“ስመኘውን ማን ገደላቸው?”—አበቃለት እንዴ?
ዋሪ አባፊጣ
አንድ የእውነትን ፅንሰ- ሃሳብ መሰረት ያደረገ የሩቅ ምስራቆች ተረት አለ—በአንድ አዛውንት አርሶ አደር ዙሪያ የሚያጠነጥን። አዛውንቱ ሰባት ልጆች ነበራቸው። ከእለታት አንድ ቀን ሁሉንም ልጆቻቸውን በጥብቅ እንደሚፈልጓቸው በመግለፅ፤ ከአዘቦቱ ቀናቶች በአንዱ ቤታቸው እንዲገኙ ይቀጥሯቸዋል። ልጆቹም “አባታችን ምን ሆኖ ነው?!” እያሉ ሲያስቡ ቆይተው፤ በተቀጠሩበት ቀን ቦርቀው ባደጉበት ቤት ውስጥ ይገኛሉ። ሽማግሌውም “እንኳን በደህና መጣችሁ!” በማለት ልጆቹ የተጠሩበትን ምክንያት ጉሮሯቸውን ሳል…ሳል በማድረግ እንዲህ ሲሉ መናገር ጀመሩ።…
“…ልጆቼ ሆይ! እናንተ በአሁኑ ወቅት አዕምሯችሁ ስል፣ ጉልበታችሁ ብርቱ፣ የታፈራችሁና የተከበራችሁ ጎልማሶች ናችሁ። እኔ አባታችሁ ግን በአርሶ አደር ደካማ ጎኔ እናንተን ሳሳድግ ኖሬ፤ ዛሬ ጉልበቴ የዛለ፣ ልጤ የራሰ፣ ጉድጓዴ የተማሰና ዕድሜዬ የገፋ ሽማግሌ ሆኛለሁ። ታዲያላችሁ ከወጣትነት ዘመኔ ጀምሮ አሁን እስከደረስኩበት የሽምግልና እድሜዬ ድረስ እውነትን ስፈልግ ኖሬያለሁ። ብዙም ደክሜያለሁ። ግን ላገኛት አልቻልኩም። በውጣ ውረዶች መሃል ካሁን አሁን እውነትን አገኛታለሁ ብዬ ብደክምም ሳላገኛት በማርጀቴ አዝናለሁ። እናንተ ግን ከአሁን ሰዓት ጀምሮ እውነትን ፍለጋ ብትሰማሩ እንደምታገኟት አንድ የሀገራችን ሊቅ በቅርቡ ቤቴ ድረስ መጥቶ ነግሮኛል።…”
በዚህ ጊዜ ሰባቱም ልጆች በግርምታ እርስ በርሳቸው መተያየት ጀመሩ። ሽማግሌው ግን ሃሳባቸውን አላቋረጡም።…አሁንም ጉሮሯቸውን ሞርደው መናገራቸውን ቀጠሉ። “…እውነት አጠገባችን ብትሆንም በጥቂት ወራቶች ውስጥ ፈልጎ የሚያገኛት እኔ ደካማው ሽማግሌ ሳልሆን፤ ብርቱዎቹ እናንተ መሆናችሁን ይኸው እውቅ ሊቅ አውግቶኛል። እውነትን ተክሎና ኮትኩቶ ውሃ እያጠጡ ማሳደግ እንደሚቻልም በሚገባ አስረድቶኛል። እኔም ህይወቴ ከማለፉ በፊት ‘እውነት በአበባ ትመሰላለች’ በማለት ታዋቂው ሊቅ የነገረኝን ነገር ማረጋገጥ እፈልጋለሁ። ከመሞቴ በፊት እውነትን በዓይኔ ማየት ፈልጋለሁ። እንግዲህ እውነትን ለማግኘት አበባን ኮትኩቶ ውሃ እያጠጡ ማሳደግ መሆኑን ከተገነዘባችሁልኝ ዘንዳ፤ ይህንኑ ልጆቼ እንድታረጋግጡልኝ አደራ እላችኋለሁ” አሉ።
ልጆቹ በነገሩ ቢገረሙም መሃል ገብተው ሽማግሌውን አባታቸውን ሊቋርጧቸው አፈቀዱም። አዛውንቱም ቀጠሉ።…“ የአካሌ ክፋይ ልጆቼ ሆይ! እውነትን ዘርቶና ኮትኩቶ ፍሬ ስታፈራ ማየት እንዴት እንደሚያስደስት እስቲ አስቡት! እውነትን የእውነት ወዳጅ ከተከለው የአበባ ፍሬ ማግኘት እንዴት አያስደስት?…የእውነት አትክልተኛ መሆንስ የእርካታው ልኬታ እንዴትእንደምን ተዘርዝሮ ይዘለቃል?…እናም ይህን የአበባ ዘር እንኳችሁ…ውሰዱትና ዘርታችሁ፣ አብቅላችሁና አሳድጋችሁ የዛሬ ዓመት ይዛችሁልኝ ኑ” በማለት አሰናበቷቸው። ሰባቱም ልጆች ተቋጥሮ የተሰጣቸውን የአበባ ዘር ፍሬ ይዘው ለዓመቱ አበባውን ከነፍረ ለአባታቸው ይዘው ሊመጡ ቃል ገብተው ወደ መጡበት ሄዱ።
ሴኮንድ ደቂቃዎችን፣ ደቂቃዎች ሰዓቶችን፣ ሰዓቶች ወራቶችን ወለዱና ዓመቱ ደረሰ። ሰባቱም ልጆች ተክለው ያፀደቁትን አበባና ፍሬውን ይዘው አባታቸው ቤት ተገኙ። ስድስቱ ለአባታቸው አበባውንና ፍሬውን ሲያስረክቡ፣ ሰባተኛው ልጅ ግን ከዓመት በፊት የተሰጠውን የአበባ የዘር ፍሬ ከነአፈሩ ቋጥሮ ይዞ መጣ። ሽማግሌው በቁጣ እሳት ለብሰው ሰባተኛውን ልጅ “ስማ! እነርሱ ወንድሞችህ ያዘዝኳቸውን ነገር ፈፅመው ሲመጡ አንተ እንዴት ትዕዛዜን ሳትፈጽም ትመጣለህ?” በማለት ተቆጡ። “እውነትን የንትሸፍጥ አንተ በእውነት ላይ የሸፈጥክ የውሸት አትክልተኛ በመሆንህ፤ ከዛሬ ጀምሮ ልጄ አይደለህም፤ ጥፋ ከፊቴ።” ሲሉም አመናጨቁት።
ሰባተኛው ልጅም “አባቴ ሆይ! የምትሰማኝ ከሆነ ስማኝ። እኔም እንደ ወንድሞቼ የተሰጠኝን የአበባ ፍሬ ዘርቻለሁ። ተገቢውን እንክብካቤም አድርጌያለሁ። ግን ሊበቅልልኝ አልቻለም። እውነተቱ ይህ ነው። ከዚህ በላይ የምለው የለኝም” በማለት ከቤቱ ወጥቶ መሄድ ሲጀምር፤ ሽማግሌው በለሆሳስ “ቆይ እስቲ ልጄ!” አሉት። ልጁም ፊቱን ወደ ቤቱ መለሰ።…ሰባቱንም ልጆች ተራ በተራ መመልከት ጀመሩ።…ከመቀመጫቸው እመር ብለው በመነሳትም ወደ ሰባተኛው ልጃቸው እየተመለከቱ፤ “ልጄ ሆይ! የእውነተኛ ሰው ቃል እውነት ሆኖ ካልታመነ ከቶ የማን ይታመናል?” አሉ። ስድስቱ ልጆች ተደናግጠው “እንዴት?” ሲሉ በአንድነት ጠየቋቸው። ሽማግሌው እሳት ልሰው እሳት ጎርሰው “ቅድም በዚህ ልጅ ላይ የስድብ ናዳ ያወረድኩበት ሆን ብዬ ነው። ከእናንተ ሁሉ እውነትን ተክሎ አሳድጎ ያመጣው እርሱ ብቻ ነው። ስድስታችሁ ግን ውሸታሞች፣ ቀጣፊዎችና ሸፍጠኞች ናችሁ። ጠላቶቼ እንጂ ልጆቼ አይደላችሁም። የሰጠኋችሁ የአበባ ፍሬ የተቀቀለና በየትኛውም ዓይነት መሬት ላይ የማይበቅል ነው። እናንተ ግን የሰጠኋችሁን ፍሬ ትታችሁ ሌላ ከገበያ በመግዛት ተክላችሁ ያልሰጠኋችሁን የአበባ ፍሬ ይዛችሁልኝ መጣችሁ። የውሸት ዘበኞች ናችሁ። አደራ በሎች ናችሁ። ይህን ነውራችሁን ሀገሩ ሰው ሁሉ እናገራለሁ። በማህበረሰቡ ውስጥ ማንም እናንተን ማመን የለበትም። ከእንግዲህ እኔ አባታችሁ አይደለሁም፤ እናንተም ልጆቼ ስላሆናችሁ ከፊቴ ጥፉ” በማለት እየሰደቡ ከቤታቸው አባረሯቸው ይባላል።
ይህ የእውነትን ምንነት የሚያስገነዝበን ተረት ረጅም ቢሆንም፤ በውስጡ በርካታ አስተማሪ ቁም ነገሮች ስላሉት ጉዳዩን በቅርቡ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን “ኢንጅነር ስመኘው ራሳቸውን አጠፉ” ካለው እውነታ ጋር ላያይዘው ወደድኩ። ይህን የፖሊስ መግለጫ ተከትሎ፤ “ምርመራው ክፍተቶች አሉበት” የሚሉ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ሃሳባቸውን በተለያዩ ማህበራዊ ድረ ገፆች ሲያሰፍሩ ተመልክቻለሁ። ጉዳዩ ብዙዎችንም አነጋግሯል። ይህም መጥራት ያለበት “እውነት” ያለ መሆኑን የሚያመላክት ይመስለኛል። ሁኔታውም “ስመኘውን ማን ገደላቸው?-አበቃለት እንዴ?” ያስብላል።
ብዙዎች ‘ፖሊስ ሀገር በታማኝት ተግባሩን እንዲወጣ የሰጠችውን አደራ በብቃት አልፈፀመም’ የሚል ሃሳብ ማራመዳቸው፤ ከአዛውንቱ እውነትን ፍለጋ ለልጆቻቸው ከሰጡት አደራ ጋር ተመሳስሎብኛል። ርግጥ ፖሊስ ከራሱ የምርመራ ውጤት በመነሳት ‘ኢንጂነሩ ራሳቸውን ገድለዋል’ የሚል ድምዳሜ አቅርቧል። ይህ ትክክል ነው—በፖሊስ እይታ። አብዛኛው ሰው ግን ያራመደው ሃሳብ ‘የለም! ኢንጂነሩ የተገደሉት በሰው ነው!’ የሚል ድምዳሜ የያዘ ይመስላል። በዚህ ረገድ ፖሊስ የሚሰራው ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ መረጃንና ማስረጃን አቀነባብሮ አንድ ዓይነት ድምዳሜ ላይ መድረስ እንደመሆኑ መጠን፤ ‘አደራውን አልተወጣም’ የሚለው እሳቤ ብዙም ሚዛን የሚደፋ ሆኖ አልታየኝም። ባይሆን እንኳን፤ ልክ ስድስቱ ልጆች የተከተሉትን የተሳሳተ እውነትን ፍለጋ መንገድ ሄዶበት ሊሆን ይችላል ቢባል በመጠኑ የሚያስኬድ ሊሆን ይችላል። ይህ መላ ምት ብዙ መነሻዎች ሊኖሩት ይችላሉ።
እንደሚታወቀው እኛ ሀገር ውስጥ የፖሊስ ስራ ዘለግ ያለ ዕድሜን ያስቆጠረ ቢሆንም፤ ትኩረት ተሰጥቶትና በረቀቁ መንገድ ተደራጀቶ ስራውን ይከውን ነበር ብሎ ለመናገር ርግጠኛ መሆን አይቻልም። ላለፉት 27 ዓመታት የፖሊስ ስራ እንዴት ይከናወን እንደነበር፤ ዛሬ ሙዚየም የሆነው “ማዕከላዊ” እንዲሁም ማረሚያ ቤቶች ህያው ምስክሮች ናቸው። ታራሚዎች ስማቸው ወደ “ተሰቃዩች” የተለወጠ ይመስል፤ እንደምን አሳራቸውንና ፍዳቸውን የበሉ እንደነበር በመንግስት ቴሌቨዥን መስኮቶች የተመለከትነው እውነታ ነው። ይህም ፖሊስ ሳይንሳዊና ስነ ምግባርን በተከተለ መንገድ አለመከወኑን የሚያሳይ አንድ አስረጅ ነው። ሆኖም ፖሊስ አሁን በምንገኝበት ህዝባዊ የለውጥ ሂደት በሪፎርም ስራ ላይ ስለሆነ ሀለንተናዊ ቁመናውን ያሻሸላል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ። በተለይ እየታዩ ካሉ ውስብስብ የወንጀል አፈፃፀሞች አኳያ ራሱን አቅም በፈቀደ መጠን ዓለም ከደረሰበት የምርመራ ጥበብ ጋር ማቆራኘት ይኖርበታል። ይህም የምርመራ ስራውን ተዓማኒ በማድረግ እውነትን ዘርቶና ኮትኩቶ በማሳደግ ‘የእውነት አትክልተኛ’ እንዲሆን ያደርገዋል ብዬ እምናለሁ። ይህ ሲሆንም የምርመራ ውጤቱን ሲያቀርብ ቀዳዳዎችን ደፍኖ ብቻ ሳይሆን እንደ ኢንጂነር ስመኘው አሟሟት ከፖሊስ የተለየ ሃሳብ ያላቸው ዜጎች እንዲበራከቱ አያደርግም።
ያም ሆኖ ግን እኔ የፖሊስ የምርመራ ውጤት ትክክል አይደለም የሚል መነሻ የለኝም። ማስረጃውም ይሁን መረጃው የለኝም። ሆኖም ህዝባዊ ዓመኔታን ለማግኘት አሰራሩ ስልጡን፣ ሳይንሳዊና አብዛኛው ህዝብ የሚያመነው መሆን አለበት ብቻ ነው የምለው።
በበኩሌ በህግ እውነታ የማምን ዜጋ ነኝ። አንድ ህጋዊ አካል ሀገርን ወክሎ ምርመራ እስካደረገ ድረስ፤ ምርመራው ትክክል አይደለም የሚል ድምዳሜ ተገቢ አይመስለኝም። ምክንያቱም በሳይንሳዊ መንገድ የተካሄደ ሌላ የምርመራ ውጤት እስከሌለ ድረስ ተቀባይነት የሚኖረው የህግ ሰውነት ያለው አካል ስለሆነ ነው። ከዚህ ውጭ ሊሆን የሚችለው ነገር የራስ ፍላጎትና እምነት ብቻ ነው። ፍላጎትንና እምነትን ማዳመጥ ደግሞ በግለሰባዊ እይታ ውስጥ ብቻ የሚታይ የ“ቢሆን ዓለም” መላ ምት ከመሆን የሚዘል አይመስለኝም። ይህ ደግሞ “የእውነት አትክልተኛ” አያስብለንም።
እናም ህዝቡ በሰላም ወጥቶ እንዲገባ ጠንክሮ እየሰራ ያለውን ፖሊስ፤ ከራስ ፍላጎትና እምነት በመነሳት እንደ ሩቅ ምስራቃዊው አዛውንት ልንረግመውና “ከፊቴ ጥፋ” ልንለው የምንችልበት ተጨባጭ ምክንያት የሚኖር አይመስለኝም። ይልቁንም መጠየቅ የሚገባን፤ ራሱ ፖሊስ “ኢንጂነሩ ራሳቸውን ነው የገደሉት” በማለት መግለጫ የሰጠበት ዕለት፤ የአሟሟታቸውን መንስኤ አጣርቶ እንደሚያቀርብ የገባውን ቃል እንዲያፋጥን ነው። እናም “ስመኘውን ማን ገደላቸው?”—አበቃለት እንዴ? ብለን ልንጠይቅ ይገባል። ምላሽም መኖር አለበት። ምላሹን ስናገኝም የአሟሟቱን ሙሉ ስዕል ይዘን ድምዳሜ ላይ ልንደርስ እንችላለን። እስከዚያው ግን፤ ፖሊስን እየደጋገምን፤ “ስመኘውን ማን ገደላቸው?”—አበቃለት እንዴ? እያልን ልንጎተጉተው ይገባል እላለሁ።