Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የዓለም ሰላም አነሳሽ

0 365

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የዓለም ሰላም አነሳሽ

አዲስ ቶልቻ

ኤርትራ በ1882 ዓ/ም በይፋ የጣሊያን ቅኝ ግዛት ከመሆኗ በፊት የኢትዮጵያ አካል ነበረች። ይህ የሁለቱ ሃገራት አንድነት ከግማሽ ክፍለ ዘመን በላይ ለሚሆን እድሜ ተቋርጦ ቆይቶ በ1944 ዓ/ም ዳግም ተመልሷል፣ ኤርትራ የራስዋ ፓርላማ ኖሯት በፌዴሬሽን ከኢትዮጵያ ጋር ስትቀላቀል። በኋላም ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ በ1954 ዓ/ም የኤርትራ ፓርላማን አፍርሰው አርትራን አንድ ጠቅላይ ግዛታቸው አድርገው ከኢትዮጵያ ጋር ቀላቅለዋታል። እንግዲህ ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር በፌዴሬሽን ከተቀላቀለችበት ከ1944 እስከ 1983 ዓ/ም ደረስ ለአራት አስርት ዓመታት ገደማ ዳግም የኢትዮጵያ አካል ሆና ቆይታለች።

የኤርትራ ህዝብ በ1882 ዓ/ም ከኢትዮጵያ የተነጠለው በፍቃዱ አልነበረም። በቅኝ ገዢ አውሮፓዊቷ ጣሊያን በሃይል ተገዶ እንጂ። በ1944 ዓ/ም ከኢትዮጵያየ ጋር በፌዴሬሽን የተቀላቀለው በምርጫው ነበር። ራሱን በራሱ የማስተዳደር መብቱ እንደተጠበቀ የኢትዮጵያ አካል የሆነው ወዶና ፈቅዶ ነበር። በኋላ ይህ ራስን በራስ የማስተዳደር መብት ተንዶ በንጉሠ ነገሥቱ ግዛት ስር መጨፍለቁን ግን አልወደደውም። እናም ከዚህ በኋላ ባለው ጊዜ ለነጻነቱ ተዋግቷል። ከ1950ዎቹ አጋማሽ በኋላ ያሉት ሶስት አስርት ዓመታት የኤርትራ ህዝብ መራራ የነጻነት ትግል ያካሄደበት ነበር። እናም በ1983 ዓ/ም በወረሃ ግንቦት ነጻነቱን ተቀዳጀ። በ1983 ዓ/ም ግንቦት ከኢትዮጵያ ተነጥላ በዴፋክቶ እውቅና ራሷን ማስተዳደር የጀመረችው ኤርትራ፣ በ1985 ዓ/ም ግንቦት  በህዝበ ውሳኔ ነጻ የሃገረ ኤርትራ መንግስት ሆና ተቋቋመች።

በዚህ የኤርትራ ህዝብ ውሳኔ ያልተደሰቱ ኢትዮጵያውያን ቢኖሩም፣ በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ብሄሮችና ብሄረሰቦች፣ እንዲሁም በቀቅቱ የነበረው በብሄሮችና ብሄረሰቦች ተወካዮች የተቋቋመው የኢትዮጵያ የሽግግር መንግስት የኤርትራን ህዝብ የነፃነት ውሳኔ አክብሮ ተቀብሏል። ከሃገረ ኤርትራ መንግስት ምስረታ በኋላ በሁለቱ ሃገራት መንግስታትና ህዝቦች መሃከል መልካም ግንኙነት ነበር። ይህ መልካም ግንኙነት ግን አምስት ዓመታትን መሻገር አልቻለም። በ1990 ዓ/ም ግንቦት ወር ዋዜማ ላይ እንከን ገጠመው። ሁለቱ መንግስታት በወሰን ጉዳይ የተካረረ አለመግባባት ውስጥ ገቡ። ይህ የተካረረ አለመግባባት ከሰባ ሺህ በላይ የሚሆኑ የሁለቱን እህትማማች ሃገራት ልጆች ህይወት ወደበላ ጦርነት ተቀየረ።

ከጦርነቱ በፊት የነበረውን የሁለቱን ሃገራት መንግስታትና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት የተመለከተ ሃገራቱ ጦርነት ውስጥ የገባሉ ብሎ በፍጹም አይገምትም። ይሁን እንጂ መሆን ያልነበረበት ጦርነት ውስጥ ገቡ። ጦርነቱ ካበቃ በኋላ፣ ወደጦርነት ያስገባቸው የድንበር ጉዳይ በዓለም አቀፍ ዳኝነት ውሳኔ ቢሰጥበትም፣ ወሰን ተካለው ጥሩ ጎረቤታሞች መሆን አልቻሉም። ሁለቱም ወታደሮቻቸውን ማዶና ማዶ በተጠንቀቅ አሰልፈው ሰላምም ጦርነትም ያልሆነ ሁኔታ ውስጥ ቆይተዋል።

ሁለቱ ሃገራት ጥብቅ ታሪካዊ ትስስር አላቸው። የአንድ ሃገር ህዝብን ያህል የባህል መመሳሰል አላቸው። ቋንቋ ይጋራሉ። በመልክና በአካል ቅርጽ አንዱን ከሌላው መለየት አይቻልም። አንድ የዘር ግንድ ያላቸው ህዝቦች ናቸው። ከዚህ አኳያ ሲታይ ሁለቱም ወዳጅነት የሚፈልጉት መሆኑ ለጥያቄ የሚቀርብ ጉዳይ አይደለም። ይሁን እነጂ እርቅ እንዲወርድ ብዙ ሙከራዎች ቢደረጉም አልሳካ ብሎ ቆይቷል።

ዘንድሮ ግን ይህ የእርቅ እምቢታ ተሸንፈ። ወጣቱ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ የዘረጉት የሰላም እጅ በአዛውንቱ የሃገረ ኤርትራ ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ተቀባይነት አገኘ። ይህ ብዙዎችን ያስገረመ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስልጣን እንደተረከቡ ያቀረቡት የሰላም ጥሪ ተቀባይነቱን ማግኘቱን ተከትሎ፣ በእድሜ አንጋፋቸው ወደሆኑት የኤርትራ ፕሬዝዳንት ተጓዙ፣ እርቁን ተጨባጭ ለማደረግ።ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ  የልኡካን ቡድን በመላክ ተጨባጭ እርቅ የሚወርድበትን ጊዜ በዲፕሎማሲ ፕሮቶኮል ማጓተት አለመፈለጋቸው እጅግ የሚደነቅ የሰላም ፈላጊነት ማሳያ ነው።

ይህ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ የዲፕሎማሲ ፕሮቶኮልን ዘለው የወሰዱት የሰላም እርምጃ በኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂም ተቀባይነት አግኝቶ ከጥቂት ቀናት በኋላ ወደኢትዮጵያ መጡ። አንድ ወር በማይሞላ ጊዜ ውስጥ የተከናወነው የሁለቱ ሃገራት መሪዎች ጉብኝት፣ ተስፋ አስቆርጦ የነበረውን የሁለቱን ሃገራት እርቅ እውን ከማደረግ ባሻገር ህዝቦቻቸው በዚያው አፍታ ዓመታትን ተሻገሮ በሰላሙ ዘመን ወደነበረው የወንድማማችነት ግንኙነት ተመለሰዋል። ሁለቱ መሪዎች አንዱ በሌላው ሃገር ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት ህዝቡ የገለጸው ስሜት የሁለቱ ሃገራት ህዝቦች ሳይወዱ ተራርቀው የቆዩ መሆናቸውን ይናገራል።

ሁለቱ ሃገራት አጠቃላይ የሰላም ስምምነት መፈራረማቸውን ተከተሎ አንዱ በሌላው ሃገር ኤምባሲያቸውን አቋቋሙ፤ አምባሳደሮቻቸውንም ላኩ። የሃገራቱን የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ለማጠናከር ተቋርጦ የነበረውን የተሌኮሚዩኒኬሽን አገልግሎታቸውን ቀጠሉ፤ የሁለቱም ሃገራት አየር መንገዶች ለሃያ ዓመታት ያህል አቋርጠውት የነበረውን በረራ ጀመሩ። ኢትዮጵያ በኤርትራ ወደቦች መጠቀም የምትችልበትን ሁኔታ የማጥናት ስራ ተጀመረ። ከአራት ወር በፊት ይህ ይሆናል በሎ የገመተ ኢትዮጵያዊና ኤርትራዊ አልነበረም። የሃገረ ኤርትራ ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂም ቢሆኑ ይህ ይሆናል ብለው ያሰቡ አይመስለኝም። ኢጋድ፣ የአፍሪካ ህብረት፣ የተባበሩት መንግስታት ወዘተም ይህ ይሆናል በለው አልገመቱም። ድንገተኛና አስገራሚ፣ ግን ታሪካዊ ሁነት ነው።

ይህን ታሪክ የሰሩት የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ ናቸው። ይህ ድንቅ ታሪካዊ ተግባር እውቅና ሊሰጠው ይገባል። የጠቅላይ ሚኒስትሩ ተግባር በዓለማችን ታሪክ ውስጥ በጉልህ ተከትቦ ይኖራል። ይህ ጉልህ ታሪካዊ ተግባር እውቅና ሊሰጠው እንደሚገባ ያመኑት በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስዊድን አምባሳደር ኦል ስኩግ የስራ ዘመናቸውን ጨርሰው ሲሰናበቱ ባደረጉት ንግግር፤ የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ከአጎራባቻቸው ኤርትራ ጋር ላደረጉት ስኬታማ የሰላም ጥረት እውቅና ለመስጠት መስከረም ወር ላይ የሚካሄደው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ስብሰባ ላይ ግንባር ቀደም ተናጋሪ ሊሆኑ ይገባል የሚል አስተያየት አቅርበዋል። ሚ/ር ስኮግ በንግግራቸው፤ የዚህ አይነት የጠላትነት ሁኔታን ወደሰላም የሚቀይር ታሪካዊ መሪ ሲገኝ የተባበሩት መንግስታት ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ግንባር ቀደም ተናጋሪ ማደረግ የለብንም? ሲሉ ጠይቀዋል፤ ለጉዳዩ የሰጡትን አጽንኦት በሚያሳይ አኳኋን።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ለሰላም ላበረከቱት ጉልህ አስተዋጽኦ የክብር ተናጋሪ እንዲሆኑ ማድረግ ተገቢ ነው። ይህ መሆኑ የተባበሩት መንግስታት የተቋቋመለት ዋነኛ ዓላማ የሆነውን የዓለም ሰላም በማረጋገጥ ረገድ ጉልህ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ሰዎች መሪዎች እውቅና መስጠት ነው።

በአጠቃላይ፤ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የስዊድኑ የተባበሩት መንግስታት አምባሳደር ኦልፍ ስኩግ እንደገለጹት ሁኔታዎችን ወደበጎ የቀየሩ መሪ ናቸው። ይህ ሰላም አልባ የነበረውን ሁኔታ በሚያስደንቅ ቅስፈትና መጠን ወደሰላም የመቀየር እርምጃ በተመሳሳይ ሁኔታ ውስጥ ለሚገኙት የዓለም ሃገራት በሙሉ አነሳሽ ነው። በመሆኑም የዓለም ሰላምን ለማረጋገጥ እንደተወሰደ እርምጃ የሚቆጠር ነው። እናም አምባሳደር ስኩግ እንዳሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይና የፈጸሙት ሰላምን የማረጋገጥ ተግባር ዓለም አቀፍ እውቅና ሊሰጠው ይገባል።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy