Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

…የንግድ ለንግድ ግንኙነት

0 264

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

…የንግድ ለንግድ ግንኙነት

 

ዮናስ

 

ከአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት የተገኘ መረጃ እንደሚያመለክተው በአንድ የንግድ ትርዒት ብቻ ከአፍሪካ፣ ከኤሲያ፣ ከአውሮፓና ከመካከለኛው ምስራቅ ምርትና አገልግሎታቸውን ለማስተዋወቅ በዓመት ከ12 እስከ 18 የሚሆኑ አገራት ባለሀብቶች ወደ ኢትዮጵያ ይመጣሉ። በዚህም ከ97 እስከ 110 የሚደርሱ የውጭ ድርጅቶች ይሳተፋሉ፡፡ ከ97 እስከ 100 የሚደርሱ የአገር ውስጥ ድርጅቶችም የሚሳተፉ ሲሆን፤ ይህም በአምስት ዓመት ሲሰላ ከውጭ ከ 485 በላይ እንዲሁም ከአገር ውስጥ ደግሞ እስከ 415 ተሳታፊዎች ይገኛሉ። ባለፉት 5 ዓመታት የተዘጋጁ የንግድ ትርዒቶችን ከ 35 ሺ በላይ ሰዎች ተጎብኝተዋል። ሰሞኑን ደግሞ ከግብጽ የውጭ ንግድ ምክር ቤት ተመሳሳይ ነገር ተሰምቷል።

 

በኢትዮጵያ እና ጆርዳን የንግድ ትዕይንት ሊያካሂድ መሆኑን ያስታወቀው ምክር ቤት ከግብጽ ላኪዎች ማሕበር ጋር በመተባበር በኢትዮጵያ የንግድ ትዕይንት ለማከናወን ዝግጅቱን መጨረሱን የድርጅቱ ምክር ቤት ዋና ዳይሬክተር ማሃ ሳላህ መናገራቸውን የግብጽ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል። ስለሆነም የንግድ ትእይንቶችን ፋይዳ ከአጠቃላዩ ሃገራዊ የኢኮኖሚ ግንባታ አኳያ ማየት ተገቢ ይሆናል።

  

በኢትዮጵያ የሚካሄዱ ዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒቶች እየጨመሩ መጥተዋል፡፡ የንግድ ትርዒቶቹ በቴክኖሎጂና እውቀት ሽግግር ፣የውጭ ባለሀብቶችን በመሳብ፣ የሀገር ውስጥ ምርትና አገልግሎትን በማስተዋወቅና በመሳሰሉት አገሪቱን ምን ያህል ተጠቃሚ አድርገዋል በሚለው ላይ ግን ከዘርፉ ጋር ግንኙነት ያላቸው ባለሙያዎች የተለያየ ሃሳብ ይሰነዝራሉ፡፡

 

የየትኛውም ሀገር ኤኮኖሚ በተገቢው ሁኔታ የሚንቀሳቀሱ፣ በንቃት የስራ ፉክክር ውስጥ የገቡና አድማሳቸውን ዘወትር የሚያሰፉ ውጤታማ የንግድ ዘርፎችን የሚንከባከብ ከሆነ ያለማቋረጥ የማደግ እድሉ ሰፊ ነው፡፡

እነዚህ የንግድ ዘርፎች የምንላቸው የኤኮኖሚው ቁልፍ ተዋናዮች በሁሉም ሀገራት ከሞላ ጎደል በተመሳሳይ ሁኔታ የተዋቀሩና የሚታወቁ ናቸው፡፡ ለመዘርዘር ያህልም፣ በፍብረካ፣ በግብርና፣ በኃይል ማመንጨትና አቅርቦት፣ በግንባታ፣ በትራንስፖርት፣ በመገናኛ፣ በማአድን ፍለጋና ማውጣት፣ በባንክ አገልግሎትና በመሳሰሉት የንግድ መስኮች የተሰማሩ ድርጅቶችን በየፈርጃቸው ወክለው የሚገኙትን ዘርፎች ያጠቃልላሉ፡፡

ባለፉት ጥቂት ምዓተ- ዓመታት የነበረው የዓለም ኤኮኖሚያዊ ታሪክ እንዲሚያሳየው ሀገራት እነዚህን የንግድ ዘርፎች ተሟልተው እንዲገኙና ተገቢውን አስተዋፅዎ እንዲያበረክቱ በማድረግ ቀድመው ከመንቀሳቀስ የተሻለ አማራጭ አልነበራቸውም፡፡ ይህም የሆነበት ምክንያት አንድ ህብረተሰብ ካለው የሰው ኃይል፣ የቁሳቁስና የፋይናንስ ሀብት ጋር በተያያዘ ሊኖረው የሚገባውን የአቅም መጠንና ይዘት ዘርፎቹ ስለሚወክሉ ነው፡፡ በሌላ አነጋገር ህብረተሰብ እነዚህን አቅሞች ጥቅም ላይ ማዋሉ ወይም አለማዋሉ፣ ካዋላቸውም በምን ያህል መጠንና ቅንጅት ጥቅም ላይ የመዋላቸው ጉዳይ የየሀገራትን የእድገትና ልማት እርምጃ ሲወስኑ ቆይተዋል፡፡

በዚህ ረገድ አንዳንድ ሀገራት ቀድመው በመንቃት አቅጣጫቸውን አስተካክለው በመጓዝ ያለሙት ግብ ላይ ለመድረስ በቅተዋል፡፡ ከተገነዘቧቸው ነገሮች መካከል፣ ለምሳሌ፣ እያንዳንዱን ቁሳዊ ሀብት ካለው የሰው ሀብት ጋር በሚገባ በማቀናጀትና ወደ ምርት በማስገባት ለህብረተሰብ ጠቃሚ አስተዋፅዎ በሚያበርክትበት ደረጃ ላይ ማድረስ እንደሚቻል ማዋቁ አንዱ ነው፡፡

የዚህ ፍሬ- ነገርና ትርጉም ሲተነተን የሰው ልጅ የፈጠራ ችሎታና በስራ ረገድ የሚያሳየው ትጋት፣ ሁኔታዎች በሚፈቅዱት መጠን በቁሳቁስና በገንዘብ ቢደገፍ ታምቆ የቆየን አቅም ህብረተሰባዊ ጥቅም ሊሰጥ በሚችል የምርት እንቅስቃሴ ውስጥ ማስገባት ይቻላል የሚለውን እንድምታ ይሰጠናል፡፡ ይህ ከሆነ ደግሞ የፈጠራ ሰዎች፣ አምራቾች፣ ነጋዴዎችና ሌሎች ከማምረት ጋር ተያያዥ በሆኑ ስራዎች ውስጥ የሚሳተፉ ሰዎች የየድርሻቸውን ጥቅም ከማግኘታቸው በተጨማሪ በህብረተሰቡ የኤኮኖሚ ትስስር ሰንሰለት ውስጥ ተሳትፏቸውም ሆነ የሚሳተፉበት የስራ ዘርፍ ቦታና ዋጋ እንዳላቸው ይገነዘባሉ፣ ስለሆነም ለወደፊቱ የተሻለ ለመስራት ይነሳሳሉ፡፡

 

የግሉ ዘርፍ ስሙ በከፊል እንደሚገልፀው ግለሰቦች በበላይነትና በነፃነት የሚሳተፉበት፣ በዚህም ምክንያት ኤኮኖሚያዊና ማሀበራሰባዊ ጥቅሞች ለሁሉም የሚዳረሱበት፣ ነገር ግን ይህ እንዲሆን ግለሰብ ተዋናዮች ኃላፊነትና ተጠያቂነት በተሞላ መንፈስ መንቀሳቀስ እንዳለባቸው እናያለን፡፡ ይህ ሲባል ግን ሁሉም ግለሰብ ተዋናይ ለህሊናውም ይሁን ለተቀመጡ ህጎችና ደንቦች ሲል በኃላፊነትና በተጠያቀነት መንፈስ ተንቀሳቅሶ የተነሳበትን ዓለማ በጨዋነት ያከናውናል ተብሎ የሰላም እንቅልፍ የሚተኛበት ሁኔታ የለም፤ ምክንያቱም አልፎ አልፎ መስመር መጣሱ አይቀርምና፡፡ በተመሳሳይም፣ የግሉ ዘርፍ ለሁሉም የህብረተስብ-ነክ ችግሮች በቂ መልስ በመስጠት ይፈታቸዋል ተብሎ አይጠበቅም፡፡ ለሁሉም እንከኖች መስተካከልና መልስ ማግኘት የሌሎች ዘርፎች በንቃት መሳተፍ አስፋላጊ ነው፡፡ በዚህ ረገድ የንግድ አውደ ርእዮች የሚኖራቸው ፋይዳ ቀላል ግምት የሚሰጠው አይደለም።  

 

በንግድ ትርዒትና ባዛሮቹ የአገሪቱን የኢንቨስትመንት አማራጮች በማስተዋወቅና የቴክኖሎጂ ሽግግርን በመፍጠር ውጤቶች ተመዝግበዋል፡፡ የአገር ውስጥ ምርትና አገልግሎትን ለማስተዋወቅም ሰፊ ዕድል ተፈጥሯል፡፡ ይህ አይነቱ አውደ ርእይ የንግዱን ማህበረሰብ ምርትና አገልግሎት ከሚያስተዋ ውቅባቸው መንገዶች አንዱና የገበያው ሞተር ተብሎ የሚታመንበት ነው። አብዛኛዎቹ የንግድ ትርዒቶች የወደፊት ደንበኞችን ለማግኘት እንዲሁም ስምምነቶችን ለመጨረስ የሚደረጉ እንጂ “የተወሰነ ነገር ሸጬ እጠቀማለሁ” የሚል እሳቤን ያነገቡ አይደሉም።

 

የቴክኖሎጂ ሽግግር ፣ በኢንቨስትመንት የመሳተፍ እንዲሁም ባሉበት አገር ሆነው ምርት ለመላክ ቅርንጫፎችን የመክፈትና ወኪሎችን የማዘጋጀት ሥራም በብዛት መከናወኑን፣ ከዚህም የውጭ ሀገር የንግድና ባዛር ተሳታፊዎች ከአገር ውስጥ ባለሀብቶች ጋር የሚመሰርቱት የቢዝነስ ግንኙነት ትልቁን ድርሻ እንደሚወስድ ይጠቅሳሉ።አዳዲስ ቴክኖሎጂዎቻቸው ለአገር ውስጥ ተመሳሳይ ኩባንያዎች ብቻ ሳይሆን ለጎብኚዎችም ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳላቸው የዘርፉ ጠበብቶች ይገልጻሉ ።

 

የንግድ ሚኒስቴር እንደሚለው ከሆነ ደግሞ የንግድ ትርዒቶች ምርቶቻቸውን ሲያዘጋጁ ፣ሲያከማቹ ፣ሲያጓጉዙ ምን ዓይነት ቴክኖሎጂ እንደሚጠቀሙ፣ ለምርቱ ጥራት የሚያደርጉት ጥንቃቄ በተሞክሮነት መወሰዱን ይጠቅሳል፡፡ የውጭ ኩባንያ ምርትና አገልግሎቱን ለማስተዋወቅ ሲመጣ ለሆቴል ኢግዚቢሽን ለሚታይበት ቦታ የሚያወጣው ገንዘብ ብሎም ለሥራው ሰዎችን እንደሚቀጥር የሚጠቅሱት ጠበብቶች   ይህም ለአገሪቱ ትልቅ ትርፍ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ከሁሉም በላይ ግን እነሱን በመሳብ ባለሀብት ሆነው ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲገቡ ማድረግ ያስፈልጋል ሲሉ ያብራራሉ፡፡

 

አፍሪካውያን የእርስ በርስ የንግድ ግንኙነታቸው እምብዛም ከመሆኑ አንጻር ግብጽ የምታዘጋጀውን አውደ ርእይ ፋይዳ ያጎላዋል። አፍሪካውያን በአመዛኙ የንግድ ግንኙነታቸው ከአፍሪካ ውጪ ካሉ አገሮች ጋር በመሆኑ በርካታ የአፍሪካ ኩባንያዎች በንግድ ትርዒቶች ላይ የመሳተፍ እድላቸው አነስተኛ የነበረ ከመሆኑ አኳያ ሲሰላ የሚፈርሰውን የገዘፈ ግንብ ያመላክተናል፡፡

በየዓመቱ በቋሚነት ከሚዘጋጁ ዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒቶች ውስጥ አንዱ “አዲስ ቻምበር ዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒት” እየተባለ የሚታወቀው ተጠቃሽ ነው፡፡ ይህ ንግድ ትርዒት በዚህ ስያሜው ላለፉት 20 ዓመታት ሲካሄድ ቆይቷል፡፡ አምና ለ21ኛ ጊዜ በተካሄደው ዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒት 180 የአገር ውስጥና የውጭ ኩባንያዎች ስለመሳተፋቸው መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

 

ካለፉት ሦስት ተከታታይ ዓመታት አንፃር ሲታይ በ21ኛው የንግድ ትርዒት ወቅት የተሳተፉ የውጭ ኩባንያዎች ቁጥር ቢቀንስም፣ ከ27 አገሮች የተውጣጡ ኩባንያዎች እንደታደሙበት ተጠቅሷል፡፡ በወቅቱ እንደተገለጸው በንግድ ትርዒቱ ከሚጠበቁ የውጭ ኩባንያዎች መካከል ተሳትፏቸው ከቀነሱባቸው ምክንያት አንዱ በርካታ ኩባንያዎችን ሲያሳትፉ የቆዩት ቱርክና ግብፅን የመሰሉ አገሮች ኩባንያዎቻቸውን ባለመወከላቸው ነው፡፡ የግብፅ ኩባንያዎችም በአምናው የንግድ ትርዒት ወቅት ላለመሳተፋቸው ምክንያት እንዳላቸው በወቅቱ ጠቅሰው በዚህ  ዓመት በሚዘጋጀው 22ኛው ትርዒት ላይ በትላልቅና በርካታ ቁጥር ባላቸው ኩባንያዎች እንደሚወከሉ ማረጋገጣቸው ይታወሳል፡፡ ይህ የንግድ ትርኢት የኢንቨስትመንት ፕሮሞሽንና የንግድ ለንግድ ግንኙነት እንዲጎለብት የአገር ውስጥ ኩባንያዎችን ከውጭ ኩባንያዎች ጋር በማስተሳሰር የንግድ ትርዒቱ እንደ ድልድይ ያገለግላል፡፡

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy