Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ሠላምን በዘላቂነት

0 401

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ሠላምን በዘላቂነት

                                                      ደስታ ኃይሉ

በአገራችን አንዳንድ አካባቢዎች ተፈጥረው በነበሩ ግጭቶች ሳቢያ ከመኖሪያ ቀዬዎቻቸው ተፈናቅለው የነበሩ ወገኖችን ወደ ቀድሞ መኖሪያዎቻቸው የመመለስ ተግባር ተጀምሯል። ወትሮም ቢሆን በሕዝቦች መካከል አንዳችም ግጭት አለመኖሩን እና የተፈጸሙ ተግባራት የትኛውንም ብሔር የሚወክሉ አይደሉም። ስለሆነም ተፈናቃይ ወገኖች በቀጣይም በየቀያቸው ለሠላማቸው ዘብ መሆን አለባቸው።

የአገራችንን ሠላም በዘላቂነት ለማረጋገጥ ጫካ ገብተው የነበሩ ታጣቂ ኃይሎች በሠላማዊ መንገድ ለመታገል ወደ አገር እየተመለሱ ባሉበት በአሁኑ ሰዓት፣ በየአካባቢው ብቅ ጥልቅ የሚሉ ግጭቶች የሠላማችን ጠንቅ ሊሆኑ አይገባም። በመሆኑም ለዘላቂ ሠላም ሁሉም ዜጋ መረባረብ አለበት።

የአገራችን ህዝቦች ለግጭት አንዲትም ስንዝር ቦታ የሚተው አይደሉም። አንዳንዴ ግጭት የመፍትሔው አካል ሊሆን ቢችልም፣ እዚህ አገር ውስጥ ለሚፈጠሩ ችግሮች ግጭት መፍትሔ ሆኖ ሊወሰድ አይችልም።

እንዲያውም ግጭት ችግሮቻችንን የሚያወሳስብ ስለሆነ ልንከላከለው ይገባል። ምክንያቱም እዚህ ሀገር ውስጥ የሚካሄዱ ግጭቶች ምክንያት አልባና አንዳንዴም አሳፋሪ ከመሆናቸው ሌላ ግጭቶቹ ፈፅሞ የህዝቡን ፍላጎት መሰረት ያላደረጉ መሆናቸው ነው።

ይሁን እንጂ በአገራችን አንዳንድ አካባቢዎች መነሻውን ድንበር በማድረግ የሚከናወኑ የግጭት ተግባራት አሉ። እነዚህ ግጭቶች መነሻቸው ህዝብ አይደለም። ህዝብ ለሰላም እንጂ ለግጭት ቦታ ሊኖረው አይችልም። ይሁንና አሁንም ቢሆን ለግጭት የሚሆን ምህዳርን በተቻለ መጠን ማጥበብ ያስፈልጋል።

እርግጥ የፌዴራል መንግሥትና የክልል መንግሥታት ከመልካም አስተዳደርና ከሙስና ችግርሮች ጋር በተያያዘ ህዝቡን በማወያየት እርምጃ ለመውሰድ ተንቀሳቅሰዋል። ህዝቡ የተቀበላቸውን እርምጃዎችን ወስደው ውጤት እያመጡ ነው።

እንደሚታወቀው ሁሉ ከማናቸውም ችግሮች በስተጀርባ ግጭቶችን ተገን አድርገው የራሳቸውን አጀንዳ ለማሳከት የሚጥሩ ለውጡን ያልተቀበሉ ኃይሎች አሉ። እነዚህ ሃይሎች የተጀመረውን ለውጥ ለመቀልበስ በመሯሯጥ ላይ የሚገኙ ናቸው።  

መንግስትና ህብረተሰቡ ለግጭት ሃይሎች የሚሆን ምቹ ምህዳርን ማሳጣት ወሳኝ ነው። ምክንያቱም አንድን ነገር የሚፈጥር ምክንያት መዝጋት ከተቻለ ችግሩ ሊፈጠር ስለማይችል ነው። ከተፈጠረም በህዝቡ ትብብር በቁጥጥር ስር ለማዋል ስለማያዳግት ነው። በመሆኑም ለግጭት ገፊ የሆኑ ጉዳዩችን በመተው ሰላም ላይ ማተኮር የህዝብ ሚና መሆን ይኖርበታል።

ወጣቶች የሰላም ጠባቂዎች መሆን አለባቸው። በተለይም ጥቅማችን ተካብን የሚሉ የለውጥ አደናቃፊዎችን ዴሞክራሲያዊና ህጋዊ በሆነ መንገድ መታገል ይኖርባቸዋል። ወጣቶች ግጭት አራጋቢዎችና ለውጥ አደናቃፊዎች ቀደም ባሉት ጊዜያት በፈጠሩት እኩይ ሴራ አንድም ስንዝር መራመድ ያቃታቸው መሆናቸውን ማወቅ አለባቸው።

ለውጡን የሚቃወሙ ጥቂት ሃይሎች በዘመናት የትስስር ድር የተጋመዱት ህዝቦችን የአእምሮ ዕድገትና የፈጠራ ክህሎት እንዳይዳብር፣ ተወዳዳሪነታቸው እንዲደናቀፍና ድህነትና ኋላቀርነት በክልሉ ስር ሰዶ እንዲቆይ ያላቸውን ክፉ ምኞት ለመተግበር ጥረት ቢያደርጉም ለሰላሙ መጠበቅ መስራት አለበት።

የኢትዮጵያ ህዝቦች በተፈጥሮ በተቸራቸው ቋንቋ የመጠቀም መብታቸው ለዘመናት ተነፍጎ ከኖረበት ሁኔታ ራሳቸውን በማላቀቅ ዛሬ ላይ ቋንቋቸው የሳይንስ፣ የጥናትና ምርምር እንዲሁም የእድገት ምንጭ በመሆን ከፍተኛ ለውጥ አስመዝግበዋል። ዛሬ ደግሞ በአዲስ የለውጥ መንገድ ላይ ናቸው።

የህዝቦች አዲስ ኢትዮጵያዊ መንፈስና አንድነት የሚያሳበዳቸው እነዚህ ግጭት አራጋቢዎች አዲስ የፍቅር መንገድ ሲያዩ የጥፋትና የብተና አቋሞቻቸው ከመቃብር በታች ይውሉብናል በሚል ስጋት ከፍተኛ ትግል ሊያደርጉ ይችላሉ።

እነዚህ አካላት ተገቢ የሆኑ የህዝቦችን ጥያቄዎች ከመጠን በላይ በማጎንና ለግጭት መንስኤ እንዲሆን በማድረግ እንዲሁም የድንበር ይገባኛል ጥያቄዎችን በማጦዝ እኩይ ሴራቸውን ሲፈፅሙ ተመልክተናል። አስተዳደራዊ መለያዎችን እንደ ድንበር አካላይነት በመውሰድ ችግር ፈጥረዋል። ይህ እጅግ አሳዛኝ ተግባር ነው። መንግስትም በዚህ ተግባር ላይ የተሳተፉ ሃይሎች ላይ እርምጃ ወስዷል። በቀጣይም ተጠናክሮ ይቀጥላል። ይሁን እንጂ አሁንም የሰላምን ዋጋ በመገንዘብ አካባቢያዊ ሰላምን ማስጠበቅ ያስፈልጋል።

በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶች ቢኖሩም ዋናው ጉዳይ ግጭቶቹን ፌዴራላዊ ሥርዓቱና ማህበረሰቡ ባካበታቸው የግጭት አፈታት መንገድ መፍታት ከመቻሉ ላይ ነው። በጌዴኦና በጉጂ ብሔረሰቦች መካከል የተፈጠረውን ችግር ለመፍታት መንግስት የሄደበት መንገድ የዚህ አባባሌ ጉልህ ማሳያ ነው።  

በተለይ ኢትዮጵያ የምትከተለው ፌዴራላዊ ሥርዓት ካለፉት ጊዜያት ጋር ፈፅሞ በማይገናኝ መልኩ ለዚህ ነባራዊ ችግር ትኩረት ሰጥቶ በመስራቱ ሁኔታውን በመለወጥ ላይ ይገኛል። የአገሪቱ ህዝቦች ያላቸውን የተፈጥሮ ሃብት በአግባቡ እንዲጠቀሙና ከሌሎች ህዝቦች ጋር በመተሳሰብ የጋራ ሃብታቸው እንዲሆን ለማድረግ ጥረት እየተደረገ ነው።

ዜጎች በጋራ ተሳስበውና ተፈቃቅደው በአንድነት የሚኖሩበትን አስተማማኝና ህዝቦችን ተጠቃሚ ያደረገ ለውጥ ተፈጥሯል። እንዲህ ዓይነቱ ችግሮች በለውጡና በህዝቦች የግጭት አፈታት ባህል መሰረት እልባት የሚያገኙ ናቸው። ሆኖም አሁንም ሰላምን አጠንክሮ መያዝ ያስፈልጋል።

በተለያዩ ግጭቶች ሳቢያ የሚፈጠረው የሰላም እጦት፤ ሌላው ቀርቶ ጧት ወጥቶ ማታ የመግባት ጉዳይ በህግና በስርዓት ሳይሆን በጉልበተኞች ፍላጎት እንዲወሰን ያደርጋል። ጉልበተኞቹ ከሚፈልጉት ጊዜና ዕውቅና ውጭ ማንም ሰው መነቃነቅ አይችልም።

ዜጎች የሚያቀርቧቸው ማናቸውም ጥያቄዎች ህጋዊና ሰላማዊ መሆናቸውን ማረጋገጥ ይኖርባቸዋል። ጥያቄ ማቅረብ መብት ቢሆንም በምንም መንገድ ወደ ግጭት ማምራት አይኖርበትም።

ህግንና ስርዓትን በመከተል ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ እየተቻለ ወደ ግጭት ማምራት አላስፈላጊ ነው። ለጥያቄዎች መልስ ለማግኘት ሲባል ህገ ወጥ አካሄድን መከተል መልሶ የሚጎዳው ጥያቄ አቅራቢውን አካል ነው። እንዲህ ዓይነቱ የተሳሰተ መንገድ የአገርን አቅም ከመፈታተን በላይ የጥያቄው ባለቤት የሚፈልገውን እንዳያገኝ ያደርጋል። እናም ምንግዜም ሰላምን መሻት ህጋዊነትን ማረጋገጥ ይገባል። ተፈናቃዩችም ወደ ነበሩበት ቦታ በሚሄዱበት ሰዓት ለአብሮነትና ለመቻቻል ቅድሚያ በመስጠት የየቀያቸውን ሰላም በዘላቂነት በመጠበቅ ይኖርባቸዋል።

 

 

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy