ለሐሳብና ጥያቄዎቻችን አጥር እናብጅ
አሸናፊ መለሠ
ያለፍንበት የታሪክ መንገድ በታላላቅ ተቃርኖዎች የተሞላ ነው፡፡ በአንድ ወገን ለወራሪ ጠላት ፈፅሞ የማይንበረከክ ስነልቦናን የታጠቁ፣ ደረታቸውን ለጥይት ለመስጠት የማያመነቱና ለሀገር ሉዓላዊነት መሞትን በክብር ሞትነት የፈረጁ ጀግኖችን የፈጠረች ናት – ኢትዮጵያችን፡፡ በዚህ የተነሳ ድንበሯ የተከበረ፣ ህዝቦቿም የታፈሩ ሆነው ኖረዋል፡፡ በሌላ በኩል ለዘመናት የተጓዝንበት የገዢና ተገዢ ስነልቡና ህዝብ ስልጣንንና ባስልጣንን እንዳይጠይቅና “ታሪካዊ ሚናው” መገ’ዛት ብቻ እንደሆነ ሲነገርና በዚህ ሚናውም ለዘመናት ሲመራ ሳይሆን ሲገ’ዛ ለመኖር ተገዷል፡፡ በውርስ፣ በጦርና በተንኮል ወደ ስልጣን የሚወጣውም ሀይል በተመሳሳይ የሲመት እጣውን አንድም ከአምላክ ስጦታ ጋር እየሰፋ፣ አልያም ወደ ታጠቀው አፈሙዝ እያመለከተ ራሱን የስልጣኑ ብቸኛ ባለመብት አድርጐ የገዛ ሕዝቦቹን “ቀጥቅጦ በመግዛት” ተወጥሮ ኖሯል፡፡
ይህን ዘላለማዊ የመሰለ ህግ ግን ህዝቦች በይሁንታ ተቀብለው ኖሯል ማለት አይቻልም፡፡ ይልቁንም ፍትሐዊ አስተደዳርን መድረሻቸው ያደረጉ ልዩ ልዩ ጥያቄዎችን በማንሳት ጨቋኝ ስርዓቶችን ሲታገል ቆይቷል፡፡ በዚህም የተለያዩ ውጤቶች ማስመዝገብ ችሏል፡፡ እነዚህ ውጤቶችም ቢሆኑ ሙሉ በሙሉ ሕዝባዊና ዴሞክራሲያዊ አስተዳደርን በማስፈን ተቋጭተዋል ማለት አይቻልም፡፡ የብዙዎቹ የትግል ውጤቶች በሂደት በሌሎች የቡድን ሐሳቦች እየተቀለበሱ ህዝቡን ለዳግም ትግል ሲዳርጉትና ተጨማሪ ዋጋ ሲያስከፍሉት መቆየታቸው እስካሁን የምናየው አስገራሚ ሀቅ ነው፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህም ባለፉት በርካታ አመታት የታዩ ስር የሰደዱ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን መነሻ በማድረግ ሕዝቡ የተናጠልና የተደራጀ ትግል አካሂዷል፡፡ በውጤቱም ምናልባት ከ100 ዓመት በኋላ በሀገራችን በሕዝቡ ዘንድ ተስፋን የሰነቀ የለውጥ ድባብ ሰፍኗል፡፡ ይህ የለውጥ ድባብም አብዮት ሊባል በሚችል ደረጃ የዜጎችን ተሳትፎ ያነቃቃ፣ ስልጣን ላይ ያለውን ሃይልና የተፎካካሪ ፓርቲዎችን ወደአንድ ሀገራዊ መንፈስ ያጠራራና በሐይማኖት፣ በፖለቲካና በማህበራዊ ፍትህ ዙርያ ታላቅ መግባባትን የፈጠረ ሆኗል፡፡ ይህ ብቻም ሳይሆን ከዚህ በፊት ባልተለመደ አኳኋን የውስጣዊው የፖለቲካ እንቅስቃሴ ተፅእኖ ወደቀጠናው ሀገራት በመሸጋገር አብሮ የመስራት መንፈስን አበልጽጓል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ ይህ ለውጥ ባስገኛቸው የለውጥ አቅሞች መነሻነት በሀገሪቱ ያልተለመደ ዓይነት የሀሳብ ውዥንብር ሰፍኗል፡፡
የዚህ የሀሳብ ውዥንብር ዋነኛ መነሻ ባለፈው ሩብ ክፍለ ዘመን ጠብቦ የነበረው ሀሳብን የመግለፅ መብት በድንገትና ያለገደብ ነፃ መውጣቱ ነው፡፡ ይህንን ሀሳብን የመገለፅ ነፃነት በሁለት ከፍሎ ማየቱ ጠቃሚ ነው፡፡
የመጀመሪያው ጉዳይ በእነዚያ አመታት የታፈኑት እነኚህ ሀሳቦች ለሀገራችን ወቅታዊና ታሪካዊ ችግሮች መፍትሔን ለማዋለድ የሚያስችሉ ሆነው መገኘታቸው ሀሳብን የመገለፅ ነፃነት በመልካም አጋጣሚነት ሊታይ ይችላል፡፡ ከዚህም ባሻገር ሀሳብን የመግለፅ ነፃነት ሀሳቦችን ብቻ ሳይሆን የተሻለ ሀሳብን የሚያመነጩና የሚያራምዱ አዳዲስ ምሁራንንና አክቲቪስቶችን ወደ ሀገራዊ መድረኩ የሚያመጣ በመሆኑ አወንታዊ ጎኑ እጅጉን ከፍ ያለ ነው፤ በፖለቲካዊ ምህዳሩ ላይም ተጨማሪ አቅም መፍጠሪያ ናቸው፡፡
በሌላ በኩል ይህን ሀሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት ተገን አድርገው ለዘመናት ታፍነው የቆዩ “ደረጃቸውን ያልጠበቁ” ሀሳቦችን በአደባባይ እየተመለከተን መገኘታችን ነው፡፡ ሀሳቦቹ ለዓመታት በግለሠቦች ልቦና ታምቀው የቆዩና በየወቅቱ በሚነሱ የሀሳብ ፍጭቶች ራሳቸውን ሳይፈትሹ አልያም ራሳቸውን ዘመኑ ከሚፈልገው ተለዋዋጭ ሁኔታ ጋር ሳያመሳክሩ ወደ አደባባይ በመውጣታቸው ኋላቀርነት ተጠናውቷቸው ቢገኝ አይገርምም፡፡ ከዚህ ይልቅ አፈናው የሃሳቦቹን አመንጪ አዕምሮዎች ለዘመናት ተቆጣጥረው ለተሻለ ሃሳብና ድርጊት ይውል የነበረን አቅም ማክሠማቸው አሳዛኝነቱ ያይላል፡፡
ይህም ሆኖ ሃሳቦቹ በኔ ብያኔ “ኋላቀር” ተብለው በመፈረጃቸው ብቻ ሌሎችን አያስከትሉም፤ ለድርጊት አያነሳሱም ማለት አይደለም፡፡ እንደውም እየሆነ ያለው በተቃራኒ ነው፡፡
እንደማህበረሠብ በማህበረሰሠብ መሪዎች (በሃይማኖት አባቶች፣ በምሁራን፣ ’ባገር ሽማግሎዎችና አንዳንዴም በፖለቲካ አመራሮች) ላይ ያለን እምነት ከፍተኛ ነው፡፡ በመሆኑም አንዳንዴ የሃሳቡን ይዘት፣ አመክንዮና ተጨባጭነት በቅጡ መርምረን ሳይሆን የሃሳቡን ባለቤት አምነን እንከተላለን፡፡ ይህም አቅም ሆኖን በእነዚህ መሪዎቻችን ከጥፋት ድነናል፣ ወደተሻሉ መንገዶችም ተመርተናል፡፡ በአንፃሩ እንደግለሰብ ብቻ ሳይሆን እንደማህበረሰብም ጭምር ብዙ የመከራ ገፈቶች ቀምሰናል፡፡
ይህ አይነት አካሄዳችን ነገሮችን የመረዳት አቅማችንን በማሳደግና ስለጉዳዮች፣ በተለይም በፖለቲካዊ፣ ሃይማኖታዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ ልዩ ትኩረት በማድረግ ሃሳብን በሃሳብ ማሳደግንና ሃሳብን በሃሳብ ማምከንን ልንካን ይገባል፡፡
በዚህ ወቅት ያለውን የሀሳቦች ያደባባይ ጉዞ ከሉጠት (evolution) ንድፈ-ሀሳብ አንፃር መመልከቱ ወሳኝ ነው፡፡ የለውጡ ንድፈ-ሀሳብ ዋነኛ ማጠንጠኛ ህግ ተፈጥሯዊ ምርጫ (natural selection) ነው፡፡ ይህ ተፈጥሯዊ ምርጫ “ስዩመ እግዚያብሔራዊ”ና ቋሚ ሳይሆን ከተለያዩ የሀሳብ ፈተናዎች፣ ማለትም በዘመን፣ በቦታና በሁኔታ እንዲሁም በይዘትና ምክንያታዊነት ተፈትነው የተሻሉት ብቻ አሸናፊ ሆነው ህልውናቸውን የሚያስቀጥሉበት ሃሳብ ትንቅንቅ ነው፤ “survival of the fittest” ይለዋል የንድፈሃሳቡ ፈጣሪ ዳርዊን፡፡ በመሆኑም የሀሳቦችን ወደ አደባባይ መምጣት በጐ ጐኑን መቀበሉን እደግፋለሁ፡፡ ነገር ግን ሁሉም ሀሳቦች ሀገር አይገነቡምና፣ ሁሉም ሀሳቦች ሰላማዊ አይደሉምና ፀረ ሕዝብ ይዘት ያላቸውን፣ በጋራ ተግባብቶ የመኖር ነባር ባህላችንን ለማጥፋትና ፅንፈኝነትን በመስበክ “እኔ ብቻ ልክ ነኝ ” ባዮችን ነጥሎ መታገል ይገባል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ የአንዳንድ ቡድኖች መነሻ ሀሳብ ይህ የለውጥ አውሎ ነፋስ ጠራርጎ ለወሰዳቸው “ያሮጌ ዘመን ቁማርተኞች” ምቹ የፀረ ህዝብ እንቅስቃሴ ኮርቻ እንዳይሆኑ ያሻል፡፡
በመሆኑም ቡድኖችና ግለሰቦች ለሚያነሷቸው ጥያቄዎችና የተሻለ ሀገር ለመፍጠር ያስችላል በሚል ለሚያቀርቧቸው ሀሳቦች ሀላፊነት መውሰድ፣ የሀሳባቸውንና የጥያቄአቸውን መነሻና መድረሻም ጠንቅቆ መረዳት ያስፈልጋል፡፡ ይህም ሀሳባቸውን ተተግኖ የራሱን ፍላጐት ለመጫን የሚሞክርን የተንኮል ባለሟል አስቀድሞ ለመመከት እድል ይሰጣል፡፡ ከዚህም ባሻገር የጥያቄና ሀሳቦችን ግብ፣ ወቅታዊነትና የመላሻችንን ማንነትና ወቅታዊ አቅም ለመፈተሽ እድል ስለሚሰጥ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ቀውሶችን ለመቀነስና ሰላማዊውን አውድ ለማስፋት ተጨማሪ አቅም ይሆናል፡፡ በአጠቃላይ ሀሳቦቻችንና ጥያቄዎቻችን በሚያበረክቱት ማህበረሰባዊና አገራዊ ፋይዳ ልክ ወቅታዊነታቸውን ጠብቀን ቅደም ተከተላዊ ስደራ እና አጥር ልናበጅላቸው ይገባል፡፡