Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ) እስካሁን የርዕዮተ ዓለም ለውጥ አለማድረጉን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ተናገሩ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ስልጣን ከመጡ ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ ከጋዜጠኞች ጋር ቆይታ አድርገዋል።

0 1,105

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ) እስካሁን የርዕዮተ ዓለም ለውጥ አለማድረጉን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ተናገሩ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ስልጣን ከመጡ ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ ከጋዜጠኞች ጋር ቆይታ አድርገዋል።
በዚህ ወቅት ከጋዜጠኞች ለተነሱ ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽ ኢህአዴግ እስካሁን የርዕዮተ ዓለም ለውጥ አለማድረጉን ጠቅሰው፥ ድርጅቱ በጥልቅ ተሃድሶ መስመር ላይ መሆኑን አስረድተዋል።
ኢህአዴግ በሂደት ራሱን እያሻሻለና ተሃድሶ እያደረገ እዚህ መድረሱን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ በአዳዲስ ሃሳቦች የሚስተዋለውን ፍላጎት ለመመለስ እየሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።
ድርጅቱ በቅርቡ ባካሄደው ጉባኤ በተወያየባቸው አጀንዳዎች በመግባባት መጠናቀቁን ጠቅሰው፥ በኢህአዴግ ልዩነት አለ በሚል የሚናፈሰው ወሬ መሰረት የለውም ብለዋል።

በሁሉም የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች አሁን የመጣውን ለውጥ ሙሉ በሙሉ የተቀበሉና ያልተቀበሉ ግለሰቦች እንጅ እንደ ድርጅት ልዩነት እንደሌለም ነው የተናገሩት።
ከዚህ ጋር ተያይዞም ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ለውጡን አልተቀበለም በሚል የሚቀርበው ወቀሳ አግባብ አለመሆኑንም አንስተዋል።

በህወሓት ውስጥ ለውጡን ደግፈው ለህዝቡ ሰላምና ብልጽግና የሚሰሩ አመራሮች የመኖራቸውን ያክል ለውጡን ያልደገፉ እንዳሉም አስረድተዋል።

ይህ ለውጥን ያለመቀበል ጉዳይ ግን በአራቱም የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ውስጥ የሚታይ መሆኑንም ነው የገለጹት፤ በጉዳዩ ላይ ህወሓት ብቻውን ሊወቀስ እንደማይገባ በመጥቀስ።
ቀጣዩ ምርጫና የኢኮኖሚ አሻጥር፥ በኢህአዴግ ምክር ቤት ባለው መቀመጫ በህዝብ ብዛት ቁጥር እየተሰራ አይደለም በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄም፥ ኢህአዴግ ግንባር ከመሆኑ አንጻር አራቱ ድርጅቶች በእኩል ድምጽና በመግባባት ተስማምተው እንደሚሰሩ ገልጸዋል።

ከዚህ አንጻርም አንዱ የበላይ አንደኛው የበታች በመሆን አይሰሩምም ነው ያሉት በምላሻቸው።
በቀጣይ ከሚካሄደው ምርጫ ጋር በተያያዘ በሰጡት ምላሽና ማብራሪያም ኢህአዴግ የምርጫ ጊዜውን የማራዘም ሀሳብ የለውም ብለዋል።

መንግስት ምርጫው ያለ ምርጫ ኮረጆ በዘመናዊ የኤሌክትሮኒክስ መሳሪያ በታገዘ መንገድ በታቀደለት ጊዜ እንዲካሄድ ፍላጎቱ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
ከዚህ አንጻርም ሁሉም የሚያምንበትና ተዓማኒነት ያለው የምርጫ ተቋም እንዲፈጠር እንሰራለንም ነው ያሉት።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ በሃገሪቱ የኢኮኖሚ አሻጥር መስተዋሉን ጠቅሰው፥ ለዚህ አሻጥር መፍትሄ የሚያፈላልግ ግብረ ኃይል ተቋቁሞ ወደ ስራ መግባቱንም አውስተዋል።
ይህ የኢኮኖሚ አሻጥር ህዝቡን የታየው ለውጥ በታሰበው መልኩ እየሄደ አይደለም የሚል አንድምታ እንዲይዝ ለማድረግ ያለመ ስለመሆኑም በመግለጫቸው ጠቁመዋል።

በዚህ የኢኮኖሚ አሻጥር ሳቢያ ወደ ኢኮኖሚው መፍሰስ የነበረበት በርካታ ገንዘብ በግለሰቦች እጅ ስር እንደሚገኝም አብራርተዋል።
ከዚህ ጋር ተያይዞ ከኢትዮጵያ ወደ ተለያዩ ሃገራት ገንዘብ መውጣቱን በተመለከተም፥ መንግስት የተባለውን ገንዘብ የማስመለስ ፍላጎት እንዳለው ጠቅሰው ለሂደቱ ሁሉም ተባባሪ እንዲሆኑም ጠይቀዋል።

ፕራይቬታይዜሽን እና የትምህርት ፍኖተ ካርታ፥ አንዳንድ የመንግስት የልማት ድርጅቶችን በፕራይቬታይዜሽን ለማዘዋወር በሚደረገው ሂደት በተቋቋመው ከሚቴ ውስጥ ከሙያቸው ውጭ የተመደቡ ሰዎች ጉዳይ እንዴት ይታያል የሚል ጥያቄም ተነስቶላቸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩም በአካሄዱ ግልጽነትን ለማስፈንና ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል የተሳተፈበት እንዲሆን በማሰብ ከሙያቸው ውጭ ስራውን በቅንነት የሚሰሩ ሰዎች መመደባቸውን አስረድተዋል።

የስራውን አካሄድ በተመለከተም በየመሃሉ ሂደቱ ስለሚገለጽ በዛ ደረጃ መገምገም እንደሚቻል ጠቅሰዋል።
ውይይት እየተደረገበት ያለው የትምህርት ፍኖተ ካርታ አንድን ቋንቋ በሌላ ክልል ማስተማር መልካም ነው የሚል እሳቤ የያዘና ይህ ጉዳይ በውይይት እየዳበረ የሚሄድ መሆኑንም አስረድተዋል።

የውጭ ምንዛሪ እና የድንበር ጉዳይ፥ የተመዘገበው ኢኮኖሚያዊ እድገት በሌሎች ዘርፎች ላይ በርካታ ለውጦችን ቢያመጣም በውጭ ምንዛሪ ግን እጥረት ማጋጠሙን አውስተዋል።
ኮንትሮባንድና የውጭ ምንዛሪ ግብዓቶች ከመንግስት ይልቅ ወደ ግለሰቦች መግባት፥ ለዘርፉ ዋነኛ ችግር መሆኑንም ጠቅሰዋል።
ከዚህ አንጻርም በቅንጅት መስራት፣ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ እንዲሁም ከጎብኝዎች እና ከውጭ ወደ ሃገር ውስጥ ከሚላከው ገንዘብ የሚገኘውን ምንዛሪ በህግ አግባብ ጥቅም ላይ እንዲውል ማድረግ ይገባል ብለዋል።

ከድንበር ጋር በተያያዘም ከሱዳን አጎራባች በሆኑ የአማራ ክልል አካባቢና በሱዳን በኩል ያለው የድንበር ወሰን መልክ ባለመያዙ ችግሮች መከሰታቸውን ገልጸዋል።
በቅርቡም በመሪዎች ደረጃ ውይይት ተደርጎ በሁለቱም በኩል ታጣቂዎች ከድንበር እንዲርቁና ጥበቃውን በጋራ ለማካሄድ ስምምነት ተደርሷልም ነው ያሉት።
የድንበር ማካለሉ ጉዳይም በድርድር የሚፈታ ይሆናል ያሉት በሰጡት ምላሽ።

በሶማሌ ክልል ተፈጥሮ ከነበረው ችግር ጋር በተያያዘም የቀድሞው የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር፥ አቶ አብዲ ሙሐመድ ኦማር ጉዳይ ወደፊት በህግ የሚታይ አግባብ እንደሚታይ አንስተዋል። እሳቸውም ሆነ ሌሎች ስልጣንን አለአግባብ የተጠቀሙ ይጠየቃሉ ነው ያሉት።

ኢትዮጵያና ኤርትራን ማን አስታረቀ በሚል ለቀረበውም ጥያቄ የሀይማኖት አባቶች፣ የፖለቲከኞች፣ የሀገራት መሪዎች የሁሉም ድምር ውጤት ነው ብለዋል።
ዋናው ጉዳይ ችግሩ መፈታቱ እንጂ የሸምጋዮች ጉዳይ መሆን የለበትም፤ እርቁን ማን አስጀመረው ሳይሆን የተጀመረውን ሰላም ማስቀጠል መሆኑን ተናግረዋል።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy