Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የ “ሰጎን ፖለቲካ”

0 630

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የ “ሰጎን ፖለቲካ”

ዮናስ

 

ኢትዮጵያ ባልተጠበቀ፣ በሚደንቅ፣ በሚያሳሳ የለውጥ ምዕራፍ ውስጥ ገብታለች፡፡ አዲሱን ምዕራፍ ያልተጠበቀ የሚያደርገው ከኢትዮጵያ ሕዝቦችና ወጣቶች ትግል ከገዥው መንግሥት የረገጣና የድቆሳ መስተጋብር ውስጥ ተፈልቅቆ የወጣ በመሆኑ ነው፡፡ ለውጡን የሚያስደንቅ የሚያደርገው ደግሞ የለውጥ ኃይሉ ቅንብር ነው፡፡ የለውጥ ኃይሉን ቦታ የያዙት ከኢሕአዴግ ከራሱ ውስጥ የተመዘዙና ከተቃዋሚ ውስጥ የተፈለቀቁ የዴሞክራሲ ወገኖች፣ ከኢትዮጵያ ሕዝቦችና ወጣቶች ጋር አንድ ላይ ገጥመው ነው፡፡ ያም ሆኖ ግን የ “ሰጎን ፖለቲካ” እና ፖለቲከኛነት ወደኋላ እንዳይቀለብሰን እያሰጋን ነው።

የ “ሰጎን ፖለቲካ” የሚባለው ፈሊጥ ብዙ ጊዜ የሚነሳው ጎሰኛ ጥቃትንና አውዳሚነትን ዝም ብሎ ማሳለፍ፣ አሸዋ ውስጥ ጭንቅላቷን እንደቀበረችው ሰጎን መሆኑን ለመግለጽ ነው፡፡ የአባባሉ አጠቃቀም ያስጨነቀንን እውነታ የሚናገር ቢሆንም፣ የጥላቻ ጥቃትንና ንብረት አጥፊነትን እንኮንን እናስቁም ከማለት ያላለፈና ችግሩን ሊነቅል የሚችል የፖለቲካ ማሻሻያ ላይ ያላተኮረ ነው፡፡ በሌላ አነጋገር ዛሬ “የሰጎን ፖለቲከኛነት” ዋና መገለጫ ሆኖ ያለው ስለሰጎን እያወሩ በሰላምና በዴሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታ ላይ በሚገባን ተሳትፎ ልክ ዳተኝነት ማሳየታችን ነው፡፡

 

የሰላምነና የፀጥታ ጉዳይ ምንግዜም በዜጎች ስብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ውስጥ ቅድሚያ የሚሰጠው ወሳኝ ተግባር ነው። ሰላምና ፀጥታ ባልተረጋገጠበት ሁኔታና አካባቢ ውስጥ አንዳችም የለውጥ፣ የልማትና የዕድገት እንቅስቃሴዎች ሊታሰቡ አይችሉም። በአሁኑ ወቅት አገራችን በታላቅ የለውጥ እንቅስቃሴ ውስጥ ሆና ሳለች አላስፈላጊና ለህዝብና ለሃገር የማይበጁ አስነዋሪ ድርጊቶች እየተበራከቱ ነው። በሃሳብም ሆነ በተግባር አዲሱ የፍቅር፣ የመደመርና የአጋርነት እሳቤ በሁሉም ህብረተሰብ ዘንድ ተገቢውን ቦታና ክብር አግኝቶ ለውጡ ወደፊት እንዲወነጨፍና እድገታችን እንዲፋጠን መትጋት ሲገባ ወደ ኋላ የሚቀለብሱ አዝማሚያዎች እየተስተዋሉ ነው ። በአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ለተከታታይ ሁለትና ሦስት ዓመታት ከቆየንባቸው የሰላም መደፍረስና የዜጎች መፈናቀል እንቅስቃሴ እየወጣን ያለንበት ይህ ወቅት እጅግ ተስፋ ሰጪ በመሆኑ  እኒህን ቀልባሾች መፋለም ጊዜው የሚጠይቀው ጉዳይ ነው።

 

ለሩብ ምዕት ዓመታት ያህል የኢትዮጵያ ሕዝቦች የኖሩበት ብሔርተኛ ፖለቲካና አገዛዝ ያደረሰው አዕምሯዊ መከታተፍና የመናቆር ሥነ ልቦና፣ ጭፍን ብሔረሰባዊ ጥቃትና መበቃቀል ውስጥ እስከ መግባት ድረስ ህሊና ነስቶ ቀይቷል፡፡ በቶሎ ለችግሮቻችን መፍትሔ እስካላመጣን ድረስም መመለሻ የሌለው መጨፋጨፍ መጨረሻችን እንደሆነ አመላካች የሆኑ ድርጊቶችን እያየን ነው፡፡ የሚያሳስበው ደግሞ በዚህ የመጠፋፋት አፋፍ ላይ ሆነንም  እውነታን ያለመቀበል ሽምጠጣና ምኞታዊ ፖለቲካ እየተናነቀን መገኘቱ ነው፡፡ ለውጡን እጅግ በጣም አሳሳቢ የሚያደርገው ደግሞ አሁን አገራችን ውስጥ በየቦታውና በየቀኑ የሚታየውን አለመረጋጋት፣ መፈናቀል፣ ውድመት፣ ጥቃት፣ ሁከትና ግርግር እያመነጨ የሚዘረግፈው ሁኔታችንና አሰላለፋችን ነው፡፡

 

የለውጥ ተቃዋሚዎች መፈክርና ዓላማ፣ እንዲሁም ዝርዝር ምክንያት ገና ፈርጦ የወጣ ባይሆንም የዚህ ጎራ ችግር ለ“እናሸንፋለን፤አንጠራጠርም” ብቻ የሚተው ቀላልና ተራ ነገር አይደለም፡፡ የተጀመረውን ለውጥ አሳሳቢ የሚያደርጉትና ለአደጋም ያጋለጡት የለየላቸው የለውጥ ተቀናቃኞች ብቻ አይደሉም፡፡ በለውጥ ፈላጊውም ረድፍ ውስጥ ኢሕአዴግን በመቀበል የተጠመዱና በዚህ የሰከሩ፣ የለውጡን ዋነኛ ባህሪና ፀጋ ማለትም በሕገ መንግሥቱ ውስጥ ሆኖ ለውጥ ማራመድንና ማምጣትን፣ ስለዚህም ሕገ መንግሥቱን የሚቃወሙ ትርጉም ስለሌለውና ሕገ መንግሥቱን አሽቀንጥረው ካልጣሉት በስተቀር ዕውን ስለማይሆነው “የሽግግር መንግሥት” የሚያወጉ፣ የለውጡ አደጋዎች ናቸው፡፡

 

በደም ፍላት ከታወረና ከሰከረ፣ ጥቃትን፣ ጥላቻን፣ ውድመትን የትግል ዘይቤው ካደረገ አፍላ ጊዜ ውስጥ ወጣን ብንልም፣ ሕግ የማስከበር ተግባር በጉልበተኞች እጅ ሲገባ በዓይናችንና በሕይወት ጭምር እየመሰከርን ነው፡፡አምባገነንነት አይዞህ ባይ እንዲያጣ፣ አድራጊ ፈጣሪነት ሕዝብን መፍራት እንዲጀምር፣ ለአድራጊ ፈጣሪነት ሕጋዊነትን ማቀዳጀት እንዲቀር እንጂ፣ የሕግ አስተዳደር ድራሹ ጠፍቶ ዘልማድ እንዲሻርና ሥርዓት አልበኝነት እንዲነግሥ አልታገልንም፡፡ በትግሉ ውስጥ የታየው ጥቃት ጥላቻና አውዳሚነት የወንጀል መከላከል፣ የፍርድና የፍትሕ ሥርዓቱ አካልና መሣሪያ ይሁን አላልንም፡፡  ሻሸመኔ ላይ የታየውን አሰቃቂና አረመኔያዊ ወንጀል መፈጸም እስኪቻል ድረስ ከልካይና ሃይ ባይ የታጣው፣ በ“እንቁላሉ ጊዜ ልክ አይደለም” እያልን መናገርና ማሳፈር ባለመቻላችን ነው፡፡ የዚህ ዳተኝነት ዋና ማዕዘን ደግሞ በዓይነ ደረቅነት ወይም በምኞታዊነት ውስጥ የመደበቅ ግትርነት ነው፡፡

 

በብሔርተኛነት የተሟሹ ማኅበራዊ አዕምሮዎች በደሩበት (ኅብረ ብሔራዊ የጋራ ትግል በደከመበት) እና ዴሞክራሲ ከይስሙላ ባላለፈበት አገር ውስጥ ደግሞ እንኳን ሥልጣን ግለሰባዊ ፀቦች ሳይቀሩ በብሔረሰቦች ዓይን እየታዩ፣ የጅምላ አምባጓሮና የሰፋ ግጭት መክፈቻ እስከመሆን ድረስ ችግር ያባዛሉ፡፡ እነዚህን መሰል ችግሮችን ሁሉ የማስወገድ ሥራ በየብሔርተኛነት ከተጣበበ አዕምሮና ፖለቲካዊ አደራጃጀት መውጣትንና ከወገንተኛነት በፀዱ አውታራት ላይ ዴሞክራሲን መገንባት ይጠይቃል፡፡ ራስን ማታለል ካላማረን በቀር ደግሞ በኢትዮጵያ እስካሁን በብሔረተኛ ሩጫዎች ያገኘናቸው ልምዶች ይህንን እውነት ለመገንዘብ አያንሱንም፡፡

 

ሕገ መንግሥቱን እናሻሽል ከማለት በፊት ለዴሞክራሲ ድል ግድና ተቀዳሚ የሆኑ በሕገ መንግሥቱ ውስጥ የሚቻሉ ተግባሮች አሉ፡፡ አዘላለቃችንን የሚወስኑና አደጋዎችን ለማምከን የሚረዱ መሠረታዊ ጉዳዮች ላይ ሳይረባረቡ ወደ ሕገ መንግሥት ማሻሻል አወዛጋቢ ጉዳይ መግባት፣ የትግሉን ኃይል ክፉኛ ይከፋፍላል፡፡ በአሁኑ ጊዜ አስቸኳይ በሆነው ፓርቲያዊነት ባልተጠናወታቸው አውታሮች ላይ፣ ዴሞክራሲን መሠረት በማስያዝ ለውጥ ላይ ትኩረትን ማሰባሰቡ በጣም ተመራጭ ነው፡፡ ይህም ባለው ሕገ መንግሥት ውስጥ ከኢሕአዴግ የለውጥ ኃይሎች ጋር የሚቻል ነው፡፡

 

እሳትና ጭዳቸው ወጥቶ የነበሩ ቡድኖች አገር ቤት እየገቡ ነው፡፡ እነዚህ ቡድኖች ውስጥ በሕግ ሽብርተኛ ተብለው የተፈረጁ፣ በፍርድ የሞት ቅጣት የተወሰነባቸውን መሪዎቻቸውም ይገኙበታል፡፡ እነዚህ ሁሉ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊካንና አገርን መገንባትን ጉዳያችን ብለው የተሰባሰቡበት፣ በሕገ መንግሥቱ ውስጥ የሚንቀሳቀሱበት፣ ነፃ የብዙኃን ማኅበራትና ነፃ የሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ተሳትፎዎች የሚፍለቀለቁበት መልካም የፖለቲካ አየር መፍጠር የመጀመርያው ግዳጃቸው ነው፡፡ የፖለቲካ ወገንተኝነት የሌላቸውና የማይነካኳቸው፣ የዴሞክራሲ ተቋማትንና አውታራትን ማሰናዳት የሚቻላቸው እንዲህ ያለ የፖለቲካ አየር ሲፈጠር ነው፡፡ ሕግ ማክበርንና ማስከበርን፣ ሕገወጥነትን መግታትን ባልዘነጋ በዚህ የፖለቲካ አየር ውስጥ ደግሞ ከሁሉም በላይ ከቡድኖች የፖለቲካና የድምፅ ትርፍ ይልቅ ለጤናማ፣ ደህነኛ የሰላማዊ የምርጫ ዘመቻና ላልተጭበረበረ ነፃ የድምፅ አሰጣጥ ሥር መያዝ መጨነቅን ያበለጠ የኅብረተሰብ ንቃተ ህሊናንና ግንዛቤን የማጎልበት ሥራ ማከናወን ይቻላል፡፡ ቀላልም ይሆናል፡፡

 

አገር ውስጥ ያሉና ውጭም የነበሩ ስለመከረኛው የሽግግር መንግሥት፣ ስለብሔራዊ የዕርቅ መንግሥት፣ ወዘተ. ጥያቄ/ስብሰባ ጉባዔ ሲያነሱና ሲጥሉ ይሰማሉ፡፡ ይህን ጥያቄ‹ውድቅ የሚያደርገው ከዚህ ቀደም ኢሕአዴግ የሽግግር መንግሥትን ጥያቄ ያጥላላው ስለነበር፣ አሁን ደግሞ በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ በአሜሪካ የዋሽንግተን ስብሰባ መልስ ላይ “ግዴላችሁም አያዋጣም እኔ ሽግግር እሆናችኋለሁ” ስለተባለ ብቻ አይደለም፡፡ የሽግግር መንግሥት ጥያቄ እንደ እውነቱ ከሆነ ያለውን ሕገ መንግሥት እንዝለለው፣ እንለፈው ማለትን መንደርደሪያውና ግቡ ያደረገና ሁኔታው ከባሰም በሥርዓት ቅልበሳና ወይም በፀረ ሕገ መንግሥትነት መከሰስ መኮነንን ስለሚያስከትልም ጭምር ነው፡፡

 

ዛሬም በአዲሱ የዓብይ አህመድ  ጅምር የለውጥ ሒደት ውስጥ በሥርዓት ቅልበሳና በፀረ ሕገ መንግሥትነት ውግዘትና ፍረጃ ማምጣት የቻሉ አንዳንድ ያልተወደዱ ባህሪዎች፣ ኢሕአዴጎች ውስጥ ቃላትና መግለጫ መወራወርን ሲያመጡ ዓይተናል፡፡ እኒህን መግለጫዎች መሰረት ያደረጉ የጸጥታ መታወኮችንም ቀምሰናል። እንዲህ ባለ ሁኔታ ውስጥ እንዲያውም ቀደም ብለን ከላይ እንደገለጽነው የሕገ መንግሥቱን መዝለቅ፣ የህልውናቸው ዋስትና አድርገው የሚያዩና በለውጡ ውስጥ አሠላለፋቸው ገና ያልለየላቸው ወገኖች በሕገ መንግሥት ይከበርና ሕገ መንግሥታዊ መብታቸውንና ነፃነታቸውን በማስተግበር ስም በአገር ህልውና ላይ አደጋ ሊጠሩ፣ የሚንቀለቀል እሳት ሊጭሩ የሚችሉ ሃይሎችንም ታዝበናል፡፡ ከሐምሌ 28 ቀን 2010 ዓ.ም. ጀምሮ ሶማሌ ክልል የሆነው የዚህ ሙከራ ነው የሚሉ ጥቂቶች አይደሉም፡፡

 

ይህንን አደጋ ደግሞ ይበልጥ ያባባሰውና የሚዘገንን ግፍ እንዲያስመዘግብ ያደረገው በተለይም የታጠቀ የክልል ኃይል፣ ብሔርተኛና ፖለቲከኛ በመሆኑ ነው፡፡ ይህንን ግን ሕገ መንግሥቱ ራሱ ያፈራው ዕዳ ነው የሚሉም አሉ፡፡ ሕገ መንግሥቱ በዚህ ሁሉ የምዕራፍ ሦስት ሰብዓዊ መብት ድንጋጌዎቹ ተመሽጎ እያለ፣ እያንዳንዱን ክልል ከሌላው አንፃር “እኛ” እና “እናንተ”፣ በእያንዳንዱም ክልል ውስጥ በራሱ ባለቤትና ባዳ፣ ነዋሪና መጤ ያደረገ ሥርዓት መነሻ በጭራሽ አይደለም፡፡ ሊሆንም አይችልም፡፡ ይህን አደጋ ያመጣው ከይዘቱ ይልቅ የሕገ መንግሥቱ አያያዝ እና የሰጎን ፖለቲካ  ነው፡፡

 

ሕገ መንግሥቱ ከታች ጀምሮ እስከ ክልል፣ ከክልል እስከ ፌዴራል ደረጃ ያሉ የሥልጣን አካላት በሕዝብ ወሳኝነት እንዲደራጁና እንዲመሩ ይደነግጋል፡፡ ክልል ገብ ጉዳዮችን ለክልሎች፣ ክልል አለፍና ከክልል አቅም በላይ የሆኑ ጉዳዮችን ለፌዴራል ማለትም ለማዕከላዊ ለያይቶ የሰጠ ሕገ መንግሥት ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ሕገ መንግሥቱ የኢትዮጵያ ሕዝቦችን አስማምቶ ለማስተዳደር በፍፁም አያንስም፣ አይጠብም፡፡  

 

በሌላ በኩል እኛን የሚያሳስበን እና እያሰጋን ያለው ነገር ውሸቶች እና አሉባልታዎች በተወሰኑ የሀገሪቱ አካባቢዎች ውስጥ በሕዝቦች መካከል አለመረጋጋትን፣ የኃይል እርምጃ መውሰድን፣ ሞትን፣ እልቂትን እና መጠነ ሰፊ የንብረት እና የሀብት ውድመትን እንዲያስከትሉ ሆነው በጥቅም ላይ እየዋሉ የመገኘታቸው ሁኔታ ነው፡፡

የአሉባልታ መሳሪያው ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድን እና የመንግስታቸውን ሕጋዊ ቅቡልነት ለማሳጣት እና ወገን እና ሀገር ወዳዱ መሪ በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ውስጥ እየተካሄደ ባለው ሰላማዊ የለውጥ ሂደት አንጸባራቂ ኮከብ በመሆን የተጎናጸፉትን ከፍተኛ የሆነ የሕዝብ አመኔታ ለመሸርሸር እና ለማጥፋት ሲባል ሆን ተብሎ ታስቦበት፣ በስሌት እና በታቀደ መልኩ እየተካሄደ ያለ መሰረተ ቢስ ዘመቻ እንደሆነ መገመት አይከብድም፡፡

አሁን በሃገራችን የግለሰቦች እና የፕሬስ ነጻነት ድሎችን ለማጠናከር መልካም አጋጣሚ አግኝተናል፡፡ የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ እና የሕዝባዊ ተጠያቂነትን ለመመስረት እና ተቋማዊ ለማድረግ መልካም አጋጣሚ አግኝተናል፡፡ ሰብአዊ መብቶች ዋጋ የሚያገኙበት እና የሚከበሩበት ባህልን ለመመስረት መልካም አጋጣሚ አግኝተናል፡፡ ሁሉንም ነገር እንደ ዋስትና መውሰድ አንችልም፡፡ ነጻነትን ለማግኘት ከባድ ነገር ነው፡፡ ሆኖም ግን ነጻነትን ለማጣት ቀላል ነገር ነው፡፡ ስለዚህ ሁሉም ኢትዮጵያውያን ዓይኖቻቸውን ካገኘነው ስጦታ ላይ ሊተክሉና ከሰጎን ፖለቲካ ሊወጡ ይገባል፡፡

 

በህብረተሰብ ውስጥ ዘለቄታዊ ሰላምን ለማምጣት ጥይትን ሳይሆን የምርጫ ካርድን መጠቀም እንዳለብን ታላቁ አፍሪካዊ መሪ አስተምረውናል፡፡ አዲስ የወደፊት እኩልነት እና ለሁሉም ሕዝቦች ፍትህ ለማምጣት የሚቻለው በእውነት እና በብሄራዊ እርቅ ብቻ ነው፡፡ ሁላችንም መናገር እና መፍትሄዎችን መስጠት አለብን፡፡ ከሁሉም የበለጠ ደግሞ ኢትዮጵያ ከአምባገነናዊ ስርዓት ወደ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት እንድትሸጋገር ለማገዝ የእራሳችንን ሚና መጫወት አለብን፡፡

በአሁኑ ጊዜ ኢትጵያውያንን እንደገና በመከፋፈል ለመግዛት በመሞከር ላይ የሚገኙት የጨለማው ጎን ኃይሎች እራሳቸውን ተከፋፍለው፣ ስርዓት አጥተው፣ ተበታትነው፣ በተሳሳተ ሀሳብ ላይ ወድቀው፣ ተስፋ ቢስ እና ስሜታዊ ሆነው አገኙት፡፡

በአንድነት፣ በወንድማማችነት፣ በእህትማማችነት እና በኢትዮጵያዊነት መንፈስ እንዲህ በሙሉ እና በቅርበት ሆነን የመታየታችን ሁኔታ እንዴት እጅግ እንደሚያስደስተን እና አነርሱ ደግሞ በተስፋየለሽነት እና በአግራሞት ሁኔታ ላይ ወድቀው የሚገኙ መሆናቸውን መመልከት በጣም ስሜትን የሚቀሰቅስ ሁኔታ ነው፡፡

ምንም እንኳ እንደ ገና ዳቦ ብንቆራረስ እና ብንከፋፈልም ሁላችንም በአንድ ዕጣ ፈንታ ስር ያለን አንድ ኢትዮጵያውያን ሕዝቦች ነን፡፡

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy