Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

በሁለት ኢሕአፓዎች መካከል ውዝግብ ተነሳ

0 1,321

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የህቡዕ ትግሌን ትቼ በይፋ ለመታገል አገር ቤት ገብቻለሁ ያለው የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) እና በውጭ አገር የሚገኘው እውነተኛው ኢሕአፓ እኔ ነኝ በሚለው መካከል ውዝግብ ተነሳ፡፡

በቅርቡ አዲስ አበባ የገባው ቡድን ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በውጭ አገር ያሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ወደ አገር ውስጥ ገብተው ሰላማዊ ፖለቲካዊ ትግል እንዲያደርጉ ያቀረቡትን ጥሪ በመቀበል፣ የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) በኢትዮጵያ ሕጋዊና ሰላማዊ ትግል ለማድረግ መዘጋጀቱን አስታውቆ ከ46 ዓመታት የህቡዕ ትግል በኋላ ወደ አገር ቤት መግባቱን አስታውቆ ነበር፡፡

ይሁን እንጂ መቀመጫውን በአሜሪካና በፈረንሣይ ያደረገውና የድርጅቱ ስምና ዓርማ እውነተኛ ባለቤት እኔ ነኝ የሚለው ኢሕአፓ፣ ‹ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ይድረስልኝ› ብሎ ባወጣው መግለጫ አገር ቤት የገባውን ቡድን ተችቷል፡፡

በውጭ ያለው ቡድን በመግለጫው፣ ‹‹መስከረም 12 ቀን አዲሶቹ ባለሥልጣናት ኢሕአፓ ነን የሚሉ ሕገወጥ ግለሰቦችን ወደ አዲስ አበባ ጋብዘው፣ አቀባበል ሊያደርጉላቸውና በድርጅቱ ስምም ሊያንቀሳቅሷቸው ያቀዱ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡ እነዚህ ግለሰቦች ኢሕአፓን ከድተው ከሄዱ አሥር ዓመታት አስቆጥረዋል። በአሁኑ ጊዜ እነዚህን ግለሰቦች ጠርቶ መስተንግዶ መስጠት እነ መለስ ዜናዊ ሥልጣን ሲይዙ እንደተደረገው ሁሉ፣ አስመሳዮችን በኢሕአፓ ስም  ለማንቀሳቀስ የሚደረግ ከንቱ ጥረት መሆኑን ሕዝብ ሁሉ አውቆ ይህን ተንኮልና ሴራ ውድቅ እንዲያደርገው እንጠይቃለን፡፡ ኢሕአፓን ማግለልና ማጥፋት የሻዕቢያ፣ የወያኔ፣ የግንጠላ ኃይሎችና የፀረ ኢትዮጵያ ባዕዳን ተልዕኮ ሆኖ ለረዥም ዓመታት መቆየቱን የማያውቅ የለም ማለትም እንፈልጋለን፤›› ብሏል፡፡ ‹‹መስከረም 12 ቀን ወደ አዲስ አበባ ለመግባት በዝግጅት ላይ ያሉት ግለሰቦች ከአሥር ዓመት በፊት ‘ከመለስ ዜናዊ አገዛዝ ጋር አብረን እንሥራ፣ ሕገ አራዊቱን እንቀበል፣ ትግሉን አቁመን እጅ እንስጥ፤’ በማለት ሐሳብ ያቀረቡ፣  አቋማቸው ለድርጅቱ አባላት ሁሉ ቀርቦ ተቀባይነትን ሲያጣ የድርጅቱን ጉባዔ ረግጠው የወጡ ናቸው። ከድርጅቱ ከተለዩ በኋላ ከዚያ በፊት  ባልታየ  መንገድ ራሳቸውን ኢሕአፓ፣ ዴሞክራሲ፣ ከዚያም ኢሕአፓ አንድነት በሚል ሰይመው የኢሕአፓን ስም ለመቀማት ቢሞክሩም፣ ሳይሳካላቸው ቀርቶ  በቁጥር ተመናምነው ሲባዝኑ ኖረዋል። ከዚያም ወዲህ ጉባዔ ረግጣችሁ መፈርጠጣችሁና የድርጅቱን ሕጋዊ ስም መጠቀማችሁ ስህትተት መሆኑን አምናችሁ ወደ ድርጅቱ ተመለሱና በሕጉ መሠረት አቋም የምትሉትን ማቅረብ ትችላላችሁ የሚል ተደጋጋሚ ጥያቄ ቢቀርብላቸውም፣ አሻፈረኝ  ብለውና ኢሕአፓነትን ተቃርነው ቆይተዋል፤›› ሲል በመግለጫው አትቷል፡፡

ሆኖም አዲስ አበባ የገባው ኢሕአፓ ነኝ ያለው ቡድን በወቅቱ፣ ‹‹ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኢትዮጵያ ውስጥ በመካሄድ ላይ ያለው ለውጥ አሳታፊ የፖለቲካ ምኅዳር እየፈጠረ መሆኑን በመገንዘብና በዶ/ር ዓብይ የሚመራው መንግሥት ላቀረበው ጥሪ ምላሽ በመስጠት፣ ኢሕአፓ አገር ውስጥ ሕጋዊ ዕውቅና አግኝቶ በይፋ ለመታገል ወስኗል፤›› ማለቱ ይታወሳል፡፡

በወቅቱ በሰጠው መግለጫም የፓርቲው አመራሮች አገር ቤት ሲገቡ ከተለያዩ  የመገናኛ ብዙኃን ጋር አባላቱን የማስተዋወቅ፣ በቀይ ሽብር የህሊናና የአካል ጉዳት የደረሰባቸውን የመጎብኘትና የማስተዋወቅ፣ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ስብሰባዎችን የማድረግ፣ አመለካከቱን ከሚጋሩ ግለሰቦች ጋር በቀጣይ ዕርምጃዎች ላይ ውይይት ማድረግ፣ ከተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ጋር እንዲሁ ውይይት የማድረግ መርሐ ግብሮችን መያዙን አስታውቆ ነበር፡፡

በወቅቱም በ1964 ዓ.ም. ተቋቁሞ ራሱን ይፋ ያወጣው ከ1966 ዓ.ም. አብዮት አንድ ዓመት በኋላ እንደሆነ በመግለጽ፣ በኢትዮጵያ በይፋ እንዳይንቀሳቀስ በመታገዱ ምክንያት ለ46 ዓመታት ህቡዕ ለመግባት መገደዱን አስታውቆ ነበር፡፡

ነገር ግን ተቀማጭነቱን በአሜሪካና በፈረንሣይ ያደረገው ቡድን፣ ‹‹ኢሕአፓ አንድና አንድ ብቻ ነው። ስሙም ዓርማውም በሕግ የተመዘገበ ነውና አጭበርባሪዎቹን ማስተናገድ ሕገወጥ መሆኑን ለዘመኑ ባልሥልጣናት ተነግሯቸዋል፡፡ የጥላቻና የግንጠላ አባ ወራዎችን እየሰበሰቡ ያሉት ባለሥልጣናትና ባዕዳንም ለኢትዮጵያ የቆመውን አገር ወዳድ ድርጅት ስለሚጠሉ፣ አስመሳዮችን ተክተው ሊያጠፉት ጥረት በማድረግ ላይ ናቸው፤›› ሲል አስታውቋል፡፡

‹‹አገራችን ለከፍተኛና አስከፊ አደጋ ተጋልጣለች፡፡ ኢትዮጵያዊነት እየተጠቃ ነው፡፡ ኢትዮጵያን ከጥፋት ለማዳን ከፍተኛ ርብርብ በሚያስፈልግበት በአሁኑ ጊዜ፣ ኢሕአፓ እያካሄደ ያለውን ትግል ለማኮላሸት ስሙን ነጥቀው በቦሌ ወደ አገር የሚገቡት ግለሰቦች የትግሉ እንቅፋት መሆናቸውን ሁሉም ዜጋ እንዲገነዘበው እንፈልጋለን፤›› ሲል አዲስ አበባ የገባውን ቡድን አውግዟል፡፡

ethiopianreporter.com

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy