Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ጥቁሩ ገበያ…

0 676

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ጥቁሩ ገበያ…

                          ስሜነህ

 

ኢትዮጵያን ከኬንያ በሚያገናኘው የሞያሌ መንገድ ላይ 24 ሰዓት የኮንትሮባንድ ዕቃዎች በሞተር ብስክሌቶች እንደሚተላለፉ የአካባቢው ነዋሪዎች መናገራቸውን የተለያዩ ዘገባዎች እያመላከቱ ነው፡፡ ሞተረኞች  ከዋናው መንገድ ወጣ ብሎ የሚገኘው “መጋራ” የሚባለው አካባቢ የሚገኘውን ጫካ አሳብረው የአቦስቶን ኬላ ካለፉ በኋላ፣ ወደ ዋናው መንገድ በመግባት የጫኑትን ለጥቅም ተጋሪዎቻቸው ያስተላልፋሉ፡፡ ይኼንን ድርጊት የሚፈጽሙት አንድ ሞተረኛ አስቀድመው በመላክ አካባቢው ከሥጋት ነፃ መሆኑን ካረጋገጡ በኋላ ነው፡፡ ልባሽ ጨርቆች፣ የኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎች፣ የቤት ቁሳቁሶችና የተለያዩ ሲጋራዎች በብዛት ሞተረኞቹ በሕገ ወጥ መንገድ የሚያስገቧቸው ዕቃዎች ናቸው፡፡

 

በዋናነት የኮንትሮባንዲስቶችን ሰንሰለት በመበጠስ የኢትዮጵያ የዶላር ክምችት እየጨመረ በመጣበት በዚህ ወቅት፤ አገራችን በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ ከሦስት ቢሊዮን በላይ የዶላር ክምችት ተቀማጭ ማድረግ በቻለችበት በዚህ ጊዜ ሂደቱን የሚቀለብሱ ፍንጮች አሁንም እየተስተዋለ መሆኑ ያሳስባል። ኮንትሮባንድን በመቆጣጠር ረገድ የተጀመረው ጥረትም እየተፋዘዘ ለመሆኑ ከላይ የተመለከተው ዘገባ ሁነኛ ማሳያ ነው። ስለዚህ ጥንቃቄ።  

 

በአገራችን ዘላቂ ሠላምን፣ የልማት ተጠቃሚነትንና የሕዝቦች አንድነትን በማረጋገጥ ወደ ቀጣይ የልማትና የዕድገት ጉዞ ለመዝመት ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ የሪፎርም ሥራዎች እየተከናወኑ ነው፡፡ በአገር ውስጥ የሕዝብን አንድነት  በማስጠበቅ ከጎረቤት አገሮች ጋር ሰላም በመፍጠር ቀጣይነት ያለው የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ መንግሥት እያካሄደ ያለው አገራዊ ለውጥና ንቅናቄ በተለይም ለንግዱ ዘርፍ የላቀ ትርጉም አለው፡፡

 

ንግድ ለአገራችን ኢኮኖሚ መጎልበት ከግብርናው ያልተናነሰ ሚና አለው፡፡ የኢኮኖሚያችን ማርሽ በሆነው የንግዱ ዘርፍ የሚፈለገውን ለውጥና ዕድገት ማምጣት የሚቻለው በሁላችንም ተሳትፎ ዘላቂ ሠላም ሲረጋገጥ ብቻ ነው፡፡ ከአገር ውስጥና ከጎረቤት አገሮች ጋር የተረጋጋና ቀጣይነት ያለው ዘላቂ ሰላም ሲረጋገጥ ጤናማ የንግድ እንቅስቃሴ ይኖራል፡፡ ከክልል ክልልና ከአካባቢ አካባቢ ጤናማ የሆነ የንግድ ዕቃዎችና አገልግሎቶች የሚንቀሳቀሱትና የተረጋጋ ገበያ የሚኖረው በሠላም የበላይ ጠባቂነት ብቻ ነው፡፡  

 

የወጪ ንግድ የአገራችን ኢኮኖሚ ዕድገት መሰላል እንደመሆኑ መጠን ምርቶቻችንን ወደ ውጭ በመላክ የውጭ ምንዛሪ ግኝታችንን ለማሳደግ አሁን የተጀመረው አገራዊ ንቅናቄ፣ አንድነትና ሰላም ለአገር ውስጥም ሆነ ለወጪ ንግዳችን ውጤታማ አፈጻጸም በጣም ወሳኝ ነው፡፡  ሮይተርስ እንደዘገበው የሃገራችን የአንድ ቦንድ ዋጋ በ0.583 ሳንቲም ዶላር ጭማሪ በማሳየት በ100.25 ዶላሮች ለመሸጥ በቅቷል፡፡ የአገሪቱ ቦንድ ካለፈው ሳምንት ረቡዕ ወዲህ ብቻ የሦስት ዶላር ጭማሪ ዋጋ አስመዝግቧል ተብሏል፡፡

 

በናይሮቢ ስታንቢክ ባንክ የምሥራቅ አፍሪካ ኢኮኖሚስት ጂብራን ቁሬይሺ ሲናገሩ በአገሪቱ እየታየ ባለው ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ለውጦች የተነሳ ዓለም አቀፍ ኢንቨስተሮች የኢትዮጵያን ቦንድ ለመጫረት ከፍተኛ ፍላጎት እያሳዩ ይገኛል ብለዋል፡፡ የሮይተርሱ ዘገባ  የኢትዮጵያ ቦንድ በአሥር ሳምንታት ውስጥ ከፍተኛ ጭማሪ አስመዝግቧል ይላል፡፡

 

ዶክተር ዓብይ አህመድ  አገራቸውን ብቻ ሳይሆን ምሥራቅ አፍሪካን ጭምር እለውጣለሁ ብለው መነሳታቸውን የጠቀሰው ሮይተርስ የወሰዱት የኢኮኖሚና የፖለቲካ ለውጥ ደግሞ ከወዲሁ በዓለም የቦንድ ገበያ ላይ የአገሪቱን ተፈላጊነት ከፍ በማድረግ ውጤት እያመጣላቸው ነው፤ ሲል አስቀምጧል፡፡

 

በኢትዮጵያ መደበኛ ባልሆነው የውጭ ምንዛሪ ገበያ (ጥቁር ገበያ) አንድ የአሜሪካን ዶላር 40 የኢትዮጵያ ብር ገብቶ የነበረው ባለፉት ጥቂት ቀናት ውስጥ ብቻ በፍጥነት ወርዶ ከነበረው የመደበኛ ገበያ ምንዛሪ ጋር እኩል መሆኑ የሪፎርሙን ውጤት የሚያጠይቅ ነው፡፡ ከወትሮው ባልተመለደ ሁኔታ ብዛት ያለው የውጭ ገንዘብ ይዘው የሚቀርቡ ደንበኞች የተበራከቱባቸው ባንኮች፣ ለዚሁ አገልግሎት በቅርንጫፎቻቸው ውስጥ ራሱን የቻለ የውጭ ገንዘቦች ማስተናገጃ መስኮት ከፍተው ማስተናገድ ጀምረዋል፡፡ ከዚህ ቀደም የውጭ ምንዛሪ አገልግሎት ሰጥተው የማያውቁ የባንክ ቅርንጫፎች ሳይቀሩ የውጭ ገንዘቦችን የመመንዘር ዕድል እንዳገኙ ታይቷል፡፡

 

ከአንዳንዶቹ ቅርንጫፎች እንደሚነገረው፣ ለመንፈቅ ዓመት ያህል የውጭ ገንዘብ ይመንዘርልን ጥያቄ የሚያቀርብላቸው ደንበኛ አያገኙም ነበር፡፡ አንዳንዶቹ የመንዝሩልኝ ጥያቄ እንደማያስተናግዱም ሲገለጽ ይመደጣል፡፡ በተለይም የገንዘቡ መጠን አነሰ፣ ከ100 ዶላር በታች አንቀበልም የሚሉ፣ ለመመንዘር የሚመጣውን ሰው ወዝፈው የሚያውሉ፣  የመታወቂያና የሌሎች ሰነዶችን የኮፒ ጋጋታና መሰል ጣጣ የሚያበዙት ባንኮችና በዚህ የተመረሩት ተገልጋዮች፣ ወደ ባንክ መሄድ ከማይፈልጉባቸው ምክንያቶች ውስጥ እንዲህ ያሉትን የተንዛዙ ቢሮክራሲዎች ለመሸሽ እንደሆነ ሲጠቅሱ ይደመጣሉ፡፡ ዋናውና መሠረታዊው ወደ ባንኮች ለምንዛሪ የማይሄዱበት ምክንያት ግን በባንክና በጥቁር ገበያው መካከል የነበረው የምንዛሪ ዋጋ ልዩነት ነው፡፡

 

በአሁኑ ወቅት በባንኮቹና በጥቁር ገበያ ዘርዛሪዎች መካከል ያለው የዋጋ ልዩነት በመጥበቡ፣ በርካቶች ወደ ባንኮች በማቅናት ሲዘረዝሩ ታይተዋል፡፡ በቀን የሚመነዘረው የውጭ ገንዘብ ብዛት አስገራሚ ሆኗል፡፡ ባለፉት 15 ቀናት ውስጥ ወደ ባንኮች  የሄደውና የውጭ ገንዘብ የዘረዘረው ተገልጋይ ቁጥር ከዚህ ቀደም ቀርቦ የማያውቅ መሆኑን የተለያዩ ባንኮች ለመገናኛ ብዙሃን ከሚሰጧቸው መግለጫዎች መታዘብ ተችሏል፡፡   

 

በሁለት ሳምንታት ውስጥ ከሌሎች ባንኮች ይልቅ ከፍተኛ መጠን ያለው የውጭ ገንዘቦች ቁጥር ስለመመንዘሩ ለነዚሁ መገናኛ ብዙሃኖች የሚጠቅሰው ንግድ ባንክ፣ በየዕለቱ በአማካይ ከሦስት ሚሊዮን ዶላር በላይ እየመነዘረ ስለመሆኑ አስታውቋል፡፡ እስከ ሐምሌ 30 ቀን 2010 ዓ.ም. ድረስ በነበረው መረጃ መሠረት፣ ንግድ ባንክ ብቻውን ወደ 50 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ መመንዘሩን ለመረዳት ተችሏል፡፡

 

የግል ባንኮችም የውጭ ገንዘቦችን ለመመንዘር የሚመጡ ደንበኞች ቁጥር ከዚህ ከቀደም ባልታየ መጠን ማስተናገዳቸውን እየገለጹ ነው፡፡ በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ ንግድ ባንክና 16ቱ የግል ባንኮች በጥቅሉ ወደ 100 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ የውጭ ገንዘብ እንደመነዘሩ ተገምቷል፡፡በውጭ ምንዛሬ ረገድ  ከወደ እንግሊዝም ተስፋ ሰጪ ነገር ሰሞኑን ተደምጧል።

 

የእንግሊዝ መንግሥት በኢትዮጵያ ለሚካሄዱ የሥራ ዕድል ፈጠራ ዘርፎች ብሎም ለታክስ ሥርዓቱ ማሻሻያ ፕሮግራም ድጋፍ የሚውል የ115 ሚሊዮን ፓውንድ ወይም የ4.025 ቢሊዮን ብር ዕርዳታ ሰጥቷል፡፡ በእንግሊዙ ዓለም አቀፍ የልማት ተቋም (ድፊድ) እና በገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር መካከል በተፈረመው ስምምነት መሠረት፣ የ80 ሚሊዮን ፓውንድ ዕርዳታው ኢትዮጵያ ለምታከናውናቸው የሥራ ዕድል ፈጠራ መስኮች የሚውል ነው፡፡ ቀሪው 35 ሚሊዮን ፓውንድ ደግሞ በአብዛኛው በእንግሊዝ መንግሥት ተቋማት ድጋፍ እየተደረገለት ለሚገኘው የታክስ ሥርዓት ማሻሻያ ፕሮግራም ትግበራ የሚውል ነው፡፡

 

የሥራ ዕድል ፈጠራ ፕሮግራሙ መንግሥት እያስፋፋቸው በሚገኙት የኢንዱስትሪ ፓርኮችና በሌሎችም መስኮች ከሚያስፈልገው የሰው ኃይል ውስጥ ለ100 ሺሕ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር የሚችልበትን ዕገዛ ለማድረግ የሚውል የሚውል መሆኑም ተመልክቷል።መንግሥት ከሁለት ዓመታት በፊት በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጉባዔ ወቅት ይፋ ባደረገው መሠረት፣ ኢትዮጵያ በምታካሂደው የኢንዱስትሪ ማስፋፊያ ዕቅድ ውስጥ ከሚፈጠሩት የሥራ ዕድሎች ውስጥ በኢትዮጵያ የተጠለሉ ስደተኞችም የዕድሉ ተጠቃሚ ይሆናሉ፡፡ በመሆኑም 30 ሺሕ ስደተኞች በኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥም የሥራ ዕድል እንዲያገኙ ለማድረግ መነሳቱን የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል፡፡

 

ዲፊድ በድረ ገጹ እንዳሰፈረው መረጃ ከሆነ በኢትዮጵያ ከ890 ሺሕ በላይ የደቡብ ሱዳን፣ የሶማሊያ፣ የሱዳንና የኤርትራ ስደተኞች በተለያዩ ካምፖች ውስጥ ተጠልለው ይገኛሉ፡፡ ይህ የስደተኞቹ ቁጥር ኢትዮጵያን በአፍሪካ ሁለተኛዋ ከፍተኛ የስደተኞች መጠለያ አገር እንደሚያሰኛት ተቋሙ ይጠቅሳል፡፡

 

በታክስ አሰባሰብና ረገድ ኢትዮጵያ ከሰሃራ በታች ከሚገኙ አገሮች ከኢኮኖሚው አኳያ ያለው ድርሻ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ እስከ 13 በመቶ እንደነበር ሲገለጽ ቆይቷል፡፡ ይሁንና ይኼንን የሚያሻሽል የታክስ ሥርዓት ማሻሻያ ፕሮግራም መተግበር ከጀመረ ሰነባብቷል፡፡ ማሻሻያው የሕግ ማዕቀፎችን ጨምሮ በታክስ ኦዲትና በመሳሰሉት መስኮች ለውጦች ማድረግ መጀመሩም ሲጠቀስ ቆይቷል፡፡በነዚህና መሰል ድጋፍና የፖሊሲ ማሻሻያዎች ጥቁሩን ገበያ መስበር ብቻ ሳይሆን ላይመለስ መቅበር ግን ግድ ይለናል።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy