Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ለጠንካራ ተፎካካሪነት ጥምረት

0 321

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ለጠንካራ ተፎካካሪነት ጥምረት

ስሜነህ

 

የኢትዮጵያ መንግሥት የዴሞክራሲ ምህዳሩን ለማስፋት አልሞ እየሰራ ያለበት ጊዜ ቢኖር አሁን ያለንበት ወቅት ነው። በመሆኑም በይቅርታ፣ በመደመርና በፍቅር እሳቤ ላለፉት ዓመታት በአመለካከታቸው፣  ወይም በፖለቲካ አቋማቸው የተሰደዱና ከአገር የወጡ ዜጎችን በየደረጃው ጥሪ በማድረግ በሰላማዊ መንገድ የያዙትን ሃሳብ ይዘው በሀገር ውስጥ ያለውን የለውጥ መንፈስ እንዲደግፉ እያደረገ ይገኛል። አክቲቪስቶችና ሌሎችም በምንም ሁኔታ ሳይገደቡ ነፃ ሃሳባቸውን እንዲያንፀባርቁና በሃሳብ የበላይነት በማመን ነገሮች በሰለጠነ መንገድ አገርን በሚጠቀም ሁኔታ እንዲመሩ እየሰራ ይገኛል።  

 

በዚሁ አግባብ ከአገር ውጭ ያሉ በርካታ ቁጥር ያላቸውና የተለያየ የፖለቲካ አቋም ያላቸው ወደ ሀገር ቤት እየገቡ በተፈጠረው ምቹ የፖለቲካ ምህዳር ለመጠቀም መፈለጋቸውን በይፋ እየገለፁ መሆኑም ይታወቃል። የሃገራችንን ነባራዊ ወቅታዊ ሁኔታ መሆን ካለበትና ሊሆን ከሚገባው ይልቅ እየሆነ ካለው ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ አንጻር ስንመለከት እጅግ በጣም የተለያየ፣ ፈጽሞ ሊቀራረብ የማይችል፣ አብሮ ሊያሰራ የማይችል፣ ፍጹም ተቃራኒ ሀሳብና አቋም ያላቸው ኃይሎችና አካላቶች ሕብረት ፈጥረናል ሲሉ ግን እስካሁን አልተደመጠም።   

 

ሲጀመር ከሕገ መንግሥቱ አንጻር ሕገ መንግሥቱን ፈጽመው ከአመጣጡ አንስቶ የሚቃወሙ፣ አንቀበልም የሚሉ፣ መሻሻል አለበት የሚሉ፣ መለወጥ አለበት የሚሉ፣ እንደወረደ ተግባር ላይ መዋል አለበት የሚሉ፤ ከሥርዓት አንጻር የሥርዓቱን መሠረት የሚቀበሉና የማይቀበሉ፤  ከሰንደቅ አላማ አንጻር ያለውን የሚቀበሉ፣ የማይቀበሉ፣ የራሳቸውን የሚሹ፤ በርዕዮተ ዓለም እጅግ የተራራቀ፣ የተቃረነ እንዲሁም የተደራጀና ትርጉም ያለው ርዕዮት የሌላቸው ኃይሎችና አካላት፤ ከአሰራር አንጻር ሥርዓቱ እንዳለ እንዲቀጥል የሚሹ፣ እንዲሻሻል የሚሹ፣ የሽግግር መንግሥት እንዲቋቋም የሚሹ ኃይሎችና አካላት፤ ከለውጥና አካሄድ አንጻር ደግሞ መጠነኛ ማሻሻያ ማድረግ የሚሹ፣ የጎላ ለውጥ ማድረግን የሚሹ እንዲሁም መሠረታዊ ለውጥ የሚሹ ወዘተ አካላት፤ አሁን እየመጣ ካለው ለውጥ አንጻር እራሳቸውን በምን አግባብ እያነጹ እንደሆነ ግልጽ የወጣ ነገር የለም።

 

አስቀድሞ ሲያነሱ የነበረው የምህዳር መጥበብ ጉዳይ ከተፈታ መንፈቅ ሊሞላው ቢሆንም እነዚህ ሃይሎች ዛሬም የወረቀት ነብር ላይ ሆነው መቆየታቸውና ከትችት ሱስ አለመላቀቃቸው በሃገሪቱ የለውጥ ሃይሎች እየተገነባ ካለው እና ሊገነባ ከታሰበው የዴሞክራሲያዊ ስርአት አኳያ ያሳስባል። በዶክተር አብይ የሚመራው ገዢ ፓርቲና መነግስት በኩል በግንባሩ ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ የለውጥ ፍላጎትና በተግባር የተገለጠ እርምጃ በመታየቱ ልክ፤ ሃገራችን ዛሬ ያለችው እጅግ የተለያየ ፍላጎትና አቅም ያላቸው ግለሰቦች፣ ቡድኖችና ድርጅቶች በለውጥ አስፈላጊነት ላይ የሚስማሙ መሆኑም በነቢብ መስተዋሉም እውነት ነው። ያም ሆኖ በተቃዋሚዎቹ በኩል  ምን አይነት? አድማሱ እስከምን የደረሰ? በማን የሚመራ? በምን ዓላማ? ለምን? የሚለው ላይ ትርጉም ባለው መንገድ የጋራ መግባባት ላይ የደረሰ አለመሆኑን የሚያሳዩ በርከት ያሉ አስረጂዎች መጥቀስ ይቻላል፡፡

 

በነዚህ ሃይሎች በኩል መግባባት ያለ ሚመስለው በስሜት (Emotion) እና በአስተያየት (Opinion) እንጂ ትርጉም ባለው ሃሳብ (Idea) ፣ እሳቤ (Thought) እና ርዕዮት /ርዕዮተ ዓለም/ (Ideology) ላይ እንዳልሆነ ከመንፈቅ ቆይታቸው እያስተዋልን ነው፡፡ ሃገራችንን ለረዥም ዓመታት ወደ ኋላ ካስቀሯት ዐቢይ ምክንያቶች መካከል “በጋራ ካላሰባችሁ ፤ እንደኔ ካላሰባችሁ፣ እኔ እንደምለው ካልሆናችሁ፣ የኔ መንገድ ብቻ ፣ ያለእኔ ሌላው መንገድ ሁሉ መጥፎ ነው ∙∙∙∙ ወዘተ” አይነት የገዢው ፓርቲና ገዥ ለመኾን የሚሹ ኃይሎች ብቻ ሳይኾን ተገዥዎችም ብንሆን መስማት የምንፈልገውን ብቻ የመስማት፣ ማንበብ የምንሻውን ብቻ የማንበብ፣ የኛ ጀግኖችና የምናደንቃቸውን ግለሰቦች በአመክንዮና በዕሳቤ ላይ ተመርኩዘን ሳይሆን በአብዛኛው እኛን የሚመስሉንና መምሰል የምንሻቸው፣ የውስጣችንን የሚነግሩን ፤ እሱን ስለነገሩን የምንደሰትባቸው መሆናቸውን የተመለከተው አስተሳሰብ  አንዱና ዋነኛው ነው። ምንም እንኳ የሰው ልጅ ባሕሪና ጠባይ ለዚህ ተጋላጭ መኾኑ ዕውነት (Truth) እና እውነታ (Reality) መሆኑ ባይዘነጋም ምክንያታዊነትና ዲሞክራሲያዊ ዕሴትን ባሕል ከማድረግ አንጻር ግን ተቃርኖው በተለይ አዲሱ የለውጥ አመራር እየወሰዳቸው ከሚገኙ የለውጥ እርምጃዎች አንጻር በጣሙን አሳሳቢ ይመስላል፡፡

 

ከዴሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታ አኳያ አዲሱ የለውጥ አመራር ካሳየው ፍላጎትና ተጨባጭ እርምጃዎች አንጻር አሁን በሃገሪቱ ውስጥ የተጠናከረና ጉልበት ኖሮት የተዋቀረ የተፎካካሪ  ፓርቲ አለ ማለት ያስቸግራል፡፡ በዚህም የተነሳ ተቀናጅተውና ሃይላቸውንና አቋማቸውን አስተባብረው ገዢውን ፓርቲ ሊሞግቱና ገዢውን ፓርቲ ሊቋቋሙት ብቃት ያላቸው ፓርቲዎች ውህደት አይታይም፡፡ ክቡር ጠቅላይ ሚንስትሩም እንደመሻታቸው ላይሆንልኝ ይችል ይሆን ብለው ከሚሰጉባቸው ጉዳዮች ዋነኛው ይህ ሳይሆን አይቀርም። ከሃምሳ በላይ የሚሆኑ ፓርቲዎችን ከሰሞኑ ባወያዩበት ወቅት ይሀ አይነቱ መነጣጠላቸው እንኳንስ ለሃገር ኢህአዴግን ለመፎካከርም የማያስችላቸው እንደሆነ አጽንኦት መስጠታቸው ለዚሁ ስጋታቸው አስረጅ ሆኖ ሊጠቀስ ይችላል።

አሉ እንኳ ቢባል ስለሃገሪቱ ዴሞክራሲያዊ ስርአት በሚበጅና ግንባታውን በሚያፋጥን ደረጃ በምሁራንም የተጠናከረና የተዘጋጀ ተቃዋሚ የሌለ መሆኑም በብዙዎች ዘንዳ እያነጋገረ እና ምርጫው መራዘም አለበት እስከማለት ያደረሰ መሆኑም እየተስተዋለ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ የኢህዴን መስራችና ኢህአዴግን ጠንቅቀው የሚያውቁት ስለመሆኑ ብዙዎች የሚናገሩላቸው አቶ ያሬድ ጥበቡ ሰሞኑን ለተለያዩ ሚዲያዎች የሰጡት ቃለ ምልልስ ሁነኛ አስረጅ ይሆናል።

እኔ አሁንም የሚያሳስበኝ በሁለት ዓመት ውስጥ ወደ ዲሞክራሲያዊ ምርጫ እንገባለን የሚለው ጉዳይ ነው፡፡ በደንብ ታስቦበታል ወይ የሚል ጥያቄ አለኝ። የሽግግር ዕድል ሲገጥመን ይሄ አራተኛው ነው፡፡ የኢትዮጵያ ትልቁ ችግር ደግሞ የተገኘውን የሽግግር ሂደት፣ በስነ ስርአት ለማስቀጠል አለመቻል ነው። ወይ በወታደራዊ የበላይነት አሊያም በአንድ ቡድን የበላይነት የሚጠናቀቅበት ሁኔታ ነው ሲፈጠር የኖረው። የዚህ ዋነኛ ምክንያት ደግሞ የተገኘውን እድል ለመጠቀም ሁሉንም ያካተተ ረጅምና የሽግግር መድረክ አዘጋጅተን ስለማናውቅ ነው፡፡ ∙∙∙∙∙”  በማለት አቶ ያሬድ በሰፊው ማብራሪያ ሰጠውበታል። ቢያንስ ለዴሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታ ወሳኝ ናቸው ከሚባሉት መካከል ከሲቪል ማህበረሰቡ እና፤ ከማህበራት፤የተዋቀረ የተቃዋሚ ፓርቲም የለም፡፡ የህብረተሰቡን ሃይል ያካተተም እንቅስቃሴም ሆነ ተቃዋሚ ሃይል የለም፡፡ በኢትዮጵያ ያለው የፖለቲካ ተቃዋሚዎች ችግር ከ1960ዎቹ ጀምሮ የኖረው ያረጀው ችግር ነው፡፡አሁንም በሃገራችን ያሉት እኒያ ተስፋ የቆረጥንባቸው የተቃዋሚ ሃይሎች፤ የተከፋፈሉ፤እኒያ በነጋ በመሸ ቁጥር በረባ ባልረባው ጉረሮ ለጉረሮ የሚተናነቁትና ዋናውን ሊታገሉት የሚገባውን ሃይል የዘነጉት ናቸው።   

ገዢውን ፓርቲና አመራሮቹን በስድብ ክምር ማጥላላትን፤ጥርስን በመንከስ ማንኳሰስ የተቃዋሚውን ፓርቲ አስተሳሰብ ከፍተኛነት ከማቅለሉ ባሻገር ለዴሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታ ምንም ፋይዳ የለውም። ተቃዋሚዎች ለተጠያቂነትና ለመልካም አስተዳደር ያላቸውን ሃሳብና ራዕይ ያዛንፍባቸዋል እንጂ የሚየስገኝላቸው ጠቀሜታም ሆነ ትርፍ የለውም፡፡ አብዛኛዎቹ የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት በስልጣን ላይ ስላለው ገዢ ሃይል የሚጠቀሙበት ቋንቋ ቁጣ፤ፍርሃት፤የበታችነት ስሜትን የሚያሳይ፤ነው፡፡ እዚህ ላይ ግን ቢያንስ ጥቂቶች እውነትን ይዘው በቆራጥነትና በአመክንዮ የሚናገሩ መሆናቸው ሊዘነጋ አይገባም፡፡ ይህም ሆኖ ደግሞ ለዴሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታ በሚበጅ አግባብ የገዢውን ፖሊሲዎች፤ፕሮግራሞችና ፕሮጄክቶች፤በሰከነ ጥናትና ግምገማ፤ በምርምር አቅርበው የሚናገሩና በምትኩም የተሸለ ጥናት የሚያቀርቡ አሉ ብሎ ለመናገር ግን ያስቸግራል ፡፡

 

የአቶ ያሬድ ምልከታ እንደለውጥ አመራሩ መሻት እና ስለ ሃገራችን የዴሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ለምርጫ ውድድር ከመዘጋጀት ባሻገር ብዙ ሊጫወቷቸው የሚገቧቸው ሚናዎች ያሉ መሆኑን የሚያጠይቅ ነው፡፡ የአባሎቻችውን የደጋፊዎቻቸውንና የጠቅላላውን ሕብረተሰብ ንቃተ ሕሊና ማዳበርና ለትግሉም ማዘጋጀት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ፖሊሲያቸውን በሚገባ በማዳረስና በማስረዳት ሕብረተሰቡን ማስተማር አለባቸው፡፡ ክርክርና ውይይት በማዘጋጀት፤በአስፈላጊ ርእሶች ላይ በመነጋገርና ሕዝቡንም ተሳታፊ ማድረግ ሁኔታዎችን እያነሱ ችግሮችን በማንሳትና መፍትሔዎችን በመጠቆም የሃገሪቱን የወደፊት ራዕይ መጠቆም አለባቸው፡፡ ሁኔታዎችን በማስተካከል የዴሞክራሲ ባሕል የሚዳብርበትን መንገድ ቀያሽ ሊሆኑ ይገባል፡፡ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ስኬታማ መሆን የሚችሉት ለወጣቱና ለሴቶች አስፈላጊውን የአመራር ስልጠና ለመስጠት ማቀድና መተግበር ሲችሉ ነው፡፡ የብዙዎቹ ተቃዋሚ ድርጅቶች አመራሮች ሃምሳውን ዓመት የዘለሉ ሲሆኑ በአመራሩ ላይ ያሉትም የሴቶች ቁጥር አናሳ ነው፡፡ “ዕድሜ ቁጥር እንጂ ሌላ አይደለም” በወጣቱና በዕድሜ ጠገብ ፖለቲካ መሃል ግልጽ የሆነ ልዩነት አለ፡፡ ወጣቱ ትውልድ ታላቅ የመነሳሳት ፍላጎት፤ ቅልጥፍና፤ቆራጥነት፤ በዓላማው ላይ መራመድን ይቀይሳል። ያንንም ተግባራዊ ለማድረግ ፈጣንና ቆራጥ ነው፡፡ ያደርገዋል፡፡ ስለዴሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታ ተቃዋሚ ፓርቲዎችም ከሚዲያውና ከሲቪል ማህበረሰቡ ጋር በመሆን ተቀናጅተው ወደ ሕዝቡ መድረስ አለባቸው፡፡

 

ክቡር ጠቅላይ ሚንስትሩ የሰጡትን ምክር አንድምታ ከተመለከትነው ውየተከፋፈለ ተቃዋሚ ግልጋሎቱ  የገዢው ፓርቲን እድሜ ማራዘም ነው የሚል መልእክት መሆኑን ሊገነዘቡ ይገባል ፡፡ የገዢው ፓርቲ ሃይልም ሆነ ተቃዋሚውን አሳንሶ ማየትና እንዳሻው መሆን ዋናው መሳርያና ምክንያት የተከፋፈለ ተቃዋሚ ነው፡፡ የተባበረ፤አቋሙ የተስተካከለ፤ዴሞክራሲያዊ ተቃዋሚ ነው ለኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት፡፡ እንዲህ አይነቱ ተቃዋሚ ታዲያ በመቻቻል በስምምነት በመግባባት ላይ መሰረቱን ያዋቀረ የተባበረና የብዙሃኑን ፍላጎትና ራዕይ መሰረት ያደረገ ተቃዋሚ ሃይል ነው፡፡ ሕብረቱ በሕዝቡ ፍላጎትና እምነት ላይ መሰረቱን ያደረገ ሲሆን ሂደቱ ለምርጫ ውድድር መዘጋጀት ብቻ ሳይሆን ሰፊ ምህዳር ያለው ፖሊሲ በመቅረጽ የሰፋ ውክልና ሊኖረው የሚችልና ለምርጫውም ቢሆን ሰፊ ድጋፍ የሚቸረው ሕዝባዊ ተቀባይነትና አመኔታ የተጣለበት አለኝታ ይሆናል፡፡ በሕብረት ውስጥ ሰፊ የሆነ ሃሳብና እቅድ የሚቀርብ በመሆኑ ይህንንም ወደ ተግባር ለመለወጥ የከረረ ውይይትና እሰጥ አገባ ተካሂዶበት ወደ ዴሞክራሲያዊ ውሳኔ ስለሚደርስ የአብዛኛውን ሕዝብ ፍላጎት የሚያካትት ዓላማቸውን የሚያስፈጽም በመሆኑ ሊፈጠር የሚችለውን አለመግባባት ሁሉ በውይይት ፈትቶ ለውሳኔ ይደርሳል፡፡ የኢትዮጵያ ተቃዋሚ ፓርቲ እራሱን በሕብረት በሚያጣምር ፖሊሲ ላይ በማጠናከር መቆም ሲችልና በአንድነት አንድ ሆነው ሲንቀሳቀሱ ገዢውን ፓርቲና ፖሊሲዎቹን ለመሞገት ብቃት ይኖረዋል፡፡ይህ ደግሞ የለውጥ አመራሩን መሻት የሚያሳካና የሃገራችንን የዴሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታ የሚያፋጥን እዛው ሳለም የሚያጠናክር ይሆናል።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy