Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ቴዲ አፍሮና የፕሮሞሽን ኩባንያው በኮንሰርት ምክንያት እየተወዛገቡ ነው

ከእኛ ጋር የገባውን ውል ሰርዞ ከሌላ ጋር መዋዋሉ ወንጀል ነው››

0 2,086

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ከእኛ ጋር ገባውን ውል ሰርዞ ከሌላ ጋር መዋዋሉ ወንጀል ነው››

ጆየስ ኢቨንትስና ፕሮሞሽን

‹‹ሥራውን ለመሥራት ከሚችልና ታማኝ ከሆነ ጋር ሁሉ መሥራት እንችላለን››

አቶ ጌታቸው ማንጉዳይ የቴዲ አፍሮ ማኔጀር

‹‹ኢትዮጵያ›› የሚለውን የድምፃዊ ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) አልበም በአምስት ሚሊዮን ብር መግዛቱን የሚናገረው ጆየስ ኢቨንትስና ፕሮሞሽን፣ ከድምፃዊው ጋር በኮንሰርት ዝግጅት ምክንያት በተፈጠረ አለመግባባት ውዝግብ ውስጥ ገቡ፡፡

‹‹ኢትዮጵያ›› የተሰኘው አልበም አክሳሪ መሆኑንና በቀጣይ በሚሠራው የሙዚቃ ኮንሰርት ኩባንያቸው እንደሚካስ በመተማመን በአምስት ሚሊዮን ብር መግዛታቸውን የተናገሩት የፕሮሞሽኑ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ፍቅሩ አበጀ፣ በቀጣይ ለሚያደርጉት ኮንሰርት ውል የፈጸሙ ቢሆንም ቴዲ አፍሮ ውሉን ሰርዞ ከሌላ ኩባንያ ጋር መዋዋሉን ገልጸዋል፡፡

በየኮንሰርቱ እንደ ሁኔታው ሊገኝ ከሚችለው ገቢ ክፍያ እንደሚፈጽሙ ስምምነት ላይ ደርሰው እንደነበር የሚናገሩት ዋና ሥራ አስኪያጁ፣ የመጀመርያውን ኮንሰርት ያዘጋጁት በባህር ዳር ስታዲዮም እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ በባህር ዳር ስታዲዮም ብዙ ሕዝብ የታደመ ቢሆንም፣ ገሚሱ ሳይከፍል መግባቱን አክለዋል፡፡ ያም ቢሆን ኮንሰርቱ እንዳበቃ ከተነጋገሩትና ውላቸው ከሆነው 1.2 ሚሊዮን ብር ውጪ አምስት ሚሊዮን ብር እንዲከፈለው መጠየቁን አቶ ፍቅሩ ገልጸዋል፡፡ ከብዙ ድርድሮች በኋላ 3.5 ሚሊዮን ብር እንዲሆን ተስማምተው፣ ሁለት ሚሊዮን ብር በካሽ ወዲያውኑ መክፈላቸውንና 1.5 ሚሊዮን ብር ደግሞ በቼክ መክፈላቸውንም አክለዋል፡፡ ቀሪውን 1.5 ሚሊዮን ብር ሊከፍሉ የተስማሙት በሚያዝያ ወር 2010 ዓ.ም. ኮንሰርት ሠርተው ቢሆንም፣ ሳይሰሩ መቅረታቸውንም አቶ ፍቅሩ ገልጸዋል፡፡

ነገር ግን ቴዲ አፍሮ ለእሳቸው ሳይነግራቸውና ውሉም ሳይፈርስ መቀመጫውን አሜሪካ ካደረገ ላየንስ ኢንተርቴይንመንት ከሚባል ድርጅት ጋር ውል ፈጽሞ፣ ኮንሰርት ለማቅረብ በዝግጅት ላይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ይኼ ለምን ይሆናል ብለው ሲጠይቁት፣ ‹‹እንደተጎዳችሁ አውቄያለሁ፣ ገንዘባችሁን ኮንሰርት እየሠራሁ እከፍላችኋለሁ፤›› እያለ የማይሆን ምላሽ መስጠት መጀመሩን አስረድተዋል፡፡ ይኼ ስህተት ከመሆን ባለፈ ሕገወጥና በወንጀልም የሚያስጠይቅ መሆኑን አክለዋል፡፡ ‹‹እሱ የሰጠነውን ቼክ ክፈሉ እያለ ምክንያት አደረገ እንጂ፣ እኛ ሠርተን ለመክፈል ዝግጁ ነበርን፤› ብለዋል፡፡ አሁንም ከእሱ ጋር መሥራት እንደሚፈልጉ አቶ ፍቅሩ ገልጸዋል፡፡

የጆየስ ኤቨንትና ፕሮሞሽን ዋና ሥራ አስኪያጅ ያቀረቡትን ስሞታ በሚመለከት ማብራሪያ እንዲሰጡ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የቴዲ አፍሮ ማኔጀር አቶ ጌታቸው ማንጉዳይ፣ ከፕሮሞሽን ድርጅቱ ጋር አብረው መሥራታቸውን ገልጸዋል፡፡ ኮንሰርት ለመሥራትም ተስማምተው የመጀመርያው ኮንሰርት በባህር ዳር መከናወኑን አቶ ጌታቸው አስረድተዋል፡፡ ነገር ግን ሁለቱ ተዋዋይ ወገኖች ግጭት የጀመሩት ባህር ዳር ስታዲዮም የታደመው ተመልካች ቁጥር 65 ሺሕ አካባቢ ሆኖ ሳለ፣ 17 ሺሕ ነው በማለቱ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ የፕሮሞሽኑ አዘጋጆች ከአምስት በላይ በመሆናቸውና እርስ በርስ ስምምነት ስለሌላቸው፣ ከእነሱም ጋር ሊስማሙ አለመቻላቸውን አስረድተዋል፡፡

የባህር ዳር ኮንሰርትን በ1.2 ሚሊዮን ብር ለመሥራት ስምምነት መፈጸማቸውን የገለጹት አቶ ጌታቸው፣ ይህ ደግሞ በባህር ዳር አንድ አዳራሽ ውስጥ እንጂ ስታዲዮም ይፈቀዳል የሚል እምነት ስላልነበራቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ነገር ግን ስታዲዮም በመፈቀዱ ከሁኔታዎች ጋር ክፍያው እንዲስተካከልና አምስት ሚሊዮን ብር እንዲከፍሏቸው ሲጠይቁ ባለመስማማታቸው፣ 3.5 ሚሊዮን ብር ሊከፍሏቸው ስምምነት መድረሱን አረጋግጠዋል፡፡ ሁለት ሚሊዮን ብር በካሽ ተቀብለው 1.5 ሚሊዮን ብር ቼክ ቢሰጧቸውም፣ በቂ ስንቅ ስለሌለው ይዘውት አንድ ወር እንዳለፈው አስታውቀዋል፡፡

በመሆኑም የሠሩበትን ሳይከፍሏቸው ከእነሱ ጋር ሌላ ኮንሰርት መሥራት ተገቢ ካለመሆኑም በተጨማሪ፣ ራስን ዝቅ ማድረግ በመሆኑ ከሌላ ኢንተርቴይመንት ኩባንያ ጋር ለመሥራት ስምምነት መፈጸማቸውን አቶ ጌታቸው ተናግረዋል፡፡ ‹‹ሥራውን መሥራት ከሚችልና ታማኝ ከሆነ ጋር ሁሉ መሥራት እንችላለን፤›› ብለዋል፡፡

‹‹ደረቅ ቼክ ይዘን አዲስ ሥራ ይሠራሉ ብሎ ማሰብ ራስን ማጃጃል ነው፤›› ያሉት አቶ ጌታቸው፣ በአሜሪካና በኢትዮጵያ ከሚሠራና ላየንስ ኢንተርቴይመንት ባለቤት አቶ ጌታነህ ቢተው ጋር አዲስ ስምምነት ተፈራርመው ወደ ሥራ መግባታቸውን ተናግረዋል፡፡ ቴዲ አፍሮ ከሌላ ጋር መሥራት እንደሚችል ጠቁመው፣ ጆየስ ኢቨንትስና ፕሮሞሽን ግን በመገናኛ ብዙኃን ስም እንደሚያጠፋና በወንጀል እንደሚከስ እየተናገረ መሆኑ እንደማያዋጣው አስታውቀዋል፡፡ ምክንያታቸው ደግሞ ደረቅ ቼክ በእጃቸው ይዘው ዝም ያሉት በወንጀል መጠየቅ አቅቷቸው ወይም ሕጉን ባለማወቅ ሳይሆን፣ እውነታውን አውቀው ወደ ራሳቸው ይመለሳሉ በሚል መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ethiopianreporter

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy