Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

….በታላቅ ተስፋ!

0 327

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

….በታላቅ ተስፋ!

ገናናው በቀለ

የአገራችንን የትምህርት ለማጠናከር በርካታ ተግባሮች እየተከናወኑ ነው። ባለፉት ጊዜያት የትምህርት ተደራሽነትን ለማረጋገጥ ጉልህ ክንዋኔዎች ተፈጻሚ ሆነዋል። በተለይም ትምህርትን አስመልክቶ በሁለተኛው የልማት ዕቅድ የተያዘውን ቁልፍ ስራዎች ለማሳካት እየጣረች ነው።

ኢትዮጵያ ከትምህርት ግቦቿ ጋር የሚጣጣሙ የድህረ 2015 ዓለም አቀፋዊና አህጉራዊ የልማት ግቦች የዕቅዱ አካል ተደርገው ተፈፃሚ እንዲሆኑ ጥረት እያደረገች ነው። እርግጥ ትምህርትን በተመለከተ ቁልፉ ጉዳይ ጥራት ነው። ቀጥሎ ትኩረት የሚያሻቸው ከሽፋን ጋር የተያያዙ ጉዳዮች በመኖራቸው ይህንኑ ጉዳይ ለማሻሻል እየተሰራ ነው።

በዕቅዱ ላይ የመጀመሪያው ተግባር የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ሽፋን የማስፋፋት ጉዳይ ነው። በያዝነው የዕቅድ ዘመን ይህን ሽፋን በከፍተኛ ደረጃ ለማሳደግ ጥረት እየተደረገ ነው። ከዚህ ጋር በተያያዘም ለቅድመ መደበኛና የጐልማሶች ትምህርት ትኩረት በመስጠት ስራው እየተሳለጠ ነው።

እንዲሁም የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል የመምህራንና የትምህርት ቤቶችን ጥራት ለማሳደግ በሰው ሃብት ዙሪያ አቅምን ሊፈጥሩ የሚችሉ እርምጃዎች ተጠናክረው የሚቀጥሉ ይሆናሉ።

መንግስት በየደረጃው የትምህርት ጥራትን የማሻሻል ፕሮግራም ዘርግቶ እየሰራ ነው። ለኢኮኖሚ እድገቱና ለማህበራዊ ልማቱ በከፍተኛ ደረጃ የሰለጠነ ብቁ ዜጋ ማፍራት ቁልፍ ተግባር እንደመሆኑ መጠን፤ መንግሥት የከፍተኛ ትምህርት ጥራትን የማረጋገጥ ስራ በማጠናከር ተገቢውን ተግባር እየተወጣ ነው።

ለዚህም የግል ባለሃብቶች በትምህርት ዘርፍ በሰፊው እንዲሳተፉ ማበረታታት፣ ድጋፍ መስጠትና ስታንዳርዱን የጠበቀ ለመሆኑ ተገቢው ክትትልን የማድረግ ስራዎችን እያከናወነ ነው። በመንግስት የትምህርት ተቋማትም ተመሳሳይ ተግባሮችን እየፈፀመ ነው።

ያም ሆኖ ግን በመንግስት ጥረት ብቻ የትምህርት ጥራት ሊጠበቅ አይችልም። በመሆኑም ህብረተሰቡ የትምህርት ጥራትን ለማሳደግ በመደረገው ጥረት ግንባር ቀደም ተሳታፊ መሆን ይኖርበታል።

በእስካሁኑ ሂደት ህብረተሰቡ የመማር ማስተማሩ አካል እንዲሆን በማድረግ ከጥራት አኳያ የሚነሱትን ችግሮች ለመፍታት በሚደረገው ርብርብ የበኩሉን ድርሻ እንዲያበረክት ይደረጋል። በተለይ በአሁኑ ሰዓት ለውውይት የቀረበው የትምህርት ፍኖተ ካርታ በትምህርት ጥራት ላይ ትርጉም ያለው ለውጥ ሊያመጣ የሚችል ነው።

ትምህርትን ተደራሽ በማድረግ በኩልም በርካታ ስራዎች ተከናውነዋል።በአሁኑ ወቅት ትምህርት በገጠሪቱ ኢትዮጵያ ዘልቆ ገብቷል፡፡ በከተሞችም እንዲሁ ተስፋፍቷል፡፡ በአገሪቱ ያለው የትምህርት ሽፋንም ሰፍቷል፡፡ ዕድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ ህጻናት በሙሉ የሚታደሙበት ማዕድ ሆኗል፡፡ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በገጠር ቀበሌዎች ሳይቀር ተስፋፍተዋል፡፡

ይህም ዛሬ ከሶስቱ ኢትዮጵያዊ አንዱ በትምህርት ገበታ ላይ እንዲገኝ አድርጓል፡፡ ወላጆች ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤት እንዲልኩ የትምህርትን አስፈላጊነት ከማስተማር ጎን ለጎን ከተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በመተባበር  በትምህርት ቤቶች ለሚገኙ ህፃናት የምግብ አገልግሎት እየተሰጠ ነው፡፡

የወጣቱን የትምህርት እድል ለማስፋት የግል የትምህርት ተቋማት እንዲስፋፉ ተደርጓል። ይህ አገሪቱ ለልማት የምትፈልገውን የሰለጠነ የሰው ኃይል በማፍራት ረገድ የጎላ ሚና አላቸው፡፡ በአሁኑ ወቅት ከ60 በላይ የግል ዩኒቨርሲቲ ኮሌጆች የትምህርት አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛሉ፡፡

ማንኛውም ተማሪ በአዲሱ የትምህርት ዘመን ጠንክሮ በመማር የበኩሉን አስተዋፅኦ ማበርከት ይኖርበታል። በትምህርቱ መጠንከር ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ የሚደረገውን መዋቅራዊ ሽግግር ድጋፍ የሚያደርግ ነው።

እርግጥ የዛሬው ትውልድ ወጣት እድለኛ ነው። ትምህርት በሩ ድረስ ተዘርግቶለታል። ባለፉት ስርዓቶች የጥቂቶች መጠቀሚያ የሆነው ትምህርት ዛሬ የሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል በር እያንኳኳ ነው። ወጣቱ በዚህ ዕድል ተጠቅሞ ራሱንና ሀገሩን ሊጠቅም ይችላል።

ቀደም ሲል የነበረውን የትምህርት ቤቶች ስርጭት ኢ- ፍትሃዊነትን ለማስወገድ በአገሪቱ እያደገ የመጣው የትምህርት ቤቶች ቁጥር ሥርጭት ፍትሃዊነቱን እንዲጠብቅ ተደርጓል። ስርጭቱ አሁንም በቂ ባይሆንም ጉልህ ለውጦች መኖራቸውን መካድ ግን አይቻልም።

በትምህርት ሥርጭት ላይ የነበረው ኢ-ፍትሃዊነት በክልሎች መካከል ልዩነት ፈጥሮ እንደ ነበር አይዘነጋም፡፡ ይህ ኢ-ፍትሃዊ ስርጭት የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በተመጣጣነ ሁኔታ ማደግ እንዳይችሉ እንዲሁም የልማት ተጠቃሚነታቸውም ላይ ልዩነት መፍጠሩ የሚታወቅ ነው፡፡

ዛሬ ግን በእያንዳንዱ ክልል በርካታ አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች፣ ኮሌጆች እና ዩኒቨርስቲዎች ተቋቁመው የትምህርት አገልግሎት እየሰጡ ነው፡፡ በአገሪቱ የነበሩት የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ታድሰዋል፣ የማስፋፊያ ግንባታም ተደርጎላቸዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በርካታ አዳዲስ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተገንብተዋል፡፡ ወደፊትም ይገነባሉ።

እርግጥ የተማረና ብቃት ያለው ባለሙያ በሌለበት አገር ዘላቂ ልማት የሚታሰብ አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ በትምህርት ዘርፍ ያሳየችው ውጤትም አገሪቱ እያስመዘገበች ላለው የምጣኔ ሃብት እድገት መሠረት ነበር ማለት ይቻላል፡፡

ይህን እድገት አጠናክሮ ለማስቀጠል የተማረ ሃይል ያስፈልጋል። በአሁኑ ሰዓት ለመጪው የ2011 በጀት ዓመት የትምህርት አጀማመር ዝግጅት እየተደረገ ነው። ከቅድመ መደበኛ እስከ ከፍተኛ ትምህርት ድረስ በሁሉም መስኮች ዝግጅት ተጠናቅቆ ተማሪዎችን ለመቀበል እየተሰራ ነው።

ተማሪዎች በበጀት ዓመቱ ለትምህርት መዘጋጀት ይኖርባቸዋል። ትምህርት በአንድ ሀገር ውስጥ የሁሉም ነገሮች መሰረት በመሆኑ፣ ተማሪዎች የነገ ሀገር ተረካቢዎች እንደመሆናቸው መጠን ሙሉ ጊዜያቸውንና አቅማቸውን ለትምህርት በማዋል በበጀት ዓመቱ ታላቅ ተስፋን መሰነቅ አለባቸው። የነገ ራዕያቸውን ለማሳካትም ጠንክረው መስራት ይኖርባቸዋል።

ትምህርት የአንድ አገር ዕድገት ማረጋገጫ ነው። ይህ እንዲሆን ታሪዎች በትምህርት ገበታቸው ላይ ማተኮር አለባቸው። ለመጪው ዓመት በሁሉም የትምህርት እርከኖች በቂ ዝግጅት ተደርጓል። ተማሪዎች ሃሳባቸውን ወደ ትምህርታቸው በማድረግ ዓመቱን በታላቅ ተስፋ ተቀብለው አገራቸው የምትጠብቅባቸውን ተግባር መፈፀም ይኖርባቸዋል። መልካም የትምህርት ዘመን።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy