Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

“እኛም እነርሱን፣ እነርሱም እኛን ይሉናል”

0 12,295

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

“የራስን ዜጋ በመግደልና በማፈናቀል ተራ የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት ሲባል፤ እዚህም…እዚያም በወረፋ የሚፈፀሙት የሴራ ጉንጎናዎች ወዴት ነው የሚያመሩት?፣ ንፁሃን ወገኖቻችንስ ባላወቁት፣ ባላዩትና ባልሰሙት ጉዳይ ‘የጦስ ዶሮ’ እንዲሆኑ የተፈረደባቸው ለምን ይሆን?፣ የትኛውስ ወገን ነው ‘ማነህ ባለ ሳምንት…?’ በሚል ስሌት እያሰለሰ ለሚፈጠረው የወገኖቻችን ስቃይና ሰቆቃ ተጠያቂ የሚሆነው?…”

አንድ በሰሜን ሰዎች ዘንድ የሚነገር ቆየት ያለ ተረት አለ። ተረቱ በቆለኛውና በደገኛው የህብረተሰብ ክፍል መካከል የሚነገር ነው። ነገሩ እንዲህ ነው።…አንድ የደጋ ሰው ቆላውን አልፎ የሚሄድበት ብርቱ ጉዳይ ነበረው። ግና ዘመዶቹ “የለም፣ ቆላውን አልፈህ መሄድ የለብህም። በዚያ ግድም ያሉት ቡዳዎች ይበሉሃል። አይምሬዎች ናቸው!” ሲሉ ያስጠነቅቁታል፤ ያከላክሉታል።

ደገኛው ሰው ግን፤ ጉዳዩ ጥብቅ ስለሆነ ‘ቡዳዎቹን’ ፈርቶ ሊቀር አልቻለም—የግድ ቆላውን አልፎ መሄድ ነበረበት። እናም ጓዙን ሸክፎ ለጉዞ ተሰናዳ። ጉዞውን ያደረገው ግን፤ በሀገሬው ልማድ መሰረት ‘የቡዳ መከላከያ ነው’ ተብሎ የሚታመንበትን መፋቂያ ይዞ ነበር። እናም በመፋቂያው ጥርሱን እያሟጨ በለሊት ገስግሶ ወደ ጉዳዩ ያመራል።…

መድረስ አይቀርምና ደገኛው ፀሐይ ስታዘቀዝቅ ቆለኞቹ መንደር ይደርሳል። ስለመሸም፤ ‘ቡዳዎቹ’ ሳያገኙት ቡዳ ያልሆኑት ቆለኛዎች ጋር ለማደር አስቦ አንዱን የአካባቢውን ገበሬ፤ “ጌታው የቡዳዎቹ መንደር ከወዴት ነው?” በማለት ይጠይቀዋል። መፋቂያውን እያሟጨና ጥርሱን ብልጭ እያደረገ።…ቆለኛውም ገበሬውን ከነአለባበሱ ትክ ብሎ ሲመለከተው ደገኛ መሆኑን በመገንዘቡ እንዲሁም የያዘውን መፋቂያ በማጤኑ ሳቢያ ፈገግ ብሎ ድምፁን በመሞረድ፤ “ጌታዬ እነርሱም እኛን ይሉናል፤ እኛም እነርሱን እንላቸዋለን” ሲል ምላሽ ሰጠው ይባላል። ይህ ተረት የሚያመላክተን ነገር ቢኖር፤ ቆለኞቹም ልክ እንደ ደገኞቹ “እነርሱም ቡዳ ናቸው” ብለው እደሚያስቡ ነው። በሌላ አገላለፅ፤ “ቡዳውን የሚያውቀው አንድ ፈጣሪ ብቻ ነው። እናንተስ ቡዳ ያለመሆናችሁ በምን ይታወቃል?” ተብሎም ሊተረጎም ይችላል።

አንዱ በሌላው ላይ ጣቱን በመቀሰር “እኛም እነርሱን፣ እነርሱም እኛን ይሉናል” የሚለው ተረክ፤ በሁሉም የሰው ልጆች ማህበራዊ መስተጋብር ውስጥ የሚስተዋል ክስተት ነው። በተለይም በፖለቲካው ውስጥ እየገነገነ መጥቷል። በሀገራችን የለውጥ ሂደት ውስጥ ይህን መሰሉ ክስተት እየተስተዋለ ይመስለኛል። ባለፉት ጊዜያት ተፋቅረውና ተዋደው እንዲሁም ተዋልደው ሲኖሩ በነበሩት የጌዴኦና የጉጂ ህዝቦች መካከል በተቆሰቆሰ ግጭት ከሁሉቱም ወገኖች በሚሊዮን የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ከቀያቸው ተፈናቀሉ። ምን ይህ ብቻ። በኦሮሚያና በሶማሌ አዋሳኝ ክልሎች አካባቢ ይኖሩ የነበሩ ዜጎቻችን ህይወታቸውን አጥተዋል፤ አካላቸው ጎድሏል፤ ለዘመናት ተቻችለው በአብሮነት ሲኖሩ ከነበሩበት ቀያቸውም ተፈናቅለዋል።

ከሳምንታት በፊት ደግሞ፤ በቡራዩና በአካባቢው ኢትዮጵያዊያን ወገኖቻችን ባላዩት፣ ባልሰሙትና በማያውቁት ዳፋ ህይወታቸው አለፈ፤ ንብረታቸው ወደመ፤ ከቀያቸው ተፈናቀሉ—ምነም እንኳን ህዝብና መንግስት ባደረጉት ርብርብ አብዛኛዎቹ ወደ ቀያቸው ቢመለሱም። አሁን ደግሞ፤ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ውስጥ በተከሰተ ግጭት ንፁህ ኢትዮጵያዊያን መሞታቸውን እንዲሁም ከ13 ሺህ በላይ ዜጎች መፈናቀላቸውን ሰማን። ከመሰንበቻውም፤ አራት የከማሺ ዞን አመራሮች የተፈናቀሉትን ዜጎች ወደ ቦታቸው መመለስ የሚቻልበትን ጉዳይ ከኦሮሚያ አቻዎቻቸው ጋር ተነጋግረውና መግባባት ላይ ደርሰው ሲመለሱ፤ በኦነግ ስም በታጠቁ ሰራዊቶች በመንገድ ላይ መገደላቸውንና መኪናቸውም መቃጠሉን የኦዴፓ የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ አቶ አዲሱ አረጋ መናገራቸውን አድምጠናል። በዚህም ሳቢያ ሁለት ዜጎች መሞታቸውንና ሌሎች ሁለት ወገኖች መቁሰላቸውን እንዲሁም በዚህም ሳቢያ በርካታ የኦሮሞ ተወላጆች ከጉሙዝ አካባቢ ሸሽተው ወደ ወለጋ መሰደዳቸውን ሰምተናል።

ርግጥ ሀገሩን እንደሚወድና ለህዝቡ እንደሚቆረቆር ዜጋ ‘ለእነዚህ ሁሉ ችግሮች ተጠያቂው ማነው?’ ብለን ልናጠይቅ ይገባል። ተጠያቂውም በማያሻማ ሁኔታ ለህዝቡ መነገር አለበት። በመንግስት በኩል የሚሰሩት ስራዎች እንዲሁም ነገሮችን በሰከነ ሁኔታ የመመልከት በሳል አካሄድ የሚገባኝ ቢሆንም ቅሉ፤ በየጊዜው የንፁህ ወገኖቻችን ህይወት እየተቀጠፈ፣ አካላቸው እየጎደለ፣ ንብረታቸው እየወደመና እየተዘረፈ እንዲሁም በኢትዮጵያዊ እሴት ለዘመናት ተቻችለው ከኖሩበት መንደራቸው እየተፈናቀሉ መቀጠል ያለባቸው አይመስለኝም። ይህን መሰሉ ክስተት አንድ ቦታ ሊቆም ይገባል።

እናም በመንግስት በኩል እንዲህ ዓይነት ችግሮች በየቦታው በተከሰቱ ቁጥር “የለውጡ አደናቃፊዎች ናቸው” የሚለው ምላሽ በበኩሌ አጥጋቢ ሆኖ አልታየኝም። “የለውጡ አደናቃፊዎች” የሚባሉት አካላት የማይታዩና የማይዳሰሱ ሰይጣኖች አይደሉም። ወይም ከሌላ ፕላኔት የመጡ ፍጡራን አይደሉም። ተግባራቸው በትክከል እየተገለፀ በመሆኑም በትክክል የሚታወቁ የገሃዱ ዓለም እኩይ ነዋሪዎች ናቸው። ስለሆነም በትክክል ሊታወቁ ይገባል። አሁንም ቢሆን “አካፋን አካፋ” የማለት ባህል ከሌለን፤ ግልፅነትንና ተጠያቂነትን ማምጣት አይቻልም። ይህም የህግ የበላይነት እንዳይኖርና ችግሮች እየተንከባለሉ ወደ ሌላ ጥፋት እንዲሸጋገሩ የልብ ልብ ይሰጣቸዋል።

ከአንዳንድ ወገኖች ጋር በጉዳዩ ዙሪያ በግል ስናወጋ ልክ እንደ ተረቱ “እኛም እነርሱን፣ እነርሱም እኛን ይሉናል” የሚል ነገር እያደመጥን ነው። አንዱ በሌላው ላይ ማላከክ የለበትም። ሁሉም በየፊናው ለወገኖቻችን ሰላምና ደህንነት የበኩሉን ሊወጣ ይገባል። በሰላምና ደህንነት ዙሪያ የሚሰሩ ኃይሎች ችግሮች ከተፈጠሩ በኋላ ሳይሆን ከመፈጠራቸው በፊት ተገቢውን ግብረ መልስ መስጠት ይኖርባቸዋል። ይሀን ማድረግ ከቻሉ፤ እነማን በህዝብ ሰቆቃና ስቃይ እንደሚቆምሩ ለማወቅና አውቆም አስቀድሞ ለመከላከል የሚቻል ይመስለኛል።

ርግጥ ነገሩ ሁሉ ግራ የሚያጋባ መሆኑን አላጣሁትም። ነገሮች እንደ ሸማኔ ድር ከወዲያ ወዲህ እየተወረወሩ ነው። “እኛም እነርሱን፤ እነርሱም እኛን ይሉናል” እንዲሉት ዓይነት ይመስላል። ሀገራቸውንና ህዝባቸውን በሰላማዊ መንገድ ለመጥቀም ከውጭ ወደ ሀገር ውስጥ የገቡ የፖለቲካ ፓርቲዎች፤ የቡራዩው ችግር ሲፈጠር ተሰባስበው መግለጫ አውጥተዋል። ድርጊቱንም በፅኑ ኮንነዋል።

ታዲያ በጉዳዩ ላይ ስሙ ተደጋግሞ ሲነሳ የነበረው አርበኞች ግንቦት ሰባትም “የእኔ አባላት እንዲህ አያደርጉም” የሚል ምላሽ መስጠቱን እናስታውሳለን። ትንሽ ቆየት ብሎም፤ ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ የአርበኞች ግንቦት ሰባት ሁለት የሰልፍ አስተባባሪዎች በቁጥጥር ስር ውለው ጉዳያቸው ተጣርቶ መፈታታቸው ተነግሮናል። ከትናንት በስቲያም፤ የፌዴራል ዐቃቤ ህግ ሰኔ 16 ቀን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ለሀገራቸው በአጭር ጊዜ ውስጥ ላበረከቷቸው አስተዋፅኦዎች ምስጋና ለመቸር በተጠራው ሰልፍ ላይ፤ ቦምብ በማፈንዳት የተጠረጠሩ አምስት ግለሰቦች ክስ እንደመሰረተባቸው ተዘግቧል።

ከዐቃቤ ህግ ክስ መረዳት የተቻለው፤ አምስቱ ግለሰቦችና ፍንዳታውን ያስተባበረችው ቶለሺ ታምሩ የተባለች ግለሰብ፤ ቦንቡን ያፈነዱን ‘ዶክተር አብይን ለመግደልና ሀገሪቱን መምራት ያለበት ኦነግ ነው’ ከሚል አስተሳሰብ በመነሳት መሆኑም ተገልጿል። ኦነግም በቃል አቀባዩ አቶ ቶሌራ አዳባ አማካኝነት አምስቱን ግለሰቦችና የናይሮቢዋን ሴት እንደማያውቃቸው አስታውቋል። በሰሞነኛው የከማሺ ጉዳይ የኦዴፓ የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ አቶ አዲሱ አረጋ “…ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ የመጡ አመራሮች ወደ ከማሺ ዞን በመጓዝ ላይ እንዳሉ ቢላ በተባለ አካባቢ በኦነግ ስም የታጠቁ ሰራዊቶች ተሽከርካሪው ላይ ተኩስ ከፍተዋል…” ባሉት ጉዳይ ላይ ኦነግ የሰጠውን ምላሽ እኔ በበኩሌ አልሰማሁም።

ዳሩ ግን ምላሹ ምንም ይሁን ምን፤ ዋናው ነገር ‘እዚህ ሀገር ውስጥ ታጥቆ መንቀሳቀስ የሚገባው የትኛው ኃይል ነው?’ የሚለው ጥያቄ በሚገባ መመለስ ያለበት ይመስለኛል። እኔ እስከሚገባኝ ድረስና ሲገለፅም እንደሰማሁት፤ ከውጭ ወደ ሀገር ውሰጥ የገቡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሀገር ውስጥ በሰላማዊ መንገድ ለመታገል ነው የመጡት። በሰላማዊ ሁኔታ መታገል ማለት ደግሞ ትጥቅ ይዞ መንቀሳቀስን የሚያካትት አይመስለኝም። የትጥቅ ትግል ሲያካሂዱ የነበሩትም ትጥቃቸውን ፈትተው ነው ወደ ሀገር ውስጥ ለመግባት የተስማሙትም በዚሁ መልክ ይመስለኛል።

     ታዲያ የምንሰማው ነገር ምንድር ነው?…”እኛም እነርሱን፤ እነርሱም እኛን ይሉናል” ዓይነት አሮጌ ተረት እንደምን ወደ እውነታው ይወስደናል?…የራስን ዜጋ በመግደልና በማፈናቀል ተራ የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት ሲባል፤ እዚህም…እዚያም በወረፋ የሚፈፀሙት የሴራ ጉንጎናዎች ወዴት ነው የሚያመሩት?፣ ንፁሃን ወገኖቻችንስ ባላወቁት፣ ባላዩትና ባልሰሙት ጉዳይ ‘የጦስ ዶሮ’ እንዲሆኑ የተፈረደባቸው ለምን ይሆን?፣ የትኛውስ ወገን ነው ‘ማነህ ባለ ሳምንት…?’ በሚል ስሌት እያሰለሰ ለሚፈጠረው የወገኖቻችን ስቃይና ሰቆቃ ተጠያቂ የሚሆነው?…” ይህ ወገንስ ከመንግስት አቅምና ቁጥጥር ውጭ ነውን?….

 

አዎ! እነዚህ ጥያቄዎች መልስ ማግኘት አለባቸው። “በጥባጭ እያለ ማን ጥሩ ይጠጣል” እየተባለ ዝምታ መመረጥ የለበትም። የድርጊቱ ተዋንያኖች፤ ችግሮች በተፈጠሩ ቁጥር “የለውጥ አደናቃፊዎች ሴራ ነው” እየተባሉም ማንነታቸው ሳይለይና ሳይገለፅ መታለፍ አይኖርበትም። አይገባምም። እየሞተ፣ እየተሰቃየና እየተፈናቀለ ያለው የሰው ልጅ ነው። ወገናችን ነው። ዜጋችን ነው። ኢትዮጵያዊ ነው። እርሱ ሳይደላው እኛ እንድንኖር የሚያደርገን ለወገኑ የሚጨነቅ ህዝብ ነው። መንግስትም ቢሆን የሚተዳደረው ከእርሱ በሚሰበሰብ ግብር ነው። ይህ ህዝብ ‘በእኔነት’ የሚጠቀስ አይደለም—‘በእኛነት’ እንጂ።

የዚህ ህዝብ ስቃይና ሰቆቃ እንዲሁም መፈናቀል የሁላችንም ነው። “እኛም እነርሱን፤ እነርሱም እኛን ይሉናል” እንደሚባለው ተረት ከመጠቋቆም ይልቅ ለመፍትሔው ርብርብ ማድረግ ይኖርብናል። ዜጎች ሰለማቸውን በራሳቸው መጠበቅ አለባቸው። መንግስትም ለመፍትሔ የሚሆን ነገርን በማምጣት የመሪነት ሚናውን በሚገባ ይጫወት። የፀጥታ መዋቅሮቹን በሚገባ ይፈትሽ፣ በድህረ- ግጭት (Post Conflict) ብቻ ሳይሆን፤ ለቅድመ- ግጭት ተከላካይነት (Pre- Conflict Prevention) ቅድሚያ በመስጠትም መስራት ያለበት ይመስለኛል።

ወረፋ በሚመስል ሁኔታ የሚከሰቱት ግጭቶች በሀገራችን የገፅታ ግንባታ ስራ ላይ የራሳቸውን አሉታዊ ጥላ የሚያጠሉ በመሆናቸው እንዲሁም ጉዳዩ ብሔራዊ ፀጥታን የሚመለከት ስለሆነ፤ ችግር ፈጣሪዎቹ “የለውጡ አደናቃፊዎች” እየተባሉ በማይጨበጥ (Abstract) ስያሜ መታለፍ አይኖርባቸውም። እነዚህ አካላት በትክክል ታውቀው ህዝቡም የራሱን ጥንቃቄ እንዲያደርግ “የቄሳርን ለቄሳር፤ የእየሱስን ለእየሱስ” እንዲል መፅሐፉ፤ አጥፊዎች ከነተግባራቸው ተለይተው ፍጥነት በተሞላበት ሁኔታ ለህዝቡ በማሳወቅ ፊታችንን ወደ ላቀ የልማት አፈፃፀም ተግባር ማዞር አለብን እላለሁ። ታዲያ ይህን የምለው፤ የሀገራችን መድን መሆኑን ሁሌም የማምንበት “የቲም ለማ” አመራር ነገ ከግጭት ፅላሎታዊ ግርዶሽ አላቅቆን የሰላም ብርሃናዊ ፀዳልን እንደሚያላብሰን ስለምተማመን ነው። ሰናይ ጊዜ።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy