Artcles

ነፍጥና ቆመጥ ናፈቀኝ ሠላምና ዴሞክራሲ ኮመጠጠኝ

By Admin

September 17, 2018

ነፍጥና ቆመጥ ናፈቀኝ ሠላምና ዴሞክራሲ ኮመጠጠኝ

ይቤ ከደጃች. ውቤ

 

በኢትዮጵያ መንግሥት ከአምስት ወራት በፊት ለተከታታይ ሦስት ዓመታት በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በየጊዜው ሲነሳ በነበረ ቀውስ ምክንያት ሕዝብና መንግሥት ሲታመስ መቆየቱ የሚታወስ ነው። አሁንም በአንዳንዳድ አካባቢዎች ይህንን ቀውስ ለመመለስ ህዝብን ለማተራመስ የሚጥሩ ዜጎች እያየን ነው። ሰሞኑን በአዲስ አበባ እያየነው ያለው ትርምስ በብሔር ስም የዜጎችን ደም ለማፍሰስ ንብረት ለመዝረፍ የሚቋምጡ ቡድኖች ሥራ ፈቶች ተልዕኮ ነው። ለረጅም ዘመናት ሲወርድ ሲዋረድ የመጣው የነገሥታቱ የከበርቴ ሥርዓት እንደ አንደ ሀገር የኢትዮጵያን ብሔር ብሔረሰቦች በማስተባበር ከቅኝ ግዛት በመከላከል የሀገሪቱን ዳር ድንበር በመጠበቅ ነፃነቷን አስከብሯል። በዚህም እንደ ዶጋሊ ድል ና አድዋ ድል ያሉ አንፀባራቂ ታሪኮቻችን በዓለም የታሪክ መዛግብት ውስጥ ተጠቃሾች ናቸው።

በዚህም ኢትዮጵያ ከጥቁር ሀገሮች ነፀነቷን በማስከበር ብቸኛዋ ሀገር ሆና ለሌሎች በቅኝ ግዛት ሲማቅቁ ለነበሩ ሀገሮች ተምሳሌት መሆን የቻለችበት አኩሪ ታሪካችን ነው። ነገር ግን ነገሥታቱ በዘመናቸው የውጪ ወራሪ ሲመጣባቸው ሕዝቡን ከማስተባበር ና የሃገርን ዳር ድንበር ከመከላከል ውጪ የሰሩት ሥራ አልነበረም። ዴሞክራሲ በዓለም ላይ መተግበር በጀመረባቸው ዘመናት ከሀገራችን ዘውዳዊ አገዛዝ ዴሞክራሲ ባንጠብቅም ለዜጎች ዕውቅና ሰጥቶ ቋንቋቸውንና ባህላቸውን የሚችሉበት፣ ከመሬት ከበርቴዎች ብዝበዛ ተላቀው የሚኖሩበት ስልት መመቻቸት ነበረበት።

በዘውዳዊው አገዛዝ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን አመፅ ተመርኩዞ መንበረ ሥልጣኑን የነጠቀው የጊዚያዊ ወታደራዊ መንግሥት ወይም ደርግ ‘ ጊዚያዊ መንግሥት ’ በሚል ሽፋን በትረ ሥልጣኑን ጨብጦ ከአሥራ አራት ዓመት በላይ በወታደራዊ ጡንቻው ህዝብን በቆመጥና በነፍጥ (በዱላና በጠብመንጃ) ሲቀጠቅጥና ሲረግጥ እንደነበር ይታወሳል። ለዚህም በቀይሽብር ስያሜ በሰበብ አስባቡ በየአደባባዩ የተገደሉ አምልጠው የተሰደዱ ምሁራን ይገልፃሉ። በርግጥም ደርግ የቀይ ሽብርን እንዲያፋፍም ምክንያት የሆነው የኢህአፓ አባላት ነጭ ሽብር በሚል የደርግ ደጋፊ ናቸው ያሏቸውን ሰዎች መግደላቸው እንደሆነ ይታወቃል። ለዚህ ዕኩይ ድርጊት ሁለቱም አንጃዎች ተወቃሾች ናቸው። ሰሞኑን በአዲስ አበባ የኦነግ አመራሮችን ለመቀበል በሚደረግ ዝግጅት መሀል በአደባባዮች በአስፋልት ላይ እና በኤሌክትሪክና ስልክ ምሶሶዎች ላይ አርማ ለመስቀል በሚደረግ ሙከራ በአንዳንድ አካባቢዎች ግጭቶች ተነስተው ነበር።የግጭቱ መንስዔ ባንዲራ አውርደን የራሳችንን አርማ (የኦነግን መለያ) እንሰቅላለን በሚሉ ወጣቶች መካከል ነው።

በቀና መንፈስ ካየነው ችግሩ ቀላል በመሆኑ ለግጭት የሚያበቃ አይደለም ።ከስሜታዊነት ታቅበን በውይይት የምንፈታወ ነገር ነበር። ሁከት ለመፍጠር የሞከሩ አካለቶች ቢኖሩም እንኳ የኦነግ አመራር አዲስ አበባ ቤ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲገቡ በአዲስ አበባ አስተዳደር ካቢኔ አባላት አቀባበል ተደርጎላቸዋል።በመስቀል አደባበይም ብዙ ህዝብ በተሰበሰበበት በተደረገላቸው አቀባበል ህዝቡ ስሜቱንና ደስታውን ገልጿል። በመስቀል አደባባይ የቆየው ብዙ ህዝብ የተሳተፈበት የአቀባበል ሙዚቃና ዝግጅትም ተጠናቆ ህዝቡ በሰላም ወደየመጣበት ተመልሷል። በኤርትራ የነበረው የኦነግ ሠራዊትም በትግራይ ዛለአንበሳ በኩል ሲገባ በነዋሪው አቀባበል የተደረገለት ሲሆን በተመሳሳይ መልኩ በመቐሌ ከተማ ሲደርሱ በክልሉ መንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ሓላፊ አቀባበልና የምሳ ግብዣ አድርገውላቸዋል። የኦነግ ሠራዊት አባላት በሰጡት አስተያየትም በተደረገላቸው አቀባበልና ግብዣ መደሰታቸውን ጠቁመው ለትግራይ ህዝብ በጎ እንድንsራ የተሰጠን የቤት ሥራ ነው ብለዋል።

ከላይ የጠቀስናቸው ሃሳቦች ዜጎች ርስ በርስ መፋቀራቸውን ለሰላም ያላቸውን ናፍቆትና ጉጉት የሚያመላክቱ ናቸው።ይህ ሁሉ ሆኖ በአዲስ አበባ እየታየ ያለው ሁከት “የገበያ ግርግር ለሌባ ያመቻል” እንደሚባለው  ግርግር ፈጥረው ንብረት ለመዝረፍ የሚፈልጉ ሥራፈቶች ሴራ ነው። ዜጎቻችን ለረጅም ዘመናት በዘውዳዊውም ሆነ በወታደራዊው አገዛዝ በነፍጥና በቆመጥ ሲረገጡና ሲቀጠቀጡ ኖረዋል። ደርግ በአሥራ አንደኛው ሰዐት ሕገ መንግሥት አርቅቆ ራሱን ኢሕዴሪ ማለትም ኢትዮጵያ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ሪፑብሊክ መንግሥት ብሎ ቢሰይምም አፋኝ መንግሥት ስለነበር የዴሞክራሲ ስያሜውን እንጂ ጭላሉን ሊያሳየን አልቻለም። በመዲናችን አንዳንድ አካባቢዎች እየታዩ ያሉ ሁከቶችና ግጭቶች በእንጭጩ ካልተቀጩ ጉዳቱ ለሕዝብም ለመንግሥትም የከፋ ነው የሚሆነው።ሁከቶቹ ለማንም የማይበጁ ህዝብን የሚያፋጁ ስለሆኑ ህዝብ በተለይም የመዲናው ወጣቶች ራሳቸው ከዚህ ክፍ ድርጊት ሊጠብቁ ይገባል። በሰበብ አስባቡ አውራውን ፓርቲና ህዝቡን እየተነኮስን አውሬ እንዳናደርጋቸው እንጠንቀቅ። ሰላምና ዴሞክራሲን እናጣጥም ውሃ ቀጠነ እያልን ሁከትና ብጥብጥ የምናነሳ ከሆነ ነፍጥና ቆመጥ ናፈቀኝ ዴሞክራሲ ቆመጠጠኝ የምንል ይምስላል። በማህበራዊ ሚዲያ ከሚተላለፉ አሉባልታዎችን ተራ መረጃዎች እንራቅ ።እንደ አበው ብሂል “ጦር ከፈታው ወሬ የፈታው”እንደሚባለው የአሉባልታ ጠንቅ ከአንድ ሠራዊት ጦር የከፋ ነው። መንግሥትም ለተፈጠሩ ችግሮች የሚሰጠው ምላሽ ዘገምተኝነት የሚታየበት ነው።ሰው በሀገሩ የሌላ ብሔር ነህ በሚል ሰበብ ሕይወቱ ልያልፍ ሀብት ንብረቱ ሊዘረፍ አይገባም። ትናንት መብታችን ተረገጠ ብለው በውጪ ድምፃቸውን ሲያሰሙ የነበሩ አክትቪስቶች ዛሬስ ሀገር ውስጥ ሆነው ይሄ የወገን ሞት አይታያቸውም ።እንሱም በተራቸው የሰው መብት እየረገጡ ነው እንዴ ያሰኛል።

የፌዴራል፣ የአዲስ አበባና የኦሮሚያ ፖሊስ አባላት ዘገምተኝነትና ቸልተኝነት እያሳዩ ይመስላል። በጠራራ ፀሀይ ዜጎች መሞትን መዘረፍ አለበት? ዜጎች ሕይወታቸው ካለፈ በኋላ ቢደርሱ ምን ትርጉም አለው። በአሸዋ ሜዳ፣ በከታ፣ ቡራዩና ሳንሱሲ ግጭቶቹ ተፋፍመው የተወሰኑ ዜጎች ሕይወት አልፏል። ከሰባ በላይ የሚሆኑ ሰዎች በቁጥጥር ሥር ውለዋል። በመንግሥት በኩል የተሠጡ መግለጫዎች ተገቢ ቢሆንም ትልቁ መፍትሄ ግን የዜጎችን ሠላምና ፀጥታ በማስከበር የማያዳግም ምላሽ መስጠት ነው። እናዝናለን ከሚለው መግለጫ ጎን ወሳኙ ነገር የዜጎችን ሠላምና ፀጥታ ማስከበር ነውና።