Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የጅግጅጋው ጉዳይ

0 308

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የጅግጅጋው ጉዳይ

                                                            እምአዕላፍ ህሩይ

ከመሰንበቻው በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል መዲና በሆነችው ጅግጅጋ ከተማ የተፈፀመው የሰው ህይወት መጥፋት፣ የእምነት ቦታዎች መቃጠልና የንብረት ዘረፋ መከናወን አሳዛኝ ድርጊት ነው። ድርጊቱ ኢትዮጵያዊ የሆኑትን የመቻቻል፣ የመተሳሰብና አብሮ የመኖር የዘመናት እሴቶችን ፈፅሞ የሚወክል አይደለም። ርግጥ የጅግጅጋው ክስተት እንዲሁ ዝም ብሎ የተከናወነ አይደለም— የራሱ የሆነ አነሳሽ ምክንያት ያለው ነው።

እንደሚታወቀው በክልሉ የሰብዓዊና የዴሞክራሲ መብቶች ጥሰት ሲፈፀም ነበር— በተለይ በክልሉ ተወላጆች ላይ። የክልሉ ተወላጆች “የዜጎች፣ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ይከበሩ፤ የፍቅር፣ የአንድነትና የመደመር ሀገራዊ ሪፎርም በክልላችንም ተግባራዊ ይሁን” ብለው በመጠየቃቸው ብቻ ከፍተኛ ወከባና ጉዳት ደርሶባቸዋል— በተለይም በሀገር ሽማግሌዎችና በህዝብ ተወካዮች ላይ።

ታዲያ ይህ ሁኔታ ተወላጆቹን የችግሩ ቀዳሚ ገፈት ቀማሽ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል። ተወላጆቹ ለውጡን እንደሚደግፉ በማሳወቃቸው፣ የሰብዓዊና የዴሞክራሲ መብቶች እንዲከበሩ በመጠየቃቸው፣ መልካም አስተዳደርና አገልግሎት አሰጣጥ እንዲሻሻል አቤቱታ በማቅረባቸው የጥቃት ሰለባ መሆናቸው የሚዘነጋ አይደለም። ጥቃቱም በሂደት ወደ ሌሎች ኢትዮጵያዊያን መሻገሩ ግልፅ ነው።

ርግጥ እንዲህ ዓይነቶቹ ጥቃቶች በሁሉም ዜጎች ላይ ሲፈፀም ፌዴራል መንግስት እጁን አጣጥፎ አልተቀመጠም። ለጉዳዩ እልባት ለመስጠት በተለያዩ ወቅቶች ተንቀሳቅሷል። እናም በክልሉ የሚስተዋሉ የስብዓዊና የዴሞክራሲያዊ መብቶች ጥሰት እንዲፈቱ እንዲሁም በክልሉ የሚኖረው ህዝብ ከስቃይና እንግልት እንዲድን የፌዴራል መንግስት በተለያዩ ወቅቶች ከክልሉ አመራር ጋር ውይይትና ምክክር ሲያደርግ ቆይቷል።

ሆኖም ‘ሞትኩ ለስልጣን’ ባይ ጥቂት አመራሮች ችግሮቹን ከመፍታት ይልቅ፤  የማባባስና የማወሳሰብ ተግባሮችን ሲፈፅሙ ነበር። ይህ ሁኔታም በስተመጨረሻው በመግቢያዬ ላይ የጠቀስኩት አሳዛኝ ክስተት በጅግጅጋ ከተማ ውስጥ እንዲፈፀም ምክንያት ሆኗል። በጥቂት ስልጣንን የሙጢኝ ባሉ አመራሮች ፍላጎት የተፈፀመውን ይህን ድርጊት መላው የክልሉ ህብረተሰብ ሊያወግዘው የሚገባ ይመስለኛል። ምክንያቱም በክልሉ ተወላጆችም ይሁን በሌሎች ኢትዮጵያዊያን ላይ የተፈጠረው አሳዛኝ ድርጊት የትኛውንም ህዝብ ይሁን የህብረተሰብ ክፍል ስለማይወክል ነው።

ያም ሆኖ ችግሩ እንደተከሰተ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የተሰማቸውን ጥልቅ ሃዘን ገልፀዋል። የክልሉ መንግስትም የተፈጠረው ችግር ከአቅሙ በላይ መሆኑን በመግለፅ የፌዴራል የፀጥታ ሃይሎች ወደ ክልሉ ገብተው የሰላምና የመረጋጋት ስራዎችን እንዲያከናውኑ ባቀረበው ጥያቄ መሰረት፤ ህገ መንግስቱን ተመርኩዞ የሀገር መከላከያ ሰራዊትና የፌዴራል ፖሊስ ወደ ክልሉ ገብተው ህዝቦችን እንዲታደጉ አዘዋል። ይህም በክልሉ የታየውን ችግር ለመቅረፍና የዜጎችን ሰብዊና ዴሞክራሲያዊ መብት ለመጠበቅ እንዲሁም የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴን ለማረጋጋትና ክልሉ ወደነበረበት ሰላማዊ ሁኔታ እንዲመለስ የሚያደርግ ርምጃ ነው።

የኢፌዴሪ መንግስት ኮሙኒዩኬሽን ጉዳዩች ጽህፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሺዴ የመከላከያና የፖሊስ ሰራዊት ኃይሎች ወደ ክልሉ ገብተው ሰላምና መረጋጋትን እያሰፈኑ መሆናቸውን በቅርቡ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ማሳወቃቸው የዚህ እውነታ አስረጅ ነው። ኃላፊ ሚኒስትሩ በክልሉ የተሰማራው ሰራዊት ዓላማ የተፈጠረውን የፀጥታ ችግር ለማስወገድ የክልሉን ሰላም ማስከበርና የህዝቡን ደህንነት መጠበቅ መሆኑንም አስረድተዋል።

ርግጥ ሰራዊቱ ወደ ክልሉ የገባው፤ የኢፌዴሪ ህገ መንግስቱ በሚያዘው እንዲሁም በህዝብ ተወካዩች ምክር ቤት ወጥቶ በነጋሪት ጋዜጣ ላይ ታትሞ ከሐምሌ 3 ቀን 1995 ዓ.ም ጀምሮ በስራ ላይ በዋለው አዋጅ ቁጥር 359/95 መሰረት ነው። በኢፌዴሪ ህገ መንግስት በአንቀፅ 51 (4) እንደተቀመጠው፤ ከክልል አቅም በላይ የሆነ የፀጥታ መደፍረስ ሲያጋጥም ብክልልሉ መስተዳድር ጥያቄ መሰረት የፌዴራል መንግስቱ የመከላከያ ኃይልን ሊያሰማራ ይችላል።

በዚህ ህገ መንግስታዊ ድንጋጌ መሰረት፤ የፌዴራል መንግስት በክልል ጣልቃ የሚገባበት ስርዓት ለመደንገግ የወጣው አዋጅ ቁጥር 359/95 በሰብዓዊ መብት ምክንያት ስለሚደረግ ጣልቃ ገብነት በክፍል ሶስት ቁጥር 7 ላይ፤ “በአንድ ክልል ውስጥ ህገ መንግስቱንና ህገ መንግስቱን መሰረት አድርገው በወጡ ህጎች የተመለከቱትን የሰብዓዊ መብት ድንጋጌዎች የመጣስ ድርጊት ሲፈፀምና በህግ አስከባሪውና በዳኝነት አካሉ በቁጥጥር ስር ለማዋል ካልተቻለ የሰብዓዊ መብት ድርጊት እንደተፈፀመ ይቆጠራል” የሚል ድንጋጌ ሰፍሯል።

በተጨማሪም ክልሉ ለፌዴራል መንግስት ያቀረበውን ጥያቄ ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የጸጥታውን መደፍረስ ለመቆጣጠር እንደ ችግሩ ክብደት የመከላከያ ሰራዊትን ወይም የፌዴራል ፖሊስ ሃይልን ወይም ሁለቱንም እንደሚያሰማራና የሚሰማራውም ሃይል በሚመለከተው የፌዴራል መንግስት አካል የሚታዘዝ እንደሚሆን በአዋጁ ክፍል ሁለት፣ ተራ ቁጥር 5 (1) ላይ በግልፅ ተቀምጧል። እናም በእነዚህ ድንጋጌዎች መሰረት መከላከያና የፌዴራል ፖሊስ ወደ ክልሉ ገብተው ሰላምና መረጋጋትን እንዲያሰፍኑ መታዘዛቸውን መገንዘብ ተገቢ ይሆናል።           

ታዲያ እዚህ ላይ የክልሉ ፕሬዚዳንት የነበሩት አቶ አብዲ ዑመር መሐመድ ስልጣናቸውን በራሳቸው ውሳኔ መልቀቃቸውን መረዳት አስፈላጊ ነው። ምክንያቱም ስልጣን እንዲለቁ ያስገደዳቸው አካል ስለሌለ ነው። አቶ አብዲ ስልጣን እንዲለቁም ይሁን ሌላ አመራር እንዲሾም የመምረጥ መብት የክልሉ ምክር ቤት ነው። በዚህ መሰረትም በአሁኑ ወቅት ምክር ቤቱ አዲስ ፕሬዚዳንት እስኪመርጥ ድረስ፤ በጊዜያዊነት ክልሉን የሚመሩ ኃላፊ ተመድበዋል። ይሁንና የክልሉ ምክር ቤት ሹመቱን ገና አላፀደቀውም።

ያም ሆኖ በአሁኑ ወቅት የፌዴራል የፀጥታ አካላት በመግባታቸው ከተማዋና ሌሎች የክልሉ አካባቢዎች እየተረጋጉ መምጣታቸውን መረጃዎች ያስረዳሉ። ከመኖሪያቸው ሸሽተው በሃይማኖት ስፍራዎችና በሌሎች አካባቢዎች ተጠልለው የሚገኙ ዜጎችም ወደ ነበሩበት ቀየ እየተመለሱ ነው።

እነዚህ የጥቂት ቀናት እውነታዎች፤ ከክልሉ መንግስት አቅም በላይ የሆነው የፀጥታ ችግር በሰራዊቱ የሰከነ የማረጋጋት ስራ በቁጥጥር ስር እየዋለ መሆኑን የሚያሳዩ ይመስሉኛል። በክልሉ ሰላምና መረጋጋትን ለማስፈን የተወሰደው ርምጃም ተገቢ፣ ወቅታዊና ትክክል መሆኑንም የሚያረጋግጡ ጭምር ናቸው ብዬም አምናለሁ። ርግጥ በአሁኑ ወቅት በክልሉ የተገኘው መረጋጋት እንዲጠናከርና ስፋቱ እንዲጨምር የየአካባቢው የጎሳ መሪዎች፣ ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች ለሰላም የሚጫወቱትን ሚና ማጠናከር ይኖርባቸዋል። ምክንያቱም የየትኛውም አካባቢ ሰላም የሚረጋገጠው በአካባቢው ህብረተሰብ የነቃ ተሳትፎ ስለሆነ ነው።

ከሁሉም በላይ በጅግጅጋ የተፈፀመው አሳዛኝ ጉዳይ ስልጣንን የሙጥኝ ባሉ ጥቂት አመራሮች የፈጠሩት ተግባር መሆኑን አጠቃላይ የክልሉ ህዝብ መረዳት ይኖርበታል። እንዳልኩት እነዚህ ጥቂት አካላት የስልጣን ዕድሜያቸውን ለማስረዘም ሲሉ ራሳቸው በክልሉ ተወላጆችና ነዋሪዎች ላይ የፈጠሩትን የሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብት ጥሰቶች ለደባበቅ ሲሉ ሁኔታውን ሲያጋግሉ የቆዩ ናቸው።

በእኔ እምነት፤ እነዚህ ጥቂት አመራሮች በሰው ስቃይና ሰቆቃ የሚነግዱ ናቸው። እነዚህ ጥቂት አመራሮች ወትሮም ቢሆን ስለ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ደንታ የሌላቸው በመሆናቸው፤ ከስልጣናቸው ውጭ የሚታያቸው ምንም ነገር የለም። ዳሩ ግን እንዲህ ዓይነቱ ለህዝብ ያልቆመ የራስ ጥቅምን ብቻ በማሳደድ “በእኔ” ባይነት የሚቀነቀን አስተሳሰብ፤ ሀገሪቱና ህዝቦቿ እያካሄዱ ባሉት ፍቅርንና አንድነትን በሚደምረው “የእኛነት” የለውጥ ሪፎርም ሂደት ውስጥ ቅንጣት ያህል ቦታ የለውም። እንደ ጅግጅጋው ዓይነት አሳዛኝ ክስተት፤ ዜጎቿ ኢትዮጵያዊነትንና አንድነትን እያቀነቀኑ ባሉባት አዲሲቷ ኢትዮጵያ ውስጥ መቼም ቢሆን በየትኛውም ስፍራ ተቀባይነት ሊኖረው አይችልም።

እናም ይህን ሃቅ የክልሉ ተወላጆችም ይሁኑ ነዋሪዎች በሚገባ በመረዳት፤ የሁሉንም ዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን በማስከበር ላይ ከሚገኙት ከመከላከያና ከፌዴራል ፖሊስ ኃይሎች ጎን በመሰለፍ አጥፊዎችን የማጋለጥ ተግባር መከወን አለባቸው። አጥፊዎችን ህግ ፊት ማቅረብ ማለት፤ የተፈጠረውን ችግር የሚያርም እንዲሁም ዳግም እንዳይከሰት የሚያደርግ ነው። ስለሆነም የክልሉ ተወላጆችና ነዋሪዎች እየተደረገ ባለው ሰላምን የማረጋገጥና ዜጎችን ከአደጋ የመከላከል ሂደት ውስጥ ግንባር ቀደም ሆነው መሳተፍ ይኖርባቸዋል እላለሁ—በየትኛውም አካባቢ ሰላም እውን የሚሆነው በህዝቡ የማይተካ ተሳትፎ ነውና።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy