የትርንጎ ነገር
ጎበዝ አንድ አይት ነገር እያወራን ለምን አንግባባም! ሰዎች እርስበርስ ስለ ተመሳሳይ ነገር እያወሩ ሳይግባቡ ቀርተው ወደ ጭቅጭቅ ብሎም ወደ ጠብ ሲያመሩ አጋጥሟችሁ አያውቅም? አንድ ጊዜ ስለ ተግባቦት (ኮሚኒክሽን) ስልጠና በምሰጥበት ቦታ ተሳታፊዎችን ‹‹ትርንጎ›› ምን እደሆነ ያውቁ እንደ ሆነ ጠየቅኋቸው፡፡ ከተሳታፊዎች አንዱ እጁን አውጥቶ የፍራፍሬ አይነት እንደ ሆነ ነገረን፡፡ ሌላው ደግሞ ‹‹ትርንጎ›› የሰው ስም እንጂ ፍራፍሬ አይደለም አለ፡፡ በመቀጠል እስኪ ‹‹ትርንጎ›› አይታችሁና ቀምሳችሁ የምታውቁ?›› ብዬ ስጠይቅ ከሃያ ከሚበልጡ ሰልጣኞች መካከል 12 ብቻ እጅ አወጡ፡፡ እነዚህ 12 ሰዎች ትርንጎ አይቶና ቀምሶ ለማያውቁ እንዲያስረዱ ስለ ቅርጹ፣ ቀለሙ፣ ሽታውና ጣዕሙ እንዲያስረዱ ጠየቅኋቸው፡፡ በአጭሩ መልሱ 12 አይነት ነበር፡፡ ‹‹ትርንጎ›› የሰው ስም ነው ያለኝን ሰው ‹‹ትርንጎ›› የሚለውን ቃል ስትሰማ ምን አይነት ሰው ነው ወደ አሳብህ የሚመጣ? በማለት ጠየቅሁት፡፡ ሲመልስም፡- ‹‹ ቀይ፣ አጠርና ድምቡሽሽቡሽ ያለች ሴት›› አለኝ፡፡ ሌላ ጊዜ ደግሞ አዲስ አበባ ተወልዳ ያደገችውን ባለቤቴንና ባህርዳር ተወልዳ ያደገቸውን የታናሽ ወንድሜን ባለቤት ‹‹ትርንጎ›› ያውቁ እንደ ሆነ ጠየቅኋቸው፡፡ ሁለቱም እንደሚያወቁ መለሱልኝ፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ ትርንጎን እንዴት እንዳወቁ ስጠይቃቸው የሚያስገርም መልስ ሰጡኝ፡፡ የወንድሜ ባለቤት ስትመልስ የምትወዳት ታላቅ እህቷ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በምትማርበት ጊዜ ክረምት ለእረፍት ወደ ቤት ስትመለስ ከቡሬ ወይም ፍኖተ ሰላም እየገዛች ትወስድላት ስለነበር ‹‹ትርንጎን›› ሁሉጊዜ ከእህቷ ጋር አያይዛ በጣም ትወደዋለች፡፡ የኔዋ ባለቤት ደግሞ ትርንጎን የምታውቀው ከሚሴ (ወሎ) ለስራ ሄዳ ለመጀመሪያ ጊዜ እንዳየችውና ሰዎችም ‹‹ለጠንቋይ›› በስለት መልክ እደሚቀርብ እንደነገሯት እንጂ በልታም ሆነ ነክታው እንደማታውቅ ‹‹በመጸየፍ›› መልክ ነገረችኝ፡፡ ለሁለቱም ‹‹ትርንጎ›› የሚለውን ቃል ስትሰሙ ቶሎ ወደ ኣሳባችሁ ምን ይመጣል? አልኳቸው፡፡ የወንደሜ ባለቤት ‹‹እታለም›› አለች ታላቅ እህቷን በማሰብና በፈገግታ፡፡ ባለቤቴ ደግሞ ‹‹ጠንቋይ›› አለች በፍርሃትና በመጸየፍ ስሜት፡፡ ልብ በሉ ‹‹ትርንጎ›› የሰው ስም አድርጎ የሚያስበውም ሰው፣ የወንድሜን ባለቤትና የኔዋ ባለቤት በአንድ አዳራሽ አስቀምጣችሁ ከፍ ባለ ቃል፤ ወይም በተለዬ የሙዚቃ ቃናና በሙዚቃ መሳሪያ አጅባችሁ፤ ወይም በቀረርቶና በሽላላ አስደግፋችሁ ‹‹ትርንጎ›› ብትሏቸው ቶሎ ወደ አእምሮአቸው የሚመጣው ትርጉም የተለያየ ነው፡፡ እንናነተ ‹‹ትርንጎን›› ለማገለጽ ስላደረጋችሁት ጥረት በደማቁ ቢያጨበጭቡላችሁ በየልባቸው ያለው የ‹‹ትርንጎ›› ትርጉም ግን የተለያየ ነው፡፡ ወደ ስፍራቸው ሲመለሱ የሚያስቡት በመጀመሪያ የሚያውቁትን የራሳቸውን‹‹ትርንጎ›› ከነስሜቱ እንጂ የእናንተን በጩኸት የታጀበ ‹‹ትርንጎ›› አይደለም፡፡ ዛሬም በአገራችን በርካታ የ‹‹ትርንጎ ነገር›› አየሩን ሞልቶታል፡፡ በማህበራዊ ሚዲያ፣ በራዲዮና ቴልቪዥን፣ በጋዜጦች፣ በአዳራሾችና በኳስ ሜዳዎቻችን በጩኸት የምንሰማቸው በርካታ ጽንሰ-ሀሳቦች አሉ፡፡ ኢትዮጵያዊነት፣ ነጻነት፣ ዲሞክራሲ፣ እኩልነት፣ አንድነት፣ ህብረ-ብሔራዊነት፣ ወዘተ ወዘተ፡፡ ፖለቲከኞቻችን፣ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾቻችን፣ አክቲቪስቶቻችን፣ አርቲስቶቻችን፣ ጋዜጠኞቻችን፣ ምሁራኖቻችን፣ ወዘተ እነዚህን አሳቦች በመደጋገም ይነግሩናል፤ እኛም እንሰማለን፡፡ እናጨበጭባለን፡፡ ለመሆኑ ሁሉም ተናጋሪዎች በጽንሰ-ሀሳቦቹ ምንነትና ትርጓሜ ላይ ይስማማሉ? የለማ መገርሳ ‹‹ኢትዮጵያዊነት››፤ ከጁሃር፣ ከታማኝ በየነ፣ ከበረከት ስምዖን ‹‹ኢትዮጵያዊነት›› በምን ይመሳሰላል? በምንስ ይለያል? ነጻነት፣ ዲሞክራሲ፣ እኩልነት፣ አንድነት፣ ህብረ-ብሔራዊነት፣ ወዘተ በሚሉ ጽንሰ-ሀሳቦቹ ላይስ የጋራ መግባባት አላቸው? እነርሱ የፊት መሪዎች በጽንሰ-ሀሳቦቹ ላይ የጋራ መግባባት ከሌላቸው፤ ታዲያ እኛ ተርታ ዜጎች መድረክ ላገኘውና ጮክ ብሎ ለተናገረው ሁሉ አጨብጭበንና ‹‹ሆ!›› ብለን እስከየት እንዘልቃለን? ለአንዳንዱ ‹‹ኢትዮጵያዊነት›› ሲባል ‹‹ትርንጎ›› የሰው ስም ነው ብሎ እንደሚያስበው ሰው ወደ አእምሮው በቶሎ የምትመጣ ‹‹ቀይ፣ አጠርና ድንቡሽቡሽ ያለች ሴት›› ለሌላው ደግሞ ‹‹ደግና የምትወደድ ታላቅ እህት›› ለሌላው ደግሞ ‹‹ለጠንቋይ የሚቀርብ ግብር›› ሊሆን ይችላል፡፡ ‹‹ኢትዮጵያዊነት›› ከሚለው ጽንሰ-ሀሳብ ጋር መጀመሪያ እንዴት ተዋወቅን ነው ጥያቄው፡፡ የፊት መሪዎች ሆይ መድረክ አገኛችሁ፣ ሰው በእናንተ ዙሪያ ተሰበሰበ ማለት እናንተ ‹‹የእውቅት ፍጻሜ፣ የነገር ሁሉ መደምደሚያ›› ናችሁ ማለት አይደለም፡፡ እናንተ ካላችሁት ውጭ የሚያስብ ሁሉ የተሳሳተ አድርጋችሁ ማሰባችሁን ተው፡፡ ይልቅስ ‹‹ያዙኝ ልቀቁኝ›› ማለታችሁን አቁሙና ከየዘርፉ ባለሙያዎች ጋር ቁጭ በሉ፡፡ በአገራችን ጉዳይ ቁልፍ በሆኑ ጽንሰ-ሀሳቦች ላይ ተወያዩና ወጥ የሆነ ትርጓሜና ትንታኔ አብጁለት፡፡ በየ ርዕዮታችሁ የተለየ ትርጓሜ ቢኖራችሁ ልዩነታችሁ ‹‹ኃጢአት›› አይደለም፡፡ ባተረጓጎም ሰፊ ክፍተት ካለ የዘርፉ ባለሙያዎችና የዓለም አገራት ተሞክሮዎች ይዳኝዋችሁ፡፡ ያለበለዚያ በሽለላና በቀረርቶ፣ በዘለሰኛና በመንዙማ፣ በእስክስታና በጭፈራ አጅባችሁ ‹‹ትርንጎ›› ብትሉን ስለዳነኪራችሁ እናጨበጨብና ወደየቤታችን ስንመለስ ግን በየራሳችን ‹‹ትርጉም›› ታጥረን መቆራቆሳችን ይቀጥላል፡፡