Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

‘ይኸው የአፍራሾቹ ሚና…’

0 313

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

‘ይኸው የአፍራሾቹ ሚና…’

                                                      ታዬ ከበደ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በአገር ውስጥና በውጭ አገራት ያካሄዷቸው ጉብኝቶች ለአገራችን እና ለምንገኝበት የአፍሪካ ቀንድ ቀጠና ዘላቂ ሰላም መኖር መሠረት እየጣለ ነው። ይሁን እንጂ ከዚህ በተጻራሪ ሁኔታ በአገራችን የተጀመረውን ለውጥ ለማደናቀፍ አንዳንድ ተገቢ ያዕሆኑ እንቅስቃሴዎች እየተካሄዱ ናቸው።

እነዚህ አፍራሽ እንቅስቃሴዎች የለውጥ ደጋፊ የሆነውን ብዙሃኑን ህዝብ የማይወክሉ፣ በተለይም በአንዳንድ የአገራችን ክፍሎች የሚካሄዱት ግጭቶች የትኛውንም ህዝብ ወይም ሃይማኖት ውክልና የሌላቸው መሆናቸው ይታወቃል።

በስውር የሚንቀሳቀሱ ጥቂት አካላት እያራመዱት ያሉት ዓላማ ህዝቡን ስጋት ውስጥ መክተት ወይም አገራችን ለስጋት የተጋለጠች አስመስሎ በማቅረብ የተጀመረውን ሂደት በተቻለ መጠን ለማደናቀፍ እና ለመቀልበስ መጣር መሆኑ ግልጽ ነው።

በመሆኑም ብዙሃኑ ህዝብ የአገሩን ሰላምና የተጀመረውን የለውጥ ጉዞ በመጠበቅ ረገድ ግንባር ቀደም ሚናውን አጠናክሮ ሊወጣ ይገባል። ስለሆነም ህዝቡ ‘ይኸው የአፍራሾቹ ሚና…’ ብሎ በማጋለጥ የጥቂት አፍራሾችን እኩይ ተግባር ለህግ ማቅረብ ይኖርበታል።

በየትኛውም አገር ውስጥ የሰላም ጠባቂ ህዝብ ነው። ህግ ቢወጣም፣ ሰራዊት ቢቆምም ሰላሙ በህዝብ እስካልተደገፈ ድረስ እውን ሊሆን አይችልም። ከለውጡ ወዲያና ወዲህ ባሉት ጊዜያቶች በሀገራችን የታየው የሰላም ሁኔታ ይህን አባባል ይደግፋል።

ከለውጡ በፊት በነበሩት ጊዜያት በአብዛኛው የሀገራችን ክፍሎች ውስጥ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሰው ይሞታል፤ ከኖረበት ቀየ ይባረራል፤ ንብረት ይወድማል። ሆኖም ለውጡ እውን ከሆነ በኋላ ህዝቦች የተገኘውን ለውጥ በመደገፍ ሰላማዊ ሰልፎችን አካሂደዋል። ለለውጡ እውቅናም ሰጥተዋል። ይህም አንፃራዊ ሰላምን በአገራችን መፍጠር ችሏል።

ሆኖም አሁንም ቢሆን በአንዳንድ አካባቢዎች በአፍራሽ ሃይሎች በሚከሰቱ ግጭቶች ሳቢያ ችግር እየተፈጠረ ነው። ይህን ችግር ማስቆም ያለበት ህዝቡ ነው። ምክንያቱም የችግሩን ፈጣሪዎች ለይቶ ስለሚያውቃቸው ነው። ህዝብ በየአካባቢው እነማን ግጭት ጠንሳሾች እንደሆኑ፣ እነማን ሰላማዊና ህግን መሰረት አድርገው እንደሚንቀሳቀሱ ያውቃል። ከእርሱ የሚሰወር አንዳችም ነገር የለም።

ቀደም ሲል ለመጥቀስ እንደሞከርኩት በዴሞክራሲያዊ አገር ውስጥ አንድ ነገር በተፈጠረ ቁጥር የፀጥታ ሃይል ብቻ በማሰማራት ለውጥ ማምጣት አይቻልም። የየቀየው ባለቤት ህዝቡ ነው። በፀጥታ ሃይል የሚሰጥ ምላሽ መሰረቱ ምናልባት ነገሮችን ለማረጋጋት ይጠቅም ይሆናል። ይሁን እንጂ ዘላቂ መፍትሔ ሊሆን የሚችል አይመስለኝም። እናም የየመንደሩ ጠባቂና የሰላም ዘብ ህብረተሰቡ እንደመሆኑ መጠን ለሰላሙ መትጋት ይኖርበታል።

የአገራችን ህዝብ ላለፉት ሶስት ዓመታት የተራመዳቸው አባጣና ጎርባጣ ውጣ ውረዶች በአሁኑ ወቅት የሚቀራቸው ተጨባጭ ለውጦች ቢኖሩም፤ ከትናንቱ በተሻለ ቁመና እንደሚገኙ ያውቃል። አሁን የተገኘው ለውጥ የአገሪቱ እድገት ሁሉንም ዜጎች ተጠቃሚ እንዲያደርግ በማሰብ የልማት ስራዎችን የሚያከናውን ነው። የለውጡ አዲስ የአሰራር አቅጣጫዎች ህዝብን ያማከለ በመሆኑ በዓለም አቀፉ ማህበረሰብና በታላላቅ የገንዘብ ተቋማት አድናቆት የተቸረው ነው።

ህዝቡን ተጠቃሚ የሚያደርግ አዲስ አሰራር እስከተፈጠረ ድረስ እንዲሁም በህዝቡ የባለቤትነት መንፈስ የሚዘወር ሰላም እስካለ ድረስ፤ ሰርቶ መለወጥና ማደግ የማይቻልበት ምንም ዓይነት ምክንያት የለም። ሁሉም ህዝብ እኩል ተጠቃሚ የሚሆንበት አሰራር በለውጡ እየተተገበረ በመሆኑ ይህን እድል አጠንክሮ መያዝ ይገባል። ለዚህም የለውጡን አደናቃፊዎች ከውስጡ ማስወገድ ይኖርበታል።

የእነዚህን አካላት ማንነት በመገንዘብ ሊታገላቸውና ቅስቀሳቸውንም ሊያከሽፍ ይገባል። በውስጡ ያሉትን አፍራሽ ሃይሎች በመለየት እንዲሁም በየማህበራዊ ሚዲያው በሺህ የሚቆጠሩ አካውንቶችን በመክፈት የእርስ በርስ ግጭት ውስጥ እንድንገባ የሚሰሩ አካላትንም ማወቅ ይኖርበታል። ከህብረተሰቡ ውስጥ ከፍተኛ ቁጥር ያለውና ለዚህ ችግር ሰለባ ሊሆን የሚችለው ወጣት ይህን ሁኔታ መገንዘብ አለበት።

እንደሚታወቀው ሁሉ የአገራችን ወጣት ባለ ራዕይና ተስፋ ያለው ነው። የዛሬው ትውልድ ወጣት የለውጡ አካልና ባለቤት ነው። ይህ ወጣት ዛሬ “ሰርተህ ተለወጥ፤ እኔ የምትሰራበትን ምህዳር አመቻችልሃለው” የሚል የለውጥ መንግስት አለው። ችግሩን በህዝባዊ መንፈስ የሚጋራው ለውጥ አራማጅ አመራር ባለቤትም ነው። ችግር ካለ መፍትሔንም የሚያገኘው ከአዲሱ አመራር ነው።

እርግጥ በየትኛውም ሀገር ውስጥ ችግሮች ይኖራሉ። የለውጥ ሂደት ስንክሳሮች አይጠፉትም። እንኳንስ በለውጥ ሂደት ላይ በምትገኘው አገራችን ቀርቶ፣ ባደጉት አገሮችም ውስጥ ቢሆን ችግር መኖሩ አይቀርም። የአልጋ በአልጋ መንገድ በየትኛውም አገር ውስጥ የለም። በመንግስት የስራ አስፈፃሚዎችም ውስጥ ችግር ሊኖር ይችላል።

ይሁን እንጂ ችግሩን መፍታት የሚቻለው በሰላማዊና በህጋዊ መንገድ እንጂ የራሳቸው አጀንዳ ባላቸው የፈጠራ ወሬን በማህበራዊ ሚዲያ በሚረጩ አፍራሽ ሃይሎች አማካኝነት አለመሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል። እናም አንድን ጉዳይ ከማህበራዊ ድረ ገጾች ተመልክቶ ለተሳትፎ ከመነሳት በፊት የጉዳዩን ትክከለኛነት ጠለቅ አድርጎ መመልከት ይገባል።

ወጣቶች አፍላ ጉልበት ያላቸው ቢሆኑም፣ ነገሮችን በሰከነ መንገድ እንዳይመከለቱ ዕድሚያቸው ይገፋፋቸዋል። እናም ወላጆች ልጆቻቸውን ከጥፋትና ካላስፈላጊ ተግባሮች እንዲታቀቡ ጠንካራ አባታዊና እናታዊ ሚናቸውን መጫወት ይኖርባቸዋል። እንደ ህዝብ ሆነውም የአገራቸው ሰላም በአሉባልታ አራማጅ አፍራሽ ሃይሎች እንዳይደፈርስ የዜግነት ድርሻቸውን ማበርከት አለባቸው።

ህዝብን ከህዝብ ጋር ለማጋጨት የሚሰለፉ ሃይሎችን ተግባር እንደ ዜጋና እንደ ህዝብ መገንዛብ ያስፈልጋል። እርግጥ የእነዚህ ሃይሎች ፍላጎት፤ የሰላም ሳይሆን የብጥብጥና የሁከት፣ የመብት ተጠቃሚነት ሳይሆን የመብት አዋኪነትና የለውጥ ቀልባሽነት ሚናን በመጫወት ለውጡን ለማጨናገፍ መጣር ነው። ከስሮ የወደቀ ፖለቲካቸውን በግለኝነት ስሜት ለማስታመም የሚያደርጉት መፍጨርጨርም ነው።

ስለሆነም በአዲሲቷ ኢትዮጵያ ውስጥ የሰላሙና የለውጡ ባለቤት የሆነው ህዝብ የአፍራሽ ሃይሎችን ሴራ ማክሸፍ ይኖርበታል። እያንዳንዷ ሰከንድ ለሰላም ያላትን ፋይዳ ስለሚገነዘብ ሁሌም ለሰላሙ ይተጋል። የዚህ ህዝብ አካል የሆኑት ወላጆች አሁንም ወጣቶች ወደ ተሳሳተ አቅጣጫ እንዳያመሩ መምከርና መገሰፅ ይጠበቅባቸዋል። እንዲያውም ከልጆቻቸው ጋር እየተመካከሩ የለውጡን ለመቀልበስ የሚሞክሩ አካላትን ማጋለጥ አለበት።

ህዝቡ ከግጭትና ከጥፋት ምንም እንደማይገኝ ጠንቅቆ ያውቃል። ብሔር ከብሔር ጋር እንዲጋጭ የሚሰሩ አሉባልታ አራጋቢዎችም ከእርሱ የተሰወሩ አይደሉም። እነዚህን የለውጥ አፍራሽ ሃይሎችን ከምንም በላይ አምርሮ ሊታገላቸው ይገባል። የለውጡን ሂደን ለማጨናገፍ የሚሹት እነዚህ አካላት እየመጡ ያሉት በህዝቡ የመለወጥ ፍላጎት ላይ በመሆኑ በጽነ ያውግዛቸው፣ ‘ይኸው የአፍራሾቹ ሚና…’ እያለ ማንነታቸውን በማጥራት ከለውጡ ሃዲድ ላይ ሊያንጠባጥባቸው የግድ ነው።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy