Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የህግ የበላይነት ለውርርድ አይቀርብም

0 1,469

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የህግ የበላይነት ለውርርድ አይቀርብም

ኢብሳ ነመራ

የህግ የበላይነትና ስርአተ አልበኝነት ተፎካካሪዎች ናቸው። የአንዱ የበላይነት ሌላውን ይደፍቃል። የአንዱ መንገስ ሌላውን ያዋርዳል። የህግ የበላይነት ሲጠፋ ስርአተ አልበኝነት በቦታው የተካል። የህግ የበላይነት ሲነግስ፣  ስርአተ አልበኝነት ይዋረዳል። ስርአተ አልበኝነት መንግስት ህግ የማስከበር ጉልበት ሲያጣ ወይም መንግስት የተባለው ተቋም ሲጠፋ የሚፈጠር ሁኔታ ነው። የህግ የበላይነትና ህግ የማስከበር አቅም ያለው መንግስት አይነጣጠሉም። በአንድ ሃገር ስርአተ አልበኝነት ከሚነግስ መንኛውም አይነት ህግ የማስከበር አቅም ያለው መንግስት ቢኖር ይሻላል። ከጥቂት ዓመታት በፊት በሶማሊያ መንግስት ከፈረሰ በኋላ ተፈጥሮ የነበረው ሁኔታ የስርአተ አልበኝነትን ምንነት ለመረዳት አይነተኛ ማሳያ ነው።

የህግ የበላይነት በሌለበት ሁኔታ ገዢው ሁኔታ ሃያል ሆኖ መገኘት ብቻ ይሆናል። ራስን ከማንኛውም ጥቃት በመጠበቅ ሰብአዊ መብትንና ነጻነትን ማረጋገጥ፣ ቁሳዊ ጥቅም ማግኘት ወዘተ የጉልበተኞች ብቻ ይሆናል። የህግ የበላይነት ከሌለ ሰላም አይኖርም፤ የህግ የበላይነት ከሌለ የሰዎች በህይወት የመኖር መብት ሙሉ በሙሉ ዋስትና ያጣል። ሰዎች አሁንና እዚህ በሚገኙበት አፍታ እንጂ በቀጣይ ጊዜ ምን እንደሚገጥማቸው መገመት አይችሉም። የግል ህይወታቸው ከቁጥጥራቸው ወጥታ ለእድል ትሰጣለች። ጉልበተኛ መዳፍ ስር በወደቁባት በማንኛውም አፍታ ህይወታቸውን ሊያጡ ይችላሉ።  

የህግ የበላይነት ከሌለ በሰዎች መሃከል ያለው ማህበራዊ ትስስር ትርጉም ያጣል። መንፈሳዊ ፍላጎትና እርካታ ትርጉም ያጣል። ፍቅር፣ መተሳሰብ፣ መረዳዳት፣ ወዘተ ስፍራ አይኖራቸውም። የህግ የበላይነት በሌለበት ሁኔታ ሰላም ስለማይኖር የማምረት ተግባር ላይ መሰማራት አይቻልም። የህግ የበላይነት በማይኖርበት ሁኔታ ቀደም ሲል እንደገለጽኩት ሰዎች ከሚገኙበት ስፍራና አፈታ ውጭ መጪውን ሰለማያወቁት አንጻራዊ ሰላም ቢኖር እንኳን የማመረት ፍላጎት አይኖራቸውም። ያመረቱትን ለነገ፣ ለመጪው ሳምንትና ወር፣ ለከርሞ ማከማቸት ትርጉም ያጣል። በመንግስት ውሳኔና ቁጥጥር የምርትና የአገልግሎት ልውውጥ እሴት የሚኖረው የወረቀት ገንዘብ፣ የህግ የበላይነት ሲጠፋ ይህን እሴቱን አጥቶ መናኛ ወረቀት ይሆናል። ይህ የገበያ ልውውጥን አዳጋች ያደርገዋል። ሰዎች በእጃቸው ያለውን ጥሬ ሃብት/ምርት ለማከማቸት፣ ለማጓጓዘና ለመለዋወጥ አመቺ ወደሆነው ገንዘብ መለወጥ አይችሉም።

የህግ የበላይነት በሌለበት ሁኔታ የፈቀዱትን አቋም የመያዝ፣ አቋምን በሰላማዊ መንገድ የማራመድ፣ የመደራጀት፣ ሃሳብን የመግለጽ፣ ለፖለቲካ ስልጣን የመፎካከር ወዘተ ፖለቲካዊ መብቶች ትርጉም ያጣሉ። በአጠቃላይ የህግ መጥፋትና የስርአተ አልበኝነት መንገስ የሰዎችን ኑሮ ትርጉም አልቦ ያደርገዋል። የህግ  የበላይነት የሚከበረው ለመግስት ተብሎ ሳይሆን የዜጎችን የኑሮ ዋስትና ለማረጋገጥ ነው።

የዜጎችን ሰብአዊና ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ መብቶችና ነጻነቶች መነሻ በማደረግ ተጠቃሚ የሚሆኑበትንና መብትና ነጻነታቸው የሚረጋገጥበትን ህግ ማውጣት የመንግስት ተግባር ነው። ይህን ህግ በማስፈጸም የህግ የበላይነትን የማስከበር ስልጣን ያለውም መንግስት ነው። መንግስት የህግ የበላይነትን ለማስከበር የመከላከያና ሌሎች የጸጥታ ሃይሎች፣ ፍርድ ቤት፣ ማረሚያ ቤት የመሳሰሉትን ተቋማት በማደራጀት ሃይል የመጠቀም ስልጣን አለው። መንግስት ይህን ሃይል የመጠቀም ስልጣኑን የሚያገኘው የማይገሰስ በህይወት የመኖርና ይህን እውን ማደረግ የሚያስችሉ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ነጻነቶች ካሉዋቸው ዜጎች ነው፤ በውክልና።

እያንዳንዱ ዜጋ መብቶችና ነጻነቶቹን የማስከበር መብት ያለው ቢሆንም፣ እያንዳንዱ ሰው ሃይል በመጠቀም መብቶቹን ለማስከበር የሚወሰደው እርምጃ፣ ፍትሃዊውን ኢፍትሃዊ ከሆነው መለየት ስለማያስችል፤ ጉልበተኞች ጉልበት የሌላቸውን የሚጫኑበት እድል ስለሚፈጠር፣  ሃይል ተጠቅሞ መብትና ነጻነትን የማስከበር መብታቸውን በውክልና ለመንግስት ይሰጣሉ። የህግ የበላይነት ጠፍቶ ስርአተ አልበኝነት ሲነግስ ይህ ሃይልን በመጠቀም መብትን የማስከበር ለመንግስት በውክልና የተሰጠ መብት ተመልሶ በእያንዳንዱ ሰው እጅ ይወድቃል። ይህ ሲሆን ግጭት፣ የጅምላ ፍርድ፣ በየአጥቢያው የተደራጁ ቡድኖች ፈላጭ ቆራጭ  ሆነው የሚወጡበት ሁኔታ ወዘተ ይፈጠራል። ስርአተ አልበኝነት ይህ ነው።

የህግ የበላይነትን ማስከበር የመንግስት ሃላፊነትና ስልጣን ቢሆንም መንግስት እያንዳንዱን በየስርቻው የሚዶለት ሴራና የሚፈጸም ህገወጥ ድርጊት መቆጣጣር አይችልም። ሁሉም ሰላማዊ ዜጎች የራሳቸውን፣ የቤተሰባቸውንና በእይታቸው ቁጥጥር ስር ያለው አካባቢ ላይ የሰላም ስጋት ሲያጋጥማቸው ለመንግስት የጸጥታ አስከባሪ ተቋም ማሳወቅ ይጠበቅባቸዋል። የጸጥታ አስከባሪ ሊደርስ በማይችልበት ሁኔታ በአልሞት ባይ ተጋዳይነት ካልሆነ በስተቀር፣ የሃይል እርምጃ የመውሰድ ስልጣን የላቸውም። የዜጎች የህግ የበላይነትን የማስከበር ድርሻ ይህን የመስላል። ይህን ድርሻቸውን ችላ ካሉ በመንግስት አቅም ብቻ የህግ የበላይነትን የማስከበር ጉዳይ እርግጠኛ መሆን አይችልም።

የፖለቲካ ለውጥ ወይም ጉልህ የፖለቲካ ማሻሻያ እርምጃ በሚወሰድበት ወቅት፣ የተለያዩ ተገቢም ተገቢ ያልሆኑም ፍላጎቶች ስለሚወጡ የህግ የበላይነት ፈተና ይገጥመዋል። ይህ ሁኔታ አሁን በሃገራችን እየታየ ነው። በየአካባቢው ግጭቶች እያጋጠሙ ነው። ለውጡን ያመጣው ህዝባዊ ንቅናቄ ውስጥ ጉልህ ድርሻ ለነበራቸው ወጣቶች የተሰጠው እውቅና በእነርሱ ሽፋን ህገወጥነትን የሚያራምዱ ጉልበተኞች የተፈጠሩበትን ሁኔታ አስከትሏል። በውጭ ሃገራት ሲንቀሳቀሱ የነበሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ወደሃገር ቤት እንዲመለሱ መደረጉ፣ የፖለቲካ ምህዳሩን በማስፋት የሃገሪቱን ዘላቂ ሰላም በማረጋገጥ ረገድ ጉልህ ድርሻ ያለው ቢሆንም፣ እነዚህ ከሃገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ ተነጥለው የቆዩ ፖለቲከኞች የሚያንጸባርቋቸው አቋሞች ስጋት የሚያሳድሩባቸውና የሚያስኮርፏቸው ወገኖች ታይተዋል። በእነዚህ ከውጭ የመጡ ቡድኖች ሽፋን የሚንቀሳቀሱ ጀብደኛ የድል አጥቢያ አርበኞች የተፈጠሩበት ሁኔታም ተስተውሏል። አሁን በሃገሪቱ የጎራ መደበላላቅ ይታያል። ህግ አክባሪና ህገወጥ ቄሮ ተደበላለቋል። ሰላማዊ የፖለቲካ ተሳትፎ ለማድረግ ወደሃገር ቤት የገቡ ተቃዋሚዎችና በእነርሱ ሽፋን የሚንቀሳቀሱ የድል አጥቢያ አርበኞች ተደበላለቀዋል።

በዚህ ምክንያት በየአካባቢው ለውጡ የፈጠረውን ክፍተት በመጠቀም የሚያጋጥሙ ግጭቶች፣ የህገወጥና የህጋዊነት የጎራ መደበላላቅ የህግ የበላይነትን ለአደጋ ያጋለጡበት ሁኔታ ይታያል። ቀደም ሲል እንደጠቀስኩት የህግ የበላይነት መጥፋት የስርአተ አልበኝነት መንገስን ያስከትላል። የህግ የበላይነት መጥፋትና የስርአተ አልበኝነት መንገስ ቀዳሚና ብቸኛ ተጎቺዎች ደርሞ ሰላማዊ ዜጎች ናቸው።

የህግ የበላይነትን የማረጋገጥ ጉዳይ በዋናነት የመንግስት ሃላፊነትና ስልጣን ቢሆንም፣ አሁን በሃገራችን የሚታየውን በየስርቻው የሚጠነሰስና በየአጋጣሚው ድንገት የሚፈነዳ ግጭት በመንግስት ብቻ መቆጣጠርና መከላከል አይቻልም። ህዝቡ አካባቢውን በማጤን የሰላም ስጋት ሲያጋጥመው ለጸጥታ ሃይል በመጠቆም የህግ የበላይነትን የማረጋገጥ ድርሻውን ሊወጣ ይገባል።

በአጠቃላይ፣ የህግ የበላይነት መጥፋት የእያንዳንዱን ዜጋ ሰብአዊ መብት፣ የኢኮኖሚ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ነጻነት አደጋ ይጥላል። ስርአተ አልበኝነትን በማንገስ የሃገርን ህልውና አደጋ ላይ ይጥላል። የህግ የበላይነት መጥፋት የሰብአዊነት መኮስመንን ያስከትላል። በመሆኑም የህግ የበላይነት ባገኘውም ባጣውም ምንም አይደለም በሚል ለውርርድ የሚቀርብ ነገር አይደለም። እናም፣ ሁሉም ዜጋ የህግ የበላይነትን በማስከበር ተግባር መንግስትን በመደገፍ የራሱን ሰብአዊ መብትና ነጻነት፣ የሃገሩንም ህልውና ሊያረጋግጥ ይገባል።   

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy