Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

በእንባ የረጠበ እና ተስፋን የጫረ ውይይት

0 471

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

በእንባ የረጠበ እና ተስፋን የጫረ ውይይት

አሜን ተፈሪ

በቅርቡ ከኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል የወጡትን መረጃዎች ስንመለከት፤ የክልሉ ህዝብ በምን ዓይነት መከራ ውስጥ እንደ ከረመ በውል ለመረዳት የሚያስችል ነው፡፡ ክልሉን የሚያስተዳድረው የሶህዴፓ ማዕከላዊ ኮሚቴም የክልሉን ወቅታዊ ሁኔታ በጥልቀት ገምግሞ ያወጣው መግለጫ እንዳመለከተው፤ በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል የነበረው ችግር፤ የመንግስትን እና የፓርቲን ተቋማዊ አሰራር ጨርሶ ያጠፋ ስር የሰደደ ችግር ነበር፡፡

በበኩሌ፤ በግምገማው ከታዩት ዘግናኝ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች እና የመልካም አስተዳደር ችግሮች እኩል፤ የክልሉ ከፍተኛ አመራር የተጠያቂነት ነፋስ መንፈስ ሲጀምር፤ ገመናውን ለመሸፈን የሞከረው፤ በህግ መንግስታዊ የሆነውን ‹‹የራስ ዕድልን በራስ የመወሰን መብት እስከ መገንጠል›› መብት በማንሳት መሆኑ በጣም ‹‹በበደል ላይ በደል›› የሚያሰኝ ስሜት አሳድሮብኛል፡፡ ‹‹የራስ ዕድልን በራስ የመወሰን መብት እስከ መገንጠል›› መብት በህግ መንግስቱ ዋስትና ያገኘ መብት በመሆኑ፤ በተጨባጭ የሚታይ እና ብሔራዊ ማንነቴ የሚጎዳ በደል ደርሶብኛል የሚል ማንኛውም የፌደሬሽኑ አባል በሆነ ክልል ህዝብ፤ የህግ አግባብን ተከትሎ ጥያቄውን ሊነሳ ይችላል፡፡ ነገር ግን የህግ በላይነት፣ ዴሞክራሲያ መብት እና ነጻነት፤ እንዲሁም የሰብአዊ መብት የሚባል ነገር መኖሩን ጨርሶ ረስቶ፤ የክልሉን መንግስት እንደ ግል ኩባንያ በመቁጠር ህዝቡን ሲያስለቅስ የቆየ ፍፁም አምባገነን የሆነ አመራር፤ እንደ በፊቱ በኃይል ታመቆ ሊቀር የማይችል የመብት ጥያቄ ከህዝብ ሲነሳበት፤ ‹‹የራስ ዕድልን በራስ የመወሰን መብት እስከ መገንጠል›› የሚል አጀንዳ ይዞ ጉባዔ መዘርጋቱ አስገራሚ ነው፡፡ አነጋጋሪ መሆኑ እንደ ተጠበቀ ሆኖ፤ የህዝብ መብትን በተሟላ አኳኋን ለማስከበር ታስቦ በህገ መንግስት የሰፈረውን ድንጋጌ፤ አመራሩ ያለ አንዳች ታዛቢ እና ከሳሽ ህዝቡን ረግጦ የመግዛት ፍላጎቱን ለማስፈጸም ሊጠቀምበት ሙከራ ማድጉን ስመለከት፤ ‹‹የራስ ዕድልን በራስ የመወሰን መብት እስከ መገንጠል›› በሚለው ድንጋጌ ዙሪያ ያሉ አንዳንድ የተዛቡ አመለካከቶችን እንደገና ለማብላላት አነሳሳኝ፡፡

ዘግናኝ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች እና የመልካም አስተዳደር ችግሮች የሚታዩት በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ብቻ አይደለም፡፡ በሁሉም ክልሎች ተመሳሳይ ችግሮች አሉ፡፡ ሆኖም ሶማሌ ክልል በቅርቡ የታየው ችግር፤ በሌሎች ክልሎች እንደ ታየው እና በሐገራችን የተከፈተውን የመልካም ዕድል መስኮት የሚዘጋ አሳሳቢ ችግር ብቻ ተደርጎ ከመታየት ባለፈ፤ ክልሉን፣ ሐገርን እና ቀጣናውን ጭምር ለከፋ ቀውስ ሊዳርግ የሚችል አደጋ ያረገዘ ችግር አድርጎ ለመውሰድ የሚያስችል ነው፡፡

በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ከፍተኛ አመራሮች ዘንድ በሌሎች ክልሎችም በሰፊው የሚስተዋለል የመልካም አስተዳደር እጦት፣ ሙስና፣ በትንሽ ድል የመኩራራት እና ለችግሮች ደንታ ቢስ የመሆን፣ እንዲሁም በብሔርተኝነት ጭምብል ያለአንዳች ተጠያቂነት ያሻህን የመስራት አዝማሚያዎች መታየቱ ብዙ ሊገርመን አይችልም፡፡ ነገር ግን የተጠያቂነት ነፋስ ሲመጣ፤ ሲያስለቅሱት እና ሲያንገላቱት የነበረውን፤ ኢትዮጵያዊነቱን እና የፌደራል ስርዓቱን በማክበር ረገድ በሚያሳየው ልዩ ቀናዒ ስሜት መታወቅ የጀመረውን የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ህዝብ፤ ከፌደሬሽኑ ለመገንጠል በመሳብ እንቅስቃሴ ውስጥ መገባቱ እጅን በአፍ ላይ የሚያስጭን ድንቅ ነገር ነው፡፡ የመልካም አስተዳደር እጦት፣ የሙስና እንዲሁም በብሔርተኝነት ጭምብል ያለአንዳች ተጠያቂነት ያሻህን የመስራት አዝማሚያዎችን በጥብቅ ታግለን ማስወገድ ካልቻልን ከምን ዓይነት አደጋ ጋር እንደምንጋፈጥ በግልጽ የእንድንረዳ የሚያሳይ ከስተት ነው፡፡

ስለሆነም እነዚህን ችግሮች በፍጥነት በማስወገድ እና በአዲሱ የኢህአዴግ አመራር የተፈጠሩትን የመልካም ዕድል መስኮቶች በአግባቡ ከመጠቀም ባሻገር አዳዲስ መስኮቶችንም በፍጥነት እና በብዛት በመክፈት፤ የጀመርነውን ተስፋ ሰጪ የህዳሴ ጉዞ ማስቀጠል ይኖርብናል፡፡  

ይህ ሁኔታ የመፍጠር ዓላማ ያለው እና በጠ/ሚ ዶ/ር ዐቢይ አህመድ የተመራ አንድ የውይይት መደረጉ አይዘነጋም፡፡ ይህም ውይይት በእንባ የረጠበ እና ተስፋን ያጫረ ውይይት እንደነበር አይተናል፡፡ ቀደም ሲል፤ የዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ተፈፀመ የሚሉትን ዘግናኝ የሰብአዊ መብት ጥሰት ሪፖርተቶች የተመለከትኩ እና የክልሉ ተወላጅ የሆኑ ‹‹አክቲቪስቶች›› የሚያቅርቧቸውን ክሶች ስሰማ የቆየሁ ቢሆንም፤ የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ከፍተኛ አመራሮች ሲያደርሱት የቆዩትን የመብት ጥሰት ከራሳቸው ከባለጉዳዮቹ  አንደበት ስሰማው የተለየ ስሜት ፈጥሮብኛል፡፡

ጠ/ሚ ዶ/ር ዐቢይ አህመድ፣ የመንግስት ኮምዩኒኬሽን ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ እና አዲሱ የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ፕሬዚዳንት በተገኙበት መድረክ፤ የክልሉን የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የሚወክሉ የውይይት መድረኩ ተሳታፊዎች፤ እንዲሁም የመብት ጥሰት የደረሰባቸው ሰዎች የተናገሩት ነገር ልብን በሐዘን የሚሰብር ነበር፡፡ ጠ/ሚ ዶ/ር ዐቢይ አህመድን ጨምሮ በርካቶች በሰሙት ነገር እንባቸውን አፍስሰዋል፡፡ በዚሁ መድረክ በራሳቸው እና በቤተሰቦቻቸው ላይ የተፈፀመውን የግፍ ተግባር ያወሱት አዲሱ የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ሙስጠፋ፤ ወንድማቸው በግፍ እንደ ተገደሉባቸው ጠቅሰው፤ ነገር ግን ህዝቡ የደረሰበትን መከራ በቂም መንፈስ ማሰብ እንደ ሌለበት ሲያሳስቡ፤ ‹‹እኔ ወንድሜ ስለተገደለብኝ፤ የወንድሜን ገዳይ ወንድሞች የምገድል ከሆነ፤ ሁላችንም ወንድም አልባ እንሆናለን›› በማለት፤ አዲሱ የኢህአዴግ አመራር በሚከተለው የይቅርታ፣ የምህረት፣ የፍቅር እና የአንድነት መንፈስ በመመራት ለክልሉ ልማት ተግተው እንዲሚሰሩ   ገልጻዋል፡፡

ኢትዮጵያውያን ባለፈው መቶ ዓመታት ደጋግመን የወደቅንበትን ፈተና ለማለፍ፤ በድህነት እና በኋላ ቀርነት ወህኒ ቆልፎ ከያዘን የአስተሳሰብ እና የአሰራር ዘይቤ ለመላቀቅ፤ እንዲሁም ከበቀል፣ ከመገዳደል፣ ከመገፋፋት እና ከሴራ ፖለቲካ ለመውጣት ውሳኔ አድርገን እና ጥርሳችንን ነክሰን አስቸጋሪውን አቀበት ለመውጣት መዘጋጀት እንዳለብን የገለፁት ጠ/ሚ ዶ/ር ዐቢይ አህመድ፤ ‹‹ጠንክረን ከሰራን የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልልን በአጭር ጊዜ መለወጥ የሚያስችል እና ከክልሉ አልፎ ለመላ ኢትዮጵያ ሊተርፍ ከፍተኛ የተፈጥሮ ፀጋ አለው›› በማለት የክልሉ ህዝብ በመተባበር እንዲሰሩ አሳስበዋል፡፡

በመድረኩ ትኩረት ካገኙ ገዳዮች መካከል አንዱ፤ በደንብ ታቅዶ እና ዝግጅት ተደርጎበት በተደራጀ አግባብ በሐይማኖት ተቋማት ላይ የተፈፀመው ጥቃት እና ብሔርን ወይም እምነትን የተንተራሰ የግድያ እና የንብረት ዘረፋ እና ውድመት ነው፡፡ የጉባዔው ተሳታፊዎች የሆኑ የሐገር ሽማግሌዎች፣ ኡጋሶች እና የሐይማኖት አባቶች በተከሰተው የተቀነባበረ እና ሰፊ የሆነ የጥቃት እርምጃ ከፍተኛ ሐዘን እንደተፈጠረባቸው በመግለጽ፤ በጥቃቱ ጉዳት የደረሰባቸውን ወገኖች ለመደገፍ እና የተቃጠሉትን የእምነት ተቋማት መልሶ ለመገንባት ግንባር ቀደም ጥረት እንደሚያደርጉ አስታውቀዋል፡፡

በአጠቃላይ በቅርቡ በክልሉ የተከሰተው ችግር፤ የተስተካከለ አቋም የሌለው አመራር ምን ያህል የህዝብን ጥቅም በሚጻረር መንገድ እንደሚሄድ የሚያስገነዝብ ግልጽ ትምህርት አስተምሮናል፡፡ የክልሉ ገዢ ፓርቲ የማዕከላዊ ኮሚቴ ባደረገው ግምገማ፤ በክልሉ እጅግ ሥር የሰደደ የሙስና፣ የመልካም አስተዳደር እና የሰብአዊ መብት ጥሰት ችግሮች መኖራቸውን አረጋግጦ መፍትሔ ያለውን የማስተካከያ እርምጃዎችን ወስዷል፡፡ አንድ የገባዔው ተሳታፊ እንዳሉት ‹‹የክልሉ መንግስት የአንድ ቤተሰብ ንብረት ሆኖ ቆይቷል›› ሲሉ እንደ ገለፁት ያለ አምባገነናዊ አስተዳደር በሰፈነበት እና ጨርሶ የህግ የበላይነት በማይታወቅበት የግፍ አገዛዝ ፍዳውን ሲያይ የቆየው የክልሉ ህዝብ፤ በደል በቃኝ ብሎ ሲነሳ አመራሩ ራሱን በማረም ፋንታ ክልላዊ፣ ሐገራዊ እና ክፍለ አህጉራዊ ቀውስ ሊፈጥር በሚችል አቅጣጫ ለመጓዝ መምረጡ፤ አንዳንድ ነገሮችን ዳግም ለመፈተሽ የሚገፋፋ ነው፡፡

እነሱ ከህግ በላይ ሆነው የሚኖሩበትን እና የብሔር ጭንብል አጥልቀው እንዳሻቸው ለማድረግ የሚችሉበትን ዕድል ከሚያጡ፤ ህዝቡ በሐይማኖት ቢተላለቅ እንደሚመርጡ ስናይ፤ የእነሱ አምባገነናዊ ሥልጣን ጥያቄ ውስጥ ከሚገባ የህዝቦች አንድነት ገደል ይግባ ከማለት እንደሚደርሱ ስንመለከት፤ ፖለቲከኞች ምን ያህል ኃላፊነት የገደለው አስተሳሰብ እንደሚሸከሙ መረዳት እንችላለን፡፡ እነሱ ሥልጣን ከሚያጡ፤ ለህዝቦች ዘላቂ ጥቅም ዋስትና የሆነው እና ህዝቦች መክረው – ዘክረው የመሰረቱት ፌደሬሽን ቢበተን የሚመርጡ ፖለቲከኞች ሊገጥሙን እንደሚችሉ አይተናል፡፡

የያዙትን ከፍተኛ የህዝብ ኃላፊነት ወደ ጎን አድርገው፤ ህዝባቸውን አፍነው እና ረግጠው ሲገዙ የቆዩ አምባገነኖች፤ በስስት ሊያዝ የሚገባውን የህዝብ ሐብት እና ንብረት እንዳሻቸው እየበተኑ እና እየመዘብሩ መቀጠል የማይችሉበት ሁኔታ ሲፈጠር እና ተጠያቂነትን የሚያመጣ አሰራር ለማስፈን ጥረት ማድረግ ሲጀመር፤ ኢ-ሰብአዊ በሆነ ሁኔታ ዜጎችን ሲያሰቃዩ የከረሙ እና ሰውን ከአንበሳ እና ከጅብ ጋር አስረው ለአዕምሮ የሚከብድ ወንጀል ሲፈጽሙ የነበሩ ባለሥልጣናት በለመዱት መንገድ መግዛት እንደማይችሉ ሲያረጋግጡ፤ እንደ ብረት ቀጥቅጠው ሊገዙት እና እንደ ከብት ሊነዱት የሚፈልጉትን ህዝብ መብት ለማረጋገጥ ታስቦ የህገ መንግስት ዋስትና ያገኘውን ‹‹የራስ ዕድልን በራስ የመወሰን መብት እስከ መገንጠል›› መብት እንዲከበር ጥያቄ እናቀርባለን የሚል ጉባዔ ሲዘረጉ ተመልክተናል፡፡ የህዝብን መብት ለማስከበር ታስቦ በህግ የተደነገገውን አንቀጽ ህዝብን እንዳሻቸው አድርገው ለመግዛት የሚያስችል ዕድል ለማረጋገጥ ሊጠቀሙበት ሲሞክሩ አይተናል፡፡ የህዝብን መብት የወንጀል መደበቂያ ዋሻ እና ከተጠያቂነት ማምለጫ ሊያደርጉት እንደሚመኙ አስተውለናል፡፡

ይህ መብት መከበር አለበት በሚል ሽንጣቸውን ገትረው የሚከራከሩ ግለሰቦች እና ቡድኖች ያሉትን ያህል፤ ‹‹የራስ ዕድልን በራስ የመወሰን መብት እስከ መገንጠል›› መብት የህግ እውቅና ሊሰጠው የሚገባው መብት አይደለም፤ ሐገር አፍራሽ ድንጋጌ በመሆኑ ከህገ መንግስቱ ሊሰረዝ ይገባል በማለት የሚከራከሩ ግለሰቦች እና ቡድኖችም አሉ፡፡ በበኩሌ፤ መብቱን በመርህ ደረጃ ለመቃወም የሚያስችል አሳማኝ የፖለቲካ ትንታኔ ገጥሞኝ አያውቅም፡፡ ስለዚህ ‹‹እንዴት ተደርጎ›› የሚል አቋም ለመያዝ የሚያበቃ አቋም ባይኖረኝም፤ በመርህ ደረጃ ከመደገፍ ተሻግሬ እንደ ኤርትራ የ30 ዓመታት ጦርነትን ለማስወገድ የሚያስችል መፍትሔ ሆኖ ሳገኘው በተግባር ደጋፊ ለመሆን እደፋፈራለሁ፡፡ ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ፤ ‹‹የራስ ዕድልን በራስ የመወሰን መብት እስከ መገንጠል›› የሰነፍ እርምጃ መስሎ ሳይታየኝ ቀርቶ አያውቅም፡፡ የቡድን መብት የማይከበረበት ሁኔታ በተፈጠረ ጊዜ፤ ህዝቦች ‹‹የራስ ዕድልን በራስ የመወሰን መብት እስከ መገንጠል›› መብታቸውን ተጠቅመው፤ የበደሉን በር መዝጋት የሚችሉበትን ዕድል ያገኛሉ፤ ተበደልን ብለው ሲያስቡ፤ ከፌዴሬሽኑ በመነጠል የራሳቸውን ነጻ መንግስት ለመመስረት የሚችሉበትን ዕድል መፍጠር ወይም በሩን ገርበብ ማድረግ፤ ጭቆና ሊደርስብን ይችላል የሚል ስጋት የሚኖራቸው ወገኖች የሚያነሱትን ስጋት በመቅረፍ፤ ህዝቦች በፈቃዳቸው የፌዴሬሽኑ አባል ለመሆን እንዲደፋፈሩ ያደርጋል፤ በዚህም የህዝቦችን ዴሞክራሲያዊ አንድነት ያጠናክራል የሚል  ክርክር የሚያራምዱ ሰዎች እና ቡድኖችም አሉ፡፡

ይህ ክርክር ‹‹መብቶች ሊጣሱ የሚችሉት ከእኔ የተለየ ማንነት ካለው ህዝብ ጋር አብሬ ከኖርኩ ነው›› የሚል አስተሳሰብን መነሻ የሚያደርግ መስሎ ይታያል፡፡ በሌላ በኩል፤ ክርክሩ የብሔር ማንነትን ብቻ የሚመለከት ይመስላል፡፡ የቡድን መብትን ከብሔር/ብሔረሰብ ወይም ከቋንቋ ጋር ብቻ የአያይዞ የሚመለከት ሆኖ ይታያል፡፡ ነገር ግን የቡድን መብት፤ ሐይማኖትን፣ የፖለቲካ አመለካከትንም የሚጨምር መሆኑ የሚያከራክር አይሆንም፡፡ ሆኖም የዚህ መብት ደጋፊዎች፤ ‹‹የቡድን መብቴ አልተከበረም›› የሚል ጥያቄ የሚያነሳ አንድ የሐይማኖት ወይም የፖለቲካ ቡድን የመገንጠል ጥያቄ እንዲያነሳ የሚደግፉ አይደሉም፡፡ ስለዚህ የብሔር መብት እንደ ማንኛውም የቡድን መብት ዴሞክራሲያዊ ስዓትን ከማረጋገጥ ውጭ መፍትሔ ሊያገኝ አይችልም የሚል ድምዳሜ እንደይዝ ያደርገኛል፡፡

በተጨማሪም፤ ‹‹የራስ ዕድልን በራስ የመወሰን መብት እስከ መገንጠል›› መብት  መከበርን የሚደግፉ ወገኖች፤ ‹‹ለአንድ ብሔር/ብሔረሰብ የቡድን መብት መከበር ሊታገል የሚችለው የዚያ ብሔር/ብሔረሰብ አባል ብቻ ነው›› የሚል አመለካከት ያላቸው መስለው ይታያሉ፡፡ ‹‹የራስ ዕድልን በራስ የመወሰን መብት እስከ መገንጠል›› መብት ከተከበረ በኋላ፤ እንደ አንድ ቡድን ያለን የሐይማኖት ነጻነት አልተከበረም ብለው የሚያስቡ ቡድኖች መብታቸውን ለማስከበር ተመሳሳይ እርምጃ ሊወስዱ ይገባል የሚል አቋም ግን ያለ አይመስለኝም፡፡ በሁሉም ረገድ የሚነሱ የቡድን መብት ጥያቄች ሊመለሱ የሚችሉት ዴሞክራሲያዊ ስዓትን በማረጋገጥ ብቻ ነው ማለት ይቻላል፡፡

ለአንድ ብሔር መብት ለመታገል፤ የግድ የዚያ ቡድን አባል መሆን አያስፈልግም፡፡ ዋናው ነገር የፖለቲካ አመለካከት እና እምነት ነው፡፡ የብሔር ጥያቄን የሚቃወሙት ጥያቄ የሚያነሳው ብሔር አባል ያልሆኑ ሰዎች ብቻ አይደሉም፡፡ የዚያ ቡድን አባል ሆነው፤ በፖለቲካ አመለካከታቸው የተነሳ፤ አባል የሆኑበት ብሔር/ብሔረሰብ የሚያነሳውን የመብት ጥያቄን ላይደግፉ ይችላሉ፡፡ አንድም ‹‹የመደብ ቅራኔው ሲፈታ፤ የብሔር መብት ጥያቄም ይፈታል›› የሚል አቋም በመያዝ፤ አንድም የብሔር መብት ጥያቄ ወሳኙን የመደብ ትግል የሚያደናቅፍ ጥያቄ መሆኑን የሚያስቡ ኮምዩኒስቶች፤ የብሔር ጥያቄን ሊቃወሙ ይችላሉ፡፡ በሌላ በኩል፤ መኖራቸው ይታወቃል፡፡  ለግለሰቦች መብት መከበር እንጂ ለብሔር/ብሔረሰብ መብት መታገልን የማይቀበሉ የኒዮ ሊበራል አመለካከት ያላቸው (የብሔር ጥያቄን የሚያነሳው ብሔር አባል የሆኑት ጭምር) አመለካከቱን ሊቃወሙ ይችላሉ፡፡ እንዲህ ያለ ሊበራል የፖለቲካ አመለካከት ያላቸው ሰዎችም በየብሔር/ብሔረሰቡ ውስጥ ሊኖሩ ይችላሉ፡፡

በሌላ በኩል፤ በማህበራዊ ምንጩ ‹‹ብሔራዊ ጭቆና ደርሶብኛል›› የሚል ጥያቄ ከማያነሳ ብሔር/ብሔረሰብ የወጡ ሰዎች ፖለቲካ አመለካከታቸው እና በእምነታቸው የተነሳ ለመብቱ መከበር ሊታገሉ ይችላሉ፡፡ በአቀራረብ ደረጃ፤ የቡድን መብት የሚባለውን ነገር የሚቃወሙት ‹‹ብሔራዊ ጭቆና ደርሶብኛል›› የሚል ጥያቄ የሚያነሳው ብሔር/ብሔረሰብ አባላት ያልሆኑ ሰዎች ብቻ ናቸው የሚል አስተሳሰብ ያለ ይመስላል፡፡ እውነታው ግን እንደዚያ አይደለም፡፡

በተጨባጭ እንደምናየው፤ በአንድ ብሔር/ብሔረሰብ ላይ የሚደርስ በደል የሚከነክናቸው የዚያ ቡድን አባላት ብቻ አይደሉም፡፡ በበደል ለመብከንከን፤ ሰው መሆን ብቻ በቂ ነው፡፡ ለመብት መከበር የሚደረገው ትግልም፤ የሁሉም ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች ትግል ነው፡፡ የዚያ የፖለቲካ ማህበረሰብ አባል የሆኑት ቀርቶ፤ ከሐገር ውጭ ያሉ ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች ጭምር ለትግሉ ድጋፍ ያደርጋሉ፡፡ በመሆኑም ትግሉን ከአጋሮች ጋር በመሆን ለማካሄድ በመወሰን ፈንታ፤ አባል ከሆኑበት ፌዴሬሽን ለመውጣት መወሰን የልጅ ሥራ መስሎ ይታየኛል፡፡ ለረጅም ዘመናት አብሮ የኖረን ህዝብ ለማለያየት እንዲህ ቀላል ነገር አይደለም፡፡

ይህም ሆኖ አንድ ጥያቄ ሊነሳ ይገባል፡፡ የቡድን መብት የማይከበረው፤  እኛን ከማይመስሉ ሌሎች ሰዎች አብረን በመኖራችን ሳይሆን፤ ሥልጣኑን የያዘው ኃይል  ዴሞክራሲያዊ ባለመሆኑ ነው፡፡ ዴሞክራሲያዊ መንግስት ከሆነ መብቶችን ያከብራል፡፡ ዴሞክራሲያዊ ካልሆነ ደግሞ ይጥሳል፡፡ በተመሳሳይ በምርጫ ሥልጣን የያዘ ኃይል ኢ-ዴሞክራሲያዊ ሊሆን ይችላል፡፡ እናም መብት ሊጥስ ይችላል፡፡ በዚህ ጊዜ የተበላሸውን ነገር ለማረም የፖለቲካ ትግል ማድረግ ነው፡፡ በርካታ ብሔር/ብሔረሰቦች ባሉበት ሐገር ሆነ አንድ ወጥ ህዝብ በሚኖርባቸው ሐገራት ኢ-ዴሞክራሲያዊ መንግስታት ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ እነዚህ መንግስታት የግል ሆነ የቡድን መብቶችን ይጥሳሉ፡፡ እንዲህ ያሉ መንግስታትን በሰላማዊ ትግል ለማስተካከል ጥረት ይደረጋል፡፡ በሕግ የበላይነት በፀናበት ዴሞክራሲያዊ የተፈጠረ ችግር ከሆነ፤ የተሻለ ሥራ ሊሰራ የሚችል ኃይል በምርጫ ስልጣን እንዲይዝ በማድረግ ችግሩ ይስተካከላል፡፡ ይህን አማራጭ ትተን መገንጠልን የምናነሳው ሥራ የሚጠይቅ ነገርን በመሸሽ ነው፡፡ የችግሩ ምንጭ በአንድ ወቅት ስልጣን ላይ የተቀመጠ ኢ-ዴሞክራሲያዊ መንግስት እንጂ ከሌሎች ጋር አብሮ መኖር ያመጣው ችግር አይደለም፡፡ የችግሩ ምንጭ አብሮ መኖር ባለመሆኑ መፍትሔው መነጠል አይደለም፡፡ ዴሞክራሲያዊ መንግስት መፍጠር እና መቆጣጠር የመቻል አለመቻል ጉዳይ ነው፡፡

የመንግስት አስተዳደሩን ዴሞክራሲያዊ ማድረግ ሲያቅተን እንደቀላል አማራጭ የምንወስደው እርምጃ ነው – መገንጠል፡፡ ይሁንና መገንጠላችን መንግስቱን ዴሞክራሲያዊ አያደርገውም፡፡ አሁንም የቡድን መብት የሚጣስበት ሁኔታ ሊቀጥል ይችላል፡፡ የቡድን መብት ሐይማኖትን በነጻነት የማራመድ መብትን ይጨምራል፡፡ በተገነጠለው ብሔር/ብሔረሰብ ውስጥ ክርስቲያን፣ እስላም፣ አይሁድ እምነት ያላቸው ይኖራሉ፡፡ መንግስቱ ዴሞክራሲያዊ መንግስት ከሆነ መብቱን ያከብራል፡፡ መንግስቱ ዴሞክራሲያዊ ከሆነ፤ የእኛን ቋንቋ በሚናገሩ ሰዎች የሚመራ ሆነ አልሆነ፤ የግል እና የቡድን መብቶች እና ነጻነቶችን ያከብራል፡፡ ካልሆነ አያከብርም፡፡ አንድ ቋንቋ በሚናገሩ ሰዎች መካከል ጎሳን ጨምሮ ሌሎች ልዩነቶች ይኖራሉ፡፡ መንግስቱን ዴሞክራሲያዊ የማድረግ ትግሉ ከዜጎች ትከሻ የማይወርድ እና ያለ ሥራ በገዢዎች መልካም ፈቃድ ሊረጋገጥ የማይችል ነው፡፡ በተገነጠልን ማግስት ዴሞክራሲያዊ መንግስት አብሮ የሚመጣ የሚመስላቸው አሉ፡፡

በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ራሱን በራሱ የሚያስተዳድር ክልል ነው፡፡ ግን መንግስቱ የአንድ ቤተሰብ ስብስብ፤ የአንድ ጎሳ የበላይነት የሰፈነበት፤ ክልሉ የአንድ ሰው ንብረት ተደርጎ የሚታይ፤ በሌሎች ጨቋኝ አሐዳዊ መንግስታት ዘመን እንኳን ታይቶ የማያውቅ ግፍ የሚሰራበት ክልል መሆኑን አየን፡፡ በክልሉ የሚኖሩ የሌላ ብሔር አባላት መብት መከበሩ ቀርቶ፤ በስሙ የመገንጠል ጥያቄ የሚያነሳበትን ህዝብ መብት ማክበር እና  ህዝቡን በእኩልነት ማገልገል ያልቻለ ኃይል፤ የተጠያቂነት ገዳይ ሲነሳ፤ ተጣድፎ የመገንጠል መብት ጥያቄ ሲያነሳ ማየት ብዙ ነገር አሳሰበን፡፡

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy