Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ለውጡ መዋቅራዊ እንጂ የቀለም ለውጥ አይደለም

0 1,690

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ለውጡ መዋቅራዊ እንጂ የቀለም ለውጥ አይደለም

አሜን ተፈሪ

አዲሱ አመራር በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚ እና በማህበራዊ ዘርፎች የሚወስዳቸው የለውጥ እርምጃዎች፤ አንዳንዶች እንደሚሉት ገና በመልካም ቃላት ወይም በቀለም ቅብ ሥራዎች የተወሰኑ አይደሉም፡፡ ይልቅስ ገና ከመነሻው ጀምሮ አዲሱ አመራር ህገ መንግስቱን ጭምር የማሻሻል ፍላጎት ሲገልጽ፤ በአመለካከት ደረጃ የያዛቸው መሰል አቋሞች በግልጽ የሚየሳዩት አመራሩ ለለውጥ ከፍተኛ የፖለቲካ ቁርጠኝነት እንዳለው እና እነዚህ አቋሞቹ መዋቅራዊ እርምጃዎችን የሚጋብዙ እንጂ በቀለም ቅብ ሥራ የሚወሰኑ የለውጥ እርምጃዎች አለመሆናቸውን ነው፡፡ አዲሱ አመራር መዋቅራዊ የማሻሻያ እርምጃዎችን ለመውሰድ የሚያበቃ የፖለቲካ ቁርጠኝነት እንዳለው፤ አመራሩ በተለያዩ አግባቦች ከሚያከናውናቸው በርካታ ነገሮች መረዳት እንችላለን፡፡

ሌላው ቀርቶ፤ አዲሱ አመራር ድርጅቱን ‹‹ሪፎርም›› ለማድረግ ሲነሳ፤ ራሱን ለአደጋ በሚያጋልጥ በአደገኛ ሁኔታ ውስጥ ሆኖ መሆኑ፤ ለለውጡ ምን ያህል ቁርጠኛ እንደሆነ በግልጽ ያመለክታል፡፡ አዲሱ አመራር  በጥንቃቄ እና በድፍረት በመንቀሳቀሱ እና በፍጥነት የህዝብ ድጋፍ በማግኘቱ አደጋውን ተሻገረው እንጂ ብዙ ሳይራመድ ሊጨፈለቅ የሚችልበት ሰፊ ዕድል ነበረ፡፡ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ተንቀሳቅሶ ለውጥ ለመፍጠር ጥረት ሲያደርግ፤ ብዙዎች ከሚገምቱት ውጪ በሆነ መጠን በሚመራው መንግስት ተፈጸሙ የሚላቸውን ወንጀሎች በግልጽ እየጠቀሰ እና በጥፋቱም ይቅርታ እየጠየቀ ነበር፡፡ ለለውጡ ምን ያህል ቁርጠኛ እንደሆነ በግልጽ ያመለክታል፡፡  

በሌላ በኩል፤ በተለያዩ አጋጣሚዎች አመራሩ በሚያቀርባቸው ገለጻዎች እና በአጠቃላይ ዝንባሌው ካለፈው የአስተሳሰብ እና የአካሄድ ዘይቤ፤ በሐቲትም ሆነ በድርጊት ራቅ ያለ መሆኑን ስንመለከት አዲሱ አመራር የሚወስዳቸው የለውጥ ያደርገው እርምጃች ከመዋቅራዊ ለውጥ ግቢ ሳይደርሱ የሚመለሱ አለመሆናቸውን የሚጠቁሙ ናቸው፡፡ በተጨማሪም፤ ፖለቲካውን በከፍተኛ የሞራል መርህ (ፍቅር፣ ምህረት፣ ይቅርታ፣ መደመር) የሚሰራ መሆኑ እና ሐገሪቱን በግልጽ ከሚታይ ድርስ አደጋ የመጠበቅ ኃላፊነት መሸከሙን የተረዳ አመራር በመሆኑ፤ መዋቅራዊ ለውጥ ለመፍጠር ዳተኛ የሚሆን አይደለም፡፡ በእኔ አስተያየት የመዋቅራዊ ለውጡ ዋነኛ ሞተር ይኸ ቁርጠኝነት ነው፡፡ በተጨባጭ የአቅም ውሱንነት ካልተገደበ በቀር ፈጣን ለውጥ ለመፍጠር ወደ ኋላ የማይል የለውጥ ኃይል ነው፡፡ የለውጡም ዋስትና ይኸው ቁርጠኝነት መሆኑን ክልብ አምናለሁ፡፡

ከዚህ ባሻገር፤ መዋቅራዊ ለውጥ ሲባል የመስሪያ ቤት ኃላፊ መቀየር ወይም አዲስ ቢሮ ማቋቋም የሚመስላቸው በርካቶች ናቸው፡፡  መዋቅር ጸንቶ የሚገኝ አሰራርን የሚወስን አንድ ዓይነት ስርዓት ነው፡፡ አስተሳሰብ ነው፡፡ እሴት ነው፡፡ መርህ፣ ህግ እና ደንብ ነው፡፡ በአጭሩ  መዋቅር አሰራርን፣ የድርጊት ቅደም ከተልን፣ ተግባር እና ኃላፊነትን፣ ተዋረዳዊ እና የጎንዮሽ ግንኙነትን፣ ተገቢ እና ተገቢ ያልሆነ ነገርን ለይቶ የሚያስቀምጥ በግልጽ፤ ዘፈቀዳዊነትን የሚያስወግድ የሚታወቅ የአሰራር   ስርዓት ነው፡፡ በመሆኑም፤ ከፍተኛ የአስተሳሰብ እና የአመለካከት ለውጥ ከተፈጠረ፤ ለውጡ መዋቅራዊ ከመሆን ውጪ ሌላ ዕድል አይኖረውም፡፡ በመሆኑም፤ በጠ/ሚ ዶ/ር ዐቢይ አህመድ የሚመራው ለውጥ፤ በቀለም መቀየር ሊስተናገድ የማይችል እና መዋቅራዊ ለውጥን በሚያስከትል የአስተሳሰብ እና የአመለካከት ዘይቤ የተቃኘ ለውጥ ነው፡፡ ‹‹እንዲያው ይህ ለውጥ መሰናክሎቹን ሁሉ ተሻግሮ ዳር ይደርስ ይሆን?›› ብሎ መጨነቅ ተገቢ ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን ይህ የለውጥ እንቅስቃሴ በመዋቅራዊ ለውጥ የታገዘ ላይሆን ይችላል የሚል ስጋት፤ የለውጡን ምንጭ እና ባህርይ በትክክል ካለመገንዘብ የሚመነጭ ከንቱ ስጋት ነው፡፡

ስለዚህ ነው፤ ‹‹እስካሁን የታየው ለውጥ በመልካም ቃላት ብቻ የተንጠለጠለ ወይም በቀለም ቅብ ሥራዎች የተወሰነ ለውጥ ነው›› በሚል አንዳንዶች የሚያቀርቡት አስተያየት ስሑት እና ውሃ የማይቋጥር አስተያየት አድርጌ የምመለከተው፡፡ ከለውጡ ምንጭ እና ባህርይ፤ እንዲሁም ከአመራሩ ተግባራዊ እንቅስቃሴ እና አመለካከት ጋር ከተያያዘው የፖለቲካ ቁርጠኝነት ባሻገር፤ ተጨባጭ ነገሮችንም በማንሳት፤ የለውጡን መዋቅራዊ ባህርይ ማየት እንችላለን፡፡ ባለፉት አምስት ወራት የተወሰዱትን የለውጥ እርምጃዎች ስንመለከት፤ አዲሱ አመራር ገጽታን በመቀየር የለውጥ ሐዋርያ መስሎ ለመታየት የሚያግዙ ሥራዎችን ሳይሆን መዋቅራዊ ለውጦችን ለመፍጠር እየተረባረበ መሆኑን የተወሰኑ ተጨባጭ ጉዳዮችን በማየት መረዳት እንችላለን፡፡ ከትናንት ወዲያ ከሆነ አንድ ክስተት እንነሳ፡፡

ጠ/ሚ ዶ/ር ዐቢይ አህመድ መስከረም 1/2011 ዓ.ም ከኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ጋር በመሆን በኢትዮ-ኤርትራ ድንበር አካባቢ ከሚገኙ የሁለቱ ሐገራት ህዝቦች እና የመከላከያ ሠራዊቶች ጋር በዓሉን አክብረው፤ የየብስ ትራንስፖርት ግንኙነት መጀመሩን አብስረው ሲመለሱ፤ አዲስ አባባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሆነው በሰጡት መግለጫ፤ በኢትዮጵያ የመከላከያ ሠራዊት መዋቅራዊ ማሻሻያ እየተካሄደ መሆኑን ሳይሆን፤ የመዋቅራዊ ማሻሻያ ሥራው መጠናቀቁን አስታውቀው ነበር፡፡ ዶ/ር ዐቢይ ለዓመታት በምሽግ የቆየው ሠራዊት አባላት መክሳት- መጥቆራቸውን እና ያለ ዕድሜአቸው ያረጁ መሆናቸውን፤ በዚህም ማዘናቸውን ጠቅሰው፤ ‹‹የመከላከያ ሠራዊታችን ካምፕ በመግባት እንዲገግም ይደረጋል›› ካሉ በኋላ፤ ‹‹ከዚያ በኋላ ግን ሠራዊታችን ሙሉ ቁመና ያለው ሰራዊት እንዲሆን እና መለዮውን በትክክል የሚያከብር፤ ሰልፍ የሚያሳምር፣ ነገሮችን የማድረግ ብቃት ያለው፤ ለመዋጋት በቂ ዝግጅት ያደረገ፤ ከተዋጋም የሚያሸንፍ ሆኖ እንዲደራጅ ማድረግ በቀጣይ የምንሰራው ሥራ ይኖራል›› ብለዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ አክለውም፤ ‹‹የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት እንደ አዲስ እንዲዋቀር ተገርጓል›› ያሉ ሲሆን፤ ‹‹በአዲሱ አደረጃጀት መሠረት ያለውን ኃይል ሰብስቦ፣ ራሱን አብቅቶ፣ የኢትዮጵያን ሉአላዊነት ለመጠበቅ እና በልማት ሥራዎቿ በመሳተፍ የህዝቦቿ እና የባንዲራዋ አለኝታ መሆኑን የሚያረጋግጥበት ዘመን ከፊታችን ያለ መሆኑ ይሰማኛል›› ብለዋል፡፡ ይህ መዋቅራዊ የማሻሻያ እርምጃ የመከላከያ ሠራዊቱን ከፖለቲካ ወገንተኝነት የጸዳ፤ የሐገርን እና የህዝብን ሉዐላዊነት ከማስከበር ውጪ ሌላ ግዳጅ የሌለው፤ ከመጣው መንግስት ጋር አብሮ እየመጣ የማይሄድ፤ በህገ መንግስታዊ ግዳጁ ተወስኖ የሚኖር ዘላቂ እና ፕሮፌሽናል ተቋም ሆኖ እንዲደራጅ የማድረግ ሥራን የሚያካትት የመዋቅር ማሻሻያ መሆኑን፤ ጠ/ሚ ዐቢይ መግለጻቸው የሚዘነጋ አይደለም፡፡

ከዚሁ ጋር ተያይዞ ሊነሳ የሚገባው፤ የብሔራዊ መረጃ እና ደህንነትን፤ የህዝብ አመኔታ እና ከበሬታ ያለው፤ ከፖለቲካ ወገንተኝነት የጸዳ እና የህዝብ አለኝታ የሆነ ዘመናዊ ተቋም ሆኖ እንዲደራጅ የማድረግ ሥራው መጀመሩን የድርጅቱ ኃላፊ ጀነራል አደም መሐመድ ባልተለመደ ሁኔታ ህዝቡ ስለ ተቋሙ በቂ ግንዛቤ እንዲያገኝ የሚያደርግ ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ፤ የፖለቲካ ምህዳሩን የሚያጠቡ የዜጎችን ዴሞክራሲያዊ እና ሰብአዊ መብቶችን የሚጥስ ይዘት አላቸው የሚሉ ህጎችን ለማሻሻል በተደረገው ጥረት ከህገ መንግስቱ ድንጋጌዎች ጀምሮ፤ የሽብርተኝነት ህግ፣ የበጎ አድራጎት እና ማህበራት ህግ፤ የፕሬስ ህግ ወዘተ በህግ  ባለሙያዎች እና በተለያዩ ባለጉዳዮች ዳግም እንዲፈተሹ እየተደረገ ነው፡፡ የትምህርት ፖሊሲው፤ የእንባ ጠባቂ እና የሰብአዊ መብት ተቋም፤ የምርጫ ቦርድ፤ ፍ/ቤቶችን ጨምሮ የተለያዩ የፍትህ አካላትን፤ የተወካዮች ም/ቤት አሠራርን፤ የምርጫ እና የፖለቲካ ፓርቲዎችን የተመለከቱ ህጎችን፤ እንዲሁም የኢኮኖሚ ፖሊሲውን የተመለከቱ የማሻሻያ ሥራዎች (ያልተጠቀሱት የሚበዙ ይመስለኛል) እየተሰሩ መሆናቸውን እናውቃለን፡፡

በመንግስት ሚዲያዎች የሚታየው መሠረታዊ የአሰራር ለውጥ እና የገዢው ፓርቲ አባላት ያልሆኑ ሰዎች በተወሰኑ ቦታዎች መሾማቸው እንደ መዋቅራዊ ለውጥ ሊታዩ የሚገባቸው ጉዳዮች ናቸው፡፡ በመሆኑም፤ መንግስት እስካሁን መዋቅራዊ ለውጥ መውሰድ እንዳልጀመረ የሚያስቡ እና ይህን የተመለከተ ትችት የሚያቀርቡ ሰዎች የተሳሳቱ ናቸው፡፡

የፖለቲካ ፓርቲዎች ለሐገሪቱ ችግሮች መፍትሔ ብለው በሚያቀርቧቸው ጉዳዮች ወይም በችግሮቹ ምንጮች ዙሪያ ልዩነት ቢኖራቸውም፤ አብረው መስራት የሚያስችል መንፈስ መፍጠር መቻላቸው እንደ መዋቅራዊ ለውጥ ሊታይ የሚችል ነው፡፡ መንግስት ወይም ገዢው ፓርቲ ለተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ያላቸው አመለካከት ምን ያህል እንደ ተቀየረ  ለመገንዘብ፤ ጠ/ሚ ዐቢይ አህመድ በበዓለ ሲመታቸው ዕለት የተናገሩትን ማስታወስ በቂ ነው፡፡ ባለፉት ወራት ሂደት ጠ/ሚ ዐቢይ አህመድ የሳዩት ነገርም፤ በመጀመሪያው የፓርላማ ንግግራቸው፤ ስለተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች የተናገሩትን ነገር በተግባር የሚተረጉም ነበር፡፡

አሁን በገዢው ፓርቲ እና በተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል የሚታየው ዝንባሌ፤ የጋራ ችግርን በጋራ ለመፍታት ተጋግዘው የሚሰሩ እና በአንድነት መንፈስ ለጋራ ሐገር ጥረት የሚያደርጉ የአንድ ቡድን ተሰላፊዎች እንጂ፤ ለመሸናነፍ የሚጫወቱ ተቀናቃኞች አድርገን እንዳንወስዳቸው የሚያደርግ ነው፡፡ በዴሞክራሲያዊ እሴቶች ዙሪያ የጋራ አመለካከት ሲኖር፤ ገዢው ፓርቲ እና ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች፤ የአንድ ቡድን ተጫዋጮች እንጂ ባላንጣዎች አይሆኑም፡፡ ይህ ሁኔታ እንደ መዋቅራዊ ለውጥ ሊታይ የሚችል ነው፡፡መሆን ይደርሳሉ፡፡

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy