Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

“በፍቅር እንደመር፤ በይቅርታ እንሻገር”

0 434

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

“በፍቅር እንደመር፤ በይቅርታ እንሻገር”

                                                    እምአዕላፍ ህሩይ

መጪው አዲስ ዓመት “በፍቅር እንደመር፤ በይቅርታ እንሻገር” በሚል መሪ ቃል በደመቀ ሁኔታ ይከበራል። ከመሰንበቻው የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዩች ፅህፈት ቤት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ካሳሁን ጎፌ በሰጡት መግለጫ፤ በዓሉ ከሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች የተወጣጣ ከ25 ሺህ በላይ ህዝብ በሚገኝበት በሚሌኒየም አዳራሽ እንደሚከበር ተናግረዋል። አዲሱን ዓመት ደማቅ ሁኔታ ማክበር ያስፈለገበትን ምክንያትም፤ መንግስት ባለፉት ዓመታት በሀገሪቱ ተስተውሎ የነበረውን ቀውስ በትክክለኛ መንገድ በመፍታት በህብረተሰቡ ሁለንተናዊ ድጋፍና ትብብር የሪፎርም ስራዎችን በመስራት የለውጥ፣ የአንድነትና የይቅርታ ሂደት በመጀመሩ መሆኑን አብራርተዋል።

ከዚህ በተጨማሪ ባለፉት አራት ወራት ውስጥ በውጭ ሀገር ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ጋር የነበረውን ችግር መፍታት መቻሉ፣ የፖለቲካ ምህዳሩን በማስፋት በትጥቅ ትግል ሲንቀሳቀሱ የነበሩ የፖለቲካ ድርጅቶች ወደ ሀገር ቤት ገብተው በሰላማዊ ሁኔታ ለመስራት መወሰናቸው እንዲሁም የሃይማኖት መሪዎች የነበራቸውን ልዩነት ወደ አንድነት የቀየሩበት ይቅርታና አንድነት በተግባር የታየበት ወቅት ስለሆነም አዲሱን ዓመት ድምቀት በተሞላበት ሁኔታ ማክበር አስፈልጓል።

መንግስት ባደረገው ጥረት በጥቂት ውስጥ ብቻ በኢኮኖሚው መስክ የተፈጥሮ ነበረውን የውጭ ምንዛሬ እጥረት መፈታቱ እንዲሁም ኢንቨስትመንትን በመሳብና የዳያስፖራ “ትረስት ፈንድ” በማቋቋም ችግሩን በአፋጣኝ ማስወገድ በዓሉን በድምቀት ለማክበር ምክንያት መሆኑ ተገልጿል።

ምን ይህ ብቻ! በዲፕለማሲው ረገድም ከጎረቤት ሀገራት ጋር በተለይ ከኤርትራ ጋር የነበረውን ሻካራ ግንኙነት በመፍታት ወደ እርቅና ሰላም መምጣት ተችሏል። ለረዥም ዓመታት ታስረው የነበሩ የፖለቲካ እስረኞችን በመፍታት ሀገራዊ መግባባትንም መፍጠር የተቻለበት ጊዜ ነው። እናም እዚህን ተስፋ ሰጪ ሁኔታዎች በአጭር ጊዜ ማሳካት በመቻሉና የመጣውን ለውጥ በመጪው አዲስ ዓመትም ለማስቀጠል የለውጡ ባለቤት የሆነው ህዝብ ቃሉን ዳግም ለማደስ በዓሉ እንዲከበር መደረጉ ተገቢና ትክክል ነው። ታዲያ እዚህ ላይ የበዓሉ መሪ ቃል የሆነውን “በፍቅር እንደመር፤ በይቅርታ እንሻገር” የሚለውን ቃል አፍታትቶ መመልከት አስፈላጊ ነው።

በመሪ ቃሉ ውስጥ “በፍቅር መደመር” እና “በይቅርታ መሻገር” የሚሉ ፅንሰ ሃሳቦችን እናገኛለን። በፍቅር ስንደመር ፍቅር የአሸናፊነት ምስጢር መሆኑን ተገንዝበን ነው። በፍቅር ሁሉንም ማሸነፍ ይቻላል። እገሌን ከእገሌ ሳንል ሁሉንም ዜጋ በፍቅር ስንይዝ እኩይ ምግባር ያለው ቢሆን እንኳን ራሱን እንዲፈትሽ ልናደርገው እንችላለን። በስተመጨረሻም ተደምሮ ከጎናችን ልናሰልፈው እንችላለን። መውደድንና የራስ መሆንን በማሳየት የትኛውም ወገን “የእኛ” ሊሆን ይችላል።

የሰው ልጅ ህሊና ያለው ፍጡር ነው። ያመዛዝናል። በጭፍን የሚጓዝ ቢሆንም እንኳን የማታ ማታ ወደ ህሊናው መመልከቱ አይቀርም። እናም መደመር ለመዋደድና ለአንድነት እንዲሁም ለሀገራዊ አንድነት የሚጠቅም መሆኑን በፍቅር የምናሳየው ማንኛውም ዜጋ ወደ ቀልቡ ተመልሶ የእኛን ሃሳብ እንዲመረምርና የተነሳንበት ዓላማ ትክክል መሆኑን እንዲገነዘብ ማድረግ ይቻላል።

በመሆኑም መደመራችንን በፍቅር ልናደርገው የግድ ይለናል። ተደምረናል እያልን ለሁም ዜጋ እኩል በሆነ ሁኔታ ፍቅር የማንለግስ ከሆነና በፍረጃ ፖለቲካ የምንንቀሳቀስ ከሆነ የተደማሪውን አድማስ ልናሰፋው የምንችል አይመስለኝም። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ስለ መደመር ሲናገሩ ሊቀነሱ ይገባቸዋል ያሏቸውን ጥላቻ፣ ቂም በቀል፣ አደርባይነት፣ ተንኮልንና ሴራን ሁሌም ልናስታውሳቸው ይገባል። እነዚህ እኩይ ምግባሮች፤ ‘ለውጡ የግል ጥቅሜን ነክቷል’ በሚል ስንኩል እሳቤ ለቀበል የማይሹና የአክሻፊነት ሚናን እየተጫወቱ ያሉ ጥቂት ሃይሎች መገለጫ ቢሆኑም፤ እኛም ራሳችን ምናልባትም እኩይ ምግባሮቹን በውስጣችን ይዘናቸው ከሆነ፤ ልናስወግዳቸውና በፍቅር ልንቀይራቸው ይገባል። በሰላማዊ መንገድ የሚከናወን ማናቸውን ነገር ያለ ፍቅር መከወን ከባድ ይሆናልና።

ስለሆነም በፍቅር ስንደመር ማናቸውንም ከፍቅር ጋር አብረው የማይሄዱ ጉዳዩችን እርግፍ አድርገን መተው አለብን። ጥላቻን፣ ቂም በቀልን፣ እልኸኝነትን፣ ተንኮልንና ሴራን ልንጠየፋቸው ይገባል። ታዲያ የምንጠየፈው የድርጊቱን ፈፃሚዎች ብቻ አይደለም። ስሜቱ በውስጣችን ካለም ያንን ስሜት በፍፁም ፍቅርና መውደድ ልንቀይረው የግድ ይለናል። በፍቅር የምንደመረው ከእኛ ውጭ አስተሳሰብ ያለውን ዜጋን አስተሳሰብና ህገ መንግስታዊ መብቱንም በማክበር ነው።

ታላቁ ፈላስፋ ሶቅራጥስ “በራስህ ላይ እንዲሆን የማትፈልገውን ነገር በሌሎች ላይ አትፈፅም” እንዳለው፤ ያልተደመሩ ጥቂት አካላት አሊያም ቀደም ሲል ወንጀል ሰርተዋል ተብለው የሚጠረጠሩ ወገኖች የእኛን ሃሳብ አክብረው ከቻሉም ተደምረው ለሀገራቸው ትርጉም ያለው ስራ እንዲያከናውኑ የምንፈልገውን ያህል፤ ሃሳባቸው የተሳሳተ መሆኑን እያወቅንም ቢሆንም እንኳን ልናከብረውና በተገቢው መንገድም ምላሽ ልንሰጠው ይገባል። ያኔም በትክክል በፍቅር ተደምረናል ልንል እንችላለን። እናም ከላይ የጠቀስኳቸውን “በፍቅር እንደመር” ፅንሰ ሃሳብ በመያዝና ለተግባራዊነቱ ከምንግዜውም በላይ በመትጋት በአዲሱ ዓመት ቃላችንን ማደስ ይኖርብናል።

የአዲሱ ዓመት መሪ ቃል ሌላኛው ፅንሰ ሃሳብ “በይቅርታ እንሻገር” የሚል ነው። ፅንሰ ሃሳቡ “ይቅርታ” እና “መሻገር” የሚሉ ሁለት ቃላትን የያዘ ነው። ርግጥ በፍቅር መደመርና በይቅርታ መሻገር እንደ ሰንሰለት የተያያዙ ሃሳቦች ናቸው—ፍቅር የተደመረ በይቅርታ ለመሻገር አይከብደውምና።

ታዲያ እዚህ ላይ ‘በይቅርታ የምንሻገረው ምንን ነው?’ የሚል ጥያቄ ማንሳት ይገባል። አዎ! በይቅርታ የምንሻገረው ያለፉትን ችግሮችና ስህተቶች እንዲሁም የተግባሮቹን ፈፃሚዎች ነው። ባለፉት ጊዜያት ከባድ ስህተቶች፣ ኢ-ህገ መንግስታዊ ጭካኔዎችና ደባዎች ተፈፅመው ሊሆን ይችላል።

በትክክል በፍቅር የተደመረ ግለሰብ ጊዜው የይቅርታ መሆኑን የሚገነዘብ ነው። ይቅርታ የዘመናዊነት መገለጫ ነው። እኛ ራሳችን ጥፋት አጥፍተን ሌሎችን ይቅርታ እንደምንጠይቀው ሁሉ፣ ሌሎችም እኛን ይቅርታ ቢጠይቁንም ይሁን ባይጠይቁን ራሳችን ይቅርታ ማድረግ ይኖርብናል። በዚህም ይቅርታ ሊጠይቅ የሚገባውን ሰው በፍቅር ልንማርከው እንችላለን። ለዚያ ግለሰብ ወይም ቡድን ይቅርታ ባለማድረግ ስህተትን በስህተት ማረም አይኖርብንም። ይህን ካደረግን ቀደም ሲል ችግር ከፈጠረው ግለሰብ አሊያም ቡድን የተሻልን ልንሆን አንችልም።

ለሌሎች ፍቅር መስጠትና ይቅርታ ማድረግ ኢትዮጵያዊ ባህልና ጨዋነት ነው። መከባበርና መቻቻልም እንዲሁ። ትላንት ጥፋት አጥፍተዋል የሚባሉ ወገኖችን ባለመፈረጅና የተፈጠሩ ችግሮችን በደቦ ፍትህ ለመስጠት መሞከር ለዘመናት ይዘናቸው ከመጣናቸው ባህሎቻችንና ጨዋነታችን ጋር የሚጋጩ ናቸው።

ኢትዮጵያዊያን የህግ ልዕልናን የሚቀበሉና ማናቸውንም ችግሮች በህግ አግባብ የሚፈቱ ናቸው። ይህን ሲያደርጉም ይቅርታን በውስጣቸው ሰንቀው ነው። ህግን እያከበሩና ችግሮቻቸውንም አየተዳኙ የመጡ ናቸው። በፍረጃና በደቦ ፍርድ አያምኑም። ይቅርታ በሁለት ጫፍ ላይ የሚገኙ አካላትን ቢያንስ ወደ አማካዩ ነጥብ ሊያመጣ የሚችል መሆኑን ስለሚያምኑም ወደ አዲሱ ዓመት በይቅርታ ለመሻገር ቃላቸውን ያድሳሉ። ይህን ማድረግም በህዝቦች ትግል የተገኘውን የለውጥ ሂደት መደገፍ መሆኑንም ያምናሉ። እናም አዲሱን ዓመት በፍቅር ተደምረው በይቅርታ ሊሻገሩት ዝግጁዎች ናቸው።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy