Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

“እሽሩሩ…ሩሩ…ሩሩ”— እያረሩ?!

0 1,938

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

“እሽሩሩ…ሩሩ…ሩሩ”— እያረሩ?!

                                                   እምአዕላፍ ህሩይ

በአንድ በኩል፤ ለውጡን አምነው ከውጭ ወደ ሀገር ቤት የገቡ የፖለቲካ ፓርቲዎች የቡራዩውንና አካባቢውን ጉዳይ አስመልክተው፤ በጋራ በመሆን ድርጊቱን እንደሚያወግዙት መግለጫ ሲሰጡ ተመልክተናል። በሌላ በኩል ደግሞ፤ መንግስት በፖሊስ መዋቅሩ አማካኝነት ችግሩ እንዲፈጠር የሀገር ውስጥ ፖለቲከኞችና የውጭ ሃይሎች እጅ እንዳለበት ሲገልጥ አድምጠናል። በእውነቱ ይህ ምን ማለት ይሆን?…እርስ በርሱስ አይጣረስምን?…ኧረ ለመሆኑ እዚህ ሀገር ውስጥ ምን እየተካሄደ ነውስ አያስብልምን?…

 

ድምፃዊ ፍሬው ኃይሉን (ነፍሱን በአፀደ ገነት ያኑራትና) ከእነ አኮርዲዩኑ ሁሌም አስታውሰዋለሁ— አኮርዲዩኑን እየለጠጠና እያጠበበ፤ በደማቅ ፈገግታው ታጅቦ፤ መረዋ ድምፁን ከፍ…ዝቅ በማድረግ እያስረቀረቀ፤ “እሽሩሩ…እሽሩሩ…ማሚት እሽሩሩ…እኔስ ብዬሻለሁ ማሚት እሽሩሩ…ሩሩ..ሩሩ…” እያለ ሲያዜም።

ጋሼ ፍሬው፤ በተምሳሌታዊነት “እሽሩሩ…” እያለ የሚያዜምላት ደመ-ግቡ ምናባዊ ወጣት፤ በእዝነ ህሊናዬ ትታየኛለች። እርሷን ማባበል ምን ያህል እንዳንገበገበውም በገደምዳሜው የሚነግረን ነገርም፤ በአዕምሮዬ ጓዳ ውስጥ ሁሌም ሽው ይላል። ፍቅርን “እሽሩሩ…” እያለ ማስታመሙ፤ ለእርሱ ምን ያህል “አያዎ” (አይ-አዎ) ወይም ፈረንጆቹ እንደሚሉት “paradox” ዓይነት እንደሆነበት ይሰማኛል። የጋሼ ፍሬው “እሽሩሩ…ማሚት እሹሩሩ…” ቅላፄ፤ “ማሽላ እያረረ ይስቃል” እንዲል የሀገሬ ሰው፤ በውስጠ ወይራነት የሚያወሳው  የ“ማርም ሲበዛ ይመራል” ዓይነት ገለፃ፤ እያረረ በሚስቀውና ሲቆላ በሚፈካው ነጭ ማሽላ የሚመሰል ይመስለኛል።

የጋሼ የፍሬው ኃይሉ “እሽሩሩ…”ን ዘፈን በዚህ ፅሑፌ ላይ ያነሳሁት ያለ ምክንያት አይደለም—ትላንት በቡራዩና በሌሎች የሀገራችን አካባቢዎች ለተፈፀመውና ወደፊት ሊፈፀሙ ለታቀዱት ለውጡን የሚያደናቅፉ ተግባሮች የብሔራዊ ደህንነት ምክር ቤት ያወጣው መግለጫ፤ እንደ ጋሼ ፍሬው “ማርም ሲበዛ ይመራል” በማለቱ እንጂ።

ርግጥም መንግስት አጥፊዎችንና ስርዓት አልበኞችን “እሽሩሩ…ማሚት እሽሩሩ…” የሚልበት ወቅት ማክተም ይኖርበታል። ስርዓት አልበኞች እንዳሻቸው የሚፈነጩበት ሁኔታ አንድ ቦታ ላይ መቆም አለበት። ምክንያቱም በዶክተር አብይ አህመድ የሚመራው የኢፌዴሪ መንግስት፤ የበዛ ትዕግስትን ተከትሏል በሚሉ ቅን አሳቢ ወገኖች ዘንድ፤ ከአቅምና ከብቃት ጋር ለተያያዙ ትችቶች እየተጋለጠ በመሆኑ ነው። ይህ ደግሞ፤ አቅምና ብቃት ያለውን፣ ከራሱም አልፎ የቀጣናውን ሰላም አስተማማኝ ለማድረግ በመትጋት አዲስ የሰላም አየር በመስራቅ አፍሪካ ውስጥ እንዲነፍስ በማድረግ ላይ የሚገኘውን የለውጥ አመራር ድካም ፍሬ አልባ አድርጎ የመሳል ጥረት ነው። መንግስት ውስጡ እያረረ ጋጠ- ወጦችን በማያዳግም ሁኔታ የጥፋት ተልዕኮአቸውን ካላከሰመና “እሽሩሩ…ማሚት እሽሩሩ…” ማለቱን ካልተወ፤ የተፈራውን ለውጡን የማደናቀፍ ተግባር በቁጥጥር ስር ማዋልና ህዝቡ ላለፉት አምስት ወራት ያገኘውን አንፃራዊ ሰላም ግለቱን ጠብቆ ማስኬድ አዳጋች ሊሆን አለመቻሉን በርግጠኝነት መናገር አይቻልም።

ርግጥም መንግስት ስርት አልበኞችን በታጋሽነት “እሽሩሩ….” ማለቱ ዋጋ እያስከፈለው ነው። ለዚህም የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ኮሙኒዩኬሽን ጉዳዩች ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ነገሪ ሌንጮ የሰጡትን መግለጫ በአስረጅነት መመልከት ይቻላል። ዶክተር ነገሪ፤ በቡራዩና አካባቢው የተከሰተውን ችግር በመፍጠር ህዝብን ለአደጋ በማጋለጥ የፖለቲካ ዓላማቸውን ከግብ ለማድረስ ከፍተኛ ገንዘብ በመመደብ ከአዲስ አበባ ጀምሮ የተንቀሳቀሱ አካላት መኖራቸውን ሲገልፁ አድምጫለሁ።

የዚህ ጥፋት ሃይል አካል የሆነ 99 አባላት ካለው ቡድን ውስጥ፤ ስድስት የጦር መሳሪያና ሁለት መኪና እንዲሁም የባንክ ደብተርና የቡራዩ ከተማ መሬት አስተዳደር ሃሰተኛ ማህተም ተገኝቷል። የሐሰት ገንዘብን ጨምሮ መጠኑ ከፍ ያለ ገንዘብ ተይዟል። በተያዙት ሰዎች የባንክ ሂሳብ ውስጥም ስምንት ሚሊየን ብር መገኘቱም እንዲሁ።

እንግዲህ ልብ እንበል! እነዚህ የጥፋት ሃይሎች ባንክ ድረስ ሄደውና ደብተር አውጥተው ይህን ያህል በሚሊዩን የሚቆጠር ብር ሲያስቀምጡ የታወቀ አንዳችም ነገር የለም። በሀገሪቱ ውስጥ ጤናማ የፋይናንስ ደህንነት ስርዓት እንዲኖር የሚሰራው ተቋምም በዚህ በኩል ያለው ነገር የለም። ገንዘቡ የማን ነው?፣ ከየት መጣ?፣ ለምን ዓላማ?…ወዘተ የሚሉ ጉዳዩችን የሚያነሳ አካል መኖሩም አልተነገረም። ምናልባትም ተጠርጣሪዎቹ በምርመራ ወቅት ያወጡት ምስጢር ሊሆን ይችላል። ብቻ በዚህ ዓይነት ምን ያህል ህገ ወጥ ገንዘብ ወደ ባንኮች መግባቱንና ለእኩይ ሴራ መዋሉን ወይም ሊውል መዘጋጀቱን የሚያውቀው አንድ ፈጣሪ ብቻ ነው ማለት ይቻላል። በእውነቱ ልልነትና ታጋሽነት ከዚህ በላይ ዋጋ እያስከፈለንም ያሰጋል።

በፖለቲካ ስራ ውስጥ ግራ ጉንጭህን የመታህን ሰው፤ የምትመታው ግራውን ብቻ ላይሆን ይችላል—እንደ ሁኔታው ቀኝ ጉንጩንም ልትደግምለት ትችላለህ። እንዲያውም አምባገነናዊ በሆኑ መንግስታት ውስጥ፤ ፖለቲካው “ዓይን ያጠፋ ዓይኑ ይጥፋ” የሚለውንና ስልጣኔ ተሻረውን የሃሙራቢ ህግ (The law of Hammurabi) መልሰው ተግባራዊ ሲያደርጉ እንመለከታለን። ርግጥም የመፅሐፍ ቅዱሱ “ግራ ጉንጭህን ሲመታህ ቀኝህን አዙርለት” የእምነት አስተምህሮት፤ ፖለቲካ ውስጥ ሰሚ ጆሮ የለውም። ርግጥ ፅድቅ የሚያስገኘውን ሰማያዊውን መንግስትና ምድራዊውን ፖለቲካዊ ስልጣን ማነፃፀር ተገቢ አይደለም። ያም ሆኖ ታጋሽነት፣ ይቅር ባይነትና ሁሉንም ነገር በፍቅር ዓይን መመለከቱ ተገቢና ትክክለኛ ቢሆንም፤ እንደ ዴሞክራሲያዊ ሀገር ፖለቲካውን በሰለጠነና የህዝብን መብቶች ባከበረ ሁኔታ የህግ የበላይነትን ማስፈን ለነገ የሚተው ተግባር መሆን የለበትም ብዬ አምናለሁ።

ርግጥ “obsaatuu damma nyaata” (የታገሰ ማር ይበላል) እንዲል የገዳ ስርዓትን ለዓለማችን ያወረሰው አቃፊው የኦሮሞ ህዝብ፤ ትዕግስት በስተመጨረሻው ፍሬው ጣፋጭ እንደሚሆን እገነዘባለሁ። በአንፃሩም ሁሉም ነገር ልክ እንዳለው አውቃለሁ። ማናቸውም ጉዳዩች ገደብና ልጓም ሊበጅላቸው ይገባል። በጋራ ተስማምቶ ለአንድ ሀገር ለመስራትም በግልፅ የሚታወቅና ከፍ ሲልም ኃላፊነትን የሚሰጥና ግዴታን የሚጥል የሆነ መኖር ያለበት ይመስለኛል።

በአንድ በኩል፤ ለውጡን አምነው ከውጭ ወደ ሀገር ቤት የገቡ የፖለቲካ ፓርቲዎች የቡራዩውንና አካባቢውን ጉዳይ አስመልክተው፤ በጋራ በመሆን ተግባሩን እንደሚያወግዙት መግለጫ ሲሰጡ ተመልክተናል። በሌላ በኩል ደግሞ፤ መንግስት በፖሊስ መዋቅሩ አማካኝነት ችግሩ እንዲፈጠር የሀገር ውስጥ ፖለቲከኞችና የውጭ ሃይሎች እጅ እንዳለበት ሲገልጥ አድምጠናል። በእውነቱ ይህ ምን ማለት ይሆን?…እርስ በርሱስ አይጣረስምን?…ኧረ ለመሆኑ እዚህ ሀገር ውስጥ ምን እየተካሄደ ነውስ አያስብልምን?…ርግጥም የጠራ መረጃ ለህዝብ መቅረብ ያለበት ይመስለኛል። ግልፅነትና ተጠያቂነት የሚያመላክት መረጃና ማስረጃ እስካልቀረበ እንዲሁም የህግ ልዕልና መጠበቁን የሚያረጋግጥ ርምጃ እስካልተወሰደ ድረስ ብዥታ መፈጠሩ አይቀሬ ነው። ብዥታው ነገም ይቀጥላል። በእኔ እምነት፤ ብዥታው የተፈጠረው “እሽሩሩ…” ስለበዛ ነው። እናም ብዥታውን ገላልጦ ፀሐይ እንዲሞቀው ማድረግ በመንግስት ጫንቃ ላይ የወደቀ ተግባር መሆኑ መዘንጋት የለበትም።

በወርሃ ጥቅምት 1994 ዓ.ም በአዋጅ ቁጥር 257/1994 “የኢትዮጵያ ብሔራዊ ደህንነት ምክር ቤት” በሚል ስያሜ የተቋቋመው ምክር ቤት፤ በትናንትናው ዕለት ካወጣው መግለጫ መረዳት የሚቻለው፤ ለውጥ አደናቃፊዎቹ በሶማሌ ክልልና በሌሎች አካባቢዎች የከሸፈባቸውን የጥፋት ዕቅድ በሌላ ሙከራ ለመቀጠል እንዲሁም በመስከረም መጨረሻ የሚካሄደውን የኢህአዴግ ጉባኤ ለማደናቀፍ በርካታ ጥረቶች እየተደረጉ መሆኑን ነው።

የመግለጫው ይህ ክፍል የሚያሳየው ነገር፤ መንግስት አንድ ድርጊት ከመፈፀሙ በፊት በቀ መረጃ ያለው መሆኑን ነው። የድርጊቱ ፈፃሚዎች እንደማን እንደሆኑ አሊያም ሊሆኑ እንደሚችሉ የተደራጀ መረጃ ያለው ለመሆኑ ግልፅ ነው። ታዲያ ሃቁ ይህ ከሆነ ዘንዳ፤ ለምንድነው የጥፋት ሃይሎችን አስቀድሞ አንዳች ነገር ከመከወናቸውና በህዝብ ህይወትና ንብረት ላይ አደጋ ከማድረሳቸው በፊት ባሉት ቅፅበታዊ ጊዜያት ውስጥ በቁጥጥር ስር የማይውሉት?…ምናልባት የጥፋት ሃይሎቹን ስረ መሰረት ለማወቅና ይበልጥ ምርመራ አድርጎ ዋነኛው አካል ላይ ለመድረስ ታስቦ ከሆነም፤ ‘የሚደርስ ጥፋትን አስቀድሞ ለመከላከል ምን ዓይነት ርምጃ ተወስዷል?’ የሚል ጥያቄን ማጫሩ አይቀርም። እኔ በበኩሌ እንደ ዜጋ አሁንም ለውጡን ወደ ሌላ አዲስ ምዕራፍ ሊያሸጋግር የሚችል አቅጣጫ የሚያስቀምጠው የኢህአዴግ ጉባኤን ለማደናቀፍ የሚደረገውን እኩይ ሴራ ከወዲሁ ቆቅ ሆኖ በመጠበቅ እንዲከሽፍ ማድረግ ያስፈልጋል እላለሁ። ርግጥ ለውጡ የህዝብ በመሆኑ በባለቤቱ የላቀ ሚና እንደሚከሽፈም ቅንጣት ያህል ጥርጥር የለኝም። ሆኖም ዶክተር አብይና መንግስታቸው አሁንም ከፊታቸው ብርቱ ስራ የሚጠብቃቸው ይመስለኛል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የሚመራው የብሔራዊ ደህንነት ምክር ቤት ያወጣው መግለጫ ኮስተር ያለ መሆኑና የመንግስትን ቁርጠኛ አቋም በማንፀባረቁ አብዛኛውን የሀገራችንን ህዝብ ያስደሰተ ይመስለኛል። አንጀት አርስም ነው። በተለይም “…ስርዓት አልበኝነትን ከዚህ በኋላ የምንታገስበት ልብ፣ የምንሸከምበት ትከሻ የለንም።…ወጣቱ አውቆም ይሁን ሳያውቅ በህገ-ወጥ ድርጊት ላይ የሚሳተፍ ወጣትና ማንኛውም የህብረተሰብ ክፍል ህጋዊ እርምጃ የሚወሰድበት መሆኑን አውቆ ከጥፋት ተግባሩ እንዲሰበሰብ መንግስት ያሳስባል።…” የሚለው የመግለጫው ክፍል፤ መንግስት በማወቅም ይሁን ባለማወቅ የሴረኞች መጠቀሚያ እየሆነና የኢትዮጵያ ህዝብ በትግሉ ያመጣውን ለውጥ የሚቀለብሱ ሃይሎች መሳሪያ እየሆነ ያለው ወጣት፤ እየተጫወተ ያለው ሀገርን በሚያቃጥል እሳት መሆኑን የሚያስገነዝበው ነው ብዬ አምናለሁ።

ዳሩ ግን እሳቱ “ጠባሳ”ን እንደሚያስከትል ማወቅ ያስፈልጋል። “የአበራሽን ጠባሳ ያየ በእሳት አይጫወትም” እንዲሉ አበው፤ የስርዓት አልበኝነትን ጎራ ተቀላቅሎ፣ እሳትን በእጅ ይዞ የገዛ ወገን ላይ ማቀጣጠል፤ በስተመጨረሻ እሳቱ ራስን የሚለበልብና ጠባሳውም የዘለዓለም ማህተም ሆኖ እንደሚቀር ማወቅ ብልህነት ነው። ለውጡ መቼም ቢሆን ሊደናቀፍ ስለማይችል ወጣቱ ከሴረኞች “የህልም እንጀራ” ቅዠት ራሱን ማግለል አለበት።

በመሆኑም ወጣቱ ለጊዜያዊ ጥቅም ብሎ “የእነ ለውጥ አይጥሜን” ክብሪት በመያዝ ህይወቱን የሚያመሳቅልና የማይሽር ጠባሳ የሚያወጣለትን እሳት ከማንደድ መቆጠብ ያለበት ይመስለኛል—ከእንግዲህ መንግስት ውስጡ እያረረ “እሹሩሩ…ማሚት እሽሩሩ…” የሚልበት ትዕግስቱ ተሟጦ ወደ ተግባራዊው ህግን የማስከበር ስራው በቁርጠኝነት ፊቱን እንዳዞረ ትናንት በመግለጫው ነግሮናልና።     

    

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy