Artcles

መጪው በዓል…

By Admin

September 05, 2018

መጪው በዓል…

                             ይሁን ታፈረ

ኢትዮጵያዊያን 2010 ዓመተ ምህረትን አጠናቀንና 2011 ዓ.ም ለመቀበል በዝግጅት ላይ እንገኛለን። የምንቀበለው አዲስ ዓመት የብሩህ ተስፋ ምኞት የሚንፀባረቅበት ነው። ዜጎች አዲሱ ዓመት ወደ አዲስ ተስፋ የሚዘልቁበት በመሆኑ፣ “በፍቅር እንደመር፤ በይቅርታ እንሻገር” የሚለውን አገራዊ መሪ ቃል መያዝ ይኖርባቸዋል።

በውጭም ይሁን በአገር ውስጥ የሚገኙ እንዲሁም በተለያዩ ምክንያቶች በዓሉን ለመታደም ያልቻሉ ኢትዮጵያዊያን ክብረ በዓሉን በፍቅር ተደምረው እንዲሁም በይቅርታ የጥላቻ ድልድይን አፍርሰው ወደ አዲሱ ዓመት መሸጋገር ያለባቸው ይመስለኛል። በያሉበት ቦታ ሆነው አዲሱን ዓመት ሲቀበሉ፣ ይቅርታን፣ ፍቅርን፣ መደመርንና አንድነትን በማጥበቅና ከዚህ በተቃራኒ የሚስተዋሉ ችግሮችን መከላከልም አለባቸው።

በይቅርታ ከፋፋይ የጥላቻ ሁኔታን ማፍረስ ይቻላል። በአዲሱ ዓመት ወደ አንድ ሀገራዊ ስሜት መምጣትም ይገባል። ስንደመር ትልቅ መሆን እንደምንችል አይተናል። ለሁላችንም የምትበቃ አንድ ታላቅ ሀገር አለችን። ይህችን አገር ይበልጥ ታላቅ ማድረግ እነችላለን። ኢትዮጵያዊያን ሲደመሩ ሊያደርጉት የሚችሉትን ነገር በጥቂት ወራቶች ውስጥ አረጋግጠናል።

ስለሆነም ይቅርታን በማጥበቅ ልንደመርና ተመሳሳይ አቋም ይዘን መጭውን በዓል ልንቀበል ይገባናል። በፍቅርና በአንድነት አበው ያስረከቡንን የአፍሪካ የነፃነት አርማ የሆነችውን ኢትዮጵያ ለመገንባት ልጆቿ በአንድነት መቆም ከቻልን ለሌሎችም አርአያ ሆን እንደምንችል እናሳያለን።

በአዲሱ 2011 ዓ.ም ጥላቻን፣ ቂምንና ቁርሾን በይቅርታ ስሜት እንደ ተረት “በነበርነት” ማለፍ አለብን። ይህም የሁሉም አገር የሆነችውን ኢትዮጵያን በፍትህ፣ በልማት፣ በሰላምና በአንድነት መንፈስ እንድናንጻት የሚያስችለን ነው። በአዲሱ ዓመት በፍቅር ተደምረን ስንሻገር “የእኔ” ሳይሆን “የእኛ”ነት አስተሳሰብ ይዘን መሆን አለበት። እኔነት ከመደመር ጋር የሚያገናኘው ነገር ስለሌለ ልናስወግደው የግድ ነው። እኛነትን በማጎልበት ተስፋችንን በአዲስ መንፈስ ሰንቀን መጪውን በዓል መቀበል ይኖርብናል። ይህም በየተኛውም አካባቢ ከበሬታን እንድንጎናፀፍ የሚያደርግ ነው።

እንደሚታወቀው ሁሉ የተበታተነን፣ የተለያየንና በየጊዜው በሰበብ አስባቡ የሚናቆርን ህዝብ የሚያከብረው አካል አይኖርም። በአንፃሩም በአንድነት የሚጓዝን፣ በአገሩ ጉዳይ በአንድነት የሚሰራን፣ ጧትና ማታ ለሀአሩ የሚባትልን ዜጋ የማይወደውና የማያከብረው አካል ሊኖር አይችልም።

አሁን በምንገኝበት የለውጥ ሂደት ፍትህን፣ ሰላምንና አንድነትንና አገራዊ ዕድገትን ማምጣት የሚያስችል ለውጥ እውን እየሆነ ነው። ድህነት በተጨባጭ ሊማረክበት የሚችልበት ሁኔታም እየተፈጠረ ነው። ይሁን እንጂ ለውጡ ድጋፍ ይፈልጋል። ስለሆነም ሁሉም ዜጋ በገንዘቡና በእውቀቱ የድጋፉ ተባባሪ መሆን ይገባዋል።

በአዲሱ ዓመት አንድነትን ለማምጣት የሚደረገው ጥረት አካል መሆን ድህነትን ለመቅረፍ አንድ ርምጃ ወደፊት መሄድ ይቻላል። ኢትዮጵያን በየሄደበት ሁሉ ይዟት የሚዞረው ኢትዮጵያዊ ወገኔ መደመሩን በዚህ መንገድ በማረጋገጥ የአገሩን አንድነትንንና ኢትዮጵያዊነትን በመጪው በዓል በፍቅር ከፍ ማድረግ ይኖርበታል። በተለይ ወጣቱ የዚህ ተግባር ግንባር ቀደም ተዋናይ መሆን አለበት።

በአገራችን የመጣው ለውጥ ባለቤት ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ቢሆንም፣ ወጣቱ ግንባር ቀደም ተዋናይ መሆኑ አይዘነጋም። ዛሬም ለውጡን ከሌላው የህብረተሰብ ክፍል ጋር በመሆን እየጠበቀ ያለው እርሱ ነው። ስለሆነም አዲሱን ዓመት ሲቀበል ይቅርታን፣ መደመርንና ኢትዮጵያዊ አንድነትን በማጥበቅ መሆን አለበት።  

እንደሚታወቀው ሁሉ ለውጡ ከአገሪቱ ዕድገት ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል ለመጥቀም ከወዲሁ እየሰራ ነው። በአራት ወራቶች ውስጥ ብቻ ምን ያህል መስራት እንደተቻለ ወጣቱ በሚገባ ያውቃል።

ስለሆነም መጪው ጊዜ ከአዲሱ አመራር ጋር በአንድነት መንፈስ ተጠቃሚነቱን ይበልጥ የሚያጠናክርበት ጊዜ ነው። ተስፋውን ከአገሩ ጋር በማቆራኘት በመጪው በዓል ይቅርታንና ፍቅርን ለማስቀደም መስራት ይኖርበታል። አዲሱ ዓመት የፍቅር ፀዳልንና የይቅርታ ትልቅነትን የምናይበት በመሆኑ በመደመር አርአያ ሆኖ ማሳየት አለበት።   

እርግጥ ለብቻችን ሆነን የማንፈፅመውን ነገር አንድ ላይ ስንሆንና ስንደመር ከሚፈለገው በላይ ውጤት ልናመጣ እንችላለን። በመደመር ውስጥ ሁላችንም አለን—አልደመርም ብሎ ራሱን ከቀነሰው ውጭ። በዚህ የስሌት ቀመር ውስጥ የምንገኘው አንድ ላይ እንጂ ተነጣጥለን አይደለም። ስለሆነም 2011 ዓ.ም በፍቅር ልንደመር የግድ ነው።

መደመር አንድነትን ይፈጥራል። በአሁኑ ወቅት በሀገር ውስጥም ይሁን በውጭ የሚገኘው ኢትዮጵያዊ ‘እኔ ተደምሬያለሁ’ በማለት በየአደባባዩ ፍላጎቱን የሚገልፀው ወገን ከአንድነት የሚገኘውን ጥቅም ስለሚያውቅ ነው። መጪው በዓል አንድነታችንን በፍቅር የምናደምቅበት ነው።

አንድነት አንዱ የሌለውን ከሌላኛው የሚያገኝበት፣ የድምር ውጤቱም ብዙ የሚሆንበትና የሚፈለገውን አገራዊ ለውጥ ማምጣት የሚቻልበት ማስተሳሰሪያ ነው። በአንድነት የሚገኘው ለውጥ ለብቻ ቢኮን የማይሞከር፣ ነገር ግን በጋራ በመሆን ያለ ብዙ ነዋይና ጊዜ በቀላሉ እውን ልናደርገው የምንችለው ነው። ስለሆነም አንድነትን በፍቅርና በመደመር እንደምናመጣው በመጪው በዓል ላይ ቃል መግባት ይኖርብናል።

በመደመር ጎልተን፣ አምረንና ደምቀን እንታያለን። የምንናገረው ይሰማል። የምንጠይቀው ወዲያው ምላሽ ይሰጠናል። በመደመር የተፈጠረው አንድነት፣ ጠንካራነትን ፈጥሮ የምንፈልጋቸው ሁለንተናዊ ለውጦች ሁሉ እውን ይሆናሉ።

ስለሆነም በመጪው በዓል ስንደመር “እኔነትን” አሽቀንጥረን እንጥላለን። ከላያችን ላይ አሽቀንጥረን የምንጥለው “እኔነት” አንድነትን ሊያመጣ የሚችል “እኛነትን” በመውለድ፤ ችግሮች ካሉም በጋራ ተመካክረን እንድንወጣ የሚያደርገን ይሆናል። ይህን ፍላጎታችንንም በአዲሱ ዓመት እውን ማድረግ አለብን።

 

በፍቅር የተደመረ ለይቅርታ አይሳሳም። በፍቅር መደመር ይቅርታን ይወልዳል። ይቅር ባይነት ዘመናዊነትና ታላቅነት ስለሆነ ይህን በአዲሱ ዓመት ማረጋገጥ ይኖርብናል። በፍቅር ተደምረን ስናበቃ በይቅርታ ካልተሻገርን የምንፈልገውን ለውጥ ማምጣት አንችልም። ስለሆነም መጪው በዓል ተደምረን በይቅርታ የምንሻገርበት ስለሆነ ሁላችንም ለፍቅር፣ ለይቅርታና ለመቻቻል ቅድሚያ መስጠት ይኖርብናል። መልካም በዓል።