CURRENT

“ባልናገር ወዮልኝ! ብናገርም ወዮልኝ!”

By Admin

August 07, 2018

“ባልናገር ወዮልኝ! ብናገርም ወዮልኝ!”

                                                     ዕዝራ ኃይለ ማርያም

ኮሎኔል መንግስቱ ኃይለ ማርያም ፊታቸውን ሲታጠቡ አንድ ሰዓት ይጠፋባቸዋል፡፡ ለኮሎኔል ተስፋዬ ወልደ ሥላሴ ስልክ ይደውሉና “ከጓድ ሊዩኔድ ብሬዥኔቭ (በወቅቱ የሶቪየት ኅብረት ፕሬዚዳንት የነበሩት) በስጦታ የተሰጠኝ ሰዓት ከመታጠቢያ ቤት ተሰርቆብኛል፡፡ ሰዓቴ ነገ በእጄ ካልገባ በሌላ ሰው እንደምትቀየር እወቅ” ብለው ያስጠነቅቃሉ፡፡ 

ማምሻውን ሰባ ሰዎች ታስረው አደሩ፡፡ ምርመራው ተካሔደ፡፡ ስድሳ ዘጠኙ ሲመረመሩ “ወስደናል” አሉ፡፡ በነጋታው ኮሎኔል ተስፋዬ ሪፖርታቸውን አዘጋጅተው ሊያቀርቡ ሲሉ ኮሎኔል መንግስቱ “ተስፋዬ፣ የዚያን ሰዓት ጉዳይ ተወው፡፡ መኝታ ቤቴ አገኘሁት” ይላሉ፡፡ ኮሎኔል ተስፋዬም “ተገቢውን ምርመራ አካሂደን 69 ሰዎች’ኮ አምነዋል” አሉ፡፡ ተብሎ ሲወራ ነበር፡፡ ይህ የፖለቲካ ፌዝ የደርግን አምባገናነዊነት አመልካች ነበር፡፡ 

ደርግን ሰው በላና ጭራቅ በማድረግ ነፍጥ አንስተው ጫካ የገቡት “ታጋይ” ነን ባዮች፣ ዶክተር መራራ ጉዲና እንዳሉት “ጫካው ከእነሱ ወጣ እንጂ እነሱ ከጫካው አልወጡም”፡፡ ከደርግ የባሱ ገራፊና አስገራፊ ሆኑ፡፡ በእጃቸው የወደቀ ሰውን በሰይጣናዊ ጭካኔና ግፍ ማሰቃየትን ሥራቸው አደረጉ፡፡ 

ግርፊያ (ቶርች) በጣም ቀላሉ ነው፡፡ የእግርና የእጅ ጣቶች በፒንሳ መንቀል፣ በምርመራ ወቅት እግርን በጥይት መምታት፣ ብልት ላይ ሁለት ሊትር የታሸገ ውሃ ማንጠለጥልና አባለዘር ማኮላሸት፣ ለረጅም ሰዓታት እስረኛን ገልብጦ መስቀልና ውስጥ እግርን መግረፍ፣ ጺም መንጨት፣ በግራና በቀኝ ባልተቋረጠ ጥፊ መምታት፣ እርቃንን ብርድ ላይ ማስቆም፣ በኤሌክትሪክ ገመድ መግረፍ፣በጣም በሚቀዘቅዝ “ሳይቤሪያ” የሚል መጠሪያ ባለው የማዕከላዊ መሬት ስር ባለው ክፍል ውስጥ ማጎር ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ 

ለወራት እጆችን በካቴና እግሮችን ደግሞ በእግር ብረት በማሰር እስረኞች ለምግብና ለመጸዳዳት በሌሎች እስረኞች እርዳታ እንዲቆዩ ማድረግ፣ በውሃ ዉስጥ መድፈቅና ሌሎች ህያዋን በሙታን የሚቀኑበትን

ሰቆቃ መፈፀም ገራፊዎቹና አስገራፊዎቹ ለጌታቸው ዲያብሎስ የሚያስገቡት ግብር ነበር፡፡ ሀብታሙ አያሌው “ከሕወአት ሰማይ ስር” በሚለው መጽሐፉ በእስር ቤት የደረሰበትን አካላዊና አእምሮኣዊ ሰቆቃ ገልጿል፡፡ እንደ ሀብታሙ ገለጻ የእስር ቤቱ ቆይታ ሞትን እንደ እድል ያስቆጥራል፡፡ ገራፊዎቹ ከሚያደርሱት ሰቆቃና በደል በላይ ብሔረሰብን መሰረት ያደረገ ከመርግ የከበደ የገራፊዎቹ ስድብ አእምሮን የሚፈታተን “ጋር” (ድካም፣ ጭንቅና ጣር) ነው፡፡ 

“ምላስ አጥንት ባይኖረውም አጥንት ይሰብራል” እንዲሉ በእጃቸው ላይ የወደቁ እስረኞችን መስደብና ማዋረድ ኅሊናን ማቁሰያ ፍላጻ ነበር፡፡ “ከፈለጋችሁ እንደኛ ከደደቢት ጀምሩ፣ ሰባት መቶ ዓመታት ገዝታችሁ ገና አርባ ሳይሞላን ጉሮሯችን ላይ ቆማችሁ ምን አድርጉ ነው የምትሉን? እቺን ሀገር ዳግመኛ እናንተ ከምትመሯት ብትንትኗን እናወጣታለን፡፡” በማለት ይፎክራሉ፡፡ በሰላም የሚገዛለትን ሕዝብ “አፈርሳለሁ” ብሎ የሚፎክር የፖለቲካ ኃይል በዓለም ላይ ከእነሱ ውጭ ይኖር ይሆን? 

ያለምንም ሃፍረት የቤቱን ግድግዳ እንድንገፋ እያዘዙ “እኛ ትግሬዎች እንዲህ ነን፡፡ የማይሞከር አትሞክሩ፣ አማራን እንኳን ቀበቶውን ሱሪውን ካስወለቅነው ቆይተናል” እያሉ ተዘባብተውበታል፡፡ በስዬ አብርሃ እንደተገለጸው የእስር ቤቱ ቋንቋ ኦሮምኛ እስኪመስል ድረስ የኦሮሞ ተወላጆችም ብዙ ፍዳና ስቃይ አይተዋል፡፡ ጉራጌን ደግሞ “ማን ፖለቲከኛ አደረገው! መርካቶ ቸርችረህ አትበላም” እያሉ መግረፍና ማሰቃየት የተለመደ ነበር፡፡ የሰማንያ ዓመት አዛውንትና ባልቴትን በአሸባሪነት አስሮ የሚያሰቃይ ቡድን ጤነኛነትም ያጠራጥራል፡፡ 

በሀብታሙ መጽሐፍ ላይ እንደተገለጸው “ብልት በሲባጎ ታስሮ እየተጎተተ በተመረመረው አስፋው ልሳና እና ለረጅም ሰዓታት ተዘቅዝቆ በመታሰሩ ፊቱ የተጣመመው በአምቦው ኒሞና ጫሊቲ ላይ የተፈጸመው ግፍ ዘግናኝ ነው፡፡ ያልተጠቀሱ ለማመን የሚያስቸግሩ ዘግናኝ ምርመራዎች ተፈጽመዋል፡፡ የጭካኔ ሰለባ ዜጎችን ቤት ይቁጠረው ማለት ይቀላል፡፡ 

የሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ የሦስተኛ ዓመት ተማሪ የነበረው ከፍያለው ተፈራ አንድ እግሩን በጥይት ከመቱት በኋላ እስር ቤት ተጣለ፡፡ በሕክምና ስህተት በተሰጠ ምክንያት ጤነኛ እግሩ ተቆረጠ፡፡ ዶክተር ዐብይ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ ከአስር ቤት ተለቋል፡፡ ይህ ኅሊናን የሚረብሽ አካላዊና አእምሮኣዊ ወራዳና ኢ-ሰብአዊ ድርጊት ሀገርና ኢትዮጵያዊነትን አንገት የሚያስደፋ ነው፡፡ በኢትዮጵያ እስር ቤቶች ያልተፈፀመ የሞትና የስቃይ ተጋብኦት የለም። ከኢትዮጵያዊ የሞራል እሴቶች አንጻር ያልገልጽኳቸው “ጋር”ና ጉዶች አሉ፡፡ 

ሰኔ 22 ቀን 2010 ዓ.ም በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ቀርበው በድብደባ የተጎዳውን አካላቸውን ለፍርድ ቤቱ አሳይተዋል፡፡ በጋዜጠኛ ጌታቸው ሺፈራው ፌስ ቡክ ገጽ ከቂሊንጦ እስር ቤት ቃጠሎ ጋር በተያያዘ የተከሰሱት አርጋው ሞገስ ግራ እጁ በፋሻ ተጠቅልሎ ከአንገቱ ጋር ታስሮ ፍርድ ቤት የቀረበ ሲሆን አራት የእጅ ጣቶቹ መሰበራቸውን ለፍርድ ቤት ተናግሯል። እግሩ ላይ በሚስማር መመታቱን እና አራቱ የእጅ ጣቶቹ መጎዳታቸውም ለችሎቱ አሳይቷል። አቶ ቴዎድሮስ ዳንኤል የቀኝ እጁ በፋሻ እንደታሸገ እስር ቤት ውስጥ ድብደባ እንደተፈፀመበት ገልጿል። ልብሱን አውልቆ በድብደባ የበለዘ ሰውነቱን ለፍርድ ቤቱ አሳይቷል። ፍርድ ቤት ቀርበው እውነታውን በመናገራቸው ብቻ በቂሊንጦ እስር ቤት ከፍተኛ ድብደባ እንደተፈፀመባቸው ለፍርድ ቤቱ ገልጸዋል፡፡ 

ተከሳሾቹ “እስር ቤት የተደራጀ የማፍያ ቡድን እና አይ ኤስ መኖሩን፣ ከቂሊንጦ እስር ቤት አስወጥታችሁ ወደ ሌላ እስር ቤት ካላካችሁን በሚቀጥለው የሚመጣው አስከሬናችን ነው” በማለት ለፍርድ ቤት ተናግረዋል፡፡ ከሦስት ወራት በፊት ተከሻሾች ፍርድ ቤት ቀርበው የደረሰባቸውን ስቃይና ግፍ ሲናገሩ መስማት ዘግናኝ ነበር፡፡ ባለፉት ዓመታት ዋናው ገዥያችን ዲያብሎስ፣ መንግሥታቸው ደግሞ ገሀነመ እሳት ነበሩ፡፡

አፈሩን ገለባ ያድርግለትና ጸጋዬ ገብረ መድኅን አርአያ “ሕልም እውነት …እውነትም ሕልም ሲሆን” በሚል መጣጥፉ ላይ እንዲህ የሚል አንቀጽ አለ፡፡ በአይሁዶች ታልሙድ መጽሀፍ ውስጥ “ባልናገር ወዮልኝ! ብናገርም ወዮልኝ (Woe, if speak, woe if I am silent) የሚል አነጋገር አለ፡፡ ባለመናገር የዝምታ ወንጀል አለ፣ ፍርድ ቤት የሚያስቀርብ እንኳ ባይሆን የኅሊና ችሎት ይኖራል፡፡ በመናገር ከጊዜው ሹማምንት የሚመጣ አደጋ አለ፡፡ ይህም ሙሉ እድሜያችንን የሰቆቃ፣ የጋር እና የአኪላፋ (ሌባ፣ ቀማኛ እና በካይ) ዘመን ውስጥ ላለን እውነት መናገር የሚያመጣውን ጣጣ ጠንቅቀን እናውቃለን፡፡ “ማወቁን እናውቃለን፣ብንናገር እናልቃለን” ነውና ፡፡ 

በኢትዮጵያ መንግስት ማለት በብረት እጅ የሚገዛ፣ የሚያንቀጠቅጥና የሚቀጠቅጥ ሆኖ ቆይቷል፡፡ ደርግ አምባገነን ቢሆንም ግድያና ቶርች የፈፀመው በብሔረሰብ ለይቶ አልነበረም፡፡ ብሔርን ከብሔር የሚያጋጭ መርዝ ቋንቋ አልተጠቀምም፡፡ 

“በትንባሆ የገዙት ጦር ቢወረውሩት ጋያ ይወጋል” እንዲሉ በትግራይ ሕዝብ ስም የሚነግዱ የፖለቲካ ኃይሎች ዛሬም ወደ ጥፋት መንገድ እየነጎዱ ነው፡፡ እግዚአብሔር የሰጣቸውን የሽምግልና ዘመን እንደ ፍንዳታ እየተገበዙ ነው፡፡ ሰውዬው “ውሃ ሲወስደው እኔም ወደ ቆላ እወርዳለሁ ብዬ ነበር” አለ እንደሚባለው፤ የዶክተር ዐብይ “ፍቅር፣ ይቅርታና መደመር” መርሕ ለንስሐ የሚያበቃቸውና ሽምግልናቸውን በመልካም ምክር እንዲያሳልፉ የሚረዳ ነበር፡፡

በሀገራችን የጭካኔና የአረመኔነት ሰለባ የሆኑት ወገኖቻችን የታሰሩበት ክፍል ክርፋት፣ የረጋ ደም ሽታ፣ ሲቃ፣ ኡኡታ፣ ማጓራት፣ እና “ጋር” በአእምሯችን ይቀመጥ ዘንድ ምኞቴ ነው፡፡ ይህም ለበቀል ሳይሆን፣ሁለተኛ እንዳይደገም በፍቅርና ስለፍቅር፤ ለይቅርታና ስለ ይቅርታ ነው፡፡ ለታሪክም ጭምር፡፡ “ትዕቢት ለትዕቢተኞች መቃብር፣ ትኅትና ደግሞ ለትኁቶች ብርሃንና ሕይወት ናት”ና ::

መንግሥትና ሕዝብም የሚከተሉትን ያደርጉ ዘንድ ቅን ሀሳቤን አቀርባለሁ፡፡

1.ገራፊ እና አስገራፊዎች በቁጥጥር ስር ውለው፣ ተጸጽተው ሕዝብን በይፋ ይቅርታ እንዲጠይቁ፣ 

  1. መንግስት ለሟች ቤተሰቦች ካሣ እንዲከፍል፣
  2. በጭካኔ ግርፊያ ሲሰቃዩ ቆይተው ከእስር ለተለቀቁ ወገኞቻችን በመንግሥት የሕክምና   ድርጅቶች ነጻ ሕክምና እና የገንዘብ ካሳ እንዲያገኙ ቢደረግ፣
  3. የሥራ እድል ያላገኙ ወገኖች በብቃታቸው መጠን ቅድሚያ የሥራ እድል እንዲሰጣቸው፣
  4. መንግሥት እስከ ዛሬ የተፈጠረውን ጉዳትና ስቃይ አጥንቶ የሚያቀርብ አንድ ኮሚቴ አቋቁሞ በማጥናት ለሕዝብ ይፋ ቢደረግ ማለፊያ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡

             መድኃኔ ዓለም ኢትዮጵያን ይባርክ !