Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ለሰላማዊው አውድ

0 312

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ለሰላማዊው አውድ

                                                       ደስታ ኃይሉ

መንግስት የዴሞክራሲ ምህዳሩን ለማስፋት አልሞ እየሰራ ያለበት ወቅት ቢኖር አሁን ነው ማለት ይቻላል። ይህ ሁኔታም አገራችን እየተከተለች ባለችው የይቅርታ፣ የመደመርና የፍቅር አስተሳሰብ ሳቢያ፤ ባለፉት ዓመታት በተለያዩ ምክንያቶች ከአገራቸው የተሰደዱ ዜጎች ወደ አገራቸው ገብተው የያዙትን ሃሳብ በሰላማዊ መንገድ እንዲገልጹና የተያያዝነውን የለውጥ መንፈስ እንዲደግፉ በማድረግ እየተገለጸ ነው። ይህ ከአገራችን ታሪካዊ ዳራ አኳያ ስንመለከተው ታላቅ ለውጥ ነው።

የኢትዮጵያ መንግስት የፖለቲካ ምህዳሩ ይሰፋ ዘንድ በአመለካከታቸው ወይም በፖለቲካ አቋማቸው የተሰደዱና ከአገር የወጡ ዜጎችን በየደረጃው ጥሪ አድርጎ በአሁኑ ወቅት አክቲቪስቶችን ጨምሮ ማንኛውም ዜጋ ነጻ ሃሳቡ በምንም ሁኔታ ሳይገደብ እንዲያቀርብ እያደረገ ነው። ይህም የለውጥ አመራሩ ምን ያህል በሃሳብ የበላይነት የሚያምን እንዲሁም ነገሮችን በሰለጠነ መንገድና አገርን በሚጠቀም ሁኔታ ይዞ እየሰራ እንደሆነ የሚያረጋግጥ መሆኑን የሚያራግጥ ይመስለኛል።

በአሁኑ ሰዓት በውጭ የሚገኙ በርካታ ቁጥርና የተለያየ የፖለቲካ አቋም ያላቸው ሃይሎች ወደ ሀገር ቤት ገብተው በተፈጠረው ምቹ ሁኔታ በሰላማዊ መንገድ ለመንቀሳቀስ ፍላጎት ያላቸው መሆኑን በይፋ እንዲገልጹ እየተደረገ ነው። እንደ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ያሉ የፖለቲካ ሃይሎች በስማቸው በህገ ወጥ ተግባር የሚንቀሳቀሱ አካላትን እያወገዙ ነው። በአቶ ዳውድ ኢብሳ ሚመራው ኦነግ በቅርቡ እንደገለጸው፤ ወደ ትክክለኛ ዴሞክራሲ ለመሸጋገር የሚደረገውን ጥረት የሚያደናቅፍ ህገ ወጥ ድርጊትንና ስርዓት አልበኝነትን በመከላከል የህግ የበላይነት እንዲከበር ይሰራል።

በኦነግ ስም የሚደረጉ ማናቸውንም ህገ ወጥ ድርጊቶች ለማስቆምና የህግ የበላይነትን ለማስከበር እንደሚሰራም አስታውቋል። ኦነግ የኦሮሞን ህዝብ ሰላምና ደህንነት ለማደፍረስ ሳይሆን ህዝቡን ከስጋት እና ሮሮ በማውጣት፣ ለህዝቡ የሚመኝለትን ሰላም እና ዴሞክራሲ ለማጎናጸፍ መቋቋሙንም አስረድቷል። ሰላምን ለማወክ እንደማይንቀሳቀስ የገለጸው ግንባሩ፤ የኦሮሞን ትግል ለማደናቀፍ በኦነግ ስም የሚደረጉ ህገ ወጥ ድርጊቶች ድርጅቱን የሚወክሉ አይደሉም ብሏል። እንዲህ ዓይነቱ በድርጅቶች ውስጥ የሚታየው ሰላም ወዳድነት እየተጠናከረ በሄደ ቁጥር የአገራችንን ዴሞክራሲ የሚያጎለብትና ሰላማዊው አውድ ይበልጥ እንዲጠናከር የሚያደርግ ነው።

ስለሆነም ከውጭ የገቡ የፖለቲካ ሃይሎች ለሰላማዊ አውድ መጠናከር መስራት ይኖርባቸዋል። ይሁን እንጂ ያለ ህዝቡ ተሳትፎ ሰላምን እውን ማድረግ ስለማይቻል ህዝቡ ሰላሙን በራሱ እንዲጠብቅ የተለመደውን ተግባሩን እንዲወጣ ማድረግ ያስፈልጋል።

እርግጥ ያለ ህዝብ ተሳትፎ ሰላምን ማምጣት አይቻልም። እናም ህዝቡ ምናልባት ጥያቄዎች ቢኖሩት እንኳን በሰላማዊና አግባብ ባለው ሁኔታ የማቅረብ ባህልን ሊገነባ ይገባዋል። ጥያቄዎች የሚመለሱት በሰላማዊ መንገድ እንጂ ህግን በመጣስ አይደለም። ህግን ጥሶ መገኘት ለሰላማዊ ጥያቄዎች ማስፈፀሚያ ሊሆን አይችልም። ሆኖም አያውቅም። ጥያቄዎችን ህገ መንግስታዊ ሥርዓቱ በሚፈቅደው፣ በተቀመጠው አሰራርና የህግ ማዕቀፍ መሰረት ማቅረብ ተገቢ ነው።

ሰላምን ማጣት የሀገርን ዕድገትን ሁለንተናዊ እድገት በመጎተት ዋጋ ያስከፍላል። ስለሆነም ህዝቡ አሁንም ቢሆን ለሰላምና መረጋጋት በቂ ትኩረት መስጠት ብቻ ሳይሆን ሰላምና መረጋጋትን ሊያሳጡን ከሚችሉ ሃይሎች ራሱን መጠበቅ ይኖርበታል። ምንግዜም በአካባቢው የሚፈፀሙ ተግባሮች ምን ያህል ሰላማዊና ህጋዊ መሆናቸውን ማረጋገጥ አለበት።

ሰላምን የማይሹ ሃይሎች ዋነኛው ግባቸው በአገሪቱ ሰላምና መረጋጋት እንዳይኖር፤ በሰበብ አስባቡ ማንኛውም መንግስታዊ ስራ በመደበኛ መልኩ እንዳይሰራ ማወክ፤ የመማር ማስተማሩ ሂደት እንዲስተጓጎል ማቀድ፤ የንግድ ልውውጥና ግብይት ላይ ሳቦታጅ መፍጠር፤ ህብረተሰቡ ውስጥ ህግ እንዲሸረሸር ማድረግ፤ የመንግስትና የግለሰብ ንብረቶችን ማውደም …ወዘተ ግቦችን በመያዝ አሁን የተጀመረውን ለውጥ ለማደናቀፍ መጣር ነው። ይህን ህዝቡ በሚገባ ማወቅ አለበት። እንዲህ ዓይነት ህግና ስርዓትን ያልተከተሉ ሁኔታዎችን በሚያይበት ሰዓት ከህግ የበላይነት አኳያ የሚስተካከሉበትን መንገድ መሻት አለበት።  

የአገራችን ሰላም በተለይም ባለፉት አራት ወራት በጥሩ መሰረት ላይ እየተገነባ መጥቷል። የህዝቡ አንድነትም እየተጠናከረ ነው። ኢትዮጵያዊነትም እያበበ ነው። ሰላማችን ሰላም በአንፃራዊነት እየጠበቀ ነው።

በየትኛውም ማህበረሰብ ውሰጥ ሰላም ያለው እሴታዊ ዋጋ የሚታወቅ ቢሆንም፤ የተረጋጋና አስተማማኝ ሰላም ያላቸው ሀገራት ሰላማቸው በጥቂት ጊዜ ውስጥ ሲደፈርስ ብሎም በትርምስና ሁከት ውስጥ ሲቆዩ የተመለከትናቸው አጋጣሚዎች ጥቂት አይደሉም። ይህም የህዝብን ተጠቃሚነት በማገድና የደቦ ፍርድ በመስጠት ሲንጸባረቅ እንደነበር እናስታውሳለን።

የአገራችን ሰላም የተገነባው በህዝቦች ፅኑ ፍላጎት ነው። ይህ ደግሞ ባለፉት አራት ወራት ተረጋግጧል። በአሁኑ ሰዓት በአጭር ጊዘዜ ውስጥ አገራችን ለወደፊቱ ብሩህ ተስፋ ካላቸው የአፍሪካ ሀገራት አንዷ መሆን ችላለች። ይህንንም የተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ከእኛ ጋር አብረው ለመስራት በሚያሳዩት ፍላጎት ማረጋገጥ የሚቻል ይመስለኛል። ሰላማችን በአንጻራዊነት እየተረጋገጠ በመምጣቱ ተቋማቱ ከእኛ ጋር ለመስራት ያላቸውን ፍላጎት እያሳዩን ነው።

አገራችን ውስጥ ግጭቶች ቢከሰቱም የለውጡ አመራር ግጭቶቹን በህገ መንግስቱና ማህበረሰቡ ባካበታቸው የግጭት አፈታት መንገዶች በጥንቃቄ መፍታት በመቻሉ ሰላምን በአንጻራዊነት ማረጋገጥ ችሏል። በጌዴኦና በጉጂ ብሔረሰቦች መካከል የተፈጠረውን ችግር ለመፍታት የለውጥ አመራሩ የሄደበት መንገድና ሁለቱ ብሔረሰቦች ወደሚኖሩበት ቀዬ እንዲመለሱ መደረጉ የዚህ እውነታ አስረጅ ነው።  

የለውጥ አመራሩ ካለፉት ጊዜያት ጋር ፈፅሞ በማይገናኝ መልኩ ለዚህ ነባራዊ ችግር ትኩረት ሰጥቶ በመስራቱ ሁኔታውን በመለወጥ ላይ ይገኛል። የሀገሪቱ ህዝቦች ያላቸውን የተፈጥሮ ሃብት በአግባቡ እንዲጠቀሙና ከሌሎች ህዝቦች ጋር በመተሳሰብ የጋራ ሀብታቸው እንዲሆን ለማድረግ ጥረት እያደረገ ነው።

እስካሁን የተደረጉት ጥረቶች አንፃራዊ ሰላም በማምጣት ዜጎች በዴሞክራሲ ምህዳሩ ውስጥ እንደልባቸው እንዲሳተፉ እየተደረገ ነው። በተለይም በውጭ ይንቀሳቀሱ የነበሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ይህን ሰላማዊ አውድ በመጠቀም ወደ አገር ውስጥ በመግባት እየተንቀሳቀሱ ነው። ይህ እንቅስቃሴያቸው የተገኘውን ሰላማዊ አውድ የሚደግፍ መሆን አለበት። ሁሉም አካል ለአገራችን ሰላማዊ አውድ መረጋገጥ ከሰራ ዴሞክራሲውም በዚያው ልክ ሰፍቶ ተጠቃሚ መሆን ይችላል።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy