊ እንዲሆን፣ የሀገራችን ህዝብ ከሰለባ ስነ-ልቦና ተላቆ ለአንዲት ሀገራችን የከፈለውን ዋጋ እያሰበ የሀገር ባለቤት መሆኑን በኩራት እንዲመሰክር የሚያስችለውን አቅም ያገኝ ዘንድ ልንሻገረው የሚገባን አዘቅት፣ ልንሰብረው የሚጠበቅብን አዙሪት አለ። ከኖረው የቸከና የመነቸከ ባህላዊ ፖለቲካን የመረዳት አስተምሮታችን ተሻግረን አዲስ የፖለቲካ መተግበሪያ (Ways of ‘Doing’ Politics) መስራት ያስፈልገናል። የምንተገብረው የፖለቲካ ሞዴል አፍርሶ በፍርስራሽ ላይ ሌላ ፈራሽ ሥርዓት ከመትከል እርግማን የተላቀቀ መሆን አለበት። ጊዜው ደግሞ አሁን መሆን አለበት። በመሆኑም ስር ነቀል ለውጥ ለተባለው ግብ መዳረሻ የሽግግር መንግስት ማቋቋም አያዋጣም የሚል ክርክር ከተነሳ አልቀረ አማራጩን መንገድ መፈተሽ የተገባ ነው።

በእኔ እምነት ከደረስንበት የፖለቲካ እድገትና ካለንበት ሃገራዊና አከባቢያዊ ፈታኝ ሁኔታዎች በመነሳት፣ ዴሞክራሲያዊ ሽግግር ለማድርግ ብንከተለው የሚያዋጣን ሂደታዊ ለውጥ (transplacement) የተባለው አማራጭ ነው የሚል አቋም አለኝ። ሳሙኤል ሃንቲግተን የተባለ አሜሪካዊ የፖለቲካ ሳይንስ ምሁር ሀያኛው ክፍለ ዘመን መባቻ ላይ የተካሄዱ ከአምባገነን አገዛዝ ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ሽግግሮች በተነተነበት “The Third Wave: Democratization in the Late Twentieth Century” በተባለው መጽሐፉ ካስተዋወቃቸው የለውጥ መተግበሪያ ዘዴዎች አንዱ ስለሂደታዊ ዴሞክራሲያዊ ሽግግር (transplacement) ነው። በሃንቲግተን እይታ በሂደታዊ ለውጥ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ እውን ሊሆን የሚችለው አገዛዝ ላይ ባለው መንግስት እና ተቀናቃኝ የፖለቲካ ወገኖች ጥምር ጥረት ነው። መንግስት በሚወስዳቸዉ ህጋዊ ማሻሻያዎች፣ በሚፈጥራቸው የተደላደለ ምህዳሮች እና የሊብራላዜሽን እርምጃ ላይ ተመስርቶ ተቀናቃኝ የፖለቲካ ሃይሎች በመደበኛና ኢ-መደበኛ በሆኑ የድርድር መስመሮች ተጠቅመው ለውጡ እውን እንዲሆን የበኩላቸውን አስተዋፆ ያደርጋሉ። ምንም እንኳን የተቀዋሚ ሃይሎች በመንግስት ውስጥ ባሉ ኢ-ዴሞክራሲያዊ ቡድኖች ላይ ተጽኖ የመፍጠር አቅም ሊኖራቸው ይችላል ተብሎ ቢታመንም እንኳን፣ መንግስትን ግን ገልብጠው አዲስ ስርአት መትከል የማይችሉበት ሁኔታ፣ በዚህ አይነት የሽግግር ዘዴ መታገዝ ካልቻለ ሀገርን አደጋ ላይ ይጥላል። በመሆኑም ከመንግስት ውስጥ የለውጥ ፋና ወጊዎች በሚነሱበት ወቅት ከነዚህ ሃይሎች ጋር በተገቢው መንገድ በመደራደር፣ ስምምነት በመፍጠር (concession)፣ ሰጥቶ በመቀበል መርህ እየተመሩ ስርዓቱን ከጨቋኝነት ወደ ዴሞክራሲያዊ መድረክነት ለማሸጋገር ይቻላል ይላል።

ኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ የተዋረድ እና የጎንዮሽ የሆኑ በርካት ጽንፎች አሉ። እነኝህን ጽንፎች ማቀራረብና መካከለኛ መስመር ላይ ማምጣት ረዥም ጊዜ ይጠይቃል። በፖለቲካ መስመር ውስጥ ዴሞክራቶች እና ፀረ-ዴሞክራሲያን በተለያየ ጎራ ተሰልፈው ገመድ በሚጓተቱበት ሰርዓተ ማህበር ውስጥ በአጭር ጊዜ ዴሞክራሲን የወል ግብ ማድረግ ከባድ ይሆናል። ለዚህም ነው ተጀምሯል ያልነው የለውጥ መስመር የአኩራፊ ቀደምት የስልጣን ወሰን አስጠባቂ ወገን እና የፀጥታ ሃይሉ ጥላ የአጠላበት ነው የምንለው። ተደጋግሞ የሚቀርበው ማስረጃ ዶ/ር አብይ አዲስ የተባለውን ካቢኔ ያዋቀሩበት መንገድ ነው። በተጨማሪም ጡረተኞቹ የህውሃትና የብአዴን መሪ ተብዬዎች ከሰሞኑ መቀሌ ላይ ሲናገሩ እንዳዳመጥነው ለ27 ዓመታት በተጓዙበት መንገድ ለመቀጠል እንደሚፈልጉ ቢያንስ ቅዠታቸውን ነግረውናል። በመሆኑም ዴሞክራሲያዊ ሽግግሩ ሰላማዊ፣ ዘላቂና አስተማማኝ እንዲሆን ሂደቱ ከላይ ወደታች (top-down) መሆን ያለበት እና በአንፃራዊነት ዘገምተኛ (gradual approach) ሂደትን መከተል ያለበት። በመሰረቱ ዴሞክራሲን ከታች ወደ ላይ (democracy from below) ሞክረነው ካንዴም ሁለቴ ከሽፏል። ለዚህም ነው ሦስተኛውን አብዮት በሃይል ለማምጣት ከሞክርን ያሰብነውን ዴሞክራሲያዊ ሽግግር ያለመሳካት ስጋት ብቻ ሳይሆን ሀገርን የሚሰዋ አደጋ ሊሆን የሚችለው።

እውነት ነው ኢህአዴግ ውስጥ የተፈጠረውን የለውጥ ንቅናቄ የፈጠረውም ሆነ አዳዲሶቹን መሪዎች ወደ ስልጣን ማማ ያመጣቸው የህዝብ ግፊት ነው። ይሁንና ለውጡ ከግብ እንዲደርስ ባለቤት ያስፈልገዋል። የለውጥ ሃዋርያ ሆነው ብቅ ያሉት ሰዎች በያዙት መስመር ወደ ፊት እንዲጓዙ እድል ሊሰጣቸው ይገባል። ከቦታ ቦታ እየተዟዟሩ  ለመፍጠር የሚሞክሩት የማረጋጋትና የጋራ ሃገራዊ ራዕይ የመፈጠር ሂደት፣ ዝግባ ዝግባ የሚያክሉ የአገዛዙን ሰዎች ከመድረኩ ገለል የማድረግ ሙከራው፣ የሥርዓት ሽግግሩን ለማስጀመር ጎባጣን የማቃናት ረባዳውን የመደልደል ጅምር ስራ ተደርጎ ሊቆጠር ይችላል። በብዙዎች እንደሚባለው ስርዓታዊ መዋቅሩን በአንድ ጊዜ ከላይ እስከታች በመናድ አዲስ መዋቅር መትከል ቀላል ጉዳይ አይሆንም። ይልቅ ደረጃ በደረጃ ማሻሻያዎች እያደረጉ የተቋማትን ይዘትና ቅርፅ በመቀየር ለውጡን የተሳለጠ (readjust) በማድረግ አላስፈላጊ ግጭትን ወይም የለውጥ ተቀዋሞን መቀነስ ያስችላል። ተቋማትና መዋቅሮች በሂደት ሲለውጡ ህግጋትና ፖሊሲዎች አብረው እየተሻሻሉ ይመጣሉ።

ይህን መሰሉ ሂደታዊ ለውጥ ፋይዳው ዘረፈ ብዙ እንዲሆን ከሚያደርጉት ጉዳዮች አንዱ ለተቃዋሚ ሃይሎች የሚፈጥረው ምቹ ሁኔታ ነው። ከጊዜ ወደ ጊዜ የሲቪል መብቶች፣ የፖለቲካ ነፃነቶች እየሰፉ ሲመጡ ተቃዋሚ የፖለቲካ ሃይሎች ከኖረው የተሳዳጅነት መንገድ ወጥተው፣ ሃሳብና ሃይላቸውን አደራጅተው በተሻ ለመስተጋብር እና የድርድር አቅም በመቅረብ ገዢውን ሃይል ለመሞገትም ሆነ እንዲመጣ የሚፈለገው ለውጥ እውን እንዲሆን የሚያስችል አቅም ይፈጥርላቸዋል። ምናልባትም ከሁለት አመት በኋላ በሚደረገው ምርጫ ላያሸንፉ እና ስልጣን ላይዙ ይችሉይሆናል። በቀጣይ ምርጫዎች የተሻለ አቅም አደርጅተው መምጣት ከቻሉ በሌሎች ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በመሰረቱ ሃገራት የምናየውን ሰላማዊ ሽግግር ለማድረግ አቅም ይፈጥርልናል።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy