Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ልዕልናው እንዲከበር…

0 347

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ልዕልናው እንዲከበር…

ገናናው በቀለ

የኢፌዴሪ መንግስት የህግ የበላይነትን ከማስከበር አኳያ በርካታ ጉዳዩችን አከናውኗል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በቅርቡ በሰጡት ጋዜጣዊ መገለጫም መንግስት ኡንም የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ የያዘውን ቁርጠኝነት የሚያሳይ ነው። እርግጥ የህግ የበላይነትን በአንድ አገር ውስጥ ማስከበር ለህዝቦችና ለአገር ያለው ጠቄታ ከፍተኛ ነው።

የህግ ልዕልና ካልተከበረ የዜጎች ሁለንተናዊ ጥቅም አደጋ ላይ ይወድቃል። መንግስት የህግ የበላይነትን የማስከበር ሃላፊነትም ሆነ ግዴታ ያለበት አካል እንደመሆኑ መጠን ተግባሩን ይወጣል።

በአሁኑ ሰዓት በተደጋጋሚ እየተጠየቀ ያለውን የሰኔ 16 ቀን 2010 ዓ.ም ሁኔታና የኢንጅነር ስመኘው በቀለን ግድያ ጉዳይንም መንግስት በጥንቃቄ እየመረመረ ይገኛል። ህዝቡም የሚመለከተው አካል ጉዳዩን አጣርቶ እስከሚያቀርብ ድረስ በትዕግሰት መጠበቅ ያለበት ይመስለኛል።

ስለሆነም እዚህ አገር ውስጥ የህግ ልዕልና ለድርድር የማይቀርብ በመሆኑ ህዝቡ መንግስት ይህን አገራዊ ሃላፊነቱንና ግዴታውን ለመወጣት በሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎች ውስጥ የተለመደውን ጉልህ ሚናውን መወጣት አለበት።

ማናቸውም ተግባር ያለ ህዝቡ ቀጥተኛ ተሳትፎ እውን ስለማይሆን፣ የህግ የበላይነት ልዕልና እንዲከበር ህዝቡ የአንበሳውን ድርሻ ወስዶ መንቀሳቀስ ይኖርበታል። ምክንያቱም ህግንና ስርዓትን ማክበር ከአንድ ከሰለጠነ ማህበረሰብ የሚጠበቅ ተግባር ስለሆነ ነው።

እንደሚታወቀው ህገ መንግስታዊ ስርዓቱ ለህግ የበላይነት ቅድሚያ ከመስጠት አልፎ በህገ መንግስቱ አንቀፅ ዘጠኝ ላይ እንዲደነገግ አድርጓል። በዚህ አንቀፅ ስር የህግ የበላይነት በሀገራችን የሚኖረው ሁኔታ በሚገባ ተብራርቷል።

ኢትዮጵያ ያፀደቀችው ህገ መንግስት የህግ የበላይነትን ለማስጠበቅ ሲል ከህግ አግባብ ውጪ ስልጣን መያዝ የተከለከለ መሆኑን ያስረዳል። የትኛውም አካል ህገ መንግስቱ ላይ ከተደነገገው ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር ውጪ ነፍጥ አንግቦ ስርዓቱን በኃይል ለመጣል የሚያደርጋቸው ማናቸውም ተግባራት አይፈቀዱም።

በማናቸውም ቦታ የህግ የበላይነት ልዕልና ካልተጠበቀ በሀገሪቱ የሚረቀቁ ማናቸውም ህጎች በሚፈለገው መጠን ገቢራዊ ሊሆኑ አይችሉም። ህጎች በሚፈለገው መጠን ገቢራዊ ካልሆኑና በቸልታ የሚታለፉ ከሆኑ የዜጎች መብቶች አይከበሩም።

በገ መንግስቱ ላይ የዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች እንዲሁ ለይስሙላ የተደነገጉ አይደሉም። ዜጎች ሰዎች በመሆናቸው ሳቢያ የተጎናፀፏቸው መብቶች ናቸው።

ማንኛውም አካል የህግ የበላይነት እንዳይሸረሸር መፍቀድ አይኖርበትም። እንዲህ ዓይነት ዝንባሌ በሌላኛው እሳቤ የህግ የበላይነት ዕውን እንዳይሆን መፍቀድ ስለሆነ ነው። የህግ የበላይነትን መፃረር ስርዓት አልበኝነትን ይፈጥራል። ስለሆነም ስርዓት አልበኝነት እንዳይፈጠር የህግ የበላይነት ልዕልና መከበር ይኖርበታል።

የህግ ልዕልና ካልተከበረ ከሌለ ሰላም የሚባልን ነገር ማሰብ አይቻልም። ሰላም ከጠፋ ደግሞ ስለ ልማትና ዴሞክራሲ ማሰብ አይቻልም። ፀረ-ዴሞክራሲያዊነት ቦታውን ይረከባል። ይህ ሁኔታ ደግሞ እንደ እኛ ሰላምን፣ ልማትንና ዴሞክራሲን ለማሳለጥ በለውጥ ጎዳና ላይ ለሚገኝ አገር እንቅፋት ነው።

ኢትዮጵያ ሰላምን በማረጋገጥ ሂደት ውስጥ ለብሔራዊ ደህንነቷ ስጋት የሆኑ እንቅስቃሴዎችን መከላከልና መቆጣጠር ያስችላት ዘንድ የህግ የበላይነትን ማረጋገጥ ይኖርባታል። ይህ ካልሆነ የተጀመረው ለውጥ የታሰበለትን ግብ ሊያመጣ አይችልም።

ህግና ስርዓት ባልተተገበረበት ሁኔታ ዜጎች በሰላም ስራቸውን አያከናውኑም። ይህም የአገራችን እድገት የሚጎትት ነው። ስለሆነም ሁሉም ህግንና ስርዓትን በማስከበር የድርሻውን ተግባር መወጣት አለበት።

ሰላምን ለማምጣት የህግ የበላይነትን ማክበር ያስፈልጋል። ስለሆነም በሰላሙ ላይ የማይደራደርና ለግጭት ኃይሎች የሚሆን ምቹ ምህዳር የማይፈጥር ህዝብ እንዲኖር መንግስት ይፈልጋል። በአንዳንድ አካባቢዎች የሚታዩት የህግ የበላይነትን የሚጥ ጉዳዩች ሰላምን የሚያኮሰምኑ ናቸው።

ከግጭት የሚገኝ ምንም ዓይነት ጥቅም እንደሌለ ማንም የሚያውቀው ነው። የግጭቱ አራማጆችም ጥቅሜ ተነካ የሚሉ ሃይሎች እንጂ ህዝብ አይደለም። ሊሆንም አይችልም። ማንኛውም ህዝብ የሚፈልገው ሰላምን ስለሆነ ነው።

ኢትዮጵያ የጀመረችው የዕድገትና የዴሞክራሲ ሥርዓት ባህል ግንባታ ሂደት ስኬታማ ሆኖ እንዲቀጥል፤ አስተማማኝ ሠላም የሰፈነበት ምህዳርን መፍጠር የግድ ነው። ምክንያቱም ሀገራችን ፈጣን ልማትን ማምጣትና ከተመፅዋችነት መላቀቅ ብሎም ዴሞክራሲን መገንባት የሞት ሽረት ያህል የህልውና ጉዳይ አድርጋ ስለያዘችው ነው።

ታዲያ ሰላምን በማረጋገጥ ሂደት ውስጥ ለብሔራዊ ደህንነቷ ስጋት የሆኑ እንቅስቃሴዎችን መከላከልና መቆጣጠር ያስችላት ዘንድ የህግ የበላይነትን ማረጋገጥ የግድ ይላታል።

የህግ የበላይነት ሲኖር ሁላችንም ከሚገኘው ሀገራዊ ጥቅም ተካፋዩች እንሆናለን። የህግ የበላይነት በህገ መንግስቱ ላይ የተረጋገጠ ብቻ ሳይሆን፤ ለአገራችን ጠቃሚነቱ ታምኖበት እንዲተገበር ምክንያት የሚሆን ነው። ህግና ስርዓትን የበላይ አድርጎ መመልከት ሰላምን፣ ልማትንና ዴሞክራሲን የሚያፀና ነው።

ዛሬ ኢትዮጵያ ውስጥ የግልና የቡድን መብቶችን ያጣመረ ዴሞክራሲን እየተገነባ ነው። እነዚህና ሌሎች ዓለም አቀፍ የዴሞክራሲያዊና የሰብአዊ መብት እምነቶች ለህዝብ ቀርበው እስከ ታች ድረስ የወረደ ሰፊ ውይይት ተካሂዶባቸው ማሻሻያ ከተደረገባቸው በኋላ፤ በህገ መንግስትነት እንዲፀድቁና ህዝቡ በፍላጎቱ እውን እያደረጋቸው እንዲመጣ የሚያደርግ ነው።

ቀደም ባሉት ጊዜያት ተነፍገው የነበሩት የግለሰብ መብቶች ከቡድን መብቶች ጋር ሚዛናዊ በሆነ ዕይታ መሳ ለመሳ እንዲሄዱ ይደረጋል። እነዚህ ሁሉ የሚተገበሩት የህግ ልዕልና በተገቢው መንገድ ሲረጋገጥ ነው።

የህግ የበላይነት እንደ አገር እንድንቀጥል የሚያደርገንና ስርዓት አልብኝነትን ተቃውመን አንድንቆም ያደርገናል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በቅርቡ በሰጡት መግለጫ ላይ መንግስት የህግ የበላይነትን ለማስከበር ቁርጠኛ መሆኑን አስታውቀዋል። ይህ ቁርጠኝነት በህብረተሰቡ ሊታገዝ ይገባል። ስለሆነም ዜጎች ህግንና ልዕልናውን ከሚጋፉ ተግባራት በመታቀብና ለሌሎችም አስተማሪ በመሆን አገራዊ ሃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል።

    

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy