Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

በዜጎች ደም የሚረማመደው ማነው?

0 1,558

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

በዜጎች ደም የሚረማመደው ማነው?

                                                    እምአዕላፍ ህሩይ

‘ህዝቡ በሰላም ወጥቶ እንዲገባና ህይወቱን በሰላማዊ መንገድ መምራት ይችል ዘንድ፤ ህጋዊ ስልጣንና ኃላፊነት የተሰጠው አካል ይህ ሁሉ ነገር ሲፈፀም ምን እየሰራ ነበር?’ የሚሉ ቅን አሳቢ ወገኖች ተበራክተዋል።…እውነትም፤ ማን ነው በዜጎች ደም እጁን እየተለቃለቀ ያለው?፣ የትኛውስ ወገን ነው፤ እንደ ጲላጦስ  

‘ከደሙ ንፁህ ነኝ’ ብሎ እጁን በንፁህ ውሃ ሊታጠብ የሚችለው?…

 

በአዲስ አበባ የወሰን አካባቢዎች የተፈፀመው ዘግናኝ ድርጊት ልብ ይሰብራል። ዜጎች በቡራዩና በአካባቢው በተደራጁ ዘራፊዎችና ወሮበሎች አማካኝነት ተገድለዋል፣ ተዘርፈዋል፣ ሴት እህቶቻችን ተደፍረዋል፣ ከኖሩበት አካባቢም ተፈናቅለዋል። በእውነቱ ድርጊቱ “ወዴት እየሄድን ነው?” የሚያስብል ነው። የአስተሳሰባችን ልኬታና የዝቅጠታችን መጠን እስከየት ድረስ እንደወረደ የተፈፀመው አሳፋሪ፣ ከኢትዮጵያዊ ባህልና ጨዋነት ያፈነገጠው ዘግናኝ ተግባር አፍ አውጥቶ ይናገራል። በእጅጉ ያሳዝናል።

ይህ ዘግናኝና አሳፋሪ ድርጊት፤ ለዘመናት ያካበትናቸው ኢትዮጵያ እሴቶቻችንን ምን ዓይነት ጅብ በላቸው ያስብላል። በለውጡ የመጣውን የዶክተር አብይ አህመድን ፍቅርን፣ ይቅርታንና መደመርን አላዳመጥንምን?፣ በሚሌኒየም አዳራሽ በ2011 ዓ.ም ዋዜማ ላይ የገባነውን ‘በፍቅር እንደመር፤ በይቅርታ እንሻገር’ ብለን የተግባባነውን ቃልስ እንደምን ዘነጋነው?፣ ኧረ ለመሆኑ ሰናይ ምግባራችንን የበላው ቡዳ ምን ዓይነት ነው?…ወዘተርፈ ጥያቄዎችን ያጭራል—በቡራዩና አካባቢው የተካሄደው ልብ ሰባሪ ድርጊት።

ዛሬ ‘ህዝቡ በሰላም ወጥቶ እንዲገባና ህይወቱን በሰላማዊ መንገድ መምራት ይችል ዘንድ፤ ህጋዊ ስልጣንና ኃላፊነት የተሰጠው አካል ይህ ሁሉ ነገር ሲፈፀም ምን እየሰራ ነበር?’ የሚሉ ቅን አሳቢ ወገኖች ተበራክተዋል። እነዚህ ወገኖች ‘ለመሆኑ በዜጎች ደም የሚረማመደው ማነው?’ ሲሉም ይጠይቃሉ። እውነትም፤ ማን ነው በዜጎች ደም እጁን እየተለቃለቀ ያለው?፣ የትኛውስ ወገን ነው እንደ ጲላጦስ ‘ከደሙ ንፁህ ነኝ’ ብሎ እጁን በንፁህ ውሃ ሊታጠብ የሚችለው?…ርግጥ መልስ የሚያስፈልገው ጥያቄ ነው። ግና ለምላሹ ‘የጦስ ዶሮ ፍለጋ’ መዞር አያስፈልግም—እውነተኛ ምላሽን መስጠት እንጂ። ይህን መመለስ ያለበት አቅሙም ይሁን ብቃቱ ያለው መንግስት ብቻ ነው። የሌላ ወገን የ‘እንዲህ ሊሆን ይችላል’ ደፈናዊ መላ ምት ምላሽ በስሜት የታጨቀ ጉንጭ አልፋ ክርክር ከመሆን አይዘልም። ‘እንዲህ ዓይነቱ ነገር እንዳይፈፀም ወደፊት ምን መደረግ ይኖርበታል?’ ብሎም በዘለቄታዊ ጉዳይ ላይ ፊት ለፊት በግልፅነት መነጋገር ተገቢ ነው ብዬ አምናለሁ። ይህን መከወን ያለበት መንግስት ነው።

አንዳንድ የማህበራዊ ድረ ገፅ ተቅበዝባዥ ወገኖች ያልተቀደደውን ሲሰፉ፣ የተሰፋውን ሲቀዱ፣ የተፈጠረውን ችግር ሲያባብሱ፣ ያልተፈጠረውን ሲጨምሩ እየተመለከትናቸው ነው። በስሜት ፈረስ ላይ ቁጭ ብለው ካራ እየሳሉ ሲጋልቡም እያየናቸው ነው። እንዲህ ዓይነቶቹ ህዝብን ለተጨማሪ ደም መፋሰስ ሊዳርጉ የሚችሉ ጉዳዩች ልጓም ሊበጅላቸው ይገባል። አሊያ ግን ማጣፊያው ነው የሚያጥረን። እናም መንግስት ኮምጨጭ፣ ጠንከር ብሎ የህግ የበላይነትን ለማስከበር መስራት ይኖርበታል። የሚያስፈልው ይኸው ነው—‘ኦሮማይ—በቃ!’ ማለት ይገባል።

አንድ ድርጊት ከተፈፀመ በኋላ ፍራሽ አንጥፎ መቀመጥ ተገቢ አይደለም። ፍራሽ አንጥፈን እንዳንቀመጥ አስቀድሞ መከላከል ያስፈልጋል። አስቀድሞ የመከላከል ስራው በሁሉም የፀጥታ አካላት አማካኝነት መፈፀም አለበት። በዕዝ ጠገግ (chain of command) አማካኝነት ከመንደር አንስቶ እስከ ሀገር ድረስ ለሰላምና ፀጥታ የሚያስፈልጉ መዋቅሮችን በማበጀት ችግሮችን አስቀድሞ መካከል እንደሚቻል እንኳንስ የተለያዩ መዋቅሮች ያሉት መንግስት ቀርቶ፤ እኔ ተራው ዜጋም የማውቀው ጉዳይ ነው።

የፀጥታ ኃይል እስከ ታች ድረስ ወርዶ ከህዝብ ጋር ያለውን ተገቢና ትክክለኛ ትስስር መፈተሽ ይገባል። ምንም እንኳን በየትኛውም አካባቢ የሰላም ባለቤት ህዝብ ቢሆንም፤ የፀጥታው ኃይል ከህዝቡ ጋር በየጊዜው እየተገናኘ ማወያየትና በጉዳዩ ዙሪያ ማንቀሳቀስ ይኖርበታል። እዚህ ጋ ያለውን ልል ወይም ስስ ቦታ በተገቢው መንገድ መፈተሽ ይገባል። የአቅም ውስንነት አሊያም ምንቸረገኝነት ወይም ቸልተኝነት ካለም ጠለቅ ብሎ ማየት ተገቢነቱ አጠያያቂ አይሆንምመፈተሽና መፍትሔ ማበጀት ያስፈልጋል።   

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ስትራቴጂካዊ መሪ ናቸው። ተግባራቸው ሀገሪቱ በተፈጠረው የለውጥ ሂደት ውስጥ እንዴት መጓዝ እንዳለባት የስትራቴጂ አመራር መስጠት ነው። ታች ድረስ ወርደው ታክቲካል ነገሮችን በየመንደሩ እየዞሩ ሊሰሩ አይችሉም። አይጠበቅምም። ለተፈፀመው ጥፋት ስራን ቆጥሮ ተረክቦ ቆጥሮ የሚያስረክብ ተግባሪ አካል አለ። ይህ ስራ ታች ያለው የአስፈፃሚው አካል ነው። ሌላ የማንም አይደለም። የህዝቡን የየዕለት ውሎና አዳር በተገቢው ሁኔታ ሳይዘናጉ የማረጋገጥ ተግባርና ኃላፊነት ታች ያለው የአስፈጻሚው አካል ነው። በተለይም የፀጥታው አካል። እናም ጣትን በስሜታዊነት ስራው ወዳልሆነ ሰው መጠቆም ትርፉ ትዝብት ብቻ ነው የሚሆነው።

ያም ሆኖ አሁንም እዚያ ቦታ ያለውን አሰራር በማያዳግም መልኩ ፈትሾ እልባት መስጠት ያስፈልጋል። የግለሰቦች፣ የኃላፊዎችና የተቋማት የማስፈፀም አቅም ሁኔታ በማያዳግም መልኩ ሊፈተሽ ይገባል። ይህን ማድረግ ካልተቻለ፤ የሰላም ዋስትናችን አደጋ ላይ ከመውደቁ ባሻገር፣ እንደ ሀገር የመቀጠላችን ጉዳይ ጥያቄ ውስጥ መግባቱ የሚቀር አይመስለኝም።

በዜጎች ደም የሚረማመደው ማነው? የሚለውን ጥያቄም ከተደጋጁት ዘራፊዎችና ወሮበሎች አኳያ ምላሽ መስጠት ለነገ የሚተው ተግባር አይደለም። ይህን ፅሑፍ እያሰናዳሁ እያለ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ፖሊስ ኮሚሽን በቡራዮና አካባቢው የሰው ህይወት በማጥፋትና ንብረት በማውደም ተጠርጥረው የተያዙ ግለሰቦች ቁጥር 200 መድረሱን አስታውቋል። ይህ ተጠርጣሪዎችን ይዞ ህግ ፊት የማቅረብ ስራ ሊመሰገን የሚገባው ነው። የንፁሃን ደም ፈስሶ መቅረት ስለሌለበት የተደራጁ ቦዘኔዎች ህዝብን እየገደሉ፣ ንብረት እየዘረፉና ሴት እህቶቻችንን እየደፈሩ መቀጠል የለባቸውም። ተግባራቸው በእንጭጩ ሊቀጭ ይገባል።

ዜጎች ወደ አላስፈላጊ ድምዳሜ እንዳይሄዱ መጠንቀቅ ያስፈልጋል። ለዚህም ዘራፊዎቹና ወሮበሎቹ እነማን ናቸው?፣ ለእንዲህ ዓይነቱ እንጥፍጣፊ ኢትዮጵያዊ ጨዋነት ለጎደለው አሳፋሪ ተግባር የተነሳሱት በራሳቸው ነው ወይስ በሌላ አካል አቀናባሪነት?፣ ህብረተሰቡስ መገለጫው ካልሆነው ከዚህ አሳዛኝ ድርጊት ምን ሊማር ይችላል?…ወዘተ የሚሉ ጥያቄዎችን ግልፅነት በሰፈነበት ሁኔታ የመመለስ ስራ አሁንም ጉዳዩን በያዘው አካል ትከሻ ላይ የወደቀ ነው። “የቄሳርን ለቄሳር” እንዲል መፅሐፉ፤ የዚህ ድርጊት መነሻ፣ የፈፃሚዎች ሚና እና መድረሻው ጥርት ባለ ሁኔታ ተገልፆ ህዝቡ እንዲማርበትና ዳግም እንዳይከሰቱ የራሱን አቋም እንዲይዝ ማድረግ ያስፈልጋል።   

ትክክለኛው መረጃና ማስረጃ ባይኖረኝም፤ በየማህበራዊ ሚዲያው እዚህ ሀገር ውስጥ በአንዳንድ አካባቢዎች ድብቅ ሴራ እየተከናወነ መሆኑ እየተነገረ ነው። ሴራው የታቀደ፣ ሆን ተብሎ የሚከናወን እንዲሁም የራሱ ግብና ዓላማ ያለው ይመስላል። ህዝብን እርስ በርስ የማስተላለቅ፣ የሃይማኖት ግጭት የመፍጠር፣ በማህበራዊ ሚዲያዎች ችግሮችን ባልተፈጠሩበት መልኩ ጣራ እስኪነኩ ድረስ የማጦዝ…ወዘተ ድርጊቶች የሴራው ተጠቃሽ አካላት ናቸው። ስለሆነም ሴራውን ህዝቡ ነቅቶ እንዲከታተልና በለውጡ የተገኘው የሀገራችን አንፃራዊ ሰላም እንዲቀጥል ዋነኛው ጉዳይ፤ “በዜጎች ደም የሚራመደው ማነው?” ለሚለው ጥያቄ በቁጥጥር ስር ከዋሉት ተጠርጣሪዎችና ከአስፈፃሚ አካላት ተግባሮች በመነሳት ፈጣንና ተገቢ የሆነ ምላሽ ለህዝቡ መስጠት ነው። ምላሹን በተገቢው ሁኔታ የማስረዳት ኃላፊነት (Proof of Burden) የወደቀው ደግሞ በአስፈፃሚው አካል ላይ ነው። ሰላም ለሀገራችን፤ ሰላም ለህዝባችን!!

 

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy