Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

መንግሥት የዜጎችን በህይወት የመኖር መብት ማረጋገጥ እንደሚገባው ተጠቆመ

0 1,174

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

አዲስ አበባ፡- በየጊዜው እየጨመረ በመጣው ብሔር ተኮር ጥቃት የዜጎች ህይወት እየጠፋና አሳሳቢ እየሆነ በመምጣቱ መንግሥት የዜጎችን በህይወት የመኖር መብት ማስጠበቅ እንደሚገባው ምሁራን አሳሰቡ፡፡
በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ ሀሳባቸውን ያካፈሉት የወልዲያ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር አቶ ኑሩ አህመድ እና አንትሮፖሎጂስት ዶክተር ገረመው ዱቃ የህዝቡን የእርስ በእርስ የመተማመን መንፈስ እንዳይጠፋ መንግሥት የህግ የበላይነትን ማስከበር እንደሚገባው ገልጸዋል፡፡
መንግሥት ህጋዊ እርምጃ ለመውሰድ ያሳየው ቸልተኛነት የሰዎችን በህይወት የመኖር መብት አደጋ ላይ እየጣለው እና በሥርዓት አልበኞች ላይ እርምጃ ባለመውሰዱ የህግ የበላይነት እንዳይከበርና ሥርዓት አልበኞች የልብ ልብ እንዲሰማቸው እንዳደረገ አቶ ኑሩ ተናግረዋል፡፡ እንዲሁም መንግሥት ለህዝቡ ቃል ከመግባት ባለፈ ወደ ተግባር በመግባት የህዝቡን ሰላም ሊያስጠብቅ እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡
በአገሪቱ እየተከሰቱ ላሉ ብሔር ተኮር ጥቃቶች ኃላፊነት የሚወስድ አካል መኖር እንዳለበት የተናገሩት አቶ ኑሩ ህዝብ ለአደጋ ከተጋለጠ በኋላ ‹እኛን አይወክልም› በማለት ብቻ መታለፍ እንደሌለበት ጠቁመዋል፡፡ በየአካባቢው ተመሳሳይ ብሔር ተኮር ግጭትና ጥቃት እየተበራከተ በመሆኑ በህዝብ መካከል ምክክር በማድረግ ትክክለኛ ብሔራዊ እርቅ በማድረግ የማያዳግም መፍትሄ ማምጣት እንደሚያስፈልግም አመልክተዋል፡፡
ወደ አገር ቤት እየገቡ የሚገኙ የፖለቲካ ፓርቲዎችም በትክክል አቋማቸውን ማሳወቅ እና ላለው ለውጥ ምን እንደሚያበረክቱ በግልጽ ማስቀመጥ እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎቹን በመደገፍ ምክንያት ለሚደርሱ ግጭቶችም ፓርቲዎቹ የመገሰጽና ስለሰላም ደጋፊዎቻቸውን ማስተማር እንዳለባቸውም ተናግረዋል፡፡
‹‹ተጎጂዎች የጸጥታ አካላትን ትብብር ጠይቀው ሊያገኙ አለመቻላቸውን እየተናገሩ በመሆኑ የጸጥታ ኃይሉ ህብረተሰቡን ከጥቃት የመጠበቅ ተነሳሽነት እንዳለው እየታየኝ አይደለም›› በማለት ከሚደርሱ ጥፋቶች አንጻር አስቀድሞ መከላከል እንኳን ባይቻል ጥቃቶቹ ይህንን ያህል እስኪባባሱ መጠበቅ እንደማይገባም ተናግረዋል፡፡
ዶክተር ገረመው ዱቃ በበኩላቸው በኢትዮጵያ እየተስተዋለ ያለው ብሔር ተኮር ጥቃት ማብቂያ እንዲኖረው ህዝቡ ያዳበረውን እርስ በእርስ ከጥቃት የመጠባበቅ ባህሉን ሊያዳብር እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡ መንግሥት የህግ የበላይነት ማስከበርና ነጻነትን ነጣጥሎ ማየት እንደሚገባውና ህግን የማስከበር ግዴታውን ሊወጣ እንደሚገባም መክረዋል፡፡
የተፈጠረው የነጻነትና ዴሞክራሲን የመገንባት መንገድ ህገወጦችን ማፍራት ስለሌለበት ህግ የማስከበር ሥራ መሠራት እንዳለበት ገልጸዋል፡፡
የህዝቡን እርስ በእርስ መተማመን እንዳይሻር ደግሞ ትልልቅ ሰዎችና በየአካባቢው የሚገኙ ሽማግሌዎች የበኩላቸውን ሊወጡ እንደሚገባም አመልክተዋል፡፡
‹‹የተለያየ የፖለቲካ አመለካከት ያላቸው ግለሰቦች ህዝብ ውይይት አድርጎ መቋጫ ያላበጀላቸው በርካታ ጉዳዮች ባሉበት ሁኔታ ማስቀደም ያለባቸው ሁሉም ዜጋ ኢትዮጵያን እንደቤቱ በማየት ተረጋግቶ የሚኖርበትን ሁኔታ ማመቻቸት ነው›› ያሉት ዶክተር ገረመው ሁሉም ለአገሪቱ ሰላምና ለህዝብ ደህንነት ኃላፊነት ሊሰማው እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ እንዲሁም የኢትዮጵያውያን ሞት ሁሉንም ስለሚመለከት ‹እኔን አይወክለኝም› የሚል የፖለቲካ ጨዋታ እንደማያዋጣና የዜጎች ህይወት መጥፋት እንዲቆም መንግሥት የህግ የበላይነትን ሊያስከብር እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

አዲስ ዘመን ጋዜጣ መስከረም 12 ቀን 2011 ዓ.ም
በሰላማዊት ንጉሴ

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy