Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ለለውጥ እንጂ ለነውጥ አንቸኩል!

0 286

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ለለውጥ እንጂ ለነውጥ አንቸኩል!

ህይወት አደም

በተለያዩ አካባቢዎች እየተስተዋሉ የሚገኙት ሁከትና ግርግሮች ለምንሳሳላት ውድ ኢትዮጵያ ክብርና ልዕልና የማይመጥኑ ናቸዉ፡፡ ሁከትና ግርግሮቹ ውድ በሆነዉ የሰው ልጅ ሕይወት ላይ የተቃጡ፤ፈልጎ ባልሸመተው ብሔሩ ላይ ያነጣጠሩ፤በተፈጥሮ የተቸረው ከቦታ ቦታ የመንቀሳቀስ መብቱን የገቱ፤የሐይማኖት ነጻነትና መብቱን የጣሱ ናቸው፡፡

በየቦታው በሚፈጠሩ ሁከትና ግርግሮች የአጀንዳ ማስፈፀሚያነት እየዋለ  የሚገኘው የነገ ሀገር ተረካቢ የሆኑት ወጣቶች ጉልበት ነው፡፡ ወጣት ድንጋይ ፈንቅሎ፤ ተራራ ንዶ ድህነትን ድባቅ የመምታት ጉልበት ባለቤት መሆኑ እሙን ነው፡፡ ይሁን እንጂ በተገቢው ካልተመራና ቅኝቱ ካልተስተካከለ የተገነባ ህንጻ ደርምሶ፣ሥርዓት አፍርሶ ሀገርን ወደ መቀመቅ ማውረድ የሚያስችል ጉልበትም ባለቤት ነው፡፡

በጽኑ መሠረት በተገነባ ሥርዓትና በተገነባው ሀገር የመጀመሪያ ተጠቃሚ ወጣቱ ኃይል ነው፡፡ በፈረሰ ሥርዓትና በፈረሰ ሀገር የፊት ለፊት ተጎጂውም እራሱ ወጣቱ ነው፡፡ ወጣቱ ኃይል ከጉልበቱ ይልቅ  ጭንቅላቱን ሲያስቀድም የማመዛዘን፣ የመረዳትና ነገሮች አሻግሮ የማየት አቅሙ ይጨምራል፡፡ በተቃራኒው ወጣቱ ጉልበቱን ሲያስቀድም ሕይወቱንም፣ አገሩንም ለአላስፈላጊ ጥፋት ይጋብዛል፡፡ ስንት ጀግኖች  ሲዋደቁላት የኖረች ሉዓላዊት ሀገር ክብር ለጠላት አሳልፎ ይሰጣል፡፡ በስተመጨረሻም በየቦታዉ በዋዛ ፈዛዛ ፈርሰዉ ክብራቸዉን እንዳጡት ሀገሮች የባዕድ ኃይል መፈንጫ፤ የተደራጁ ሽፍቶች መራገጫ የአሸባሪዎች መቀመጫና ሥምሪት መስጫ ማዕከል መሆንን ያስከትላል፡፡

በዘርፉ ተመራማሪዎች እንደሚታወቀው የሰው ልጅ ጭንቅላት የአስተሳሰቡ ማዕከል ናት፡፡ የአጠቃላይ እንቅስቃሴው መዘውር መሆኗ ነው፡፡ ይህንን እንቁ የሆነውንና ለሰው ልጅ ብቻ የተሰጠውን አስተሳሰብ ሰው በሁለት መልክ ሲጠቀምበት ይስተዋላል፡፡ አንድ አንዶች ለልማት፣ ሰውን ለመርዳት፣ ሰውን ለማፋቀር እና ውድ የሆነውን የሰው ሕይወት በሚታደጉ የበጎ አድራጎት ተግባራት ላይ ያውሉታል፡፡ ሌሎች ደግሞ ለክፋትና ለተንኮል፣ ውድ የሆነውን የሰው ሕይወት ለመቅጠፍና ያልተገባ ጥቅም ለማጋበስ ሲያውሉት ይስተዋላል፡፡

መነሻው ከአዳምና ሔዋን አንድ ምንጭ የሆነዉን ሰዉ በዘር፣በጎሳና በሰፈር በመከፋፈል ከአንድነት ይልቅ ልዩነት፣ ከመወዳጀት ይልቅ መጠላላትና መገፋፋት፣ ወገኑን አቅፎ ከመስራት ይልቅ ማግለል፣ማሳደድና ማባረር ላይ ተጠምደው ርባና የለሽ ተግባር ይፈጽማሉ፡፡ ለበጎ ተግባር መዋል ይገባው የነበረውን ማህበራዊ ሚዲያ ለዚህ አፍራሽ ተግባራቸዉ በስፋት ሲጠቀሙት ማየት  የተለመደ ሆኗል፡፡

ማህበራዊ ሚዲያውን ሲፈልጉ ለተሳሳተ መረጃ ማሰራጫነት ሲፈልጉ ደግሞ ለሁከትና ግርግር ማስጀመሪያ አዋጅ ደወልነት ያውሉታል፡፡ በማህበራዊ ሚዲያ ትክክለኛ መረጃ በማሰራጨት ለእዉቀትና ቴክኖሎጂ ሽግግር የሚጠቀሙ አካላት የመኖራቸውን ያህል በከፍተኛ ሁኔታ ለፈጠራ ወሬዎችና አሉባልታዎች የሚጠቀሙበትም ቁጥራቸው ቀላል አይደለም፡፡ የጥፋት አጀንዳ ከመቅረጽ ባለፈ የሚፈልጉትን የህብረተሰብ ክፍል ማዕከል አድርገው የተንኮል ችግኝ ኮትኩተው ለማሳደግ ጥረት የሚያደርጉ አካላት መኖራቸዉም በስፋት እየተስተዋለ ይገኛል፡፡ ወጣቱ የእነዚህን አካላት የአስተሳሰብ ዝቅጠት በማጋለጥ እርቃናቸውን ማስቀረት ይኖርበታል፡፡

ብዙ ጊዜ ወጣቱ በማህበራዊ ሚዲያ ያገኘውን መረጃ ሰምቶ ለመተግበር ሲሽቀዳደም ይስተዋላል፡፡  ባልተጣራና ትክክለኛነቱ ባልተረጋገጠ መረጃ ተመስርቶ ለእርምጃ መሽቀዳደም ተገቢ አይደለም፡፡ ውጤቱም ስርዓት አልበኝነት፣ ደም መፋሰስና አላስፈላጊ የሕይወት መስዕዋትነት የሚያስከትል መሆኑን  ልንገነዘ ይገባል፡፡ ወጣትነትን በበሰለ አስተሳሰብ ገርተውና ምክንያታዊ ሆነው ትውልድን በማነጽ አደራን መወጣት ይገባል፡፡ ይህን ማድረግ የቻሉ ወጣቶች በሕይወት ሲኖሩ በማህበረሰባቸው የክብር ካባን ለመደርብ ይታደላሉ፡፡ለሀገራቸው የማይመክን ዘርን ይዘራሉ፡፡  

ወጣት የሰማውንና ያገኘነውን መረጃ ትክክለኛነቱ  ምን? ማን? እንዴት? መቼና ለምን? ብሎ በመጠየቅ በጠራ መረጃ ላይ ተመስርቶ የተዛቡ ሀሳቦች መሞገት ይኖርበታል፡፡ ሚዛናዊ ያልሆኑ ሀሳቦችን ታግሎ ማምከን ያስፈልጋል፡፡ ሆን ብለው የሚያወናብዱ ህብረተሰቡን በአሉባልታና በበሬ ወለደ ወሬ የሚንጡ አካላት እርቃናቸው እንዲቀሩ ማድረግ ተገቢና አስፈላጊ ነው፡፡ ትክክለኛ መረጃ በመያዝ አፍራሽ ተግባራቸውን ፀሐይ ማስመታትና በአሉባልታነቻቸው እንዲሸማቀቁ ማድረግ ይገባል፡፡ በሀገራችን አንድ አንድ አካባቢ እንደሚታየው ህግና ሥርዓት ባለበት ሀገር ባልተጣራ ወሬ በስሜት በመነዳት  የምስኪን ግለሰቦችን ህይወት ከመቅጠፍ መቆጠብ ያስፈልጋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ እንደተናገሩት መግደል መሸነፍ መሆኑን በወሬ ሳይሆን በተግባር በማሳየት የለውጡ ዋና ተዋናይ መሆናችንን ልናስመሰክር ይገባል፡፡

አልፎ…አልፎ የሚስተዋሉ ግጭቶችና የግጭት አዝማሚያዎችን በሰለጠነ መንገድ ማምከን ካልተቻለ በተስፋ የምንጠብቃት የበለፀገች ኢትዮጵያን የማየት ዕድላችን ተስፋ ብቻ ሆኖ ይቀራል፡፡ የዛሬ ትዉልድ ከስህተቱ ካልተቆጠበ እንደ ትናንቱ ድህነትና ኋላ ቀርነት ለቀጣይ ትዉልድ በማውረስ ተወቃሽ ሆኖ መቀጠሉ አይቀርም፡፡ ስለዚህ የአደናቃፊዎችን አስተሳሰብ መሸከም ሳይሆን ማምከን ይኖርብናል፡፡ በአጠቃላይ ወጣቱ ሙሉ አቅምና ጉልበቱን ለለውጥ በማዋል ከነውጥ ኃይል ራሱንና ሀገሩን በመጠበቅ መደመሩን በተግባር ብቻ ማሳየት አለበት እንላለን፡፡

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy