ህግ የማያከብር ህዝብና ህግ የማያስከብር መንግስት ህልውና የለውም
ኢብሳ ነመራ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ነሃሴ 19፣ 2010 ዓ/ም ለሃገር ውስጥና ለውጭ ጋዜጠኞች መግለጫ ሰጥተዋል። ጠቅላይ ምኒስትሩ ወደሃላፊነት ከመጡ ወዲህ ባሉት አራት ወራት ጊዜ ውስጥ ለጋዜጠኞች መግለጫ ሲሰጡ ይህ የመጀመሪያቸው ነው። ይሁን እንጂ በመግለጫው ላይ የተሳተፉት ጋዜጠኞች ቁጥር በተሳታፊ ብዛት ሪከርድ ሳይይዝ አልቀረም፤ 150 ያህል ጋዜጠኞች ነበር በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ የተገኙት። እርግጥ ጥያቄ የማቅረብ እድል ያገኙት ጥቂቶቹ ናቸው። የሁሉም አለመጠየቅ ግን የቀረ ጥያቄ መኖሩን አያመለከተም። እድል ያገኙት ጋዜጠኞች ያነሱት ጥያቄ፣ እድል ያላገኙት ሊያነሱት የተዘጋጃቡበት የሚሆንበት እድል ሰፊ ነው። ዋናው ነገር ሶስት ሰአት ተኩል በፈጀው የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋዜጣዊ መግለጫ መነሳት ያለባቸው ወቅታዊ ጉዳዮች በሙሉ ተነስተዋል ማለት ይቻላል። በዚህ ጽሁፍ በጋዜጠኞች ከቀረቡትና በጠቅላይ ምኒስትሩ ማብራሪያ ከተሰጠባቸው ጉዳዮች መሃከል በተለይ የህግ የበላይነትን የሚመለከተው ላይ በማተኮር አሁን በሃገሪቱ ካለው ነባራዊ ሁኔታ አኳያ ለመመልከት ወድጃለሁ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሁን በሃገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች የተፈጠሩ ግጭቶችንና የደረሱ ጉዳቶችን መነሻ በማደረግ መንግስት የህግ የበላይነትን በፍጥነት በማስከበር ረገድ ችግር ነበረበት የሚል ጥያቄ ቀርቦላቸው ነበር። ጠቅላይ መኒስትሩ የህግ የበላይነት ለድርድር እንደማይቀርብ ነው የገለጹት። ይሁን እንጂ ከዚህ ቀደም በተለይ በለውጥ ወቅት ሲደረግ እንደነበረው ተቃራኒን በሙሉ ላለመጨፍለቅ ጥንቃቄ መደረጉን ጠቅሰዋል። እንዲሁም ተጠርጣሪዎችን በጅምላ አፍሶ ከማጣራትና ከጥርጣሬ ውጭ የሆኑትን ጥፋተኛ አይደላችሁም ብሎ ከማሰናበት ይልቅ አጣርቶ በመያዝ ለፍርድ ለማቅረብ በተደረገው ጥረት ምክንያት አጥፊዎችን ለፍርድ የማቅረቡ ሂደት መዘግየት እንደታየበት አስረድተዋል።
እንግዲህ ሁሉም የኢትዮጵያ ህዝብ እንደሚያወቀው ባለፉ ጥቂት ወራት አዲስ አበባን ጨመሮ በተለያዩ የሃገሪቱ አካባቢዎች ከዚህ ቀደም ያልተለመዱ የወንጀል ድርጊቶች ተፈጽመዋል። ሰኔ 16፣ 2010 ዓ/ም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ ላከናወኑት ተግባር እውቅና ለመሰጠትና ለማመሰገን በመስቀል አደባባይ በተጠራ ህዝባዊ ትዕይንት ላይ በህዝብ መሃከል ቦምብ ፈንድቶ ሁለት ሰዎች ህይወታቸውን ማጣታቸው፣ በመቶዎች የሚቆጠሩ የአካል ጉዳት የደረሰባቸው መሆኑ ይታወሳል። ሃምሌ 19፣ 2010 ዓ/ም በዚሁ በመስቀል አደባባይ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ስራ አስኪያጅ ኢ/ር ስመኘው በቀለ በመኪናቸው ውስጥ ተገድለው ተገኝተዋል።
በተለያዩ የሃገሪቱ አካባቢዎች የእርስ በርስ ግጭቶች አጋጥመዋል። በኦሮሚያና በደቡብ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች በተለይ በጉጂ ዞንና በጌዴኦ አካባቢ ባጋጠመ ግጭት በሰው ህይወት ላይ ጉዳት ደርሷል። አንድ ሚሊየን ያህል ዜጎች ተፈናቅለዋል። በኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሱማሌ አካባቢ የቆየው ግጭትም አላቆመም። በቅርቡ በምስራቅ ሃረርጌ በታጣቂዎች በተወሰደ እርምጃ ከ40 በላይ ዜጎች ህይታቸውን ሲያጡ ተመሳሰሳይ ቁጥር ያላቸው የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል።
በኣማራ ክልል ዜጎች በብሄራዊ ማንነታቸው ብቻ በአሰቃቂ ሁኔታ በድንጋይ ተወግረው የተገደሉበት ሁኔታ አለ። በዚሁ ክልል በተለይ በሰሜናዊ የክልሉ አካባቢ እህል ጭነው የሚጓዙ ተሽከርካሪዎች ተዘርፈዋል። ከክልሉ ወደትግራይ የሚጓዙ ተሽከርካሪዎችን እንቅስቃሴ ለመግታት ሙከራ ሲደረግ ቆይቷል። በኦሮሚያ ክልል በሻሸመኔ ከተማ ለአክቲቪስት ጃዋር መሃመድ አቀባበል ለማደረግ በተጠራ ትእይትንት ላይ አንድ ወጣት ቦምብ ይዟል በሚል ግምት በአሰቃቂ ሁኔታ ቁልቁል ተሰቅሎ ተደብድቦ ህይወቱ እንዲያልፍ ተደርጓል።
ከሁሉም የከፋው በኢትዮጵያ ሱማሌ ክልል በቅርቡ ያጋጠመው ነው። የክልሉ ከፍተኛ ባለስልጣናትም እጅ እንዳለበት በሚገመት ጥቃት እስካሁን ቁጥራቸው በግልጽ ያልተነገረ ዜጎች በብሄራዊ ማንነታቸውና በሃይማኖታቸው ተለይተው ተገድለዋል። አካላቸው የጎደለም አሉ። በሺሆች የሚቆጠሩ ዜጎች በዛው በክልሉ ውስጥና ከክልሉም ውጭ ከኑሯቸው ተፈናቅለው ለአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ ጠባቂነት ተዳርገዋል። ዘጠኝ ያህል የኦርቶዶክስ ክርስትና አብያተ ክርስቲያናት ተቃጥለዋል። ዘረፋምና ንብረት የማወደም ተግባርም ተፈጽሟል።
ከህግ የበላይነት መጣስ ጋር በተያያዘ በሃገሪቱ ያለው ችግር ይህ ብቻ አይደለም። በተለይ በኦሮሚያ አሁን የተጀመረውን ለውጥ ባመጣው ህዝባዊ ተቃውሞ ውስጥ ጉልህ ድርሻ ከነበራቸው ወጣቶች መሃከል የተወሰኑቱ የህግ የበላይነትን ጥሰው በማንአለብኝነት የሚንቀሳቀሱበት ሁኔታ ተስተውሏል። ጥቂት ወጣቶች በተለይ በመሬት ወረራ፣ ኢንቨስተሮችን በማስፈራራትና በማፈናቀል፣ የራሳቸውን ኬላ አቋቁመው የትራንስፖርት እንቅስቃሴን በማስተጓጎል፣ በመንግስት ስራ ውስጥ ጣልቃ በመግባት፣ በዞንና በወረዳ ደረጃ የሚገኙ የስራ ሃላፊዎችን በማስፈራራትና በመደብደብ፣ ወዘተ ውስጥ መሳተፋቸው ታውቋል።
ነሃሴ 19፣ 2010 ዓ/ም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ፣ የህግ የበላይነትን የተመለከተ ጥያቄ እንዲነሳ ያደረገው ነባራዊ ሁኔታ ይህ ከላይ የተመለከተነው ነው። ጠቅላይ መኒስትሩ የህግ የበላይነትን በተመለከተ ያቀረቡትን ማብራሪያ፣ የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ ከተወሰደና በቀጣይ መወሰድ ከሚገባው እርምጃ አኳያ ጠቅለል አድርገን እንመልከት።
ጠቅላይ መኒስትሩ የህግ የበላይነትን በተመለከተ ባሰጡት ማብራሪያ፣ ህዝብ ህግ አክብሮ የመኖር ግዴታ እንዳለበት፣ መንግስትም ህግ የማስከበር ግዴታ እንዳለበት አንስተዋል። ህዝብ ህግ የማያከብር ከሆነ፣ መንግስትም ህግ ማስከበር የማይችል ከሆነ የህግ የበላይነት ይጠፋል። የእያንዳንዱ ሰው መብትና ነጻነት በሌሎች ሰዎች መብትና ነጻነት የተገደበ ነው። ሰዎች ነጻነታቸውን የመጠቀም መብታቸው ሌሎች በማንኛውም ሁኔታ ያላቸውን ነጻነት በማክበር ወይም ባለመንካት የተገደበ ነው። ይህ የሰዎች ነጻነት ብቸኛ ገደብ ነው። ይህ ገደብ በህግ ይደነገጋል። ሰዎች ህግ ሳያከብሩ ሲቀሩ የሰዎች ሰብአዊ መብቶችና ነጻነቶች ይጣሳሉ። መንግስት ህግ የማስከበር ግዴታ የሚኖርበት አንዱ የሌላውን መብትና ነጻነት እንዳይጥስ ለመከላከል ነው። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሃገራችን ያጋጠመው ሰዎች የሰዎችን መብትና ነጻነት የሚጥሱበት፣ መንግስትም ህግ በማስከበር መብትና ነጻነትን በመከላከል ረገድ ክፍተት ያሳየበት ሁኔታ ነው።
የህግ የበላይነት ካልተከበረ የሃገር ህልውና ያከትማል። የህግ የበላይነትን ማክበርና ማስከበር የቅንጦት ጉዳይ ሳይሆን እንደሃገር የመቀጠል ያለመቀጠል ጉዳይ ነው። ጠቅላይ መኒስትር ዶ/ር አብይም በጋዜጣዊ መግለጫቸው የህግ ልዕልና ለድርድር አይቀርብም ሰሉ የገለጹት የህግ የበላይነት የሃገር ህልውና መሰረት መሆኑን መሰረት በማድረግ ነው።
አሁን ዋናው ጉዳይ የህግ የበላይነትን ለማስከበር ምን እየተሰራ ነው? የሚለው ነው። አስደንጋጭ የነበረውን በኢትዮጵያ ሱማሌ ክልል ያጋጠመውን ችግር ለመፍታት እስካሁን ባለው ሁኔታ ፖለቲካዊ እርምጃዎች ተወስደዋል። የክልላዊ መንግስቱ ፕሬዝዳንትና የክልሉ ገዢ ፓርቲ የኢትዮጵያ ሱማሌ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢሶዴፓ) ሊቀመነበር አቶ አብዲ ኡመር በገዛ ፍቃዳቸው ከሃላፊነታቸው ተነስተዋል። ሌሎች በተፈጸመው አስከፊ ህገወጥ ድርጊት ውስጥ እጃቸው አለበት ተብለው የሚጠረጠሩ አመራሮችም ከፓርቲ አመራርነት (ከማዕከላዊና ከስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልነት) ተነስተዋል። ከህግ አኳያ የመከላከያ ሰራዊት፣ የፌደራል ፖሊስና የክልሉ የጸጥታ ሃይል በቅንጅት ካከናወኑት ሰላምና መረጋጋትን የማስከበር ስራ ያለፈ እስካሁን የተከናወነ ነገር የለም። እርግጥ ሰላምና መረጋጋት በሌለበት አጥፊዎችን በህግ ተጠያቂ የማድረግ ሰራ አስቸጋሪ ምናልባትም የማይቻል መሆኑ እሙን ነው።
ከዚህ በተጨማሪ ምናልባት በሺህ የሚቆጠሩ የኢትዮጵያ ሱማሌ ክልል የተለያየ የህብረተሰብ ክፍል ተወካዮች – የሃገር ሽማግሌዎች፣ የጎሳ መሪዎች፣ ኡጋዞች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የወጣቶችና የሴቶች ተወካዮች ወዘተ በክልሉ ችግሮችና የመፍትሄ አቅጣጫዎች ዙሪያ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ጋር ተወያይተዋል። የክልሉን ህዝብ የተለያየ የህብረተሰብ ክፍል በመወከል አዲስ አበባ ድረስ መጥተው ከጠቅላይ ምኒስትሩ ጋር የተወያዩት የክልሉ ተወላጆች፣ በክልሉ የነበረውን የሰብአዊ መብት ጥሰትና የመልካም አስተዳደር ችግር አሰታውሰዋል። እነዚህ ችግሮች መስተካከል እንደሚገባቸው፣ በእነዚህ ጉድለቶችና ሰሞኑን በተፈጠረው ቀውስ ተጠያቂ መሆን ያለባቸው አመራሮችም ለፍርድ እንዲቀርቡ ጠይቀዋል። በክልላቸው ይኖሩ የነበሩ የሌላ አካባቢ ተወላጆችና የክርስትና እምነት ተከታዮች ላይ የደረሰውን አስከፊ ድርጊትም አውግዘዋል፤ እንደማይደገምም ቃል ገብተዋል።
ይህ ከላይ የተወሰደው ፖለቲካዊ እርምጃ የህግ የበላይነትን ለማስከበር መደላድል ነው። በቀጣይ አጥፊዎች በህግ የሚጠየቁበት ሁኔታ ይጠበቃል። ይህ በቅርቡ ይሆናል የሚል እምነትም አለ። ጠቅላይ ምኒስትር አብይ አህመድ ሰሞኑን ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፣ በወንጀል ድርጊቱ የተጠረጠሩ የክልሉ አመራሮች ጉዳይ በህግ እንደሚታይ አስታውቀዋል።
በሌላ በኩል በኦሮሚያ ክልል የህግ የበላይነትን ጥሰው በተለይ በቄሮ ስም የሰው ህይወት ያጠፉ፣ የመንግስት ስራ ውስጥ ጣልቃ የገቡ፣ የመሬት ወረራና ህገወጥ ግንባታ ውስጥ የተሳተፉ፣ ኢንቨስተሮችን ያፈናቀሉና ያስፈራሩ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር እየዋሉ ነው። እስካሁን ባለው መረጃ ከ5 መቶ በላይ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል። እርምጃው ይቀጥላል። ይህ ህግ የማስከበር እርምጃ በክልሉ ላለቶ የነበረበትን የህግ የበላይነት በማሻሻል የዜጎችን ስጋት ያቃልላል። የተጀመረው የህግ የበላይነትን የማረጋገጥ እርምጃ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት። በደቡብ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልልም አጋጥሞ ከነበረው የወንጀል ድርጊት ጋር በተያያዘ 3 መቶ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ወለዋል። በመስቀል አደባባዩ የቦምብ ፍንዳታ የተጠረጠሩ ግለሰቦችም በቁጥጥር ስር ወለው ጉዳያቸው በምርመራ ሂደት ላይ ይገኛል። በቅርቡ በተጠርጣሪዎች ላይ ክስ ይመሰረታል ተበሎ ይጠበቃል። የኢ/ር ሰመኘው በቀለ ገዳዮችን ጉዳይ በተመለከተ ግን እስካሁን ለህዝብ የተገለጸ ነገር የለም። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ ሰሞኑን በሰጡት ጋዜጣዊ መገለጫ በዚህ የወንጀል ድርጊት ዙሪያ በቅርቡ መረጃ ይፋ እንደሚደረግ ጠቁመዋል።
ከላይ የጠቀስናቸው የህግ የበላይነትን ለማስከበር የሚደረጉ ጥረቶች መልካምና አበረታች ናቸው። በህግ የበላይነት መላላት ብዙዎች ላይ የተፈጠረውን ስጋት ቀለል አድርጓል። ይሁን እንጂ መጠኑ ይለይ እንጂ በተመሳሳይ የጅምላ ፍርድ ሰዎች በአሰቃቂ ሁኔታ የተገደሉበት፣ የትራንስፖርትና የንግድ እንቅስቃሴ እንዲቋረጥ የተደረገበት የአማራ ክልል እስካሁን የህግ የበላይነትን በማረጋገጥ የወሰደው እርምጃ አልተሰማም።የክለሉ አመራሮች የህግ የበላይነት ለድርድር የማይቀርብ መሆኑን፣ የህግ የበላይነትን ለጊዜያዊ የፖለቲካ ትርፍ ብሎ ችላ ማለት ለዘለቄታው የክልሉን ብሎም የሃገሪቱን ህልውና ፈተና ላይ የሚጥል መሆኑን ሊያስታውሱ ይገባል።
በአጠቃላይ፣ ባለፉ ጥቂት ወራት በሃገሪቱ እየታየ ያለው ወደስርአተ አልበኝነት የመለወጥ አዝማሚያ ታይቶበት የነበረው ሁኔታ መፍትሄ እያገኘ ይመስላል። ይህ የህግ የበላይነትን በማስከበር ስርአተ አልበኝነትን የመድፈቅ ተግባር ችግሮች በነበሩባቸው ሁሉም ክልሎች ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል። ህግ የማያከብር ህዝብና ህግ ማስከበር የማይችል መንግስት ያለባት ሃገር ህልውና የሚጠፋ መሆኑን በማስታወስ የህግ የበላይነት ላይ አንደራደር።