Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ህገ ወጥነትን በመታገል…

0 303

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ህገ ወጥነትን በመታገል…

                                                          ታዬ ከበደ

በመዲናችን አንዳንድ አካባቢዎች ዝርፊያ እና ንጥቂያ የሚፈጸሙ ወንጀለኞችን ለመቆጣጠር የከተማዋ ፖሊስ እየወሰዳቸው ያሉ እርምጃዎች ህግን ያማከሉ ናቸው። ህግን ማስከበር የመንግስት ሃላፊነትና ግዴታ ቢሆንም፣ የህብረተሰቡ ጉልህ ተሳትፎ ካልታከለበት ውጤት ሊገኝ አይችልም። ምንም እንኳን በመዲናዋ የሚታየው ችግር የተጋነነ ባይሆንም፣ ህብረተሰቡ ከመንግስት ጎን መቆም ይኖርበታል።

ህብረተሰቡ ወንጀሎችን በመከላከል ረገድ ሊያበረክተው የሚችለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው። ህገ ወጦች የሚሸሸጉት በህብረተሰቡ ውስጥ እንደመሆኑ መጠን፣ ህዝቡ በመሃሉ ያሉትን ዘራፊዎች አጋልጦ ለህግ ማቅረብ ይኖርበታል። የማጋለጡ አልያም ጥቆማ የመስጠት ጉዳይ በቀጥታም በተዘዋዋሪም ሊሆን ይችላል።

ወንጀለኞች መልሰው ሰላም የሚነሱት ህብረተሰቡን በመሆኑ ህገ ወጥነትን በመታገል እንደ ዜጋ ተገቢ ሚናውን ሊወጣ ይገባል። ይህም በመዲናችን ውስጥ የህግ የበላይነትንንና ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን ለማስፈን የሚረዳ ነው።

በመንግስት በኩል ችግሮችን ለመፍታት፣ ለምሳሌ የአዲስ አበባ መስተዳድር በቤቶች ላይ የጀመረው የኦዲት ሥራ ውጤትን እስካሁን በተካሄደው ማጣራት በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ብቻ በህገ ወጥ መንገድ ተይዘው የነበሩ 199 የቀበሌ ቤቶች ለችግረኞች እንዲተላለፉ ተደርጓል።

ይህ እርምጃ የህግ የበላይነትን ከማስከበርና ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን ከማረጋገጥ አኳያ ያለውን ፋይዳ ትልቅ ነው። ምክንያቱም የህዝብ ሃብት የጥቂቶች መጠቀሚያ ሳይሆን ህብረተሰቡ በፍትሃዊነት ሃብቱን እንዲጠቀም የሚያስችለው ስለሆነ ነው።

ገና ጅምር ቢሆንም መንግስት ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን በተግባር እያረጋገጠ ነው። የመስተዳድሩ እርምጃ ህገ መንግስታዊ ነው። ህገ መንግስቱ አገሪቱ ፍትሃዊ የምጣኔ ሀብት ዓላማዎችን ማራመድ እንዳለባት በግልጽ ደንግጓል።

ይህንን ዓላማ ለማረጋገጥ መንግሥት ዜጎች በአገሪቱ የሚገኘውን ሀብት በፍትሃዊነት ተጠቃሚ የሚሆኑበትን አሰራር የመቀየስ ኃላፊነት አለበት። ይህን ሃላፊነቱንም በአጭር ጊዜ ውስጥ እየፈጸመ ነው።

ዜጐች በመንግስት በኩል የሚከናወኑና ለልማት መሠረት የሆኑ የትምህርትና የጤና አገልግሎቶች፣ የምግብ ዋስትና፣ የንፁህ መጠጥ ውኃ፣ የመኖሪያና የማህበራዊ ዋስትና የማግኘት መብት እንዲኖራቸው ህገ መንግስቱ ደንግጓል።

ሁሉም ዜጋ በማንኛውም የምጣኔ ሃብት እንቅስቃሴ ውስጥ የመሰማራትና ለመተዳደሪያው የመረጠውን ሥራ የመከወን መብት እንዲሁም በመንግሥት ገንዘብ የሚካሄዱ ማህበራዊ አገልግሎቶችን በእኩልነት የመጠቀም መብት እንዳላቸው ተመልክቷል።

በስራ ላይ ባለው ህገ መንግስት ሕዝቦች የኑሮ ሁኔታቸው የመሻሻልና የማያቋርጥ እድገት የማግኘት መብት እንዳላቸው ተቀምጧል። ዜጐች በብሔራዊ ልማት የመሳተፍ፣ በሚቀረፁ ፖሊሲዎችና ኘሮጀክቶች ላይ አስተያየት የመስጠት መብትም አላቸው።

የአገራችንን ህዝቦች እድገትና መሠረታዊ ፍላጐቶችን ማሟላት፣ መንግሥት የሚያወጣቸው ፖሊሲዎችና የሚያደርጋቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶች የአገሪቱን ሕዝቦች የተጠቃሚነት መብት የሚያስከብሩ ናቸው። ዜጐች በመንግሥት ገንዘብ በሚካሄዱ አገልግሎቶች በእኩልነት የመጠቀም መብት የፍትሐዊነት ማሳያዎች ናቸው።

ዜጐች ንብረት የማፍራት፣ በመረጡት የሥራ መስክ የመሰማራት መብቶች በማረጋገጥ በነፃ ገበያ ኢኮኖሚ ሥርዓት የሚመራ ፈጣንና ፍትሃዊ ልማት የማምጣት ጠቀሜታን ህገ መንግስቱ ይገልጻል።

በፍትሐዊ አንድነት ውስጥ የሕዝቦችን ልማታዊ አቅም ማሳደግና ለአገር ግንባታ ወሣኝ ተግባር እንዲያበረክቱ እንዲጫወቱ ማድረግ ያስፈልጋል። የዜጐችን የልማት ባለቤትነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ በልማት እንቅስቃሴዎች ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን እውን ማድረግ ነው።

በራስ አቅምና ፍላጐት ነፃ አገራዊ ኢኮኖሚ መገንባት ለአገሪቱ ዘላቂ ሠላም፣ ዴሞክራሲና ልማት ወሳኝ በመሆናቸው የፍትሐዊ ተጠቃሚነትን ጉዳይ ተገቢና ትክክል እንዲሆን ያደርገዋል።

ስለሆነም በአዲስ አበባ መስተዳድር የተካሄደው የቀበሌ ቤቶችን ለችግረኞች የመስጠት ጉዳይ የዚህ አስተሳሰብ ትክክለኛነት ማረጋገጫ መሆኑን መገንዘብ ይገባል። አንዱ እየተጠቀመ ሌላው የሚታለፍበት ምክንያት የህግ የበላይነትን የሚፃረር ስለሆነም የመስተዳደር እርምጃ ከዚህ አንጻር ግንዛቤ ውስጥ መግባት አለበት።

የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ ህገ ወጥ የውጭ ምንዛሬ ላይ ቁጥጥር ተደርጎ እርምጃ እየተወሰደ ነው። እርምጃው ተጠናክሮ የሚዘልቅ ነው። ይህም ሰላምና ጸጥታን በማረጋገጥ የህግ የበላይነትን ለማስከበር ጉልህ ሚና ያለው ስለሆነ፣ ህብረተሰቡም ህገ ወጥነትን በመታገል የሰለሙ ጠባቂ መሆን አለበት። የሰላምና ጸጥታ መረጋገጥ ደግሞ ተጠቃሚው ህብረተሰቡ በመሆኑ ለሰላሙ መትጋት አለበት።

ሰላም ወዳዱ ህብረተሰብ በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ሰላምን በማወክ ተግባር ላይ የተገኙ አካላትን በመገሰፅ፣ ለሰላም እንዲሰሩና የሰላምን እሴት እንዲያውቁ ማድረግ የቻለ ነው። ከአምስት ወራቶች በፊት ያለፋቸው ፈታኝ መንገዶች ስለ ሰላም ጠቀሜታ እንዲገነዘብ አድርገውታል።

አሁን በለውጥ ጎዳና ላይ የሚገኘው ህዝብ በለውጥ ተስፋ ላይ ያለ ነው። ለውጡ በተሻለ ተጠቃሚነት ላይ የሚያደርሰው ነው። ሰላሙንና ጸጥታውን እውን እያደረገለት ይገኛል። በዚህ በኩል የሚታዩት አንዳንድ ሰላምን የሚያሳጡ ችግሮችን መታገል አለበት።

ችግሮቹ የአገርን ኢኮኖሚ የሚጎዱ እንደ ህገ ወጥ ምንዛሬ ዓይነት ሊሆኑ ይችላሉ። እርግጥ ህብረተሰቡ የችግሮቹን ምንጮች ያውቃቸዋል። እነማን በህገ ወጥነት ተሰማርተው እየሰሩ መሆኑን ይገነዘባል። ከህብረተሰቡ የሚሰወር ነገር ባለመኖሩም የህገ ወጥ ምንዛሬ መፈልፈያዎችን ያውቃል።

መንግስት ህገ ወጥነትን በመታገል ኢኮኖሚውን መታደግ ይቻላል ብሎ ያምናል። ይህን አስተሳሰቡን ለመተግበር ህገ ወጦች ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል። በመዲናዋ የተለያዩ አካባቢዎች ህገዋ ፈቃድ ሳይኖራቸው ይህን ተግባር ሲፈጽሙ የነበሩ አካላት ሱቆቻቸው እንዲታሸግና በህግ እንዲጠየቁ አድርጓል።

እንዲህ ዓይነቱ ህገ ወጥነትን በመታገል የህግ የበላይነትን የማስፈንና ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን የማረጋገጥ ጉዳይ ነገም የሚቀጥል ነው። ህጋዊነትን ለማጠናከር የህብረተሰቡ ሚና ወሳኝ በመሆኑ ከመንግስት ጎን በመቆም ዜጎች አገራዊ ሃላፊታቸውን መወጣት አለባቸው።

 

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy