Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

በኦሮሚያ ክልል የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ብሄርን መሰረት በማድረግ የሚፈፀሙ ጥቃቶቸን አወገዙ

0 1,132

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

በኦሮሚያ ክልል የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ብሄርን መሰረት በማድረግ የሚፈፀሙ ጥቃቶቸን አወገዙ

በኦሮሚያ ክልል የሚንቀሳቀሱ አምስት የፖለቲካ ፓርቲዎች ብሄርን መሰረት በማድረግ የሚፈፀሙ ጥቃቶቸን አወገዙ።

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር፣ የኦሮሞ ፌደራላዊ ኮንግረስ፣ የተባበሩት የኦሮሞ ነፃነትና አንድነት ግንባር እንዲሁም የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ግንባር ወቅታዊ ጉዳዮችን አስመልክተው በዛሬው እለት መግለጫ ሰጥተዋል።

ፓርቲዎቹ በመግለጫቸው ማንነትን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶችን እናወግዛለን ያሉ ሲሆን፥ በዚህ ተግባር ላይ የተሳተፉ አካላትም በአፋጣኝ ተለይተው በህግ ፊት ቀርበው ተጠያቂ እንዲደረጉም ጠይቀዋል።

የኦሮሚያ ክልል በአዲስ አበባ ላይ ያለው ልዩ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እንደሚሰሩም አስታውቀዋል።

አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ መሰረት አዲስ አበባ ከተማ የሁሉም ብሄር ብሄረሰቦች መኖሪያ ከተማ ከመሆኗ አንፃር የሁሉም ህዝቦች የግልም ሆነ የቡድን መብት ያለአንዳች መሸራረፍ እንዲጠበቅ ለማድረግ ድርጅቶቹ የበኩላቸውን እንደሚወጡም በመግለጫቸው አረጋግጠዋል።

አንዳንድ አካላት በብሄር ብሄረሰቦች መካከል ጥርጣሬ እንዲፈጠር ደፋ ቀና እያሉ ይገኛሉ ሲሉም ፓርቲዎቹ በመግለጫቸው አንስተዋል።

ሆኖም ግን ይህ አይሳካላቸውም ያሉት ፓርቲዎቹ፥ መላው ሰላም ወዳድ ህዝብም የእኒዚህን ኃይሎች እኩይ ተግባር ለማክሸፍ አብሮ እንዲቆምም ጥሪ አቅርበዋል።

የመገናኛ ብዙሃንን በተመለከተም አንዳንድ የመገናኛ ብዙሃን ከሙያ ስነ ምግባሩ ያፈነገጠ እና ሚዛናዊነት በጎደለው መልኩ እየዘገቡ መሆኑንም ፓርቲዎቹ በመግለጫቸው አንስተዋል።

እነዚህ በሀገር ውስጥ እና በውጭ ሀገራት የሚገኙ መገናኛ ብዙሃን ህዝብን ከህዝብ ለማጋጨት ተግተው እየሰሩ ነው ያሉት ፓርቲዎቹ፥ መገናኛ ብዙሃኑ በህግም በታሪክም ፊት ተጠያቂ መሆናቸውን አውቀው ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ አሳስበዋል።

በሀገሪቱ እየታየ ያለውን ለውጥ በመተለከተም ፓርቲዎቹ በመግለጫቸው፥ “ሀገሪቱ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በለውጥ ሂደት ውስጥ መሆኗ ይታወቃል፤ የመንግስት ስልጣንም ለውጡን በሚፈልጉና ከስርዓቱ ከተገኙ ሀይሎች እጅ እንዳለ እንገነዘባለን” ብለዋል።

እነዚህ ሀይሎች በዚህ የሽግግር ወቅት ዘላቂ ለውጥ እንዲመጣ ሁኔታዎችን ያመቻቻሉ ብለን እናምናለን ያሉት ፓርቲዎቹ፥ ይህንን ለውጥ በማጠናከር ወደ ፊት እንዲራመድ በማድረግ የድርሻቸውን እንደሚወጡም አረጋግጠዋል።

ሆኖም ግን በዴሞክራሲያዊ መንገድ በምርጫ ተወዳድሮ ስልጣን እንዲያዝ ለማድረግ እየተሰራ ባለበት ወቅት አንዳንድ አካላት በአቋራጭ ስልጣን ለመያዝ እየተሯሯጡ ነው፤ እንዲህ አይነቱ ተግባር ሀገሪቱን ወደ ቀውስ ሊያስገባት ይችላል ብለዋል።

በመሆኑም አሁን ያሉ ተቋማት በህገ መንግሥቱ መሰረት በትክክል እንዲሰሩ ተደርጎ በነጻ፣ ተአማኒና በቂ ፉክክር በተደረገበት ህዝባዊ ምርጫ ወደ ዴሞክራሲ የሚደረገውን ሽግግር ብቻ የምንደግፍ መሆኑን እንገልጻለን ሲሉም አስታውቀዋል።

የፌደራል ስርዓቱን በተመለከተም፥ የብሄር ብሄረሰቦችን ጥያቄ ለመመለስ ሲባል በብሄር ላይ የተመሰረተ የፌደራል ስርዓት መዘርጋቱ ይታወሳል ያሉት የፖለቲካ ፓርቲዎቹ፤ ሆኖም ግን ለፌደራሊዝም ሥርዓት ደንታ የሌላቸው ኃይሎች ሥርዓቱ የችግሩ መንስኤ እንደሆነ አድርገው ለማቅረብ እየሞከሩ መሆኑን በመግለጫቸው አንስተዋል።

የኦሮሞ የፖለቲካ ድርጅቶች ከህገ መንግስት አግባብ ውጪ የፌደራሊዝም ስርዓቱን ለማፍረስ የሚደረገውን ሙከራ እንደማይቀበሉትና በህልውናቸው ላይ የተቃጣ አደጋ አድርገው እንደሚመለከቱትም በመግለጫቸው አመላክተዋል ሲል የዘገበው ኤፍቢሲ ነው።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy