Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

‘ኦ! የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ…!’

0 77,296

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

‘ኦ! የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ…!’

                                                     እምአዕላፍ ህሩይ

“…በጉባኤው ላይ የዶክተር አብይ አርአያነት በሁለት መንገድ ተገልጿል— አንድም፤ በተመድ ዋና ፀሐፊ እማኝነት፣ ሁለትም፤ ሀገራችንን ወክለው ጉባኤው ላይ በተገኙት በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ አማካኝነት። የመንግስታቱ ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ በንግግራቸው የአሜሪካውን ፕሬዚዳንት፤“…ዶናልድ ትራምፕ ቅድሚያ ለአሜሪካ ከማለት ይልቅ፤ ከኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የመደመርን ቀመር መማር ያለባቸው ይመስለኛል” በሚል የተገለፀ ነው።…”

ሰሞኑን በተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) 73ኛ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ሀገራት በመሪዎችና በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ተወክለው ተገኝተዋል፤ በአሜሪካዋ ኒውዩርክ ከተማ። ሀገራችንን ወክለው ኒውዩርክ የተገኙት የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ ናቸው። ምንም እንኳን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ሀገር ውስጥ ባላቸው ሌሎች ተደራራቢ ስራዎች ምክንያት በጉባኤው ላይ መገኘት ባይችሉም፤ ስማቸው ግን በጉባኤው አዳራሽ ውስጥ ከፍ…ከፍ ተደርጎ ሲጠራ ነበር—በአርአያነት እየተወሳ።

በጉባኤው ላይ የዶክተር አብይ አርአያነት በሁለት መንገድ ተገልጿል። አንድም፤ በተመድ ዋና ፀሐፊ እማኝነት፣ ሁለትም፤ ሀገራችንን ወክለው ጉባኤው ላይ በተገኙት በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ አማካኝነት። የመንግስታቱ ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ በንግግራቸው የአሜሪካውን ፕሬዚዳንት፤“…ዶናልድ ትራምፕ ቅድሚያ ለአሜሪካ ከማለት ይልቅ፤ ከኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የመደመርን ቀመር መማር ያለባቸው ይመስለኛል” በሚል የተገለፀ ነው። የዋና ፀሐፊው አባባል፤ የዶክተር አብይ “የመደመር ፍልስፍና” አቃፊና ሁሉንም አሸናፊ የሚያደርግ መንገድ መሆኑን ለመጠቆም ያለመ ይመስለኛል። ርግጥም አንድ ሀገር ‘እኔ ልቅደም’ ከማለት ‘ሁላችንም እንቅደም’ የሚል መሪ ሃሳብ ማንሳት የጋራ ተጠቃሚነትን፣ ፍትሐዊነትንና ርዕታዊነትን የሚያመጣ እንዲሁም ዓለምን ሊያግባባ የሚችል ቋንቋ ይመስለኛል። ታዲያ ከሚስተር ጉተሬዝ እይታ በመነሳት፤ “የመደመር ፍልስፍና” ልክ እንደ ጥበብ ዓለም አቀፍ ቋንቋ (Universal Language) መሆን የሚገባው ይመስለኛል።

ያም ሆኖ በዶክተር ወርቅነህ የተወከለችው ኢትዮጵያ በጠቅላላ ጉባኤው ላይ እንደ ተሳታፊ ሀገር ስኬታማ ተግባራትን ከውናለች። በተለይም ሌሎች እማኝነታቸውን የሰጡበትን የዶክተር አብይ ሁለተኛው የአርአያነት ተግባር በማውሳትና ገፅታችንን በመገንባት ረገድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ተገቢውን ሚና ተጫውተዋል ብዬ አምናለሁ። ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ በጉባኤው ላይ ባደረጉት ንግግር፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ በሀገር ውስጥ ያደረጓቸውን ጉልህ ስኬታማ ተግባራትን ዘርዝረዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የሀገራቸውን ዴሞክራሲ ከማጎልበት፣ ሁሉንም የፖለቲካ ሃይል የሚያስተናግድ ሰፊ ምህዳር ከመፍጠር፣ አንድነትን ከማጠናከርና ሌሎች በሀገር ውስጥ ያከናወኗቸውን ተግባሮችን ለጉባኤተኛው አስረድተዋል። እንዲሁም ሀገራችን ከኤርትራ ጋር የነበራትን የ“ሞት አልባ ጦርነት” ሁኔታ በመቀየር ሁለቱ ሀገራት ወደ ሰላምና ሁለገብ የትብበር ማዕቀፍ እንዲመጡ የተጫወቱን ውጤታማ ሚናም አንስተዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ እንደ ሶማሊያ ያሉ የቀጣናው ሀገራትም በዚህ የትብበር ማዕቀፍ ውስጥ ገብተው አብረው እንዲሰሩ የተከናወኑ ሁለንተናዊ ጥረቶችን አብራርተዋል። ለዚህም ከስብሰባው ጎን ለጎን የተካሄደው የተመድና የአፍሪካ ህብረት የጋራ ግብረ ሃይል ስብሰባም ይህም እውነታን አረጋግጧል። ግበረ ሃይሉ በምስራቅ አፍሪካ ቀጣና እየመጣ ያለው ለውጥ ዙሪያ ውይይት አድርጎ፤ በክፍለ አህጉሩ የመጣውን ለውጥ አድንቋል። በተለይ የቀጣናው ሀገራት መሪዎች በመካከላቸው ያለውን አለመግባባቶች ለመፍታት ያሳዩት ከፍተኛ የአመራር ብቃት፤ ለምስራቅ አፍሪካ ሰላም ትልቁን ሚና እንደተጫወተም ምስክርነቱን ሰጥቷል። ተግባሩም ከድንበር ጋር በተያያዘ ለሚወዛገቡ ሀገራት ምሳሌ ሊሆን እንደሚችል ገልጿል። ታዲያ ከዚህ እውነታ በስተጀርባ ያለችውና ተነሳሽነቱን የወሰደችው ኢትዮጵያ የአንበሳውን ድርሻ መጫወቷ የሚዘነጋ አይደለም። እናም ይህን ገልፆ በማስረዳት ገፅታን ከመገንባት አኳያ የዶክተር ገበየሁ ቡድን ጉልህ ሚና ስለ መጫወቱ አስረጅ ይመስለኛል።  

ዶክተር ገበየሁ በጉባኤው ላይ ያነሱት ሌላኛው ጉዳይ ስደተኞችን የተመለከተ ነበር። በንግግራቸውም፤ ኢትዮጵያ ከተለያዩ ሀገራት ለሚመጡ ስደተኞች የምታደርገውን ድጋፍ አጠናክራ እንደምትቀጥል አስታውቀዋል። ሀገራቸው ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽንና ሌሎች ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ተባብራ እየሰራች መሆኑን የገለፁት ሚኒስትሩ፤ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ስደተኞችን የሚያስጠልሉ ሀገራት የሚደርስባቸውን ጫና እንዲወጣና ሶስተኛ ተቀባይ ሀገራትም የድርሻቸውን መፈፀም እንደሚገባቸው አሳስበዋል።

ይህ የዶክተር ገበየሁ ንግግር እንዲሁ ዝም ብሎ የተባለ ነገር አይደለም— በአሁኑ ወቅት ሀገራችን ወደ አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ ስደተኞችን አቅፋ በመያዝ የስደተኞቹ ሁለተኛ ሀገር ከመሆኗ አኳያ የሚታይ እንጂ። በጉባኤው ላይ፤ የዓለም ባንክ ፕሬዝዳንት ጂም ዮንግ ኪም፤ ኢትዮጵያ ለስደተኞች እያደረገች ያለችው ትምህርት የመስጠትና የስራ ዕድል የመፍጠር ድጋፍን ምስጋና ችረውታል። የተመድ የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን ኮሚሽነር ፊሊፕ ግራንዴ በበኩላቸው፤ ዓለምአቀፉ ማህበረሰብ ስደተኞችን የመቀበልና የመደገፍ ኃላፊነት እንዳለበትም በመግለፅ የዶክተር ወርቅነህን ሃሳብ አጠናክረዋል። ይህም ሀገራችን እንደ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት መስራች አባልነቷ፤ ድርጅቱ የተቋቋመበትን ዓላማ ከሰብዓዊነት አኳያ እየደገፈች መሆኑን አመላካች ይመስለኛል። በዚህ ረገድም የሚታይ የገፅታ ግንባታ ስራ መከናወኑን መግለፅ የሚቻል ይመስለኛል።

የተመድ ጠቅላላ ጉባኤ፤ ኢትዮጵያ የፀጥታው ምክር ቤት ተለዋጭ አባል ሆና ከተመረጠች በኋላ ለሁለተኛ ጊዜ የተካሄደ ነው። በዚህ ጊዜ ውስጥ ሀገራችን በሰላም ማስከበርም ይሁን የቀጣናውን ሰላም ዘላቂ ከማድረግ አኳያ ከፍተኛ ሚና ተጫውታለች። ይህም  በመንግስታቱ ድርጅት አዳራሽ ውስጥ ከተነሱት ጉዳዩች ውስጥ አንዱ ነው። ኢትዮጵያ የተመድ መስራች አባል ሀገር እንደመሆኗ፤ ለዓለም ሰላምና ደህንነት በትጋት እንደምትሰራ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አረጋግጠዋል።

በእኔ እምነት፤ ይህ የሀገራችን ሰላም ወዳድነት ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ወትሮም የሚያውቀው ቢሆንም፤ ሀገራችን ሁሌም የዓለም አቀፉን ሰላም ለመደገፍ ፊቷን አዙራ እንደማታውቀው ሁሉ፤ ዛሬም ይሁን ነገ ይህን ተግባሯን ይበልጥ አጠናክራ እንደምትቀጥል ያሳወቀችበት መድረክ ነው። በዚህ መድረክ ላይ ዶክተር ወርቅነህ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት በኤርትራ ላይ የጣለውን ማዕቀብ እንዲያነሳ መጠየቃቸው፤ ሀገራችን ቀጣናው ከማዕቀብ ውጭ በነፃነት፣ በሰላምና በጋራ ተጠቃሚነት እንዲያድግ ካላት ፍላጎት የመነጨ ይመስለኛል።

ርግጥ በቀጣናዊ ትብብር ውስጥ አንዱ ሌላውን በመጥቀምና የሌላውም ድምፅ በመሆን ተደጋግፎ ማደግ ይቻላል። አንድ ወገን በማዕቀብ ውስጥ ሆኖ በሙሉ አቅም ተደጋግፎ ለማደግ እንቅፋት ይሆናል። የምስራቅ አፍሪካ ህዝቦች በአንድነትና በእኩልነት የተፈጥሮ ፀጋዎቻቸውን ለመጠቀም ከማንኛውም ተፅዕኖ ነፃ መሆን ያለባቸው ይመስለኛል። ኢትዮጵያ በኤርትራ ላይ የተጣለው ማዕቀብ እንዲነሳ ጉባኤውን ስትጠይቅ፤ መነሻዋ ይኸው እውነታ ይመስለኛል። እናም ምንም እንኳን ማዕቀቡን የማንሳት መብት ያለው የፀጥታው ምክር ቤት ቢሆንም፤ ኢትዮጵያም እንደ ተለዋጭ አባልነቷ በኤርትራ ላይ የተጣለው ማዕቀብ እንዲነሳ ነገም ይሁን ከነገ በስቲያ ግፊት ታደርጋለች ብዬ አስባለሁ። ምክንያቱም ጉዳዩ የቀጣናው ሀገራት እጅ ለእጅ ተያይዘው በፍትሐዊነትና በጋራ ተጠቃሚነት ለማደግ የሚያደርጉትን ጥረት እንዳያሰናክል ከማለም አኳያ መከናወን ያለበት ስለሆነ ነው።  

ያም ሆኖ እኔ በበኩሌ፤ በ73ኛው የተመድ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ የተመራው የኢትዮጵያ ልዑክ በዶክተር አብይ አህመድ አማካኝነት በሀገራችን ውስጥ ምን እየተከናወነ እንደሆነ፣ ስደተኞችን ከመቀበልና ከመደገፍ እንዲሁም የቀጣናውንና የዓለምን ሰላም ከማስጠበቅ አኳያ ምን እየተሰራ እንደሆነ በሚገባ ሁኔታ ተገልጿል። ዓለምም አድናቆቱን ችሮናል። “የመደመር ፍልስፍናችን” በአምስት ወራት ውስጥ ከሰፈር እስከ ዓለም በአርአያነት እየቀረበ ነው። ይሀም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ ተግባራቸውን በተገቢው ሁኔታ መወጣታቸውን የሚያሳይ ይመስለኛል። ርግጥም ከላይ የጠቀስኳቸውና ሌሎች በጉባኤው ላይ የተነገሩ ለጊዜው የማላስታውሳቸው የገፅታ ግንባታ ስራዎች እጅግ አስደምመውኛል። እናም በግሌ ‘ኦ! የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ…!’ እንድል አድርገውኛል። መጪው ጊዜ “በቲም ለማ” ቅንጅታዊ አሰራር ብርሃናማ ስለመሆኑ አንድ ዘለላ ፍንጣቂ ማሳያ ነው ብዬም አስባለሁ። ሰናይ ጊዜ።           

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy