Artcles

መዲናዋን የጎዳት ምናገባኝ የሚሉት ስሜት

By Admin

September 10, 2018

መዲናዋን የጎዳት ምናገባኝ የሚሉት ስሜት

ይቤ ከደጃች ውቤ

     እኔ ምናገባኝ የሚሉት ሐረግ ፣

       እሱ ነው ሀገሬን ያረዳት እንደ በግ፣

       የሚሉትን ግጥም ልፅፍ አሰብኩና ፣

        ምናገባኝ ብዬ ተውኩት እንደገና።

እንደ መግቢያ የወሰድኩት ግጥም አንድ ገጣሚ ባሳተሙት መድብል ላይ ያነበብኩት ነው።ግጥሙ በጋራ የመብላት እንጂ በጋራ የመሥራት ልምድ ለሌለን፤ በጋራ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ  እኔ ምናገባኝ በሚል ለምንኮፈስ ዜጎች መማሪያ ይሆናል።በአንድ ቤት በጥቂት ሀብትና ንብረት እንኳ አባወራም ወይም እማወራ ቢያርፉ ‘ለኔ ይገባል ለኔ ይገባል’ በሚል ሰበብ የቤተሰብ አባላት ይጋጫሉ።ተካሰው ወደ ፍርድ ቤት የሚሄዱም ብዙ ናቸው።ሀብታቸውን አቀናጅተው በጋራ ለመሥራት ድህነትን ለመዋጋት ሲጥሩ አይታይም።የሀገራችንም ባህልም መጠላለፍ የሞላበት መደጋገፍ ደግሞ ያነሰበት ነው ማለት ይቻላል።

አዲስ አበባ ከተማ ከዩናይትድ ስቴትሱ ኒውዮርክ እና ከስዊዘርላዱ ጀኔቭ ከተማ ቀጥሎ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽንን የመሳስሉ ዓለም አቀፍ ተቋማት መቀመጫ ከአህጉር አቀፍ ደግሞ እንደ አፍሪካ ኅብረት ዋና ጽህፈት ቤት የመሳሰሉ ደርጅቶች ና ሌሎች ክፍለ አህጉራዊ ተቋማት  ጽህፈት ቤትነት እያገለገለች ያለች ከተማ ነች።

መዲናዋ የብዙ ሀገሮች ኤምባሲ፣ ዓለም አቀፍ እና አህጉራዊ ድርጅቶች የሚገኙባት ባሏት ደረጃቸውን የጠብቁ የስብሰባ አዳራሾች እና ባለ ኮከብ ሆቴሎች ዓለም አቀፍ ስብሰባዎች  በየጊዜው የሚካሄድባት ታላቅ ሚና ያላት ከተማ ናት።ባለፈው ሳምንት እንኳ ከተካሄዱ ስብሰባዎች መካከል ዓለም አቀፍ የፖስታ አገልግሎት ድርጅት ስብሰባ አንዱ ነው።

አዲስ አበባችን ከላይ እንደተጠቀሰው የብዙ ኤምባሲዎች ዓለም አቀፍና አህጉር አቀፍ እንዲሁም ክፍለ አህጉራዊ ተቋማት መቀመጫ ሆና ለነዋሪው ለውጪ ዜጎችም እንደ ስምዋ መሆን አልቻለችም።መዲናችን በአካባቢ ጥበቃ በአረንጓዴ ተክሎችና ያልተዋበች የአበባ መዐዛው ቀርቶ የረገፈ አበባ የማይታይባት ሲወርድ ሲዋረድ በመጣ ውስብስብ ችግር የታጠረች መሆኑዋን ተዟዙሮ ማየቱ ብቻ  አሳማኝ ነው።በተክሎች ና በዕፅዋት ልምላሜ የሚታወቁት ፓርኮቻችንም መልካም ስማቸው ተዘንግቶ በሱሰኝነት ለታጠሩ ወጣቶች ምቹ መሸሸጊያ ሆነዋል።

በከተማዋ በየቦታው የሚጣሉ የውሃ ማሸጊያ ፕላስቲኮች፣ፌስታልና ሌሎች ላስቲኮች በፍሳሽ ትቦዎችና ወንዞች እንዲሁም በየመንገዱም እየተጣሉ ‘እኛ ነን አበባ’ የሚሉ ይመስላሉ።እነዚህን በየቦታው ከመጣል ሰብስቦ በዳግም ዑደት(Recycling) ለአገልግሎት የሚበቁበት ሁኔታ ቢመቻች ለነዋሪዎች የሥራ ዕድል የሚፈጥሩ፣መዲናዋንም ከብክለት የሚያጠሩ ይሆናሉ።የታሸገ ውሃ ማምረቻዎች ለዜጎች የፈጠሩትን የሥራ ዕድል፣ግብር በመገበር ያበረከቱትን ሚና ስናደንቅ በአካባቢ ጥበቃ በኩል የድርሻቸውን ለማበርከት ድምፃቸው አለመሰማቱን እና እጃቸው ማጠሩን ስናይ እንሳቀቃለን።

በትራንስፖርቱ ዘርፍም ቀደም ሲል በአንበሳ የከተማ አውቶቢስ ላይ ይታይ የነበረው የመጓጓዣ ወረፋና ግፊያ አሁን ወደ ግል ታክሲዎችም መሸጋገሩን ንጋትና ምሽት ላይ በየአካባቢው የሚታይ ነው።ለታክሲ የሚታየው ወረፋና እና ሰልፍ ብዛት አንዳንዴ ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ የወጡ ሰዎች ስብስብ ይመስላል። በዚህ በኩል ለመንግሥት ሠራተኞች አገልግሎት የሚሰጠው ቢሾፍቱ ባስ ችግሩን ለመቅረፍ የሚያደርገው ጥረት አርኪ ቢሆን ኖሮ በመኖሪያ ቤት ኪራይ ንረት ለተቸገረ ለእንደኔ ዓይነቱ ዜጋ በተመጣጣኝ ዋጋ ከከተማው ወጣ ባሉ አካባቢዎች መኖሪያ ቤት ተከራይቶ የሚኖርበት ምቹ ሁኔታ ይፈጠር ነበር።

ከተማችን ከኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች በሥራ አጥነትም ሆነ በሌላ ምክንያት ወጣቶችና ልጃገረዶች የሚኮበልሉባት ናት።ከዚህ ጋር ተያይዞ በከተማዋ የሚገኙ የግል መኖሪያ ቤቶች ኪራይ ዋጋ የናረበት የቤት ተከራዮች ቁጥር የጨመረበት ለአንዳንድ ተከራዮችም የማይወጡባት አቀበት የማይወርዱባት ቁልቁለት ሆና ተገኛታለች።  በዚህም ምክንያት ለዝሙት አዳሪነትና ጎዳና ተዳዳሪነት የሚጋለጡ ይገኛሉ።

ምንም እንኳን በኢህአዴግ አመራር ለመካከለኛና ዝቅተኛ ነዋሪዎች የታሰቡ የኮንዶሚኒየም ቤቶች ግንባታዎች ተካሂደው በዕጣ ለማከፋፈል ተሞክሮ ለተወሰኑ ዜጎች ተደራሽ ቢሆንም ከተመዝጋቢው ቍጥር አንፃር ውጥኑ በእንጥልጥል የቀረና ያልተጋመሰ ነው ማለት ይቻላል።

ለድሆች የታሰበው የኮንዶሚኒየም ቤቶች ግንባታ ‘በጣም ለከፈለ’ በሚል ቀጭን ትዕዛዝ አቅጣጫውን ስቶ፣ ድሆችን ዘንግቶ፣ ባለሀብቶችንና ዲያስጶራዎች አንስቶ የመኖሪያ ቤት ተደራሽ ማድረግ የቻለ “ስኬት” ነው። የኮንዶሚኒየም ዕጣ ከደረሳቸው መካከል የግል ቤት ያላቸው፣የቀበሌ ወይም የቤቶች ኤጀንሲ ተከራይ የሆኑ ይገኙበታል።ከፊሎቹ የተከራዩትን ቤት ሳያስረክቡ የኮንዶሚየም ቤት ተረካቢ መሆን የቻሉ ናቸው። እነዚህ ሰዎች በሁለት ቢላ እየበሉ ነዋሪውን በቤት እጥረትና በኪራይ ዋጋ ንረት እያጉላሉ ያሉ ‘እኔ ምናገባኝ’ በሚል ስሜት ጥቅማቸውን የሚያሳድዱ በሰው ቁስል ላይ እንጨት የሚሰዱ ናቸው ማለት ይቻላል።    ይህ ሳይታወቅ ቀርቶ ሳይሆን ‘በእከክልኝ ልከክልህ’(tit for tat) መንገድ ታይቶ እንዳልታየ የታለፈ የኪራይ ሰብሳቢዎች ተግባር ነው።

በቀበሌ መኖሪያ ቤቶች ረገድም ምን ያህል መኖሪያ  ቤቶች እንዳሉ የማይታወቅበት የቀበሌ ቤት ነዋሪዎች ከወረዳ አስተዳደር ሹማምንቶች ጋር በመመሳጠር ሰነድ እየተሰረዘና እየተደለዘ ቤቶች በስም ዝውውር የሚሸጡበት መንገድ ሠፊ ነው።እንደዚህ ዓይነቱ ተግባር በአዲስ ከተማ ፣በአራዳ ፣በልደታና በቂርቆስ ጎልቶ ቢታይም በከተማዋ አስፋልት ዳር የሚገኙ የቀበሌ መኖሪያ ቤቶች በስም ዝውውር ወይም ሽያጭ ለነጋዴዎች አልያም ለሌሎች ሰዎች የሚተላለፉበት መንገዱ ብዙ ነው።   

በቀድሞው ከንቲባ አቶ ድሪባ ኩማ ዘመነ ሥልጣን በተካሄደ የጋራ መኖሪያ ህንፃዎችና የቀበሌ ቤቶች ቆጠራ ለተጠቃሚ ከተላለፉ ኮንዶሚኒየም ቤቶች 3‚331 ተዘግትው የተቀመጡ፣712 ቤቶች ከባንክ ጋር ውል ሳይፈፅሙ በነፃ የሚኖሩ ሰዎች የተገኙባቸው ሲሆኑ 33 መኖሪያ ቤቶች ደግሞ ከግንባታው ዓላማ ውጪ የንግድ ቤት የተደረጉ፣አንድ ሺህ ቤቶች የቀበሌ ቤት ባላስረከቡ ግለሰቦች የተያዙ መሆናቸው ተደርሶበት ነበር።

ከአስራ አራት ዓመት በፊት በከተማዋ የቀበሌ ቤቶች በተደረገ ቆጠራ 150 ሺህ ቤቶች የነበሩ ሲሆን በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት በተካሄደ ቆጠራ 140 ሺህ መኖራቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ።ይህም በመንገድ ልማት የፈረሱ ከግል ይዞታ ጋር የተቀላቀሉ ቤቶች መኖራቸው መገለፁ የሚታወስ ነው።በከተማዋ የሚሠሩ የንግድ ህንፃዎች ድርብ አገልግሎት(mixed use building) የሚሰጡ ይደረጋል ማለትም ለንግድና ለመኖሪያ ቤት የሚያገለግሉበት መንገድ ይመቻቻል ቢባልም  ይህን መተግበር አልተቻለም።

የቀበሌ መዝናኛ ክበቦች መካከለኛ ገቢ ላለው ዜጋ በተመጣጣኝ ዋጋ የምግብ አገልግሎት እንዲሰጡ በወታደራዊው ደርግ ዘመን የተከፈቱ ቢሆንም ከደርጋ ውድቀት በኋላ ወደ ግሮሰሪ ለማደግ ቢችሉም ገቢያቸውና ወጪያቸው የሚቆጣጠር አካል የሌለበት የጥቂት ግለሰቦች ኪስ ማደለቢያ ከመሆን የዘለለ ሚና የሌላቸው ሆነዋል።

በወጣቶች ማዕከላት በኩልም የተገነቡት ህንፃዎች በማንና እንዴት እንደተያዙ የማይታወቅበት፣ከጨዋታ ውጪ የወጣቶችን ስብዕና ሊገነቡ የሚችሉ ከፊሎቹ እንደ ቤተ መፃሕፍት ያለ አገልግሎት ወይም የንባብ ቦታ የሌለበት፣ ለማዕከሎቹ ወጪ የሚመድበው አካል ሆነ የተገኘው ትርፍ መጠን የማይሰማበት ቦታ ነው።ለህንፃዎቹ ግንባታ ከወጣው ወጪ አንፃር ለወጣቱ ያበረከተው አስተዋፅዖ ወይም አዎንታዊ ሚናው ምንድነው? ብንል የማይታወቅበት፣ ‘ግልፀኝነት’ የሚባለውን መርህ የሚጥስ ነው ማለት ይቻላል።

እንደ  መብራት ኃይል፣ ውሃና ፍሳሽ፣ ቴሌ እና መንገዶች ባለሥልጣን ያሉ ተቋማት እርስ በርስ ተናበው መሥራት ባለመቻላቸው አንዱ ሲገነባ ሌላው ደግሞ የራሱን ለመገንባት ሲያፈርስና ሲደረምስ የሚታይበት ‘ነገራችን ሁሉ የእምቧይ ካብ የእምቧይ ካብ’ የሆነበት እኔ ምናገባኝ የሚል እሳቤ የነገሠበት ነው።በአጠቃላይ እኔ ምናገባኝ የሚሉት ስሜት መዲናዋን እየጎዳት የነበረበት ዘመናት ውስጥ ነበርን ማለት ይቻላል።        

ካለፉት አምስት ወራት ወዲህ ኢህአዴግ በጎ የለውጥ ጅማሬዎችን አሳይቶናል።የለውጥ ጅማሬዎቹ ፓርቲው ያለውን ተቀባይነት የሚያጎለብቱ ናቸው።ለውጡ ሥር እንዲሰድና መሬት እንዲወርድ የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ መቀጠል አለበት።ከላይ ያነሳናቸው ችግሮች የአመራሮቹ ችግሮች ብቻ አይደሉም የከተማው ነዋሪ ሁሉ ክፍተት ነው።  ከላይ በጠቀስናቸው ችግሮች ላይ ደረጃው ይለያያል እንጂ የሁላችንም ድርሻ አለበት።የቀበሌ ቤት እያለን ሳናስረክብ ኮንዶሚኒየም ወስደናል፣ቢያንስ አንድ ከአገልግሎት ውጪ የሆነ የውሃ ማሸጊያ ፕላስቲክ የጫት ገረባ እኔ ምናገባኝ በሚል ስሜት በየቦታው ጥለናል።

ስለዚህ አዲሱ የምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ አስተዳደር በድረ ግብር (network) የታጠሩ እንከኖችን ለማስወገድ መጣር ፣ ኪራይ ሰብሳቢነትን እና የቢሮክራሲ ሰንሰለቶችን መበጣጠስ ይጠበቅባቸዋል። ከላይ የተጠቀሱ ችግሮችን ደረጃ በደረጃ ፈር ለማስያዝ ከታገሉ በምርጫ በሚደርስበት ጊዜ ‘ታከለ ታገለ’ ተብሎ ይዘመርላቸዋል። በአዲሱ ዘመን ሁላችንም ለከተማችን ብሎም ለሀገራችን መልካም አስተዋፅዖ በማበርከት እኔ ምናገባኝ ከሚል ስሜት መላቀቅ ይጠበቅብናል ስል እንኳን ለአዲሱ ዓመት አደረሳችሁ ዘመኑ የሰላም የፍቅር የብልፅግና እና የመደመር እንዲሆን በመመኘት ነው።