Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ከስሜት ባርነት እንላቀቅ

0 313

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ከስሜት ባርነት እንላቀቅ

ስሜነህ

 

በአሁኑ ወቅት በአገራችን እየመጣ ያለውን ለውጥ ባልተገባ መንገድ አቅጠጫ ለማሳት የሚሞክሩ የግል ጥቅመኞች በአንዳንድ አከባቢዎች ህግወጥነት እንዲሰፍንና ህግና ስርዓት እንደሌለ ለማስመሰል ሲጥሩ ይስተዋላል። ይሁን እንጂ ይህ ተቀባይነት የሌለውና መንግስትም እንደመንግስት የህግ የበላይነትን ለማስከበር ቁርጠኛ መሆኑና በአቋምም በተግባርም በግልፅ እያረጋገጠ ነው፡፡በዚህ ረገድ የፌዴራል መንግስትም ሆነ ክልሎች በእርምጃ ላይ መሆናቸውን ማረጋገጥ ይቻላል። ይህንን ከኦሮሚያ፣ ከአማራ፣ ከኢትዮ ሶማሊያ ወዘተ ክልሎች ሰሞንኛ እንቅስቃሴና እርምጃዎች  ማየት ይቻላል።

 

ከዚህ በተጨማሪ በለውጥ ሂደት እንደሚያጋጥሙ የሚጠበቁ ችግሮች የለውጡን ሂደት እየተገዳደሩት ነው። ስለሆነም የተገኘውን ነፃነት በአግባቡ በመያዝ ተቋማዊ እንዲሆን ለውጡን መደገፍ ሲገባ ከዚህ ተቃራኒ በሆነ መንገድ የሚደረገው እንቅስቃሴ ከወዲሁ ካልተገታ ስርዓት አልበኝነት እንዲነግስ ሊያደርግ የሚችል ዝንባሌ እየተስተዋለ መሆኑን በአንክሮ ተመልክቶ የህግ የበላይነት ለማስፈን የሚያስችሉ ስራዎች በጥብቅ ክትትል ሊሰሩ ይገባል፡፡ በዚህ ረገድ ህዝቡ፣ የፀጥታና ደህንነት አካላት በለውጡ መንፈስ የበኩሉን ሚና ሊጫወት ይገባል።  “∙∙∙∙∙∙በአንድ በኩል በህግና በስርአት ለመተዳደር ተስማምተው እንመለሳለን ካሉ በኋላ በሌላ በኩል የአስተዳደር ስራን በእጃቸው ለማስገባት የተለያየ እንቅስቃሴ የሚያደርጉ ከሆነ አደገኛ ነው፤ መፈቀድም የለበትም፡፡ መንግስት አለ። ህግና ስርአት ማስከበር አለበት፡፡ የመንግስት መንግስታዊ መብት በድርጅቶች ሊነጠቅ አይገባም፡፡ መፈቀድም የለበትም፡፡ ቁጥጥር መኖር አለበት፡፡ በሌላ በኩል ነፃ ተቋማት ፈጠራ ላይ ያተኮረ ውይይትና ክርክር ተጀምሮ፣ ድርጅቶች ስራ እንዲሰሩ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ወደ ሃገር ቤት የምንመለስ ሰዎችና የፖለቲካ ድርጅቶች በመጀመሪያ የሃገራችንን ሁኔታ በደንብ መረዳት ያለብን ይመስለኛል፡፡ ከሃገር ወጥተን በነበርንባቸው 20 እና 40 ዓመታት ውስጥ በሃገሪቱ ያለው ነባራዊ ሁኔታ ምንድን ነው የሚለውን ጊዜ ወስደን መረዳት ይኖርብናል፡፡ እኔ በ1997 ዓ.ም መጥቼ ነበር፡፡ አሁን ከ13 ዓመት በኋላ ስመጣ፣ አዲስ አበባ ውስጥ ብዙ አይነት የስነ ልቦና ለውጦችን እያየሁ ነው፡፡ ብዙ ነገር ለማጥናትና ሆደ ሰፊ ለመሆን ፍቃደኛ መሆን አለብን፡፡∙∙∙∙” ይህን ያሉት የኢህዴኑ መስራች አቶ ያሬድ ጥበቡ ናቸው።

ማኅበራዊ አካባቢያችን ያሳደገን መልካም ምግባሮቹንና ሐሳቦቹን እየሰጠ ብቻ ሳይሆን ጥላቻዎቹን፣ ሸሮቹን፣ ጭፍን አመለካከቶቹንና አቋሞቹን ሁሉ እየሰጠን ነው፡፡ በየዕድገት ደረጃችን እያንዳዳችን የሚኖረን የልቦናና የህሊና ሙሽት፣ በውጫዊ ሰበዞችና በእያንዳንዳችን ውስጣዊ አቅም መስተጋብር የሚወሰን ነው፡፡ በዚሁ አመሉ ምክንያት ከሰው ጋር በቀላሉ ሊጋጭ ይችላል፡፡  ብዙ ወጣቶችም ዛሬ “ትግሬ የሚባል ሰው!…”፣ “አማራ! አማራ! …”፣ “ኦሮሞ ድሮስ…” ወዘተ የሚሉ ዓይነት ጅምላና ግልብ ሹክሹክታዎችንና የተዛቡ ግንኙነቶችን እየተነፈስን ያደግን ወጣቶች ደግሞ፣ የሚቆራኘን ጭፍን ድምዳሜና ጥላቻ ቀመስ ዝንባሌ የህግ የበላይነትን ሳይቀር አደጋ ላይ እየጣለብን ነው።

 

አንድ ቀን በአዳራሽ ተገናኝቶ እየተላቀሱ ይቅር በመባባል ያደጉበትን፣ የኖሩበትንና አሉታዊ ስሜትና አመለካከት ማጠብ አይቻልም፡፡ ላዩን ስሜታችን ሲቀልና እፎይታ ሲሰማን የለቀቀን ይመስላል እንጂ፣ ከሥር አሸልቦ ይቆይና ለግርሻ የሚስማማ አጋጣሚ ሲያገኝ ብቅ ይላል፡፡ የሆነ አናዳጅ ድርጊት ተፈጥሮ ገና ማን እንዳደረገው እንኳ ሳይታወቅ “ያለነሱ ይኼንን የሚያደርገ የለም!! እነሱ! እነሱ! …” የሚል ጭፍን ግምት ውስጥ ከገባንና ግምታችንን የእውነት ያህል አምነን ከበገንን፣ ከዚያም ይባስ ብለን አንድን ጥፋት የጠቅላላው ብሔረሰብ ባህርይ አድርገን አቅራቢያችን ያገኘናቸውን ንፁኃን ለመበቀል ከተነሳሳን እዚያው ጥላቻ ውስጥ ነን ማለት ነው፡፡ ይህ ደግሞ ሃገርን በሁለት እግሯ የሚያቆመውን የህግ የበላይነት አደጋ ላይ መጣል ነው። ጥላቻንና ጭፍን ፍረጃን ተገላገልነው ማለት የምንችለው ጥፋቶችንና ጠቦችን የመላ ብሔረሰብ ከማድረግ ፈንታ፣ የግለሰቦች አድርጎ መውሰድ ውስጥ ስንገባ ነው፡፡ እዚህ ውስጥ እስካልገባን ድረስ  የህግ የበላይነት ጠፍቶ ስርአተ አልበኝነት መንገሱ አይቀሬ ይሆናል።

 

የጭፍን ስሜቶችና ድምዳሜዎች ተገዢ ሆኖ አንድ ነገር በተፈጸመ ቁጥር፣ የጭፍን ቁጣና ግምታዊ ፍርድ ፈረሰኛ ሆኖ የግርታ ቅጣት በንፁኃን ላይ ማውረድ ዘግናኝ እውርነት ነው፡፡ የስሜት ባርነትም ነው፡፡ ለዚህ ዓይነት እውር ቀጪነት እጅ ሰጥቶ ከዛሬ ነገ የቁጣ እሳት ወረደብኝ እያሉና ጅምላ ማኅበረሰብን እየፈሩ መኖርም (ሲመቸው የዚያው ዓይነት ጅምላ ተበቃይነት የማያጣው) ሌላ የባርነት ገጽ ነው፡፡

 

በአንዲት የሐሰት ወሬ ወደ ጅምላ ቁጣና ጭፍን ዕርምጃ ለመነዳት ከመቅለል በላይ መጫወቻ የመሆን ምን ውድቀት አለ?። ቦምብ ይዟል የሚል ሽውታን እውነት ይሁን ውሸት ለማጣራት ጊዜ ሳይሰጡ፣ ለ21ኛው ክፍለ ዘመን ያረፈደችው ኢትዮጵያ በዴሞክራሲና በፍትሕ ውስጥ ለመኖር በምትጥርበት ሰዓት፣ ራስ ሕግ ሆኖ በዘመነ አረመኔነት በነበረ ጭካኔ ሰውን ቀጥቅጦ ከመግደል በላይ የኋሊት ጉዞ ምን አለ? ። የማገናዘብና የርህራሔ አቅምን ለአንድ ግፈኛ ፈላጭ ቆራጭ አስረክቦ ብጤ ፍጡርን የሚከትፍና በእሳት የሚያንጨረጭር የግፍ በትር መሆን ደግሞ ከሁሉም የከፋ ነው፡፡

 

ወጣቱ ባንድ ጊዜ አገር ተረካቢም ገንቢም የመሆኑ ሚስጥር በታላላቆቹ ሥር የሚበስልና የሚተባ ለጋ ግን ባለብዙ ዕምቅ አቅም መሆኑን ከዘነጋ፣ ታላላቆቹም (ምሁራንና መዓት ፖለቲከኞች) መግራት የማይችሉ ተመልካቾች ከሆኑ ከዚህ የበለጠ ተያይዞ ጉዞ ወደ መቀመቅ መውረድም ይመጣል። የጅምላ ቀጪነትና ተቀጪነት መጫወቻ ከመሆን ነፃ ለመውጣት ለጅምላ አመለካከት መነሻ የሆኑ የተበላሹ እውነታዎችንና ግንኙነቶችን ለይቶ እስከ መቀየርና በሁለት በኩል ያሉ ብሶቶችንና ጉዳቶችን እስከ መረዳትና እስከ መጋራት የዘለቀ ዕርቅ ማድረግ፣ ዕርቁም እየጠነከረ እንዲሄድ መከባበርና መተሳሰብ ያልተለየው መቀራረብን እያሳደጉ መሄድ ግድ ነው፡፡

 

ብሔረተኛ ፖለቲካ በኢትዮጵያ መንበረ ሥልጣንና የፖለቲካ ሜዳ ላይ ነግሶ ህሊናን በጠባቡ እይታዎች ለማሟሸት መቻሉና ዜጎችን ቤተኛና ባይተዋር አድርጎ ባንጓለለ አገዛዝ ያደረሰው ጉዳት ቀላል አይደለም፡፡ የፖለቲካ ጠንቄ ባሉት ሰው ላይ ወንጀል ፈልስፎ ወይም በተውሸለሸለ (ከባዶ በማይሻል) የሰውና የሰነድ ማስረጃ  ማስፈረድ የሚቻልበት የጭቦ አገዛዝ ከፌዴራል አስተዳደር እስከ ክልሎችና የወረዳዎች ጉራንጉር ድረስ መባዛቱ አንዱ ነው፡፡

ዛሬ  የመንግሥት ክፍተት በሌለበት፣ እንዲያውም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኢትዮጵያ የመንግሥት ታሪክ ውስጥ ታይቶ በማያውቅ የሕዝብ ድጋፍ ተጥለቅልቆ ያላንዳች የእበላባይነት ፍላጎት የሙገሳ ዘፈን እየተንቆረቆረለት፣ ቅኔ እየተዘረፈለትና በክርስቲያኑም በሙስሊሙም ሕዝብ አካባቢ “ከእግዜር የተሰጠ መሪ” ለመባል በቅቶ ሳለ፣ ከቦታ ቦታ ዘግናኝ የጥቃትና የጥፋት ግርግሮች ከመፈጸም አለመገታታችን የሚያሳፍርና ጉድ የሚያደርገን ተግባር ነው፡፡ እነዚህ ጥፋቶች የቱንም ያህል “ጥያቄ አለን” ከሚል ጉዳይ ጋር ቢያያዙም፣ በብጥስጣሽ ብሔረተኝነት የህሊና መኮመታተር ምን ያህል ሰላም ነሺ ድቀት እንደሆነ የሚያሳዩ መስታወቶች ናቸው፡፡

 

አሁን በምንገኝበት የፖለቲካ ድባብ ውስጥ የማይረጭ ነገር የለም፡፡ አንዳንዶች ብሔርተኝነት (ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኛነት) አርነት መውጣት ሆኖ ይታያቸዋል፡፡ አርነት መውጣት ከጭቆና (ከብሔር ጭቆናም ሆነ ከሌላ) መውጣት ነው፡፡ ዓለም ሁሉ ዘገየም ፈጠነ የሚያመራው የሰው ልጆች ሁሉንም ዓይነት ጭቆና እያራገፉ የተያያዘ ዕጣቸውን አንድ ላይ ወደሚንከባከቡበት አቅጣጫ እንጂ ወደ ክፍልፋይነት አይደለም፡፡

 

ሌላው አስጊ ነገር የመንጋ የግርታ ሥራ  ከጀርባ ምሪት ሰጪ ቢኖርበት እንኳ ከቁጥጥር ማፈትለኩና ውጤቱ ሊገመት በማይችል ግብታዊነት ውስጥ መስገሩ ባህርይው ነው፡፡ ለዚህ ነው መንጋንና ፖለቲካን ማዛመድ አሳሳች የሚሆነው፡፡ ወንጀልና ግፍ የግድ የፖለቲካ ባህርዮች አደሉም፡፡ ቁጣ የቀዘፈው ግርታ ግን ምንም ዓይነት መልካም ጥያቄ አንጠልጥሎ ቢነሳ፣ በወንጀልና በግፍ ሥራዎች ከመጉደፍ አለማምለጡ ድሮም ዘንድሮም የታወቀ ነው፡፡

 

አምባገነንነት በሰፈነበት ኑሮ ውስጥ ሰላማዊ መተንፈሻ ያጣ የቁጣ ማዕበል በንብረትና ጠላቴ ባለው ላይ እልሁን እየተወጣ አገዛዙን በድንጋጤ ለመምታት ይችል ይሆናል፡፡ አሁን ኢትዮጵያ ዴሞክራሲ የመገንባት ዕድል ውስጥ በገባችበት ሁኔታ ውስጥ የሚመጣ የግልፍታ ማዕበል ግን በምንም ዓይነት ዴሞክራሲን ሊጠቅም አይችልም፡፡ ጅምላ ስሜትና ጉልበተኛነት እንዳዘዘን መሆንና ማድረግ እንዴት በሕግና በመብት ውስጥ የመኖር ሥርዓትን ሊያዋልድ ከቶም ቢሆን አይችልም።

ከጠቅላይ ሚንስትራችን ጋር ከሃሳባቸውና ከለውጥ አመራራቸው ጋር ተደምረናል የምንል በሙሉ ይህን የክቡር ጠቅላይ ሚንስትሩን ሰሞንኛ መልእክት ከቀልባችን እናዋህደው ዘንድ እየመከርን እናሳርግ። ኢትዮጵያዊነት የአቃፊነት ባህል ነው ያለው እንጂ አግላይ አይደለም፡፡አልፎ አልፎ የታዩት ጥፋቶች መታረም ያለባቸው ናቸው፡፡የተፈናቀሉም ወደየቀያቸው እንዲመለሱ እየተደረገ ነው፡፡ወጣቶች ለስርዓት መታገል እንጂ ራሳቸው ፈራጅ መሆን የለባቸውም፡፡

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy