Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ብዙ ያልተነገረለት የገቢ ምንጭ  

0 498

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ብዙ ያልተነገረለት የገቢ ምንጭ  

                                                         ወንድይራድ ኃብተየስ

ኢትዮጵያ የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂን በመከተል ረገድ ቀዳሚ ሥፍራን ይዛ ትገኛለች። አረንጓዴ ኢኮኖሚ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ፋይዳ ከብክለት ነፃ የሆነ ከባቢን ለመፍጠር ያለመ ነው። ከዚህ ጋር በኢትዮጵያ በየጊዜው የሚከሰተውን የድርቅ አደጋ በዘላቂነት ለመቋቋም ያለው ጠቀሜታም እንዲሁ በቀላሉ የሚታይ አይደለም።  

የኢትዮጵያ መንግሥት በተፈጥሮ የአየር ንብረት ሣቢያ በአገሪቱ የሚከሰተውን የድርቅ አደጋ ለመከላከልና በህይወትም ላይ ምንም ዓይነት ጉዳት እንዳይደርስ ባለፉት  ዓመታት ቀላል የማይባል ጥረት ሲከውን ቆይቷል። የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂን በመከተልም ድርቅን በዘላቂነት ለመከላከል አገራዊ፣ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ግዴታውን በመወጣት ላይ ይገኛል። በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን የዕቅድ ትግበራ ዘመንም ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት ሁለንተናዊ ተግባራት እየተፈፀመ ይገኛል። በዕቅድ ይዞም የሚከውናቸው ሥራዎች ከፍተኛ ነው። ለመሆኑ የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ጠቀሜታ ምንድነው። ጥቂት ነጥቦችን እንጠቃቅስ።

ለአየር ንብረት ለውጥ ችግር በዋና ምክንያትነት የሚጠቀሱት፣ ወደ ከባቢ አየር የሚለቀቁ የበካይ ጋዞች ልቀት መጨመርና የደን ሀብት እየተመናመነ መምጣት ነው። በዚህም  የዘርፉ ምሁራን ይስማማሉ፡፡ በዚህ ምክንያት የሚከሰቱ ችግሮችን ለመፍታት የበካይ ጋዝ ልቀትን መቀነስና የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂን መከተል አማራጭ የለውም። እንዲሁም የተፈጥሮ ሀብት እንክብካቤን ማጎልበትና በደን ልማት ላይ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት ሌላው መፍትሄ ነው። እነዚህም ዓለም የተስማማባቸው እውነታዎች ናቸው፡፡ በተለይም እንደ ኢትዮጵያ ላለና በግብርና ምርታማነት ላይ መሠረቱን ለጣለ ኢኮኖሚ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖው የላቀ ነው፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥትም እነዚህን ሁኔታዎች በመለየትና ችግሮቹንም ነቅሶ በማውጣት በርካታ ሥራዎች አከናውኗል፡፡ ለዚህ ተግባር ተስማሚ የሆነ፣ የሥራ ዕድልን የሚፈጥር፣ ምርትንና ምርታማነትን የሚያሳድግ የአካባቢ መራቆት ሂደትን የሚከላከል፣ የአካባቢውን ለልማት የሚውል ዕቃና አገልግሎት የማቅረብ እንዲሁም ቀጣይ አቅምን የሚያጎለብት፣ በጎ ተሞክሮን እና ቴክኖሎጂን በማሰስ ገቢራዊ ተደርጓል፡፡

በዚህ መሠረትም የአካባቢ አንክብካቤን መነሻ ያደረገ የዕፀዋትና የፍራፍሬ ልማት ቴክኖሎጂን ወደ ኢትዮጵያ በማስገባት ተግባራዊ ማድረግ ተችሏል፡፡ ቴክኖሎጂው ተራራማና ደጋማ በሆኑ አካባቢዎች በዓመታዊ ሰብሎች አመራረት ምክንያት የሚደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ የዕፀዋትና የፍራፍሬ ልማት እንዲሁም የአፈርና ውኃ ዕቀባ ሥራዎችን በማቀናጀት የሚያራምድ ነው፡፡

ይህ ተግባር የኅብረተሰቡን ገቢ በማሻሻል በተለይም ወጣቶችን አካባቢን ከሚጎዱ እንደ ደን ቆረጣ ካሉ የገቢ ማስገኛ መስኮች በማላቀቅ አማራጭ ወደሆኑ የገቢ ማስገኛ መስኮች እንዲዞሩ ረድቷል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በእርሻ ላይ የተመሠረተው ምጣኔ ሀብት ወደ ኢንዱስትሪ የሚደረገውን ሽግግር ያግዛል፡፡ ቴክኖሎጂው ከፍተኛ ዋጋ የሚያወጡ የሰብል፣ የዛፍ፣ የፍራፍሬና አትክልት ዝርያዎችን የእንስሳት ዕርባታና ድለባ፣ የንብ ማነብ ሥራዎችን አቀናጅቶ በማልማት የገቢ ምንጭንም ያሳድጋል።  

ክንዋኔው በምጣኔ ሀብት ላይ ከሚያደርሰው አዎንታዊ ተፅዕኖ ባሻገር በተፈጥሮ ሀብት ላይ የሚያደርሰውን ጫና በመቀነስ ከፍተኛ ሚናን ይጫወታል፡፡ ፊዚካላዊና ሥነ ህይወታዊ የአካባቢ ሥራዎችን በመተግበርም የተጎዱ አካባቢዎች መልሰው እንዲያገግም በማድረግ ረገድ የአፈር መሸርሸርን በመከላከል የአፈር ለምነትን ለመጨመር እገዛ ያደርጋል።  

ከዚህ ጎን ለጎን ቴክኖሎጂው የዕፀዋት እና እንስሳት ዓይነቶች እንዲበራከቱ አድርጓል፡፡ አካባቢውም በተለያዩ ዕፀዋቶች ሲሸፈን የአካባቢው ውበት ስለሚያምር ለኅብረተሰቡ የመዝናኛ ቦታን ስለሚያበረክት ንፁህ ከባቢን ለመፍጠር የሚደረገውን ርብርብ ያግዛል።  የአካባቢ ጥበቃን መሠረት አድርገው እየተሰራባቸው ካሉ ቴክኖሎጂዎች መካከል የተጎዱ መሬቶችን ከእንስሳትና ከሰው ንክኪ ነፃ በማድረግ እንዲያገግሙ የማድረግ ቴክኖሎጂ ዋነኛው ነው፡፡ ቴክኖሎጂው በዕፀዋት ሽፋን መሳሳትና በአፈር ለምነት መቀነስ ሣቢያ የተጎዱና ምርታማነታቸው የተቋረጡ መሬቶች መልሰው እንዲያገግሙ ያደርጋል። በዚህ ረገድ የበኩሉን አስተዋጽኦም ያበረክታል፡፡

ቴክኖሎጂው የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ እንዲያገግሙ ለማድረግ በየአካባቢው መልክዓ ምድር ሊተገበር ይችላል። ለአካባቢው አየር ፀባይ ተስማሚ የዕፀዋት ዝርያ በመምረጥ ተስማሚ የእርከን ዓይነቶችን መለየት እና የገቢ ምንጭ የሚያስገኙ ተግባራት ተቀናጅተው የሚሰሩበት ሁኔታ በማጤን ኅብረተሰቡ የሚጠቀምበትን መንገድ ለማሳየት ዘርፈ ብዙ ሥራዎች ተከናውነዋል። ኅብረተሰቡም የተጎዱ ቦታዎች መልሰው እንዲያገግሙ የማድረግና የማልማት ብሎም እውቀትና ክህሎቱ እንዲዳብር ያግዘዋል፡፡ ኅብረተሰቡ ከአካባቢው እንዳይሰደድ  ያደርጋል። ከዚህም ጋር የጓሮ አትክልቶችንና ፍራፍሬዎችን አልምቶ ራስንና ቤተሰብን ለመመገብ ብሎም ጤናው እንዲሻሻል በማድረግ ረገድ መንግሥት አስቀድሞ በሽታን ለመከላከል ለያዘው ዕቅድ የራሱን ድርሻ ይጫወታል፡፡

በዚህም ምክንያት በየአካባቢው ጠፍተው የነበሩ የዕፀዋትና የእንስሳት ዝርያዎች እየተመለሱ ነው። ቴክኖሎጂው ለአካባቢ ጥበቃ ከሚያበረክተው አስተዋዕኦ ባሻገር ከግብዓት አቅራቢዎች ጋር የአቅርቦት ትስስር በመፍጠር በማኅብረሰቡ ዘንድ ተቀባይነት እንዲኖረው አግዟል፡፡ ምጣኔ ሀብታዊ ጠቀሜታውም አስተማማኝ ነው። ለቴክኖሎጂ ዘላቂነትም ከፍተኛ ሚና ይጫወታል።  

እዚህ ላይ የተጎዱ መሬቶች መልሰው እንዲያገግሙ የተለያዩ አገር በቀል ዛፎችን መትከል ዋነኛው አማራጭ አድርጎ መውሰድ ይቻላል። ለዚህም በርካታ የችግኝ ማፍያ ጣቢያዎችን በብዛት መጠቀም ተገቢ ይሆናል።

ከዚህ ጎን ለጎን በዘርፉ ለተሰማሩ ባለሃብቶች ከፍተኛ ዋጋ ያላቸውን የዛፍ፣ የፍራፍሬና የአትክልት ችግኞችን ለገበያ በማቅረብ የሥራ መስክ በመፍጠር በኩል የላቀ ሚና ይጫወታል። በአነስተኛ እና ጥቃቅን ኢንተርፕራይዞች ለተደራጁ ግለሰቦች የሰብል ፍርፍሬና፣ አትክልት የዛፍ ችግኞችን አቀናጅቶ በማምረት የገቢ ምንጭን አሳድጓል።  እነዚህ ጥቅል የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂ ምጣኔ ሀብታዊ ጠቀሜታዎች ለኢትዮጵያ ብሎም ለአፍሪካ እንዲሁም ለዓለማችን ወሣኝ ጉዳዮች ናቸው። እንዲህም ሆኖ ግን ስለአረንጓዴ ልማት ብዙም አልተነገረለትም። አሁን የምንገኝበት ጊዜ ወቅቱ ክረምት እንደ መሆኑ መጠን ዜጎች ችግኞችን በግልና በቡድን በመትከል፣ ከፀደቁም በኋላ በመንከባከብ ኃላፊነታቸውን አጠንክረው በብቃት ሊወጡ ይገባቸዋል።  

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy