Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ትናንት ያጣነውን…

0 342

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ትናንት ያጣነውን…

ገናናው በቀለ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ከቻይና ጉባኤያቸው በኋላ ወደ ኤርትራ አስመራ በመሄድ አገራቱ ቀደም ሲል በተስማሙት መሰረት የተከናወኑትን ጉዳዩች ተመልክተዋል። በጉብኝታቸውም የኢትዮ-ኤርትራ ግንኙነት ከወደብ አጠቃቀም በተያያዘ ያለውን ከፍታ አብራርተዋል። በዚህ መሰረትም ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአሰብና በምጽዋ ወደቦች ተገኝተው ያደረጓቸውን ጉብኝቶች በኤርትራ በኩል ያለውን ዝግጅት በመመልከት ወደቦቹና የየብስ መጓጓዣውን ከመጀመር ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ገልፀዋል።

በተለይም የአሰብ ወደብን ለመጠቀም የሚያስችል የመንገድ ጥገና ስራ ለመጀመር ዝግጅት ላይ ነው። የሁለቱ ሀገራት ከፍተኛ የመንገድና ሎጀስቲክ ኃላፊዎች ከሰመራ እስከ ቡሬ ድረስ የሚገኘውን መንገድም ተመልክተዋል። በዚህም የአሰብ ወደብን ለኢትዮጵያ ገቢና ወጪ ንግድ ለመጠቀም የመንገድ ስራ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል።

በዚህ መሰረትም ከዲችኦቶ-አሌደአር ከተማ 64 ኪሎ ሜትር የሚሆነው መንገድ በኮንክሪት አስፓልት ደረጃ በ2008 ዓ.ም ግንባታው ተጀምሮ በአብዛኛው ተጠናቋል። ቀሪውን ከኤሊደአር- ቡሬ የሚደርሰው 71 ኪሎ ሜትር መንገድ በኮንክሪት አስፓልት ደረጃ ለመስራትም ታቅዷል። በአሁኑ ሰዓት የአሰብ ወደብን ለመጠቀም የሚስችል የጥገና ስራ ለመጀመር ተቋራጩ ማሽኖችን በማስገባት ላይ ይገኛል።

በመከናወን ላይ ያለው የጥገና ስራው ሶስት ወራት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ አጠናቆ ለአገልግሎት ለማዋል የሚደረገው ዝግጅት ተጠናክሮ መቀጠሉን መረጃዎች ያስረዳሉ። የሁለቱ ሀገራት ልዑካን ቡድን እስከ ቡሬ ድረስ ባደረጉት ምልከታ ለትራንስፖርት ምቹ ከማድረግ አንጻር ጥገና የሚስፈልጋቸው ቦታዎች ቢኖሩም፣ የአሰብ ወደብን ለመጠቀም መሰረታዊ ሊባል የሚችል ችግር አለመኖሩን አረጋግጠዋል።

ቀደም ሲል የሁለቱ ሀገራት በቅርቡ ባደረጉት የሰላም ስምምነት መሰረት ያላቸውን ሃብት በጋራ በመጠቀም ተጋግዘው ለማደግ መግባባት ላይ የደረሱ ሲሆን፣ ይህም ኢትዮጵያና ኤርትራ ያላቸውን ሃብት በጋራ አልምተው ለመጠቀም የሚያስችላቸው ነው። በአሁኑ ሰዓት በኤርትራ በኩል የአሰብ ወደብን የኢትጵያን ወጪና ገቢ ንግድ ለማስተናገድ የሚያስፈልጉ ቅድመ-ዝግጅቶች እየተደረጉ ነው።

በአሁኑ ሰዓት ከአሰብ እስከ ኢትዮጵያ ድንበር ድረስ የሚገኘው የአስፓልት መንገድም ለአገልግሎት ዝግጁ ሆኗል። ከዚህ አንጻር የኢትዮጵያ መንግስት የአሰብ ወደብን ለመጠቀም የጀመረው እንቅስቃሴ ወሳኝ ነው። ከወደቡ ጋር በሚያገኘው መንገድ በአብዛኛው ጥሩ ቢሆንም፤ አልፎ አልፎ ጥገና የሚያስፈልጋቸው ግን አሉ። ሆኖም የጎላ እንቅፋት አይደሉም። ስለሆነም ጥገናውን በአጭር ጊዜ ውስጥ አጠናቆ ለአገልግሎት ለማብቃት ርብርብ እየተደረገ ነው።

እርግጥ የሁለቱ አገራት መሪዎች ህዝባቸውን ተጠቃሚ ለማድረግ እያከናወኑ ያሉት ተግባሮች አገራቱን በምጣኔ ሃብት በማስተሳሰር መጻዒ እድላቸው እንዲቆራኝ የሚያደርግና ሁለቱም ህዝቦች ትናንት ያጡትን ዛሬ፣ ነገና ከነገ በስቲያ እንዲጠቀሙ የሚያስችል ነው። ይህን መሰሉ ዕድል የተገኘው በሀገራቱ መካከል በተፈጠረ ሰላም መሆኑ ግልፅ ነው።

ወትሮም ቢሆን የኢትዮጵያና የኤርትራ ህዝቦች መፃዒ ዕድላቸው ተያይዞ ማደግ ብቻ ነው። ላለፉት ሃያ ዓመታት በ“ሞት አልባ ጦርነት” ስር የነበሩት የድንበር አካባቢ ህዝቦች የሰላምን ዋጋ ጠንቅቀው የሚያውቁ ናቸው። ምን ዓይነት የስነ ልቦና ጫና ውስ እንደነበሩ በደንብ ይገነዘቡታል።

ሁለቱ ህዝቦች ከውጥረትና ከጭነቀት ኪሳራ እንጂ ትርፍ እንደማይገኝ በሚገባ ይረዳሉ። በኢትዮጵያ በኩል፤ ከኤርትራ ጋር በነበረው የተሳሳተ ግንኙነት የተጎዱ ህዝቦች እንዲሁም በዚያም ወገን ተመሳሳይ ሁኔታ ውስጥ የነበሩ ህዝቦች የኪሳራውን ልኬታ ያውቃሉ። አብሮ ተያያዝ ማደግ ሲቻል አለማደግ ከፍተኛ ኪሳራ መሆኑን ከትናንት ችግራቸው የሚያውቁት ነው።

በአሁኑ ሰዓት ኢትዮጵያ ተስፋ ሰጪ ኢኮኖሚ እየገነባችና በየዓመቱም የገቢና ወጪ ምርቷ በፍጥነት በማደግ ላይ በመሆኑ ተጨማሪ የባህር በር ያስፈልጋታል። ለዚህ ደግሞ ኤርትራ ሰፊ የባሀር በር ያላት አገር ስለሆነች የሁለቱ አገራት ተቀራርበው መስራት የግድ ነው። ለዚህም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የአሰብንና የምፅዋን ወደቦች በጎበኙበት ወቅት፤ ኢትዮጵያና ሶማሊያ ወደቦቹን ለጋራ ተጠቃሚነት የሚጠቀሙባቸው መሆኑን ገልፀዋል።

ሁለቱ መሪዎች ከዚህ ቀደም የደረሱባቸው ስምምነቶች፤ አገራቱን በመሰረተ ልማት በማስተሳሰር የህዝቦችን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ ያለመ ነው። እንዲሁም የአካባቢውን ዘላቂ ሰላም ለማስቀጠል ስምምነት ላይ መድረሳቸው አገራችን ከኤርትራ ጋር በመሆን ለቀጣናው አንድነትና ዘላቂ ሰላም መስፈን የበኩሏን አስተዋፅኦ እንድታበረክት የሚያስችላት ነው።

እንደሚታወቀው ሁሉ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ዘላቂ ሰላም እንዲረጋገጥ ትልቁን ድርሻ በመውሰድ ስትንቀሳቀስ ቆይታለች። ይህም አገራችን ለቀጠናው ሰላም ያላትን ቁርጠኛ አቋም የሚያረጋግጥ ነው። አሁን ደግሞ ከኤርትራ ጋር በምታደርገው ጠንካራ ስራ ቀጠናው የሰላም አየር እንዲነፍስበት የሚያደርግ ነው። ሁለቱ ህዝቦች ከተደመሩ ለቀጠናው ሰላም አንፃራዊ ሁኔታን መፍጠር ይችላሉ።

እርግጥ በአንድ ሀገርነት ጭምር አብረው የኖሩት የኤርትራና የኢትዮጵያ ህዝቦች ትስስር በሁለንተናዊ መልኩ የተሳሰረ ነው። ከሌሎች የቀጠናው ህዝቦች በተለየ መልኩ በደም፣ በታሪክ፣ በባህል፣ በቋንቋና በሃይማኖት የተሳሰሩ ናቸው።

አንዱን ህዝብ ከሌላኛው መለየት አይቻልም። ግንኙነታቸው በህይወት ቁርኝት ጭምር የተሳሰረ ነው። ስር የሰደደው ይህ የህዝቦች ግንኙነት በቀላሉ ሊበጠስ የሚችል አይደለም። ዛሬ በንግስ ለመተሳሰር እያደረጉት ያለው ጥረት ይህን ጥብቅ ቁርኝት ይበልጥ የሚያስተሳስረው ነው።

የሁለቱ ሀገራት የወደብ አጠቃቀም የጋራ ተጠቃሚነትን በማስፈን ሁለቱንም ህዝቢች ተጠቃሚ ያደርጋል። ለሃያ ዓመታት አንቀላፍተው የነበሩ የወደብ አካባቢዎችንም የሚያነቃቃ ነው።

 

በወደቦቹ በጋራ መጠቀም በአንድነት ለማደግ የሚያስችል ነው። አሁን ባለንበት ዘመን ለብቻ ማደግ ብሎ ነገር የለም። የኢትዮጵያ ዕድገት ለኤርትራ፣ የኤርትራም ብልፅግና ለኢትዮጵያ በእጅጉ ጠቃሚ ናቸው። ይህ ዕድገት ሁሉን ህዝቦች የሚጠቅምና ምስራቅ አፍሪካም በሂደት በኢኮኖሚ እንድትተሳሰር የሚያደርጋት ነው። ስለሆነም ዛሬ በወደቦች የጋራ ሃብትን ለመጠቀም የተጀመረው ትስስር፣ ትናንት ያጣነውን ልማት የሚያረጋግጥን ነው። ከዚህ አልፎም ምስራቅ አፍሪካን ወደ ብልፅግና ጎዳና የሚያመራት መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy