Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ይቅርታ— እስከ ሚኒሶታ

0 2,510

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

እምአዕላፍ ህሩይ

(ክፍል አንድ)

መግቢያ

የእርቅና የይቅርታ መንደሩ “ጨፌ አራራ” (Caffee Ararraa) ስራውን ከውስጥም ከውጭም እያጣደፈው ነው። ላለፉት ወራቶች በሀገር ውስጥ ያካሄዳቸው የፍቅር፣ የእርቅ፣ የይቅርታና የመደመር ጉዞዎች ሰምሮለታል። ከመንደር እስከ ሰፈር፣ ከሰፈር እስከ ቀበሌ፣ ከቀበሌ እስከ ወረዳ፣ ከወረዳ እስከ ክፍለ ከተማ/ዞን እንዲሁም እስከ ክልል ብሎም እስከ ሀገር ተደምሮ በአንድነት የመትመም መንገድን ተከትሏል።

ጠሪና ተጠሪ እንዲሁም ጋባዥና ተጋባዥ ሳይኖር፣ በየአካባቢው በባንዴራዎች አሸብርቆ የተካሄደው የመደመር ድባብ የነገ ተስፋን ሰንቆ ያሸበረቀ ነበር። ድባቡ ነገ እዚህ ሀገር ውስጥ ስለሚኖረው የአስተማማኝ ሰላም፣ የድሃውን ጉረሮ ስለሚያርስ የልማት ዕድገትና የዴሞክራሲ ልህቀት የሚናገር ነው ማለት ይቻላል።

በዚህ አስደማሚ ድባብ ውስጥ ሆኖ፤ “እኔ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ጋር ተደምሬያለሁ። እርስዎስ?/አንተስ?/አንቺስ?” እያለ ያልጠየቀ ተሰላፊን ከመንደር እስከ ሀገር ፈልጎ ማግኘት ከባድ ሆኖ አልፏል። እንዲህ ዓይነቱ በሀገራዊ አንድነት ስሜት ውስጥ ሆኖ ለመሪ የተሰጠ ይሁንታና ድጋፍ የኢትዮጵያችን ታሪካዊ ክስተት ይመስለኛል። እንዲያውም በሀገራችን የፖለቲካ ሂደት ውስጥ የመጀመሪያው ሳይሆን የሚቀር አይመስለኝም። ይህን ክስተት የሚሰብር “ሪኮርድ” ከተገኘ ወደፊት የምናየው ጉዳይ ይሆናል። እኔ ግን አይመስለኝም። እናም ይህ ታሪካዊ ክስተት በድርሳናት ውስጥ ተከትቦ የሚኖር ነው። ታዲያ ክስሰቱ ምሉዕ (Inclusive) ይሆን ዘንድ በውጭ የሚኖሩትን ኢትዮጵያዊያንንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያንን ማቀፍ ነበረበት።

እናም ፍቅርንና መደመርን በሀገራችን ውስጥ የፈጠረው የ“ጨፌ አራራው” መንደር፤ ይቅርታን ሰንቆ፣ ፀብና ተንኮልን አርቆ፣ ጥላቻና ቂምን አስወልቆ፣ ባህር ማዶ ያለው ዜጋው ላይ ተጋርዶ የነበረውን የልዩነት ግርዶሽ ለመቅደድ በአንድነት ጢያራ ላይ ተሳፍሮ ወደ ሀገረ አሜሪካ እንደሚያቀና ሲነገርለት ሰንብቷል። የመንደሩ ፊታውራሪና ቀያሽ መሃንዲስ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድን፣ “ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው” ያሉትን ፈላስፋውን ኦቦ ለማ መገርሳን፣ “በእምባውም ሆነ በጭንቅላቱ ያግዘኝ ነበር” የሚል ምስክርነት ከእርቁ መሃንዲስ የተቸራቸው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁንና ሌሎች ልዑካንን ያካተተው የእርቅ መንደሩ ጉዞ ከሐምሌ 19 እስከ ሐምሌ 23 ቀን 2010 ዓ.ም ድረስ ሶስት ከተማዎች ላይ ቆይታ አድርጓል። ዋሽንግተን ዲሲ፣ ሎስ አንጀለስና ሚኒሶታ ከተማዎች ላይ።

“ግንቡ” እና “ድልድዩ”

‘የምን ግንብ?፣ የምንስ ድልድይ?’ ብሎ ለሚጠይቅ ሰው፤ ግንቡና ድልድዩ የመለየትና የመገናኘት ማሳያዎች መሆናቸውን እንድይዝልኝ እወዳለሁ። መለየትና መገናኘት የህይወት ሁለት ጫፍ ናቸው። የተለያየ፤ የልዩነቱ አጥር በግንብ ሊመሰል ይችላል። የተገናኘም፤ የግንኙነቱ ስምረት በተዘረጋ አዲስ ድልድይ መገናኛ ሆኖ ሊቀርብ መቻሉ ርግጥ ነው። እናም አጥርና ድልድይ የሁለት አፅናፍ ማመላከቻዎች አሊያም ማንፀሪያዎች መሆናቸው ልብ ይባልልኝ። ለዚህም ነው— በሀገረ አሜሪካ ውስጥ “ግድቡን እናፍርስ፣ ድልድዩን እንገንባ” የሚል መሪ ቃል በእርቅ መንደሩ ተጓዦች ሲነገር ነበረው።

“የጨፌ አራራው” የእርቅ መንደር ባለሟሎች፤ እነ ዶክተር አብይ፤ ዳያስፖራው ከሀገሩ ጋር የተለያየበትን “ግንብ” አፍርሰዋል። አዲስ ግንኙነት የሚመሰርትበትን ድልድይም ገንብተዋል። የልዩነቱን “ግንብ” ማፍረስ የጀመሩት በዋሽንግተን ዲሲ ከተማ ላይ ነው፤ 25 ሺህ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በተገኙበት አዳራሽ ውስጥ። ምንም እንኳን በእንዲህ ዓይነቱ መድረክ ላይ ለመገኘት ባልታደልም፤ ዛሬ በዘመነውና የመረጃ ልውውጡ “በብርሃን ፍጥነት” እየተመሰለ በሚነገርበት ዓለም ውስጥ በመሆኔ ተዓምራዊዎቹን የይቅርታና የፍቅር እንዲሁም የመደመር መድረኮችን ተመልክቻለሁ። “ግንቡ” በመርቴሎና በመዶሻ ሳይሆን፣ በይቅርታና በፍቅር፤ “ድልድዩ”ም በልዩ ሀገራዊ የአንድነትና የመተሳሰብ መንፈስ ሲገነባ አይቻለሁ። ትውልድ ተሻጋሪ ይሆን ዘንድ ቃል ሲገባ ተመልክቻለሁ።

ዶክተር አብይ አህመድ፤ በዲሲው የመደመር መድረክ ላይ፤ “የገነባነውን ከፋፋይ የጥላቻ ግንብ ዛሬ ለማፍረስ ቃል እንግባ። ግንብ ማፍረስ ግን በቂ አይደለም። ድልድይ መገንባት ይገባናል። ርግጥ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር የተቸረውን ከበሬታና የአዲስ መንገድ እሳቤ እውቅና በዚህ አጭር ፅሑፍ ላይ ለመዘርዘር አስቸጋሪ ነው። የመድረኩ ታዳሚ ያሳየው የነበረው ደስታና የእኔነት መንፈስ ግን ከእዝነ ልቦና የሚጠፋ አይደለም። በዳያስፖራው ውስጥ ያለው የፈረሰው የልዩነትና የጥላቻ “ግንብ” ተደርምሶ ሲወድቅ እንዲሁ በእዝነ ልቦና ይታይ ነበር። ከወቅቱ የመደመር ጉዞ ጋር በተያያዘ ለዶክተር አብይ ሲቀርቡላቸው የነበሩት ጥያቄዎችና የተሰጡት ምላሾች የኢትዮጵያዊያኑንና የትውልደ ኢትዮጵያኑን አንጀት ያራሱ ነበሩ። ዳያስፖራውን ወደ አንድ ሀገራዊ ስሜት እንዲመጣ ያደረጉም ናቸው።  

በተለይ ዶክተር አብይ፤ “በይቅርታ ዛሬ እንደመር። ስንደመር ትልቅ እንሆናለን። ለሁላችንም የምትበቃ አንድ ታላቅ ሀገር በጋራ እንገንባ።” በማለት ለዳያስፖራው ያቀረቡት ጥሪ፤ ኢትዮጵያዊያኑና ትውልደ ኢትዮጵያዊያኑ ሲደመሩ ሊያደርጉት የሚችሉትን አንድ ትልቅ ምስል የከሰተ ይመስለኛል። ይኸውም የመደመር ጉዞው ዓላማ፤  በፍቅርና በአንድነት አበው ያስረከቡንን የአፍሪካ የነፃነት አርማ የሆነችውን ኢትዮጵያ ለመገንባት ልጆቿ የሆኑት ዳያስፖራዎች ጉልህ ሚና እንዳላቸው ያላቸው መሆኑን ነው።

ርግጥ ዶክተር አብይ ለዲሲዎቹ ታዳሚዎች እንዳሉት ከተነገሩን አሊያም ከምናውቃቸው ታሪኮች ውስጥ የሚያስታርቁንና የሚያፋቅሩንን መውሰድ የነበረውን የልዩነት “ግንብ” የሚደረምሰው ነው። ያ ካፋፋይ “ግንብ” ከተደረመሰ፤ “ድልድዩ” ያለ በጥቂት ጥረት ብቻ ሊገነባ የሚችል ይመስለኛል። ዳያስፖራው ጥላቻን፣ ቂምንና ቁርሾን በይቅርታ ስሜት እንደ ተረት “በነበርነት” አልፏቸው በአንድነት ከቆመ፤ የሁሉም ሀገር የሆነችውን ኢትዮጵያን ልመና እና ጬኸት በፍትህ፣ በልማት፣ በሰላምና በአንድነት መንፈስ “ድልድይ” ሊያንፃት ይችላል። ኢትዮጵያችን “የእኔ” ሳይሆን “የእኛ” ናትና።

በዲሲው መድረክ፤ አሳዛኝ ቢሆንም አንድ ተደማሪ መልዕክት ተላልፏል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የፖለቲካ አሻጥር፣ የኢኮኖሚ ተንኮልና መግደል ነውር ብቻ ሳይሆን መሸነፍ ጭምር መሆኑን ባወሱበት በዚህ መድረክ ላይ፤ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዋና ሰራ አስኪያጅ የነበሩት የኢንጂነር ስመኘውን በሰው እጅ መገደል አስመልክተው፤ “ኢንጂነር ስመኘውን መግደል ይቻላል እንጂ፣ የህዳሴ ግድብን ማቆም አይቻልም” የሚለው ልብ የሚነካ ንግግራቸው ግድያ የሽንፈቶች ሁሉ ሽንፈት መሆኑን አስረግጠው ገልፀዋል።

በእኔ እምነት ይህ ንግግራቸው ዶክተር አብይ ስለ ራሳቸው ደህንነት ሲጠየቁም ጭምር “ለውጥ አራማጁን (Reformer) መግደል ይቻል ይሆን እንጂ፤ ለውጡን (Reform) ግን መግደል ፈፅሞ አይቻልም።” ከሚል እይታቸው የሚቀዳ ይመስለኛል። ርግጥ አንድን ግለሰብ ለይቶ በመግደል በሀገር ውስጥ የተጀመረን ስራ አሊያም ለውጥን ማስቆም አይቻልም። በግለሰብ ላይ ግድያ በመፈፀም አንድን ሀገራዊ ስራ አስቆማለሁ ወይም ለውጥን እገታለሁ ብሎ የሚያስብ ካለ እርሱ ራሱ ሳይሞት በቁም ሃሳቡ የሞተ ይመስለኛል። ምክንያቱም ግለሰብ…ሰው ስለሆነ ነው። ሰው ደግሞ ህያው አይደለም። ይወለዳል፣ ያድጋል፣ ይሞታል።

ሀገር ግን ዘላቂና ቋሚ ናት። በየጊዜው በሚፈጠር የትውልድ ሰንሰለትና ፍላጎት እየተያያዘች በታሪክ ዑደት ውስጥ ጉዞዋን ትቀጥላለች። አዲሲቷ ኢትዮጵያም ዛሬ ለቁርጥ ቀን የሚሆኑ ልጆች አሏት። እናም ዶክተር አብይ በመድረኩ ላይ እንዳሉት፤ “የጀመርነውን እንጨርሰዋለን፤ ኢትዮጵያም በታላቅ ጎዳና ትገሰግሳለች።” በቃ! እውነታው ይኸው ነው። ታሪክን የሚሰሩ ግለሰቦች ሊያልፉ ይችላሉ። የሚሰራው ታሪክ ግን እንደ ሸማኔ ድር እየተዳወረ ሂደቱን ይቀጥላል።…ያም ሆኖ በዲሲው መድረክ ላይ በዳያስፖራው መካከል የነበረው የልዩነት “ግንብ” ተንዷል፤ የይቅርታ፣ የፍቅርና የመደመር “ድልድይም” ተገንብቷል።…ይህ የዳያስፖራው የጋለ ስሜት በውጤት ታጅቦና “የኢትዮጵያዊያን ቀን” ሐምሌ 21 እንዲሆን በከተማዋ ከንቲባ ተወስኖ መደመሩ ወደ ሎስ አንጀለስ አምርቷል።…

እንደ ዲሲ ሁሉ፤ ሎስ አንጀለስም ተደምራለች፤ ተደማምራለች። ከመደመር ባለፈም በዚያች ከተማ ልክ እንደ ዲሲው ሁሉ አንድ አስገራሚ ታሪክ ተሰርቷል። ከድማሬው በፊት ወደዚሁ ተደማሪ ታሪክ አመራለሁ። ይህ የታሪክ ክስተት፤ በሎስ አንጀለስ ከተማ በየዓመቱ ሐምሌ 22 ቀን “የኢትዮጵያዊያን ቀን” ሆኖ እንዲከበር የከተማዋ ከንቲባ ለዶክተር አብይ የምስክር ወረቀት ማስረከባቸው ነው። በታሪክ ላይ የተፃፈ ደማቅ ታሪክ ተደርጎም ሊወሰድ ይችላል።

አዎ! ወትሮም “ጨፌ አራራ” የፍቅር መንደር ነውና ከሀገር ውስጥ አልፎ በሰው ሀገርም ኢትዮጵያንና ዜጎቿን ከፍ አድርጓል። ሎስ አንጀለሶችን በተግባር ፍቅር አንበርክኮ ማርኳቸዋል። በእኔ እምነት፤ በዲሲም ይሁን በሎስ አንጀለስ “የኢትዮጵያዊያን ቀን” ሆኖ እንዲከበር የተወሰነው ዕለት፤ “ከጨፌ አራራ” የአስተሳሰብ ልህቀት ጋር መሳ ለመሳ የሚሄድ ሆኖ አግንኜዋለሁ—ከፍቅርና ከአንድነት የለውጥ አስተሳሰብ ጋር።…ውድ አንባቢያን! የ“ግንቡ” እና “ድልድዩ ትርክቴ በዚህ አላበቃም። ተከታዩን ምልከታዬን በክፍል ሁለት ፅሑፌ ይዤ እመለሳለሁ።ይቅርታ— እስከ ሚኒሶታ

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy