Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

በአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት አስተዳደርና ጸጥታ ጉዳዮች ቢሮ በወቅታዊ የጽጥታ ጉዳዮች ላይ የተሰጠ መግለጫ

0 3,675

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

በአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት አስተዳደርና ጸጥታ ጉዳዮች ቢሮ በወቅታዊ የጽጥታ ጉዳዮች ላይ የተሰጠ መግለጫ

በሀገራችንም ሆነ በክልላችን ለተጀመረው አዲስ የለውጥ እንቅስቃሴ ሰላም እና ልማት ፈላጊ በሆነው መላው ሀዝባችን ከፍተኛ ንቅናቄ እና ዋጋ ከፍሎ ያመጣው በመሆኑ አሁንም በህዝባዊ ንቅናቄ እና በመንግሰት መሪነት ተጠናክሮ እየቀጠለ ይገኛል፡፡
የክልላችን መንግስት የተጀመረው የለውጥ ሂደት ተጠናክሮ የሕዝቡ መብት እና ጥቅም እንዲከበር ከፍተኛ የድጋፍ እና መሪነት ስሜት በመላበስ ለውጡ ዳር እንዲደርስ ራሱን በመፈተሽ የተጀመረውን የጥልቅ ተሃድሶ ንቅናቄ አጠናክሮ ለማስቀጠል በከፍተኛ ፍላጎትና ቁርጠኝነት የህዝቡን ስሜት ጠብቆ እየተንቀሳቀሰ እንደሆነ መላው የክልላችን ህዝብ ተገንዝቧል፡፡

ይህንንም ለማረጋገጥ በቅርቡ የተደረገውን የአመራር ለውጥና ይህን ተከትሎ በጠቅላይ ሚኒስትራችን መሪነት በአጭር ጊዜ እየወሰዱት ያለውን እርምጃና እየታየ ያለውን ለውጥ በማየት በክልላችን በሁሉም አካባቢ የሚገኘው ህዝብ እድሜና ፆታ ሃይማኖት ወዘተ ምንም ነገር ሳይገድበውና ሳይለያየው በአንድነትና በፍቅር ድጋፉንና ወደ ፊት ያለውን ተስፋ ለማረጋገጥ አደባባይ በመውጣት አሳይቷል፡፡

መንግስት በሀገራችን ተፈጥሮ የነበረውን ኢ-ፍትሃዊነት፣ ጥርጣሬና ጥላቻ እንዲሁም የዜጎች ሰባዊና ዴሞክራሲ የመብት ጥሰቶች እንዲቆሙና ቀጣይም ሳይሸራረፉ እንዲከበሩ ጊዜው የይቅርታ፣ የፍቅርና የመደመር እንዲሆን ከፍተኛ ንቅናቄ በመፍጠር ላይ መሆኑ ያታወቃል፡፡ በተለይ የማይነኩ የሚመስሉ ልዩ ልዩ ታላላቅና መሰረታዊ ውሳኔዎችን በማሳለፍ የለውጡን ሁደት በተግባር አረጋግጧል፡፡ ይህም በተለያየ ምክንያት በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር እስር ቤት የሚገኙ ዜጎች በምህረትና በይቅርታ እንዲፈቱና በሀገራቸው ሁለንተናዊ የእድገት ጉዞ ተሳታፊ እንዲሆኑ ተደርጓል፡፡
ውጭ ሆነው ስለሀገራቸው ለውጥ የራሳቸውን አጀንዳ በመያዝ ሲያራምዱ የነበሩ አካላት መንግስት ያደረገላቸውን ጥሪና እየተካሄደ ያለውን ትክክለኛ የለውጥ ጉዞ ተቀብለው በሀገራቸው ውስጥ ሆነው ሰላማዊ ትግል ለማድረግ ሙሉ ፍላጎታቸውን ከመግለፅ አልፈው ሀገር ውስጥ ገብተው ከመንግስት ጋር በሰላማዊ ሁኔታ መነጋገር ጀምረዋል፡፡
ከሀያ አመት በላይ ያስቆጠረው ኢትዮ-ኤርትራ የነበረው ፍጥጫና ጦርነት የሀገራችን ኢኮኖሚ እንዲሽመደመድ ቁማር ሲሰራበት የነበረው አጀንዳ ተወግዶ በሁለቱ ሀገሮች መካከል ተፈጥሮ የነበረው ቁርሾ እንዲስተካከልና ሰላም እንዲፈጠር እንዲሁም የሁለቱም ሀገር ህዝቦች በደምና በአጥንት አንድ በመሆናቸው በተደረገው የለውጥ ጉዞ ውስጥ አንዱና ትልቁ አጀንዳ በመሆኑ በቅርቡ የሁለቱ ሀገራት መሪዎች በቅርበትና በአካል እየተገናኙ በከፍተኛ የፍቅርና የአንድነት ስሜት የህዝቡን አንድነት ይበልጥ በሚያጠናክር መልኩ ተፈፃሚ ሆኗል፡፡

ይህም በመሆኑ ከራሳቸው አልፈው በምስራቅ አፍሪካና በባህረ ሰላጤው ቀጠና ያለው የዓለም ሀገራት የመነሃሪያ መስመር የተከሰተውን ስጋት በመቀነስ የሚገኘውን ጥቅም ለማጎልበትና ተፈላጊነትን ለመጨመር ሁለቱም ሀገሮች የወሰዱት እርምጃ ታሪካዊና ወቅታዊ ድል ተደርጎ የሚወሰድ የሀገራችን መሪ ብስለትና ፍላጎት አረጋግጦ ያለፈና ዓለምን ያስደመመ ውሳኔ ተብሎለታል፡፡
ከከልላችንም የትጥቅ ትግልን አማራጭ አድርገው በኤርትራ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ የአዴሀንና ግንቦት ሰባት አትበኞች ግንባር ኃይሎችን የክልላችን መንግስት የልዑክ ቡድን አስመራ ድረስ በመላክ ድርድር በማድረግ ወደ ክልቸው ገብተው ሰላማዊ ትግል እንዲያካሂዱ እና ለዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ሂደቱ የራሳቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ የሚያስችል ስራ በመሰራቱ ባመነበትና ከቤተሰብ በመቀላቀል ላይ ይገኛል፡፡
በአጠቃላይ የክልላችን መንግስት በሀገራችን እየተካሄዱ ያሉትን ታላላቅ የለውጥ ውሳኔዎችን ሙሉ በሙሉ በመቀበል ለተፈጻሚነታቸው በሙሉ ዕምነት እየሰራ ይገኛል፡፡
በተለይም ባለፉት ጊዚያቶች ተፈጥረው የነበሩ ቀውሶች ተመልሰው የለውጡ መሰናክል እንዳይሆኑ የክልላችን የጸጥታ ሀይል ከህዝቡ ጋር በመቀናጀት የህዝቡን ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ሳይሸራረፉ ለውጡ እንዲቀጥል በከፍተኛ ጥንቃቄ እየተሰራ ይገኛል፡፡ዳግም የሰው ህይወት እንዳይጠፋና አካል እንዳይጎድል በከፍተኛ ተዕግስት ራሱ እየደማና እየሞተ የህዝቡን እንቅስቃሴ እየተከታተለ ይገኛል፡፡
ይሁን እንጂ ይህ እርምጃ በአንድም ይሁን በሌላ ጥቅማቸው የሚነካ የመሰላቸውና ውስጣቸው ለሰላም ፣ለይቅርባይነት ፣ለአንድነት እና ለፍቅር መገዛት ሽንፈት መስሎ የታያቸው ሀይሎች የለውጡን ጉዞ በተለያየ መንገድ ለማደናቀፍ ሌት ተቀን እየተረባረቡ መሆኑን ተመልክተናቸዋል፡፡
በተለይ ያረጀ እና ዘመኑ የማይፈቅደውን የማይመጥን አስተሳሰብ በማራመድ የለውጡን ጉዞ ከመላው ህዝብ ስሜትና አመለካከት በላይ እኛ እናውቃለን በሚል እብሪት በመወጠር የተለያየ ሴራ በመሸረብ ተፈጥሮ የነበረውን ሁከትና ግርግር እንዲቀጥል የሰው ህይወት በተራ ነገር እንዲጠፋ አካል እንዲጎድልና ንብረት እንዲጠፋ እንዲሁም እያታየ ያለው የለውጥ ማዕበሎ ተሸመድምዶ እንዲቀር ያለመታከት ጥረት እያደረጉ መሆናቸውን እየተመለከትናቸው ነው፡፡
በተለይ ህዘብ ከህዝብ ለማጋጨት የጥላቻ ፕሮፖጋንዳ በመልቀቅና ሁከትና ብጥብጥ በመፍጠር የሚታየውን ለውጥላለማስቀጠል በትዕቢት ውስጥ በመሆን ከለውጡ ጉዞ እራሰን ማሸሽና ለውጡን ለማደናቀፍ መውተርተር በስፋት ይታይል፡፡
በዚህም በተሳሳተ መረጃና አሉባልታ በመነዳት በተለይ አጠቃላይ ለውጡንና የህግ የበላይነትን በህገ ወጥ መንገድ ለመፈጸምና መንግስትን ተክቶ ለመስራት እየተደረገ ያለው እንቅስቃሴ ፣የክልሉ ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት የሆነውን የግብርና ምርት እንዳይሸጥና የአርሶ አደሩ ኑሮ እንዳይሻሻል የማገት፣ የመዝረፍና የማውደም ተግባር ፣በክልሉ የሚገኙ የኢንቨስትመንት ተቋማት ላይ ጥቃት መፈጸም ወ.ዘ.ተ የተገኘውን ነጻነት ይበልጥ አጠናክሮ የሚያስቀጥል ሳይሆን የህግ የበላይነትን በመጣስ የተገኘውን ለውጥ በመቀልበስ መልሶ ህዝቡ ታግሎ ያገኘውን መብት ማጣትና እንዲሁም ክልሉን ለመጉዳት የተቀየሰ እኩይ ተግባር በመሆኑ ህዝቡ ይህን ተረድቶ ነጻነቱን ጠብቆ ለማስቀጠል የህግ የበላይነትን በዚህ ተግባር የተሰማሩት አካላትን መላው ህዝባችን ትክ ብሎ እንዲመለከታቸውና እንዲገስጻቸው አስፈላጊ ይሆናል፡፡

የክልላችን የፀጥታ ሃይል በሀገራችንም ሆነ በክልላችን የተዘረጋው ሰላም አስተማማኝና ዘላቂ ሆኖ እንዲቀጥል የተጀመረው ኢኮኖሚያዊ ልማት ተጠናክሮ እንዲካሄድና የህዝቡንም ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እተገነባ ያለው ዴሞክራሳዊ ስርአት እንዲጎለብትና ዋስትና እንዲኖረው ለማስቻል መሰእዋትነት ጭምር እየከፈለ የተሰጠውን ህዝባዊና ህገ-መንግስታዊ ግዳጁን እየተወጣ ከህዝቡ ፊት ቆሞ መምራት ይጠበቅበታል፡፡
ከቅርብ አመታት ወዲህ በሀገራችና በክልላችን እየተፈጠረ ባለው ሁከትና ግርግርም ህዝባዊነቱን በማረጋገጥ በራሱ ላይ ተፈፅሞበት የማያውቁ አሰቃቂ ጥቃቶች ሁሉ እየተፈፀሙበት በአርቆ አሳቢነት ለተሰለፈለት የነፃነትና ለህግ የበላይነት አላማ ተገዥ በመሆን አሁንም የሀገሩንና የክልሉን ህዝቦች ደህንነት ለማረጋገጥ ከፍተኛ ስራ እየሰራ የሚገኝ ቢሆንም የበለጠ ተደራጅቶ ችግር ፈጣሪዎችን ለህግ በማቅረብ የክልላችን ሰላም የመጠበቅ ግዴታ አለበት፡፡
የለውጡ ሂደት ያልተዋጠላቸውና ህገወጥ ድርጊት በመፈፀም ጥቅማቸው እንዳይነካ አቅጣጫ ለማስቀየር የሚፈልጉ ሃይሎች ይህንን የማይበገር ጥንካሬና የመደመር ሚስጥር ስለተረዱትና ዓላማቸው እንዳይሳካ የሚያደርግና ተስፋ የሚያስቆርጥ ሆኖ ሲመለከቱት ልዩ ልዩ የመቃዠትና የመወራጨት እንቅስቃሴ ውስጥ በመግባት የጥፋት ተልኮ እየሰጡ ህዝቦችን ነፃነት ሲያሳጡና ሲያበሳጩት ይስተዋላሉ፡፡
የፀጥታ ሃይላችንም በመካከሉም ለመከፋፈል ሲሞክሩ የሰው ህይወት እንዳይጠፋ በትግስተና አርቆ አሳቢነት እየወሰደ ያለውን እርምጃ የፍርሃትና የመፈፀም ብቃት ችግር እንደገጠመው አድርገው ሲፈርጁት ይታያል፡፡ ነገር ግን የፀጥታ ሃይላችን እንድነቱን የበለጠ እያጠናከረ በጠናካራ ቅንጅት ግዳጁን እየተወጣ እንደሚገኝና አሁን እየታየ የመጣውን በነፃነት ሽፋን የሚደረገውን ህገ-ወጥ እንቅስቃሴ ለማስቆምና የህግ-የበላይነትን ለማረጋገጥ ዝግጁ መሆኑን በዚህ አጋጣሚ ልናስገነዝብ እንወዳለን፡፡
አልፎ አልፎ በግለሰብ ደረጃ የሚታዩ የስነ-ምግባርም ሆነ የአመለካከት እንዲሁም የእርምጃ አወሳሰድ እግሮችና ግድፈቶችን ለማረም ባህል አድረጎት በመጣውና ግንባታን መሰረት ያደረገ ክትትልና ድጋፍ እንዲሁም የግምገማ ስርዓት እራሱን እያጠራ አሁንም የተሰጠውን ህዝባዊና ህገ-መንግስታዊ ተልዕሆውን ማረጋገጥ እንደሚገባው እየሰራን እንገኛለን፡፡
የተጀመረው የለውጥ ጉዞ ሳይንገራገጭ እንዲቀጥልና አፍራሽ አጀንዳ ያላቸው ሃይሎች ከድርጊታቸው ተቆጥበው የለውጡ አካል እንዲሆኑ የሚያስችል ትዕግስት የተሞላበት ነገር ግን ደግሞ ለአደጋ የማያጋልጥና ፈጣን ምላሽ የሚሰጥ እንቅስቃሴ እያደረግን መሆናችንን እንገልፃለን፡፡
ስለሆነም በሀገራችንም ሆነ በክልላችን በመካሄድ ላይ ያለውን የለውጥ ጉዟችንን በላቀና በተፋጠነ መልኩ ለማስኬድና ህዝባችን የደረሰበትን የልማት ጥማት ጥያቄና ሞጋችነት በአግባቡ እንዲመለሱ የሚያስችሉ ሁለንተናዊ ስራዎች እየተሰሩ በመሆኑ ይህ ሂደት እንዳይደናቀፍ የሚከተሉት እንቅስቃሴዎች እንዳይፈፀሙ በጥብቅ ልናሳስብ እንወዳለን፡፡
1. በግልፅ የተቀመጡትን የዜጎችን ሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች ማለትም በህይወትም ሆነ በአካላቸው ላይ የሚደርስን አደጋና ጉዳት፣ሃሳባቸውን በነፃነት የመግለፅ መብት፣ ከቦታ ቦታ የመንቀሳቀስ መብታቸውን ንብረታቸው እና ሀብታቸው ከዘረፋና ከውድመት እንዲጠበቁ እና ሳይሸራረፉ እንዲከበሩ የህግ የበላይነት የማረጋገጡ ተልዕኮ የፀጥታ ሀይላችን በመሆኑ በክልላችን የሚገኙ የፀጥታ አመራርና ፈፃሚ አካላት ግዳጃቸውን በቁርጠኝነት እና በፅናት ሊወጡ እንደሚገባ እናሳስባለን፡፡
2. መንግስትን ተክቶ የራስን ፍላጎት ለማሳካት በማሰብ በግለሰብም ይሁን በቡድን የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ህግ ባለበት ሀገርና ክልል ፈፅሞ የማይጠበቅና መሆን የማይገባው በመሆኑ ይህን ድርጊት በሚፈፅም ግለሰብ ወይም በቡድን የተደራጀ ሀይል ላይ ህጋዊ እርምጃ በመውሰድ የህግ የበላይነት እንዲረጋገጥ ከመቸውም ጊዜ በላይ ህገ-ወጥ መሆኑን ተገንዝበን ልንቆጠብና በሚመለከተው አካል እንዲሰራ አጥብቀን እናሳስባለን፡፡
3. ህግን ለማስከበር ስልጣን የተሰጠው ማንኛዉም የመንግስት አካል በህግ እንዲሰራ የተሰጠውን ኃላፊነት ባለመታዘዝ በኃይል ወይንም በዛቻና በማስፈራራት ለማሸማቀቅ የሚደረገው እንቅስቃሴ ህገ-ወጥነት በመሆኑ ይህ ተግባር እንዳይፈፀምና እንዳይደገም አጥብቀን እናስገነዝባለን፡፡
4. የመንግስት ኃላፊነትን የተሸከሙ አካላትን በህግና ስርዓት ማንሳትና ከዚህም አልፎ በመንግስት መተካት እየተቻለ በሀይል እና በዘመቻ የመንግስትን ኃላፊነት ዋጋ ለማሳጣት የሚደረግ ማንኛውም እንቅስቃሴ የህግ ጥሰት መሆኑን ተገንዝቦ ከዚህ ድርጊት እንዲቆጠብ እያሳሰብን ይህን ተላልፎ በሚገኝ አካል ሳንወድ በግድ ህግ የማስከበር ስራ እንሰራለን፡፡
5. በክልላችን በሁሉም አካባቢዎች የሚገኙ የልማትና የኢንቨስትመንት ተቋማት እንዲሁም በአርሶ አደር ተመርተው ለገበያ የቀረቡ የተለያዩ ምርቶች ላይ የሚደረግ ቅሚያና ውንብድና፤ሀገር አቋራጭ የጭነት ተሸከርካሪዎች እና የክልሉን ኢኮኖሚ የሚጎዱ ህገ ወጥ ድርጊቶች እንዳይፈፀሙ ህግን የማስከበር ስራ ላይ የማንደራደር መሆናችንን እጠገለፅን ህብረተሰቡ የፀጥታ ሀይላችን ተባባሪ እንዲሆን ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡
6. ህዝቡ ታግሎ ያመጣዉን ነፃነት ለማስቀጠል የህግ የበላይነት እንዲረጋገጥ በተለይ ተፎካካሪ ፓርቲዎች፣ የሀይማኖት ተቋማት ፣አመራሮችና ታላላቅ አባቶች፣የሀገር ሽማግሌዎች፣ወጣቶች እና ሴቶች ልዩልዩ አደረጃጀቶች እና ማህበራት ወዘተ ለአካባቢያቸው ሰላምና ደህንነት መረጋገጥ የበኩላችሁን ሚና እንድትወጡ ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡
7. በአጠቃላይ ህብረተሰቡን ያሳተፈና ባለቤት ያደረገ ሰላምን የማረጋገጥ ስራ ለመስራት በቁርጠኝነት የተዘጋጀን መሆናችንን እየገለፅን መላዉ የክልላችን ህዝብም ይህንን ተገንዝቦ ለክልሉ ሰላምና ደህንነት መረጋገጥ ከፀጥታ ሃይላችን ጎን በመሰለፍ የተለመደውን የተጠናከረ ድጋፍና ግንኙነት አጥብቆ እንዲያስቀጥል ጥሪያችንን እናስተላልፋለን ፡፡
የለውጡ ጉዞ በሰላም ወዳዱ ህዝብና የፀጥታ ሀይላችን የጋራ ርብርብ ይረጋገጣል!!
ጳጉሜን1/2010ዓ.ም
ባሕር ዳር
አስተዳደርና ፀጥታ ጉዳዮች ቢሮ

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy