Artcles

‘…ምን ይዞልን ይመጣ ይሆን?’

እምአዕላፍ ህሩይ (“የበለፀገች ኢትዮጵያ” ድረ-ገፅ ልዩ ጥንቅር)

By Admin

September 25, 2018

እንደ መግቢያ

ገዥው ፓርቲ የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ) 11ኛ መደበኛ ጉባኤውን በሀዋሳ ከተማ ለማካሄድ በዝግጅት ላይ ነው። “በልማታዊ ዴሞክራሲያዊ ማዕቀፍ የለውጥ እንቅስቃሴያችንን በማስቀጠል የኢትዮጵያን ህዳሴ እናረጋግጣለን” በሚል መሪ ቃል ለሚካሄደውን ይህ ጉባኤ፤ አባል ድርጅቶች በተከታታይ ድርጅታዊ ጉባኤያቸውን በማከናወን ላይ ይገኛሉ።

ከአባል ድርጅቶቹ መካከል “የላቀ ሃሳብ፣ ለተሻለ ድል” በሚል መሪ ቃል በጅማ ከተማ ጉባኤውን ያካሄደው የቀድሞው “የኦሮሞ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ድርጅት” (ኦህዴድ)፣ የዛሬው “ኦዴግ”፤ ስያሜውን፣ አርማውን፣ መዝሙሩን በመቀየር እንዲሁም የተማሩ ወጣቶችን ወደ አመራርነት በማምጣት ጉባኤውን አጠናቋል። “የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ” (ኦዴግ) ተሰኝቶ፤ ዶክተር አብይ አህመድን በሊቀመንበርነትና አቶ ለማ መገርሳን በምክትል ሊቀመንበርነት የመረጠው ፓርቲው፤ አንድ ለየት ያለ ነገር አሳይቶናል። ይኸውም ፓርቲው የተማሩና አቅም ያላቸው ወጣቶች ወደ አመራርነትና ስራ አስፈፃሚነት ማምጣት መቻሉ ነው። ፓርቲው ባለ ዘጠኝ ነጥብ የአቋም መግለጫ በማውጣት ጉባኤውን ሲያጠናቅቅ፤ ሌሎች እህት ፓርቲዎች ከእርሱ ትምህርት ይወስዱ ዘንድ ምክርም ለግሷል።

ከመስከረም 17 እስከ መስከረም 21 ድረስ ይካሄዳል ተብሎ የሚጠበቀው 12ኛው የብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ብአዴን) ጉባኤ፤ “የለውጡ ቀጣይነት ለአማራ ህዝቦች ተጠቃሚነትና ዴሞክራሲያዊ አንድነት” በሚል መሪ ቃል የሚከናወን ነው። በጉባኤው፤ ድርጅቱ መጠሪያ ስሙን እንደሚቀይር ከማስታወቁም በላይ፤ የርዕዩተ ዓለም ጉዳዩንም እልባት እንደሚሰጠው በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ሲገለፅ አድምጠናል። ያም ሆኖ፤ የብአዴን ጉባኤ ለለክልሉ፣ ለኢትዮጵያ ህዝቦችና ለሀገር የሚበጁ ጠቃሚ ውሳኔዎችን ያሳልፋል ተብሎ ይጠበቃል።

“የአንድነትና የፅናት ጉባኤ ለህዳሴያችን” በሚል መሪ ቃል የሚካሄደው የህዝባዊ ወያነ ሓርነት (ህወሓት) ጉባኤም፤ በቀናቶች ውስጥ እንደሚካሄድ ተነግሯል። ከጉባኤው መሪ ቃል በመነሳት፤ ድረጅቱ በአንድነትና በፅናት እንዲሁም በሀገራዊ ህዳሴ ዙሪያ ውይይት በማድረግ አቋም እንደሚይዝና የተማሩ ወጣቶችን ወደ ድርጅቱ አመራርነት እንደሚያቀላቅል ተገልጿል። “የህዝቦች አንድነት ለሁለንተናዊ ለውጥ” በሚል መሪ ቃል የሚካሄደው 10ኛው የደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ ጉባኤም፤ ከክልሉ ተጨባጭ ሁኔታ በመነሳት እንዲሁም ለውጡን ከማስቀጠል አኳያ በስፋት ተወያይቶ ውሳኔ እንደሚያሳልፍ ተነግሯል።  

የድርጅቶቹን ጉባኤ ተከትሎ፤ ከወዲሁ የሚወጡ አንዳንድ ወረጃዎች በአባል ድርጅቶች መካከል የተለያዩ አስተሳሰቦች መኖራቸውን እየገለፁ ናቸው። ርግጥ በድርጅቶች መካከል የተለያዩ አስተሳሰቦች መኖራቸው ነባራዊ ነው—ከዴሞክራሲ አኳያ የሚጠበቅ ጉዳይ ነውና። ዳሩ ግን የአስተሳሰቦቹ ልዩነቶች የማይታረቁ መሆን ያለባቸው አይመስለኝም— በድርጅቱ አንድነት ላይ ጥላ የሚያጠላ ሊሆን ይችላልና። ርግጥ ሌሎች አባል ድርጀቶች ስለ ርዕዩተ ዓለም (Ideology) ጉዳይ ያሉት ነገር የለም። አራቱን ድርጅቶች አቅፎ የያዘው ኢህአዴግም ርዕዩተ ዓለሙን ለጊዜው እንደማይቀይር የድርጅቱ ሊቀመንበር ዶክተር አብይ አህመድ በአንድ ወቅት መግለፃቸው ይታወቃል። እንዲሁም ኢህአዴግ ስያሜውንና አርማውን እንደማይቀይር በየጊዜው ከወጡ መረጃዎች መረዳት ይቻላል። እነዚህ የድርጅቱ አቋሞች ቢያንስ ኢህአዴግ አሁን በሚገኝበት ቁመናው የርዕዩተ ዓለም ለውጥ የማያስፈልገው መሆኑን፣ ስያሜውንና አርማውንም መቀየርም አስፈላጊ አለመሆኑን የሚያመላክቱ ናቸው።

ዳሩ ግን ከአባል ድርጅቶቹ አንዱ የሆነው “ብአዴን”፤ ምንም እንኳን በቀናቶች ውስጥ በሚያካሂደው ጉባኤው ላይ የሚገልፀው ቢሆንም፤ የርዕዩተ ዓለም ለውጥ እንደሚያደርግ መጠነኛ ፍንጭ የሰጠ ይመስላል። ያም ሆኖ፤ በሁሉም አባል ድርጅቶች ውስጥ የተጠናከረ አንድነትና ስር የሰደደ መተማመን መኖሩ የሚረጋገጠው ኢህአዴግ በሚያካሂደው የሀዋሳው ጉባኤ ላይ ይመስለኛል።

በብዙዎች ዘንድ ጉባኤው ለኢህአዴግ እጅግ ወሳኝ በመሆኑ በጉጉት እንደሚጠበቅ የሚናገሩትም ለዚሁ ነው—ከመጪው መስከረም 23 እስከ 25 ቀን 2011 ዓ.ም ድረስ የሚካሄደውን የድርጅቱ ጉባኤ። የድርጅቱን ጉባኤ አስመልክቶ ዝግጅቶቹን ይህን ያህል ካስቃኘኋችሁ ዘንዳ፤ በለውጥ ሂደት ውስጥ ሊፈጠሩ ስለሚችሉ እንከኖች እንዲሁም ከጉባኤው የሀገራችን ሀዝብ ምን እንደሚጠብቅ በማመላከት ልዩ ጥንቅሩን ለመደምደም እሞክራለሁ።     

 

እንከን አልባ ጉዞ?

የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ባለፉት አምስት ወራት የተከናኑትን ዐበይት ሀገራዊ ፍፃሜዎችን በቅርቡ ሲገመግም፤ እስካሁን ድረስ የተከናወኑት ስራዎች ህጋዊ፣ ኢህአዴጋዊና ድርጅቱ ባስቀመጠው የጥልቅ ተሃድሶ አቅጣጫ መሰረት የተከናወኑ መሆናቸውን ገልጿል። ያም ሆኖ፤ በሀገሪቱ ውስጥ የተፈጠረው የለውጥ ሂደት ሁሉንም አባል ድርጅቶች በእኩል መልኩ አግባብቷል ብሎ በድፍረት ለመናገር የሚያስቸግር ይመስለኛል። ይሁንና ለውጡ ሀገራችን ከገባችበት ማጥ ውስጥ ጎትቶ የሚያወጣት ትክክለኛ መንገድ ስለመሆኑ የሚጠራጠር አባል ድርጅት የለም። ይህ እውነታ ሁሉንም ያስማማል።

በማንኛውም የለውጥ ጉዞ ውስጥ እንከኖች መኖራቸው አይቀርም። እንኳንስ በተጋጋመው የለውጥ ጉዞ ውስጥ ያለን ሀዝቦች ቀርተን፤ በአዘቦቱ ወቅትም ሀገር የሚመሩ አካላት ከተግዳሮቶች ነፃ ሊሆኑ አይችሉም። እንከን አልባ የለውጥ ሂደት በየትኛውም ሀገር አልነበረም፤ አይኖርምም። ለውጥ በራሱ የአዕምሮአዊና አካላዊ ፍትጊያን የሚጠይቅ ሆኖ በውጤትት ሊመዘገብ የሚችል ክስተት ነው። እናም ለውጡን ተከትለው የሚፈጠሩ ነባራዊ ክስተቶች ለእንከኖቹ ምክንያት ሊሆኑ እንደሚችሉ መገንዘብ ያስፈልጋል። ሁሉም እህት ድርጅቶች ይህን እውነታ በመገንዘብ ወደ ሀዋሳው ጉባኤው ማምራት ይኖርባቸዋል ብዬ አምናለሁ። ከእውነታው በመነሳትም ነባራዊውን ሁኔታ መለካትና መቻል ያለባቸው ይመስለኛል።

በእኔ እምነት፤ በአንዳንድ የግል መገናኛ ብዙሃንና በማህበራዊ ድረ ገፆች አማካኝነት መጪውን ኢህአዴግ ጉባኤ አስመልክቶ፤ በገዥው ፓርቲ አባላት መካከል የሰፋ ልዩነት አለ የሚለውን መላ ምት ልቀበለው አልችልም። ምክንያቱም የገዥው ፓርቲ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ በቅርቡ ባወጣው መግለጫ፤ በለውጡ ሳቢያ እስካሁን የተከናወሙት ተግባራት የአመራር የፈጠራ ክህሎት ታክሎበት ኢህአዴግ ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት የተከናወነ መሆኑን መግለፁን ስለማስታውስ ነው።

ዳሩ ግን አንዳንድ ወገኖች (አካላት) ከኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ውስጥ “ህወሓት” ለውጡን የማይደግፍ አድርገው ሲገልፁ እሰማለሁ። ይሁንና ይህ አባባል “ህወሓት” የገዥው ፓርቲ አካል መሆኑን የዘነጋና ገዥው ፓርቲም ‘ህወሓት አስቸግሮኛል’ ባላለበት ሁኔታ የተሰነዘረ ስለሆነ “ከይሆናል” (Scenario) የዘለለ ሊሆን የሚችል አይመስለኝም። በአንድ ወቅት የድርጅቱ ሊቀመንበር ዶክተር ደብረፅዩን ገብረሚካኤል “ህወሓት የለውጥ ድርጅት እንደመሆኑ መጠን፤ ለውጥን አይቃወምም” ማለታቸውንም አስታውሳለሁ።

ታዲያ እዚህ ላይ፤ ማንኛውም ድርጅት ውስጥ እንዳሉት ግለሰቦች ሁሉ አንዳንድ ወገኖች ከራሳቸው መነሻ በመነሳት ከለውጡ ጋር ላይጣጣሙ ብሎም ለውጡን ላይደግፉ እንደሚችሉ መገንዘብ ተገቢ ይመስለኛል። “ህወሓት”ም ውስጥ እንዲህ ዓይነት ሰዎች መኖራቸው የሚጠበቅ ነው። ከለውጡ ጋር አብረው የማይራመዱ ግለሰቦችና አካላት ካሉም በፓርቲዎቹ ውስጣዊ አሰራር የሚጠራ ይሆናል ብዬ አስባለሁ።

ከዚህ አኳያ “ኦህዴድ” ለውጡን ክልላዊና ሀገራዊ ኃላፊነቶችን ተረክበው ለውጡን ሊያስቀጥሉና የሚችሉ ጠንካራ ቋም ያላቸው የተማሩ ወጣቶችን ወደ አመራርነት እንዳመጣው ሁሉ፤ ሌሎቹ ድርጅቶችም ይህን መሰሉን ከለውጡ ጋር መሳ ለመሳ ሊሄዱ የሚችሉ አስፈፃሚዎችን ለአመራርነት ያበቃሉ ተብሎ ይታሰባል። አሊያ ግን፤ የኢህአዴግ ጉባኤ በንትርክ ተሞልቶና ልዩነቶችን ማቻቻል አቅቶት ወዳልተጠበቀ አቅጣጫ ሊያመራ የማይችልበት ምክንያት ሊኖር አይችልም። ግና ይህ ፈፅሞ መሆን የለበትም። እኔ በበኩሌ፤ ‘የዚህች ሀገር ተስፋ የተጀመረው ለውጥና የለውጡን መሃንዲስ ያቀፈው ኢህአዴግ ነው’ ብዬ ስለማምን፤ የድርጅቱ አባል ፓርቲዎች ልዩነት ካላቸውም ልዩነታቸውን አቻችለውና አንድነታቸውን አጠናክረው ለሀገርና ለህዝብ የሚጠቅም አቋም ከጉባኤው ይዘው እንዲወጡ እመኛለሁ።  

‘ምን ይዞልን ይመጣ ይሆን?’

ዜጎች የኢህአዴግን 11ኛ ጉባኤ የሚጠብቁት በተስፋና በጉጉት እንዲሁም በስጋት ነው። ቅን አሳቢና ከአንድ ጉዳይ ውስጥ በጎ ነገርን ብቻ የሚመለከቱ ወገኖች፤ የድርጅቱ ጉባኤ   በአባል ድርጅቶች ውስጥ ሊኖር የሚችሉ ልዩነቶች እንዲጠቡ፣ የህግ የበላይነትን ጨምሮ ሌሎች ህገ መንግስታዊ መብቶችና ግዴታዎች እንዲከበሩ፣ የውስጣዊ አሰራሮች ጥራት እንዲያብብ፣ ዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነትን የተከተለ አሰራር እንዲጠናከር እንዲሁም የአንድ ዓመት ዕድሜ ያህል ለቀረው ሀገራዊ ምርጫ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች በተፈጠረው የፖለቲካ ምህዳር ስፋት ልክ ሃሳባቸውን የሚገልፁበት ምህዳር እንዲመቻች ድርጅቱ ድጋፍ እንዲያደርግ ይመኛሉ። እነዚህ ጉዳዩች ከበርካታ ፍላጎቶች ውስጥ ጥቂቶቹ ናቸው።

በአንፃሩም፤ ከእነዚህ ወገኖች ስጋትን ብቻ የሚመለከቱ አካላት፤ መንግስት በቅርቡ በቡራዩና አካባቢው የተከሰተውንና አንገታችንን ያስደፋንን ችግር አስመልክቶ፤ ‘ድርጊቱ የተፈፀመው የኢህአዴግን ጉባኤ ለመረበሽ ታልሞ ጭምር ነው’ ማለቱን ተከትሎ ‘ጉባኤው ምን ይዞብን ይመጣ ይሆን?’ የሚል ሁኔታ ውስጥ ገብተዋል። ለዚህም በምክንያትነት የሚያነሱት የድርጅቱ አባል ድርጅቶች (ህወሓት፣ ኦህዴድ፣ ብአዴንና ደኢህዴን) በውስጣቸው የሚታየው ያለመተማመን ሁኔታ ለሌላ የተዘበራረቀ ችግር ሊዳርገን ይችላል የሚል ነው።

ዳሩ ግን፤ በእኔ እምነት፤ ጉባኤው ‘ምን ይዞብን ይመጣል?’ ከማለት ይልቅ፤ ምን ይዞልን ይመጣል?’ ብሎ ማሰብ ተገቢ ይመስለኛል። ምክንያቱም ጉባኤውን ሊያውኩ የሚችሉ ችግሮች በመንግስት በኩል አስቀድመው የተፈቱ፣ በጥንቃቄና በሳል በሆነ መንገድ ይያዛል ብዬ ስለማስብ ነው። ያም ሆኖ በለውጥ ሂደት ላይ ያለን ሀገር እንደ መሆናችን መጠን፤ ማንኛውም ሃሳብ የሚናቅ አይሆንም።የኢህአዴግ ሊቀመንበርና የአፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ‘…ቀን ቀን ከእኛ ጋር ማታ ማት ደግሞ ከጠላት ጋር ትዶልታላችሁ’ እንዳሉት፤ በለውጥ ወቅት የየትኛውንም ወገን አቋምንና ትክክለኛ እምነትን አጥርቶ ለማወቅ ያስቸግራል።

ስለሆነም በለውጥ ሂደት ውስጥ ማን ከማን ጋር እንደሆነ እንኳን በርግጠኝነት ለመናገር አስቸጋሪ ስለሚሆን ማናቸውንም ሃሳቦች ወስዶ ውስጣዊንም ሆነ ውጫዊ ስጋቶችን በመተንተን ዝግጅት ማድረግና እልባት መስጠት ተገቢ ይሆናል ብዬ አስባለሁ። እናም ‘ምን ይዞልን ይመጣል?’ የሚሉ ቀና አሳቢ ወገኖች ምልከታ እንደተጠበቀ ሆኖ ‘ምን ይዞብን ይመጣ ይሆን?’ ለሚሉ ወገኖችንም ስጋት መጋራት የሚያስፈልግ ይመስለኛል።

ኢህአዴግ፤ በተለይ በአሁኑ ወቅት፤ በበሳል፣ በህዝባዊ አስተሳሰብ፣ በፍቅርና በይቅርታ የሚመራው አቅም ያለው ተወዳጅ መሪ ባለቤት ሆኗል። ይህም ድርጅቱ ውስጣዊና ውጫዊ ችግሮችን በመፍታት ረገድ አቅምና ብቃት ያለው እንዲሆን አስችሎታል ብዬ አምናለሁ። እናም ይህን ብቃቱንና አቅሙን አንድም፤ ውስጣዊ አንድነቱን ይበልጥ ለማጠናከር፤ ሁለትም፤ ሊከሰቱ የሚችሉ ስጋቶችን አስቀድሞ በመድፈን ጉባኤውን በስኬት እንደሚያጠናቅቅ እምነቴ ነው።               

 

ማጠቃለያ

ምንም እንኳን ዜጎች ከኢህአዴግ ጉባኤ የሚጠብቁት ነገር ብዙ ቢሆንም፤ በዋነኛነት ግን ሀገራቸው ውስጥ ህግና ስርዓት ተከበሮ የመኖር ዋስትናቸው እንዲረጋገጥ ይሻሉ። ገዥው ፓርቲ መንግስትን እየመራ በመሆኑ፤ እዚህ ሀገር ውስጥ ለሚፈፀሙት ማናቸውም ጉዳዩችን ፈር የማስያዝ ኃላፊነትና ግዴታ አለበት። ስለሆነም ኢህአዴግ እንደ ገዥ ፓርቲነቱ የህግ ልዕልናን ከማስከበር በላይ፤ ሀገራችን ውስጥ ፈታኝ እየሆነ የመጣውን የመኖር ዋስትናን ሁኔታ በማረጋገጥ ዋነኛ ትኩረቱን በህገ መንግስቱና በህገ መንግስታዊ ስርዓቱ ላይ ማድረግ ይኖርበታል።

እዚህ ሀገር ውስጥ የሚፈፀሙ ማናቸውም ጉዳዩች ህገ መንግስቱን የሚያከብሩና በዚያው አግባብም የሚፈፀሙ እንዲሆኑ ማድረግ ይገባዋል። የለውጡ ሂደት ህጋዊና ህገ መንግስታዊ ሆኖ እየተከናወነ እንደመሆኑ መጠን፤ ህጋዊ አሰራሮችን የሚጥሱ ማናቸውንም ወገኖች የሚሸከምበት ጫንቃ እንደሌለው ጉባኤው በአቋም ደረጃ ይዞ መውጣት አለበት።

 

ድርጅቱ በጉባኤው ራሱ የሚጠናከርበትን ሁኔታ በመገምገም የአንድነት አቋም ይዞ ከመቀጠል ባሻገር፤ የዜጎችን የመኖር ህልውና እየተፈታተነ ያለውን ስርዓት አልበኝነትን የሚታገልበትን ድርጅታዊ አቋሙን ከግልፅነትና ከተጠያቂነት አያይዞ ለሚመራው ህዝብ ማሳወቅ ይጠበቅበታል ብዬ አምናለሁ። በተረፈ በሀዋሳ ከተማ የሚካሄደው የድርጅቱ 11ኛ ጉባኤ፤ የህዝቦችንና የሀገርን ህልውና በሚያስጠብቅ እንዲሁም ኢትዮጵያዊ አንድነትን በለውጡ ከታየው በላይ የሚያጠናክርበትን ሁኔታ በማመቻቸት ይጠናቀቅ ዘንድ ሰናይ ምኞቴ ነው።