Artcles

ወንጀለኛ እና አርበኛ ተምታታብን

ወንጀለኛ እና አርበኛ ተምታታብን

By Admin

August 22, 2018

ወንጀለኛ እና አርበኛ ተምታታብን

(ክፍል አንድ)

ሰዒድ ከሊፋ

የሰው ችሎታ ሦስት ነው፡፡ አንደኛው፤ ማሰብን ማወቅ ነው፡፡ ሁለተኛው፤ መናገርን ማወቅ ነው፡፡ ሦስተኛው፤ መሥራትን ማወቅ ነው፡፡ አንዳንዶቹ፤ በማሰብ ወይም በማወቅ በርትተው፤ በመስራት ይሰንፋሉ፡፡ ወሬ ብቻ ይሆናሉ፡፡ ማሰብ፣  መናገር እና ሥራ ነፍስ እና ሥጋ ሆነው መገኘት አለባቸው፡፡ ሥራ የሌለው ማሰብ ኤኬራ ነው፡፡ ማሰብ የሌለው ሥራ ሬሳ ነው፡፡ አንዳንዶች በማሰብ በርትተው በሥራ ይሰንፋሉ፡፡ ግብዞች ይሆናሉ፡፡ በተቃራኒው በሥራ በርትተው በማሰብ ሲሰንፉ፤ በትክክል ያለማሰብ ከሚያመጣው ችግር ውስጥ ይዘፈቃል፡፡ ብዙ ደክመው የሰሩት ሥራ ታጥቦ ጭቃ ይሆናል፡፡ ሥራቸውም ብላሽ ይሆናል፡፡ የተሰራው ሁሉ ይፈርሳል፡፡ እንዲሁም ሥራ የሌለው ማሰብ ንግግር አሳማሪ ብቻ ያደርገናል፡፡ በትክክል አስቦ፣ በትክክል ያሰበውን ለህዝብ አሳውቆ ወይም ተናግሮ፤  እንደገናም ያደረገውን በቃል እና በፅሁፍ በትክክል አስረድቶ፤ እንዳሰበውና እንደተናገረው የሚሰራ ሰው (ድርጅት) መሆን ያስፈልጋል፡፡

አንዳንዶች በትክክል የማሰብ (የማወቅ) ችግር ይኖርባቸዋል፡፡ በትክክል ማሰብ ባለመቻላቸው ወንጀልን እንደ አርበኝነት ያዩታል፡፡ ‹‹ወንጀልን እንደ አርበኝነት›› የሚያይ አስተሳሰብ ሲፈጠር፤ በዚህ ረገድ ግራ የመጋባት ስሜት ሲኖር፤ ችግሩ ከባድ ይሆናል፡፡ ብዙዎችን የሚያስት፤ ሐገርን እና ህዝብን የሚጎዱ ሥራዎችን እየሰራ ሊኮራ ይችላል፡፡

ሰው መግደል ወንጀል ነው፡፡ ነገር ግን በትክክል ማሰብ በማይችሉ ሰዎች ዘንድ ይህ ወንጀል እንደ ከአርበኝነት ሊቆጠር ይችላል፡፡ አንድን ሰው መግደል Humanityን (የሰውን ዘር) እንደ መግደል ወንጀል ነው፡፡ ሰውን መግደልን ተገቢ የሚያደርግ አስተሳሰብ እንደ ዘር ማጥፋት ሊቆጠር የሚገባው ነው፡፡ በዚህ መጠን ነውረኛ ድርጊት ነው፡፡

ነጻነት በተሳሳተ መንገድ ግንዛቤ ሲያገኝ ያሳስታል፡፡ ለሌሎች ሳትሰጥ አንተ ብቻህን ልታገኘው የማትችለው ነገር ነጻነት ለሌሎች ነው፡፡ ነጻነትህን የምታበዛው እና የምታሰፋው የሌሎችን ነጻነት በማክበር ብቻ ነው፡፡ የሌሎችን ነጻነት አለማክበር፤ የአንተን ነጻነት ዋስትና ያሳጣዋል፡፡

ስለዚህ ትክክለኛ ነገር ለመናገር ወይም ሐሳብን በነጻነት ለመግለፅ የተደነገገውን መብት ተጠቅሞ፤ መጥፎ ሐሳብ በመናገር በሰው ዘር ላይ የሚፈፀም ወንጀልን ለመስራት መንገድ ያመቻቻል፡፡ የዚህ ችግር መነሻው በትክክል የማሰብ ችግር ነው፡፡ በትክክል ባለማሰብ፣ በትክክል አለመናገርና በትክክል አለመስራትን ይመጣል፡፡ እነዚህ ችግሮች አንዱ በአንዱ ላይ ሲደመሩ የሚፈጠረው አደጋ ነው አሁን ያየነው፡፡

ቋንቋ የሐሳብ መግለጫ ነው፡፡ ነገር ግን ቋንቋ የሐሳብ መደበቂያ ሲሆንም እናያለን፡፡ ሐሳብ ትክክለኛ የተግባር መግለጫ መሆኑ ቀርቶ የክፉ ተግባር መሸፈኛ ሲሆን እንመለከታለን፡፡ ነጻነትን ህግ አለማክበር እና ስርዐት አልበኝነት ተደርጎ እየተወሰደ ነው፡፡ ‹‹ወንጀለኛን እና አርበኛን›› መለየት ቸግሮናል፡፡ ትክክለኛ ሐሳብ እና ተግባር የሚመነጨው በትክክል ከማሰብ ነው፡፡ ትክክለኛ ሐሳብም የሚገለጸው በቃል እና በፅሁፍ ነው፡፡ ወንጀል እና አመፃን በቃል የመደገፍ እኩይ ተግባር ሲታይ ቋንቋ የመጥፎ ድርጊት መሸፈኛ ይሆናል፡፡ ‹‹መልከ ጥፉን በስም ይደግፉ›› እንዲሉ፤ መጥፎ ድርጊትን በነጻነት ስም መሸፈን አይገባም፡፡ አንዳንድ ሐሳቦች፤ ከንግግር አጥር የማይወጡ እና ንግግር ብቻ ተብለው የሚታለፉ ይሆናሉ፡፡ ሆኖም አንዳንድ ሐሳቦች ከሚያመጡት አደጋ የተነሳ፤ በቃላት በንግግር ሚዛን የሚታዩ ሳይሆን እንደ conduct ይታያሉ፡፡ እንዲህ ዓይነት መጥፎ ሐሳቦችን የተናገረ ሰው፤ መጥፎ ድርጊትን ከአደረገው ሰው እኩል የሚታይ ነው፡፡ ህዝብን ከህዝብ የሚያጋጩ፤ ህዝብን በህዝብ ላይ የሚያነሳሱ ንግግሮች ከዚህ የሚመደቡ ናቸው፡፡ ይህን በመረዳት ነው፤ የኢትዮጵያ ህገ መንግስት፤ ህዝብን ከህዝብ የሚያጋጩ የጦርነት ቅስቀሳዎችን እና ህዝብን በህዝብ ላይ የሚያነሳሱ የጥላቻ ንግግሮችን ይከለክላል፡፡ ፍትህን እየጠየቁ፤ ፍትህን የሚያጠፉ፤ ነጻነት እና መብትን እየጠየቁ፤ የሰውን ነጻነት እና መብት ማፈን የዴሞክራሲ ትግል ማካሄድ አይቻልም፡፡ የሚሻሻሉ ነገሮች ቢኖሩት እንኳን፤ አሁን ያለውን ህገ መንግስት በማክበር መንቀሳቀስ ይኖርብናል፡፡  

የኢትዮጵያ የህግ ስርዓት፤ የህዝብ ሉዓላዊነትን፣ የህገ መንግስት የበላይነትን፣ የመንግስት እና የሐይማኖት መለያየትን፣ የሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች መከበርን እንዲሁም የመንግስት አሰራርን ግልፅ የማድረግ እና ተጠያቂነትን የማረጋገጥ ጉዳዮችን እንደ መሠረታዊ መርሆዎች በተቀበለ ህገ መንግስት ላይ የተገነባ ስርዓት ነው፡፡

ኢትዮጵያ የህግ ስርዓት በህገ መንግስቱ፣ ሐገሪቱ ፈርማ ባፀደቀቻቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶች እንዲሁም ህገ መንግስቱን መሠረት በማድረግ ተሻሽለው በወጡ የወንጀል፣ የፍትሐ ብሔር እና የሥነ ስርዓት ህጎች ወዘተ ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ ይህ የህግ ሥርዓት በፍርድ ቤት ውሳኔ ያገኙ ጉዳዮች፤ መሠረታዊ የህገ መንግስት ግጭት የሚታይባቸው ሆኖ ሲገኝ፤ የፍርድ ቤቶቹ ውሳኔ በፌደሬሽን ምክር ቤት ሥር ባለ የህገ መንግስት ጉዳዮች አጣሪ ኮሚቴ ጉዳዩ ተመርምሮ ውሳኔ የሚያገኝበት የህግ ስርዓት ነው፡፡

በ1987 ዓ.ም የፀደቀው ህገ-መንግስታችን፤ የኢትዮጵያን የፖለቲካ እና የህግ ስርዓትን በመሠረታዊ መልኩ የቀየረ ህገ መንግስት  ነው፡፡ ህገ መንግስታዊ ማዕረግ የያዙ፤ የሰብዓዊ መብት ድንጋጌዎችን ማፅናት ብቻ ሣይሆን፤ የእነዚህን መብቶች አከባበር የሚከታተሉ ተቋማትም እንዲመሠረቱ በማድረግ የተጠናከረ የፖለቲካ እና የህግ ስርዓትን ለመፍጠር ያለመ ህገ መንግስት  ነው፡፡ ህገ መንግስቱ ሰብዓዊ መብቶች እንዲከበሩ የሚደነግግ በመሆኑ፤ ‹‹ማንኛውም ሰው ሰብዓዊ በመሆኑ የማይደፍር እና የማይገሰስ በህይወት የመኖር፣ የአካል ደህንነትና የነፃነት መብት አለው›› ሲል ይደነግጋል፡፡

ታዲያ ምን ቢደረግ ችግሮች መፈጠራቸው የማይቀር በመሆኑ፤ አርኪ ሥራዎችን መስራት የሚችሉበት ቁመና ባይኖራቸውም፤ የመብቶችን አከባበር እና አተገባበር የሚከታተሉ እና የመንግስት አሰራርን ተጠያቂነት የሰፈነበት እንዲሆን ለማድረግ የሚችሉ፤ ነፃ እና ገለልተኛ በመሆን ትልቅ አስተዋጽዖ ለማድረግ የሚችሉ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን እና የእንባ ጠባቂ ተቋም የሚደገፍ ስርዓት ነው፡፡  እነዚህ ተቋማት የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን እና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለማረም እና ለማስተካከል እንዲሰሩ ማድረግ የሚችሉ ተቋማት ሆነው እንዲወጡ መስራት ያስፈልጋል፡፡ ስለዚህ የሐገራችን የፖለቲካ ስርዓት መሠረት፤ የህጎች ሁሉ የበላይ የሆነው የኢፌዴሪ ህገ መንግስት መሆን ይገባዋል፡፡

ስለሆነም፤ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በህግ በተደነገገው ከባድ ወንጀል ቅጣት ካልሆነ በስተቀር ህይወቱን አያጣም፡፡ በአካሉ ላይ ጉዳት እንዳይደርስበት የመጠበቅ መብትም አለው፡፡ ነፃነቱ የተከበረለት በመሆኑም በህግ ከተደነገገው ውጭ ነፃነቱን አያጣም ወይም ዝም ብሎ ሊያዝ እና ክስ ሊቀርብበት አይችልም፡፡ ጭካኔ የተሞላበት፣ ኢሰብዓዊ የሆነ ወይም ጭካኔ የተሞላበት ወይም ክብሩን የሚያዋርድ አያያዝ እና ቅጣት እንዳይደርስበት ህገ መንግስቱ ጥበቃ ያደርግለታል፡፡

በህገ መንግስቱ፤ በወንጀል ተጠርጥረው የተያዙ፣ የተከሰሱ ወይም በጥበቃ ስር ያሉ እና በፍርድ የታሰሩ ሰዎችን መብቶችን በመዘርዘር ጥበቃ ያደርጋል፡፡ ከፍሲል የተጠቀሱት ተቋማትም የእነዚህን መብቶች አፈፃፀምን ለመከታተል የሚያግዙ ተቋማት ናቸው፡፡ የጎዳና ላይ ፍርድ ይህን ህገ መንግስታዊ መብት የሚጥስ ድርጊት ነው፡፡

ኢህአዴግ የሚመራው መንግስት በእስረኞች አያያዝ በኩል የነበረውን ችግር በቅርቡ ለህዝብ ይፋ የሆኑት መረጃዎች በግልጽ አሳይተውናል፡፡ የነበሩትን መልካም ነገሮች በማሻሻል ለተጨማሪ ድል መስራት እንጂ ወደ ኋላ የሚመልስ እና ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ፤ ጥፋታቸው በህግ አካላት ሳይጋገጥ፤ በጎዳና ላይ ፍርድ እርምጃ መውሰድ የመብት፣ የእኩልነት እና የነጻነት ጥያቄ የሚያነሳ ዜጋን ዓላማ የሚያራክስ ተግባር ነው፡፡

‹‹በእስረኞች አያያዝ በኩል የነበሩትን መልካም ነገሮች›› ያልኩት ዝም ብዬ አይደለም፡፡ ፕሮፌሰር መስፍን ወ/ማርያም ‹‹አገቱኒ›› በሚለው መፅሐፋቸው የሚጠቅሱት ነገር አለ፡፡ እርግጥ ፕሮፌሰር መስፍን ‹‹90 ሰዎች ከመቶ ካሬ ባነሰ ግቢ ውስጥ እንዲናፈሱ›› መደረጉን የሚያማርሩ ቢሆንም፤ የእስር ቤት አያያዝን ሲገልፁ የሚጠቅሷቸው አንዳንድ መልካም አስተያየት አላቸው፡፡ ‹‹…ለእኔ የተለየ እንክብካቤ ያደርጉልኝ እንደ ነበር ሳልናገር ብቀር እውነቱን መደበቅ ይሆናል›› (አገቱኒ፣ 69) የሚሉት ፕሮፌሰር መስፍን፤ ‹‹ጠባቂዎቻችን ከላይ እስከ ታች አብዛኛዎቹ ተጋዳላይ የነበሩ ወያኔዎች ናቸው፡፡ … አብዛኛዎቹ ጠባቂዎች በበኩሌ ክፉ የምላቸው አልነበሩም›› (አገቱኒ፣70) ይላሉ፡፡

ለታራሚዎች የሚቀርበውን ምግብ በተመለከተም፤ ፕሮፌሰር መስፍን አንድ ቅር ያላቸው ነገር መኖሩን ሲገልፁ፤ ‹‹አትክልት የሚባል ነገር በምግብ ውስጥ አልነበረም፡፡ በኋላ ..…አትክልት የሚባል ነገር በምግብ ውስጥ አለመኖሩ አስገርሞኝ ለማጣራት ብሞክር፤ እስረኞቹ ራሳቸው የወሰኑት መሆኑን ተረዳሁ፡፡ ዴሞክራሲ መሆኑ ነው›. ይላሉ፡፡ በማያያዝም፤ ‹‹አይነቱ ከሚፈለገው በታች ቢሆንም፤ ብዛቱ ግን የሚያጠግብ ነበር፡፡ እንዲያውም በየቀኑ እየተረፈ የሚጣለው እንጀራ፣ ዳቦ እና ወጥ እስር ቤቱን የጥጋብ አገር የሚያስመስለው ነበር›› ይላሉ (72)፡፡

በርግጥ ሚዛናዊ ለመሆን እና ትግላችን ከነበረው የተሻለ መሆን እንዳለበት ለማመልከት፤ በዚህ በጎዳና ላይ ፍርድን ለመቃወም አነሳሁት እንጂ በመንግስት የመገናኛ ብዙሃን የተገለጸው ዓይነት የጭካኔ ተግባር፤ ፕሮፌሰር መስፍን ያነሷቸው መልካም ነገሮች በሚዲያ የተመለከትነውን ግፍ ለመሸፈን እንዲያገለግሉ አይደለም፡፡ ይልቅስ ከነበረው የተሻለ ሁኔታ ለመፍጠር ለመስራት እንድንነሳሳ ስሜት ለመፍጠር ነው፡፡ ከነበረው የወረደ ነገር አይገባንም የሚል መልዕክት ለማስተላለፍ ነው፡፡ ‹‹በለውጥ ሂደት ውስጥ ሊያጋጥም የሚችል ክፉ ድርጊት›› በሚል የሞራል ቁጣችንን ሳንገልጽ ማለፍ ስለማይገባን ነው፡፡ ተጨማሪ ክፉ ድርጊቶች እንዳይፈጠሩ መከላከያ መንገዱ እና ዋስትናው፤ ሰው በጎዳና ፍርድ በድንጋይ ተወግሮ ሲሞት ማየት የማንሻ ህዝቦች መሆናችንን ለመግለጽ ነው፡፡

ኢትዮጵያ ፖለቲካ መፋጠጥ የገነነበት እና መፈራቀቅ የበዛበት በመሆኑ፤ አንዳንዴ ህግን የማስከበር መንግስታዊ ኃላፊነትን ለመወጣት የሚደረግ እንቅስቃሴ በመብት ላይ እንደ ተቃጣ በትር የሚታይበት ሁኔታ አለ፡፡ ስለሆነም የሰብዓዊ መብት ክሶች የተቀናቃኝ ኃይልን ተቀባይነት ለማሳጣት የሚነሱ ጥያቄዎች ሲሆኑ ይታያል፡፡ የለውጥ ኃይሉ ህግን ለማስከበር የሚወስዳቸው እርምጃዎች በዚሁ አግባብ ሊታዩ የሚችሉበት ዕድል ሰፊ ነው፡፡ ነገር ግን መንግስት የዜጎችን መብት እና ነጻነት የማክበር ግዴታ እንዳለበት ሁሉ፤ ህግ የማስከበር፣ የዜጎችን በህይወት የመኖር፣ ኢሰብአዊ ከሆነ አያያዝ የመጠበቅ እና በየትኛውም የሐገሪቱ አካባቢ በነጻነት ተዘዋውሮ የመስራት መብታቸውን የማስከበር ኃላፊነትም አለበት፡፡