Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

እውን ማንነት ‘ጠባብ ጫማ’ ነውን?

“አንድ ጫማ ጠባብ ከሆነ፤ ሊጫማው የፈለገው ሰው በደምሳሳው ያሉት አማራጮች ሶስት ናቸው። አንዱ፤ ልክ የሚሆን ጫማ መግዛት ሲሆን፤ ሁለተኛው፤ እግርን ቆርጦ ከጫማው ጋር ማስተካከል ነው። ሶስተኛው ደግሞ፤ ያለው ቁጥር ይኸው ጠባብ ጫማ ብቻ ከሆነ፣ ጫማውን መተው ይሆናል። መቼም ሁለተኛውን አማራጭ…”

0 827

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

እውን ማንነት ‘ጠባብ ጫማ’ ነውን?

                                                     እምአዕላፍ ህሩይ

“አንድ ጫማ ጠባብ ከሆነ፤ ሊጫማው የፈለገው ሰው በደምሳሳው ያሉት አማራጮች ሶስት ናቸው። አንዱ፤ ልክ የሚሆን ጫማ መግዛት ሲሆን፤ ሁለተኛው፤ እግርን ቆርጦ ከጫማው ጋር ማስተካከል ነው። ሶስተኛው ደግሞ፤ ያለው ቁጥር ይኸው ጠባብ ጫማ ብቻ ከሆነ፣ ጫማውን መተው ይሆናል። መቼም ሁለተኛውን አማራጭ…”

 

በአንድ ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ “አንድነት ማለት አንድ ዓይነትነት አይደለም” ማለታቸውን አስታውሳለሁ። አባባሉ በአንድነት ውስጥ የተለያዩ ዓይነት ዘውጎች መኖራቸውን ያመላክታል። ተፈጥሮ ይህ እንዲሆን ፈቅዳለች። በአንድ ቦታ የሚገኝ ጋራ፣ ሸንተረር፣ ወንዝ፣ ቁልቁለት…ወዘተ. ከሌላው ጋር ተመሳሳይ ካልሆነ፣ አንድ ዓይነት ሊሆን የሚችል አይመስለኝም።

የሰው ልጅ ቀይ፣ ጥቁር፣ ቢጫና ሌላም ዓይነት ቀለም ያለው መሆኑ፤ የተፈጥሮ መገለጫ ነው። ሴትና ወንድ፣ ረጅምና አጭር፣ ወፍራምና ቀጭን እንዲሁም የፍላጎት ዝብርቅርቅነት የዚሁ የተፈጥሮ ጉራማይሌነት ማሳያ ነው። ሌላው ቀርቶ በአንድ ቤተሰብ ውስጥ የሚታዩት የስነ ባህሪም ይሁን የመልክ አሊያም የአካል ልዩነቶች የተፈጥሮ ዥንጉርጉርነት አመላካች ናቸው። አዎ! አንድነትን በአንድ ዓይነትነት መፈረጅ ተፈጥሮን በቅጡ አለማወቅ ይመስለኛል። እንዲያውም በተፈጥሮ ውስጥ ከአንድ ዓይነትነት ይልቅ አንድ ያለመሆን ጉዳይ ጎልቶ ይታያል የሚል ድምዳሜ ላይ መድረስ የሚቻል ይመስለኛል። እናም በእኔ ምልከታ ዶክተር አብይ “አንድነት አንድ አይነትነት አይደለም” በማለት የገለፁት እውነታ፣ የዚህ ሁሉ ተፈጥሯዊ እውነታ ገላጭ ነው።

ስለሆነም አንድ ያለመሆን ጉዳይ ወደ ማንነት ፅንሰ ሐሳብ ይወስደናል። ማንነት የሰው ልጅ በተፈጥሮው የታደለው የራሱ ሁለንተናዊ ስብዕና ነው። ከአካላዊ ቅርፅ ባሻገር፤ ባህሪው፣ አስተሳሰቡ፣ ድርጊቱና ሌሎች እርሱን ብቻ የሚገልፁ ጉዳዩች በማንነት ዘውጉ ውስጥ የሚታዩ ናቸው። እነዚህ የተለዩ ማንነቶች፤ በፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ስንክሳሮቹ ውስጥ ሊገለፁ ይችላሉ። ከዚህ ፅሑፍ ዓላማ አኳያ፣ ማንነትን ከፖለቲካዊ እሳቤው፣ በተለይም ሰሞኑን ማንነት ‘ጠባብ ጫማ’ ነው በማለት በአንድ የሀገራችን እውቅ አክቲቪስት ከተነገረው እውነታ አንፃር በአጭሩ ለመመልከት እሞክራለሁ።

የሀገራችን ሰው ፖለቲካዊ ማንነቱ አንድ ዓይነት ቢሆን ኖሮ፣ ዛሬ ሁሉም ህዝብ የአንድ ድርጅት አባል ሆኖ፣ የኢትዮጵያ ፖለቲካ በሩ ጠባብ ይሆን ነበር። ሆኖም ማንነቱ የተሰባጠረ፣ ፖለቲካዊ እምነቱ የተለያየና እሳቤውንም ዘርፈ ብዙ ነው። አሁን በምናየው ሁኔታ፤ ሀገሪቱን የሚያስተዳድረው ኢህዴግን፣ ዛሬ እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ህዝብ ከዳር እስከዳር በነቂስ ወጥቶ አቀባበል የተደረገለት የኦሮሞ ነፃነት ግንባርን (ኦነግን) እንዲሁም ቀደም ሲል በበርካታ ደጋፊዎቹ ወደ ሀገር ቤት ሲገባ አቀባበል የተደረገለትን አርበኞች ግንቦት ሰባትንና ሌሎች የተለያዩ ኢትዮጵያዊ የፖለቲካ ድርጅቶችን በየፊናው የሚደግፈው ህዝብ ለየቅል ነው። አንድ ዓይነት አስተሳሰብ ቢኖር ኖሮ፣ ሁሉም ሰው አንድን የፖለቲካ ድርጅት ይደግፍ ነበር። ሃቁ ግን ሰዎች የሚመቻቸውንና የሚፈልጉትን ነገር መገደፋቸው ባህሪያዊ መሆኑ ነው።

ማንነት የሁሉም ነገር መሰረት ነው። ማንነት የአንድነት መሰረት ነው። አንድ ሰው ማንነቱን ሳያከብር ወደ አንድነት መንገድ ሊያቀና አይችልም—በቅድሚያ በአንድነት ውስጥ ሆኖ ለመታየት ሰውዬው ራሱ ሊኖር ይገባልና። ትንሹ ነገር ከሌለ ትልቁ ነገር ሊኖር አይችልም። ትልቁ ነገር የትንሹ ጉዳይ ስብስብ ነው። ስለሆነም ለትንሹም ሆነ ለትልቁ ነገር መሳ ለመሳ የሆነ አክብሮትና እውቅና መስጠት ያስፈልጋል። አንድ ኦሮሞ፣ አንድ አማራ፣ አንድ ትግራይ፣ አንድ ጋምቤላ…ወዘተ. በማንነቱ ማግኘት የሚገባውን ነገር ማግኘት አለበት። የማንነቱ መገለጫዎች ሁሉ ከሌላው ጋር ሳይበላለጡና ሳያንሱ በእኩልነት ሚዛን ላይ ተሰፍረው መቀመጥ ይኖርባቸዋል። ይህ ሲሆንም አንድነቱን ማጠናከር ይቻላል።

በሌላ አገላለፅ፤ ማንነትንና አንድነትን ነጣጥሎ ማየት ይገባል ብዬ አላምንም። ሁለቱንም በየልኬታቸው እየሰፈሩ መመልከት አስፈላጊ ነው። ሁለቱም በየፊናቸው ሚዛናዊ እሳቤ ማግኘት ይኖርባቸዋል ብዬ አስባለሁ። ስለሆነም ማንነት ‘ጠባብ ጫማ’ ነው የሚለውን አስተሳሰብና የሃሳቡን ባለቤት ማክበር ተገቢ ቢሆንም፣ ይህን የትልቁ ኢትዮጵያዊ አንድነታችን ምስል መሰረት የሆነውን ማንነት በጠባብ ጫማነት መለካት ተገቢ ሆኖ አላገኘሁትም።

አንድ ጫማ ጠባብ ከሆነ፤ ሊጫማው የፈለገው ሰው በደምሳሳው ያሉት አማራጮች ሶስት ናቸው። አንዱ፤ ልክ የሚሆን ጫማ መግዛት ሲሆን፤ ሁለተኛው፤ እግርን ቆርጦ ከጫማው ጋር ማስተካከል ነው። ሶስተኛው ደግሞ፤ ያለው ቁጥር ይኸው ጠባብ ጫማ ብቻ ከሆነ፣ ጫማውን መተው ይሆናል። መቼም ሁለተኛውን አማራጭ የሚያስብ ሰው ጤነኛ ሊሆን አይችልም። እናም አማራጩ ሰውዬው በቁጥሩ ልክ የሆነ ጫማን ገዝቶ መጫማት ብቻ ይሆናል።

ይህን ሃቅ ‘ማንነት ጠባብ ጫማ ነው’ ከሚለው አስተሳሰብ አኳያ ስንመለከተው፤ እንዳልኩት አንድ ኦሮሞ፣ አንድ አማራ፣ አንድ ቤኒሻነጉል ወይም አንድ ተለይቶ የሚታወቅበት ማንነት ያለው ኢትዮጵያዊ፤ ‘ጠባብ ጫማ’ የተባለውን ማንነቱን ቆርጦ ሊጥለው አይችልም። ማንነቱ ‘ጠባብ ጫማ’ ሆኖበትም ያለ ተፈጥሮው ሌላ ማንነት ገዝቶ ሊያደርግ አይችልም። ተፈጥሯዊ ማንነቱ ለራሱ ሊጠበው ስለማይችል እርሱኑ ይዞ ይቀመጣል። አዎ! በእኔ እምነት፤ ያለው አማራጭ ‘ጠባብ ጫማ’ የተሰኘውን ማንነቱ ይዞ መኖር ነው። ከራሱ ጋር የሚስማማውን “ጫማ” (ማንነቱን) በመያዙም ከጠባቡ ጫማ ጭንቀት ይገላገላል። ለዚህም ነው —ማንነት ‘ጠባብ ጫማ’ ነው ብዬ የማላምነው። ምክንያቱም ‘በጠባብ ጫማ’ የተመሰለው ማንነቱ በገሃዱ ዓለም ፖለተካዊ ምልልስ ውስጥ ባሉት የግልና የቡድን መብቶች ውስጥ በእኩልነት መከበር ስላለበት ነው።

ባለፉት ጊዜያት ስለ ቡድን መብቶች ብዙ ተብሏል—አተገባበሩ “አራምባና ቆቦ” እንደሚባለው ሆነ እንጂ። ጊዜው የይቅርታ ስለሆነ እዚያ አሳዛኝ ትርክት ውስጥ መግባት አልፈልግም። ያም ሆኖ ባለፉት ዓመታት የግል መብቶች በተነፃፃሪነት አስታዋሽ አጥተው ደጅ ሲጠኑ ነበር። የመብት ያለህ እያሉ ሲጮሁ ነበር። ዳሩ ግን አሁን ባለው የለውጥ ሂደት ውስጥ ሁለቱም በእኩልነት መከበር ይኖርባቸዋል። እየተደረገ ያለውም ይኸው ነው። የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሀገር ቤት ገብተው በሰላማዊ መንገድ ሃሳባቸውን በነፃነት እንዲገልፁ ሁኔታዎች እየተመቻቸላቸው ያለውም ይህንኑ ዥንጉርጉርነታችንን በእኩልነት ለማስተናገድ ታስቦ ይመስለኛል። ኢትዮጵያ የአንድ ቡድን ወይም የጥቂቶች ሀገር አይደለችም። የበርካታ ህዝቦች መኖሪያ፣ የተለያዩ አስተሳሰቦችን ሊንፀባረቁባት የሚገባ የጋራችን ሃብታችን ናት። የአንድነታችንም መድመቂያ ናት። እናም ጉራማይሌ ፖለቲካዊ አስተሳሰብ (ዘውጌ ፖለቲከኛነት) ባለበት ሀገር ውስጥ፤ ማንነትን አሳንሶ መመልከት ከነባራዊ እውነታው ጋር መጋጨት ይመስለኛል።

ግለሰባዊ መብትን የማያከብር የትኛውም አካል የቡድን መብትን ሊያከብር አይችልም። የቡድን መብትን የማያከብርም ግለሰባዊ መብትን ለማክበር የሚሳነው ይመስለኛል። ማንነትንም ይሁን አንድነትን በሚዛናዊ መንገድ ካላየናቸው የመብቶች መሸራረፍ ብሎም እንዳለፈው ጊዜ ደብዛቸው የመጥፋት ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል።…እናም ማንነትን ማክበር ግለሰባዊ መብትን ማክበር ነው። ለግለሰባዊ መብቶች እውቅና የሚሰጥ ማንኛውም ግለሰብ ወይም ቡድን ለማንነት መብቶችም ተገቢውን የእኩልነት ስፍራ መስጠት ይኖርበታል ብዬ አምናለሁ። ይህን ማድረግ፤ የተፈጥሮን ዥንጉርጉርነት አምኖ መቀበል ጭምርም መሆኑም ሊዘነጋ አይገባም። አንድነትንና ኢትዮጵያዊነትን ይበልጥ ማጥበቅም ጭምር ነው።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy